Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ካላመረትን ከዋጋ ግሽበት አዙሪት አንወጣም

በገበያ ውስጥ የሚታየውን የምርት እጥረት ለመቅረፍ እንዲሁም ዛሬም ሆነ ወደፊት ሊከሰት የሚችል የዋጋ ንረትን ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ ምርታማ መሆን ነው፡፡ ዛሬ እየተገዳደረንና እየፈተነን ያለውን ችግር ለመፍታት ቀዳሚ ተግባራችን መሆን የሚገባው ያለንን አቅም ለማፋጠን ምርት ስናሳድግ ብቻ ነው፡፡ መጪውን ጊዜ እያሰቡ ሊኖር የሚችለውን ፍላጎት የሚመጥን ምርት ማምረትም ግድ የሚሆነው ፍላጎታችንን ያለማቋረጥ የሚጨመር በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ በተለይ በቀላሉ ልናመርታቸው የሚችሉ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን እዚሁ በማምረት ፍላጎቱን ማሟላት ካልቻልን መጪው ጊዜ ከዛሬው ይከፋል፡፡ የዛሬ የዋጋ ንረት ነገ ብሶ ሊመጣ ይችላል፡፡ ማምረት የምንችለውንም ሆነ የማንችለውን ሁሉ ከውጭ እያመጣን መቀጠል ማንችልበት ጊዜ ላይ እንደደረስን ማወቅ ይገባናል፡፡  

ከማምረት በቀላሉ ከውጭ ገዝቶ መገላገል ይሻላል ከሚለው አስተሳሰብ መውጣትና  በማስመጣት ንግድ ላይ የተመሠረተውን የንግድ ባህላችንን ሁሉ መለወጥ የሚያስፈልገን ይሆናል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ከዚህም ከዚያም እያፈላለጉ ምግብ ነክ ምርቶችን ሸምቶ ገበያውን ለማረጋጋት ወይም ፍላጎትን ለመሙላት የሚደረግ ጥረት አዋጭ አይሆንም፡፡ ብንፈልግም ይህንን የማድረግ አቅም እያጣን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የዓለም ገበያ ነዷል፡፡ ምግብ ነክ ምርቶችን ለመግዛት የሚጠይቀን ወጪ እንደእስካሁኑ ቀላል እንደማይሆን የዓለም ገበያ እየነገረን ነው፡፡

የዓለም ገበያን የሚያመላክቱ የተለያዩ መረጃዎች ቀዳሚ ዜናቸው የነዳጅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ጨመረ፣ የስንዴ በዓለማችን ተመዝግቦ የማያውቅ ዋጋ አስመዘገበ፡፡ እከሌ የምትባለዋ አገር ዘይትና ስንዴ ለውጭ ገበያ ላለማቅረብ ወሰነች የሚሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በልቶ ለማደር የሚያስፈልጉን እንደ ስንዴ ያሉ ምርቶች ዶላር ቢኖረንም ገበያ ላይ ላናገኝ እንችላለን፡፡ አሁን ባለው አያያዛችን ደግሞ ዶላሩ እንዲህ በዋዛ የሚገኝ አይደለም፡፡ ይህ ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ ወደድንም ጠላንም ከስከዛሬው በመጣንበት መንገድ የሚያስቀጥለን አይደለም፡፡ አሁን በዓለም ላይ የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና የዋጋ ንረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት አሁን ቢቆም እንኳን የዚህ ጦርነት ጦስ ያስከተላቸው ኢኮኖሚያዊ ትርምሶች በአንድ ጀምበር አይስተካከሉም፡፡ ስለዚህ የዛሬን የዋጋ ንረትና ቀውስ ብቻ ሳይሆን ለከርሞ የሚጠብቀን ተጨማሪ ዳቦ ጠያቂ ሕዝብን ታሳቢ ያደረገ ምርትና ምርታማነቱን ሊያሳድግ የሚችል ፖሊሲ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡

በተለይ ምግብ ነክ ምርቶችን እዚሁ በማምረት ራሳችንን መቻል አለብን የሚለው ቁልፍ ጉደይ ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ፖሊሲ ተቀርፆለት በተለየ መንገድ ሊተገበር ይገባል  ሲባል፣ ከውጭ መግባት የሌለባቸውን ምርቶች በሕግ ማገድና እዚሁ እንዲመረቱ ማስገደድና ማበረታታትን ጭምር ይጠይቃል፡፡

ገበያ ውስጥ ያለውን እጥረት የምንቀርፈው የሸማቹን ጥያቄ ልንመልስ የምንችለው እንዲህ ያሉ አሠራሮችን እየተገበርን ምርታማነታችንን በማሳደግ ብቻ ነው፡፡

ከውጭ የተለያዩ ሸቀጥን በማምጣት ስንጥቅ በማትረፍ ላይ የተመሠረተው የንግድ ባህላችንን መቀየር አለብን፡፡ ይህ ሲባል የስንዴና ስንዴን ግብዓት አድርገው የሚመረቱ ምርቶች በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲተኩ ግዳጅ መጣል ማለት ነው፡፡

ቀርከሐ፣ ያለምንም ጥቅም የሚበሰብስበት አገር ውስጥ መሆናችን እየታወቀ ለጥርስ እንጨት (እስቴኪኒ) የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከልክሎ እስቴኪኒ አስመጪው እዚሁ አምርት ሲባል ነው፡፡

የተትረፈረፈ ጨው በሚመረትበት አገር የውጭ ጨው ለማስመጣት ዶላር መፈቀድ የለበትም ማለት ነው፡፡ ሌሎች እዚሁ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን ዘርዝሮ በመለየት ከውጭ እንዳይገቡ ማስቆምና በአገር ምርት እንዲተኩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችንና ይህንን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ዕቃዎችን በማምጣት ዕድሜያቸውን የፈጁ አስመጪዎቻችን ከማስመጣት እዚሁ ወደ ማምረት እንዲገቡ ማበረታታትም ጭምር መሆኑን፣ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎቻችንም ከዚሁ አንፃር መቃኘት አለባቸው፡፡ በተለይ በተለይ ከምንም በላይ ያለጥርጥር ልንተገብረው የምንችለው የግብርና ምርቶቻችንን በስፋት ማምረት በመሆኑ ይህንኑ ሊያስፋፋ የሚችል ፖሊሲና ምቹ ሁኔታ መቅረፅ አገርን የመታደግ ያህል ይቆጠራል፡፡ ግብርና ሕይወቴ ነው ብሎ እስከማቀንቀን የሚደርስ መሪ ቃል በማንገብ ካልተሠራ መጪውን ጊዜ መሻገር ከባድ ይሆናል፡፡

ይህም ዛሬ ዓለም በምግብ ዋጋ ንረት በመመታቷ ብቻ ልናደርገው የሚገባ ሳይሆን፣ ከየትኛውም ኢንቨስትመንት በቀላሉ ልንተገብረው የምንችለው ግብርና በመሆኑ ነው፡፡ ሩሲያና ዩክሬን ደርጅተው የነበሩት ስንዴና ዘይት በማምረት ጭምር ነው፡፡ የእነርሱ ቀውስ ለዓለም ተርፏል፡፡ ለምርት የሚሆን የተፈጥሮ ሀብት ያለን ሕዝቦች፣ ስንዴ ለመግዛት ከዓለም አንሻማም፡፡ ባይሆን ተሻምተው እንዲገዙን ዕድል ያለን መሆኑን ተገንዝበን ይህንን መተግበር ግድ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ለመቻላችን ደግሞ በቆላ ስንዴ እየታየ ያለው ውጤት ምስክር ይሆናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአገር ምርት የመጠቀም ባህላችንን ማሳደግ በአገር ምርት መኩራት ሁሉ ይጠበቅብናል፡፡ ግብርና ሕይወቴ ማለት ዛሬ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት