Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለመገዳደል ያለንን ቁርጠኝነት ለመነጋገርና ለመቀራረብ እናድርገው›› አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የኢዜማ ምክትል መሪ

የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን የጀመሩ ቢሆንም፣ ስለማኅበረሰብ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደረጋቸው አስተዳደጋቸውና ያደጉበት አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቆዩባቸው ዓመታትም የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በማሳደግ፣ በተማሪዎች መማክርት ጉባዔ ውስጥ አመራር እስከ መሆንም ደርሰዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በዘመነ ኢሕአዴግ በ1993 ዓ.ም. ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ፓርቲ ለማቋቋም እየተመካከሩ ሳሉ፣ ኢዴፓ በመቋቋሙና ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለነበር በዚያው ዓመት የፓርቲው መሥራች አባል በመሆን የፖለቲካ ፓርቲን መቀላቀላቸውን ይናገራሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ የምክር ቤት አባልና ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ፓርቲያቸው አባል የነበረበት ቅንጅት ውስጥ እየተሳተፉ እያለ፣ በወቅቱ በተፈጠረው የምርጫ 97 ሒደት የቅንጅት አመራሮች ሲታሠሩ እሳቸውም ታስረው ቆይተዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱ በኋላ አንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲን በመቀላቀል ዋና ጸሐፊና ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ተከሰው ከስድስት ዓመታት በላይ በእስር ቆይተው በ2010 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የተፈቱት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የዛሬ የቆይታ ዓምድ እንግዳችን ናቸው፡፡ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ከለውጥ በኋላም ለአንድ ወር ያህል ታስረው የነበሩት አቶ አንዱዓለም፣ በአንድ ወሩ እስር ወቅት ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ኢዜማን ለማቋቋም ተስማምተው ከእስር እንደወጡ ኢዜማን መመሥረታቸውን ይናገራሉ፡፡ አቶ አንዱዓለም ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ ከመገናኛ ብዙኃን ጠፍተው ስለመክረማቸውና አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከታምሩ ጽጌ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት (ሰኔ 2013 ዓ.ም.) ከተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኋላ፣ በምርጫ ውድድሩ በመሸነፍዎ ምክንያት ይሁን ወይም በሌላ ጠፍተዋል፡፡ በሰላም ነው የጠፉት?

አቶ አንዱዓለም፡- ለመጥፋቴ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ አንደኛው በምርጫው ነው፡፡ መታወቅ ያለበት ነገር በምርጫው እናሸንፋለን የሚል ትንበያ አልነበረንም፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ምርጫው የኢትዮጵያን መፃኢ ዘመን ቀያሽ እንደሚሆን ቁርጠኛ ሆነው ስለተናገሩ፣ እኛም ምርጫው ከሌሎቹ ምርጫዎች የተለየና የኢትዮጵያን ንጋት አብሳሪ ይሆናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ምርጫ ከመድረሱ ስድስት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዴሞክራሲ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጡልን፣ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) እና እኔ ሆነን ሄደን አነጋግረናቸው ነበር፡፡ ‹‹አሁን በጣም የተንሰራፋ የካድሬ ሥርዓት አለ፡፡ ይህንን ይዘው እንዴት ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለው ያስባሉ? ካድሬው ለራሱ ህልውና የሚኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ እውነተኛ ድምፅ ሰጥቶ የሚፈልጋቸውን ሰዎች መምረጥ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ተግዳሮት እንዴት ሊወጡት ይችላሉ? እስካሁን ካድሬው አልተነካም፡፡ መዋቅሩም እንዳለ ነው…?›› የሚል ጥያቄ እኔ ራሴ አንስቼላቸው ነበር፡፡ ‹‹እኔ ለዴሞክራሲ በጣም ቁርጠኛ ነኝ፡፡ በዚህ ሥጋት አይግባችሁ፡፡ ምርጫው በሚቃረብበት ጊዜ የካድሬውን ሁኔታ መስመር አስይዘዋለሁ፡፡ ካድሬው ለምርጫው እንቅፋት በማይሆንበት ሁኔታ አዋቅረዋለሁ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውን ነበር፡፡ እኛም ቁርጠኛ እንደሆኑ ተሰማን፡፡ ነገር ግን የምታስታውስ ከሆነ የ1997 ዓ.ም. ምርጫም ታሪክ የተቀየረው ደብረ ዘይት ላይ ነበር፡፡ የ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም ታሪክ የተቀየረው እዚያው ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ላይ ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የመጀመርያውን የቅንጅት ስብሰባ ደብረ ዘይት ለማድረግ ሲኬድ የደብረ ዘይት ከንቲባ ከለከሉ፡፡ ከንቲባው ሲከለክሉ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ለአቶ በረከት ስምዖን (አሁን ፍርደኛ) ደወሉ፡፡ አቶ በረከትም ወዲያውኑ ተደዋውለው ከንቲባው እንዲታሰሩ አደረጉ፡፡ ሌላው ካድሬ የተወሰደውን ዕርምጃ በመስማቱ በሌሎች አካባቢዎች ሰላማዊ ነገር ተፈጠረ፡፡ የመጨረሻው ውጤት ታውቆ፣ ውጤቱን እስከሚገለብጡት ድረስ በደብረ ዘይት የተፈጠረው ሁኔታ የ1997 ምርጫን የቀየረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

      በተመሳሳይ በ2013 ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም ቅስቀሳ በሚጀመርበት ዕለት ግርማ ሞገስ የሚባል የኢዜማ አመራርን ቢሾፍቱ ላይ ገደሉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡት ቃል ስለነበር ወጥተው አደብ እንዲያስገዙና ቢያንስ አባላችን እንኳን ሞቶ ከዚያ በኋላ ያለው የምርጫ ሒደት የተስተካከለ እንዲሆን ሁላችንም ወጥተን ጮህን፡፡ የጮህነው መጮህ ፈልገን አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰምተው፣ ‹‹እንዴት እኔ በምመራው አገር የንፁኃን ደም ይፈሳል? እንዴት የሕፃናት አባት በግፍ ይገደላል? እንዴት የዴሞክራሲ ጅምራችን ይበላሻል?›› ብለው በቁጣ ወጥተው አደብ እንዲያስገዙ ነበር፡፡ ነገር ግን ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ ኦሮሚያ ሙሉ በሙሉ ጨለማ ሆነ፡፡ መንቀሳቀስም ሆነ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡ በአማራ ክልልም የኦሮሚያን ግልባጭ ወስደው ሒደቱን ተመሳሳይ አደረጉት፡፡ በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ የሕዝብ ቡሉኮ አልብሰውን ቆይተው፣ ቡሉኮውን በማንሳት ብርድ አስመቱን፡፡ ያ ለእኔ እስከ መጨረሻው ድረስ ቅስሜን ሰብሮታል፡፡ ‹‹ልናግዛቸው ይገባል›› እያልኩ ዳያስፖራውን በእሳቸው ጫማ ሆኖ እንዲያስብ ብዙ ነገር ሠርቻለሁ፡፡ አንድን ሰው ተጠራጥሮ ሥራ ከመጀመር አምኖ መጀመር ይሻላል በሚል ያደረግነው ሁሉ ከንቱ ሆኖ በመቅረቱ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ይህም ዝም እንድል አድርጎኛል፡፡ ሁለተኛው የጠፋሁት በእኛ በኢዜማ አሠራር የምክትል መሪው ኃላፊነት ዋናው መሪ በሌለበት ጊዜ ብቻ ተክቶ መሥራት ነው፡፡ በደንባችን ላይ የምክትል መሪው ኃላፊነት አንድና አንድ ዋናው መሪ ከሌለ ተክቶ መሥራት ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የእኔም ኃላፊነት ያ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ወጥቼ ለመናገር ወይም ለመታየት የሚያስችለኝ የሥራ ድርሻ ስለሌለኝ ምናልባት ለመጥፋቴም ሌላው ምክንያት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ካለዎት የፖለቲካ ልምድና ረዥም የትግል ሒደት አንፃር በተለይ አዲስ በተቋቋመ ፓርቲ ውስጥ ብዙ መሥራት ሲገባዎት፣ በደንብ በተወሰነና መሥራት በማይችሉበት ኃላፊነት ላይ መቀመጥዎ ምቾት ይሰጥዎታል? ወይስ የሥልጣን ድልድሉ አስገዳጅነት ነበረው?

አቶ አንዱዓለም፡- ደንብ ሲወጣ አንድን ሰው ታሳቢ አድርጎ አይወጣም፡፡ አጠቃላይ የፓርቲው መዋቅራዊ ሒደትን ተከትሎ የሚቀረፅ ነው፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ሆኖ ደንቡ ቢቀረፅም ትክክል ነው ብዬ አላስብም፡፡ ያም ሆኖ ግን የግድ የፓርቲውን ዲሲፒሊን  ማክበር ስላለብኝ፣ ዋና መሪው ሌሎች ሥራዎችን እንዳግዝ ካላደረጉና በትብብር ካልሆነ በስተቀር ምንም ማድረግ አልችልም ነበር፡፡ ፓርቲው አዲስ ስለነበር በደንቡ ላይ ያሉትን ግድፈቶች ያየናቸው ቆይተን ነው፡፡ አሁን ላይ እያስተካከልናቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ለመጥፋቴ ምክንያት የሆኑት እነዚህ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ ከእኔ ሥልጣን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ይበልጣል፡፡ ብዙ ሰው ስለሚያውቀኝ ስጠፋ ‹‹ምን እያደረገ ነው?›› ማለቱ አይቀርም፡፡ ሕዝብ የሰጠኝ ዕውቅና እንጂ ኢዜማ ውስጥ ያለኝ ሥልጣን ከአንድ አንቀጽ የዘለለ አይደለም፡፡ ከማማከርና መሪውን ተክቶ ከመሥራት የዘለለ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- በደንቡ የተቀመጠውን የምክትል መሪ ኃላፊነትን እያወቁ እርስዎ ምክትል መሪ ሆነው ሲሾሙ አልተቃወሙም?

አቶ አንዱዓለም፡- አልተቃወምኩም፡፡ እንዲያውም ራሴ ተስማምቼ ያደረግኩት ነው፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ከስድስት ዓመታት በላይ በእስር ቆይቼ ገና መፈታቴ ነበር፡፡ ገና አልተረጋጋሁም ነበር፡፡ የአዕምሮ መረበሽና ነገሮችን በደንብ የማዋዋጫ ጊዜ ያስፈልገኝም ነበር፡፡ የተረጋጋሁና ኃላፊነት በምወስድበት ደረጃ ላይ አልነበርኩም፡፡ ስለዚህ ራሴ ተስማምቼና አውቄ ነው የገባሁበት፡፡ ነገሮች ከተረጋጉና እኔም በሁሉም ነገር ብቁ ከሆንኩ በኋላ ደግሞ፣ ካለሁበት የኃላፊነት ቦታ ወጥቼ የፈለግኩትን የማደርግበት ወይም የምናገርበት ሁኔታ ላይ ባለመሆኔ ጠፍቻለሁ፡፡ የድርጅት ምክትል መሪ ሆኜ ሕግና ደንብን በማክበር አርዓያ መሆን እንጂ ጥሶ መገኘትን አልፈልግም፡፡ አገራችንን በአብዛኛው በንባብ ባውቃትም ሁን እንዳለችበት ዘመን መቼም ሆና አታውቅም፡፡ አጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ የታመምንበት፣ እንደ ሕዝብ ደግሞ ግራ የተጋባንበት፣ ከሚቀጥለው ደቂቃ በኋላ እንኳን ምን እንደሚፈጠር መገመት የማንችልበት፣ ሁሉም ተናጋሪና ተጠቂ ነኝ ብሎ የሚያምንበት፣ ሁሉም ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ ያልሆነበትና ግን ሌላውን የሚጠይቅበት፣ ለመናገር እንጂ ለማዳመጥ ብዙ የተዘጋጀ በሌለበት ወጥቶ የጩኸቱ አካል መሆን ያለውን ግራ መጋባት ከማስፋት በዘለለ ብዙ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ ስለማላስብም ዝም ብያለሁ፡፡ ሌላው ሰው የሚለውን ነገር ደጋግሞ መናገርም ደስ አይለኝም፣ ይሰለቸኛል፡፡ አዲስ የሆነና ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅምና በደንብ አስበህና አሰላስለህ ይዘህ ቀርበህ፣ ችግሩን ለመቅረፍና አቅጣጫ ለማመላከት ካልሆነ በስተቀር ዝም ብሎ ሌላው ስለተናገረና የሚዲያ አጋጣሚ ስላገኘህ፣ አለባበስህንና ከረባትህን አሳምረህ ለመታየት የሚደረገው ሩጫ አይመቸኝም፡፡ በመሆኑም ዝምታን መርጫለሁ፡፡ አደባባይ አልውጣ እንጂ በፓርቲያችን ውስጥ ስለአገራዊ ጉዳዮችና ስለሕዝባችን ቀጣይ ሁኔታ የተለያዩ ርዕሶችን (አጀንዳዎችን) አንስተን እስከምንዝል ድረስ እንወያያለን፣ አቅጣጫም እናስቀምጣለን፡፡ በዚህ ውይይትና ንግግር ውስጥ ልዩነት የለም ማለት አይደለም፡፡ ግን ልዩነቶቻችንን አክብረን ወደ አንድ አቋም እንመጣለን፡፡ ውጤቶችንም ዓይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫው ለመሸነፋችሁ ዋናው ምክንያት ቅስቀሳ በጀመራችሁበት ዕለት የአባላችሁ መገደል ብቻ ነው? ወይስ ተጨማሪ ምክንያቶች ነበሩ?

አቶ አንዱዓለም፡- በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ተፅዕኖዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባን ብንወስድ በየቀበሌው የነበሩ ካድሬዎች በተመዝጋቢዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድሩ ነበር፡፡ በሴፍትኔት፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተጠቃሚዎች ላይ ይደርስ የነበረው ማስፈራራት የቆየ ነው፡፡ ግን ቅስቀሳ በተጀመረበት ዕለት የሕዝቡን ቅስም ለመስበር ግድያ ተፈጸመ፡፡ ከዚያ በኋላ ፍጹም መንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ በተለይ ኦሮሚያ ላይ፡፡ ለዴሞክራሲ የሚያማልልና ግዙፍ ህልም እንድናልም አድርገው፣ ወደ ተግባር ሲገባ ግን  ምድረ በዳ ውስጥ ከተቱን፡፡ አፈናው አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ቦታ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምርጫውን የተሸነፍነው በደረሰብን የገዥው ፓርቲ (ብልፅግና) ተፅዕኖ ብቻ ነው እያሉ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- በምርጫው ዙሪያ ቀደም ብለን ጥናት (Survey) ሠርተን ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር በነበረው ሁኔታ፣ የለውጥ ወቅት በመሆኑ የገዥው ፓርቲ የማሸነፍ ዕድል ሰፊ እንደነበር እናውቃለን፡፡ የእኛ ጥያቄ የወንበሩ ቁጥር አልነበረም፡፡ የእኛ ትልቁ ጥያቄ ዜጎች በነፃነት የሚፈለጉትን መሪ መርጠው በሰላም የመመለስ ዕድል ይኖራቸዋል ወይ? የሚለው ነበር፡፡ ደግሞ በባዶ እንቀራለን የሚልም ሐሳብ አልነበረንም፡፡ በትንሹ እስከ 130 ወንበሮች እናገኛለን፣ ሌሎችም የተወሰነ ያገኛሉ፣ ግን ብልፅግና ያሸንፋል የሚል ግምት ነበረን፡፡ በተግባር የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ ግብር ከፋዮችን ስብስቦ ለምርጫ የሚውል ገንዘብ አዋጡ ማለት ምን ማለት ነው? በነጋዴው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ግልጽ ነው፡፡ የታክሲ ባለንብረቶች፣ የደረቅና የፈሳሽ ተሽከርካሪዎች ማኅበራትን፣ የባንክና የኢንሹራንስ ሠራተኞችን ገንዘብ እንዲያዋጡ ማድረግና ‹‹አናዋጣም›› ቢሉ ምን ሊከተል እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ምን ይሠሩ እንደነበር ለአንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ግን በኢትዮጵያ ሕግ ፓርቲ የሚዲያ ባለቤት መሆን ይችላል? ክርክሩ እንዴት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የመንግሥት ንብረት ለፓርቲ መቀስቀሻ የዋለበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ሁኔታ የምርጫው ውጤት ምን እንዲሆን ይጠበቃል? ይህንን ሁሉ ሰብረን ቢያንስ እስከ መቶ መቀመጫ እናገኛለን ብለን ነበር፣ አልሆነም፡፡ እነሱን ጭምር ባሳፈረ ሁኔታ ሥራቸው ፍንትው ብሎ ወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫው በተካሄደ ማግስት የኢዜማ አመራሮች፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ገልጸው መሸነፋቸውን በፀጋ የሚቀበሉ መሆናቸውንና ተፎካካሪዎቻቸውንም ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እርስዎ ከሚሉት ጋር አይቃረንም?

አቶ አንዱዓለም፡- አንዳንድ እንደዚያ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ ግን እያወራሁ ያለሁት አጠቃላይ ስለነበረው የምርጫው ሒደት ነው፡፡ በአንድ የምርጫ ክልልና ጣቢያ ላይ የተወዳዳረ ሰው የራሱን ጥረት አድርጎ ከተሸነፈ ‹‹ተሸንፌያለሁ›› ማለት መብቱ ነው፡፡ የሚያምንበትን ነገር ማድረግም ትክክል ነው፡፡ አሁን እየነገርኩህ ያለው የምርጫውን ሒደት ጥናት (Survey) ሠርተን፣ ‹‹ምርጫው ምን ይመስል ነበር?›› የሚለውን ካየን በኋላ የተገኘውን ውጤት ነው፡፡ የሠራነው ጥናት የሚያሳየው ከላይ የነገርኩህን ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩልህ የአዲስ አበባው እንደ ክፍለ አገሩ በጉልበት አልነበረም፡፡ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉልበትን በመጠቀም በድህነት ላይ የተሠራ ነው፡፡ ይህንን  ሁሉ እያየን፣ ሁሉም ነገር በአገር ስለሆነ ሰላም እንዲመጣና እንዲረጋጋ በሚል ዝምታን በመምረጣችን፣ በሕዝቡ በኩል ‹‹እንደ ተለጣፊ›› እና በገዥው ፓርቲ ደግሞ እንደ ‹‹ቂል›› ታይተናል፡፡ ግን ሞኝ ወይም ፖለቲካ ያልገባን ተሸዋጆች አይደለንም፡፡ እነሱ እንደሚሉት ‹‹ኮንቪንስና ኮንፊውዝ›› እያደረጉ እንደተጫወቱብን አይደለንም፡፡ ሕዝቡ እንደገመተውም ከብልፅግና ጋር ተለጥፈን ጥቅም ያገኘንም አይደለንም፡፡ ለአገር ብለን የመጣንበት መንገድ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ እሱም አብሮ የሚታይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በብልፅግና አሸናፊነት ተጠናቆ፣ መንግሥት በተመሠረተ ማግስት በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ምክንያት ወደ ጦርነት ተገብቷል፡፡ ላለፉት 19 ወራትም ቀጥሎ ይገኛል፡፡ እርስዎ በዚህ ጦርነት ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ምንጊዜም ቢሆን መሠረቱ የተበላሸ ቤት ችግር ይገጥመዋል፡፡ መሠረቱ ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገ ሕንፃው የመደርመስ ወይም የመፍረስ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በእርግጥ ፖለቲካን የሚያህል የተወሳሰበ ነገር ከቤት ሥራ ጋር ማመሳሰሉም ትንሽ ሊከብድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ ታሳቢ የሚደረጉ ነገሮች ስላሉ፡፡ ግን በተቻለ መጠን ፖለቲከኞች የፖለቲካውን ውስብስብነትና አስቸጋነሪት ዓይተውና ቆም ብለው ተረጋግተውና አስበው መወሰን ግድ ነው፡፡ ካልሆነ ከችግር ውስጥ እወጣለሁ ብለህ፣ ችግር ውስጥ ትገባለህ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ኢሕአዴግ ፈጣሪ ሊቀጣን አስቦ በምድር ላይ ያወረደብን መርገምት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ያ መርገምት ሲረግጠንና ብዙ ፍዳዎችን ሲያሳየን ከቆየ በኋላ፣ እንደገና ተከፋፍሎ ሌላ በታሪካችን የከፋውን መከራ አመጣብን፡፡ የተወሰነው ክፋይ ብልፅግና ነኝ ሲል፣ የተወሰነው ክፋይ ደግሞ ሕወሓት ነኝ አለ፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥፍሩ ቆሞ እያነባ፣ እየተሰቃየና እየደማ እንዲኖር ያደረገው ፓርቲ፣ እንደገና ለሁለት ተሰንጥቆና ጎራ ለይቶ አገሪቱን መከራ ውስጥ ከተታት፡፡ የጦርነቱ መነሻ ይኸው ነው፡፡ ሕወሓትም ለትግራይ ሕዝብ አስቦ ሳይሆን መዓት ነው ያመጣበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ ምንና ማን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር እንዲለያይ፣ እንዲጠላና እንዲወገዝ ነው ያደረገው፡፡ ልዩ ተጠቃሚ በማስመሰል ሌሎች ልዩ ተጠቃሚዎቹ ባለሥልጣናትና አጃቢዎቻቸው ማመሳሰያ ነው ያደረጋቸው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በምን ዓይነት ድህነት ውስጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ምንም የማያሻማው ነገር በሰሜን ዕዝ ላይ ሕወሓት በወሰደው ዕርምጃ የገዳም መነኩሴም ቢሆን ዝም ሊል አይችልም፡፡ የጎረሰውን ሳይውጥ አገር ጠባቂ ወታደር መጨፍጨፍ በባህላችንም የለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ባህል አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖተኛ፣ ጨዋ፣ ለታሪኩ የሚጨነቅ፣ ከጎረቤቱ ጋር አብሮ የሚኖር፣ ለሌላው የሚያለቅስ እንጂ ሲጠብቀው የኖረንና እርሻውን እያረሰ፣ ቤቱን እየሠራ አብሮት የኖረን ወታደር፣ ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረን ወታደር አይገድልም፣ አያርድም፡፡

እንደዚህ ያለ ድርጊት ሲፈጸም አንድ መንግሥት ያንን ለመከላከል ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ በታሪክም፣ በሕግም፣ በትውልድም ይቅር የማይባል በደል አድርሷል (ሕወሓት)፡፡ ይህ ደግሞ እስከ መጨረሻው ይከተለዋል፡፡ ይህንን ግፍ እንዴት ማወራረድ እንደሚቻል አላውቅም፡፡ ‹‹ጁንታው ሞቶ ተቀብሯል፣ ታሪክ ሆኗል፤›› ስላሉን፣ ሰላም ይመጣል ብለን አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ አልአዛር ከተቀበረበት ጉድጓድ ወጥቶ እንደገና ማሳደድ ጀመረ፡፡ አላአዛር ግን ከሞት ተነሳ እንጂ ሌሎችን አላሳደደም፡፡ ሕወሓት ግን እስከ መሀል አገር ድረስ ለጥፋት ተሰማርቷል፡፡ እኔ በግሌ በጦርነት የማምን ሰው አይደለሁም፡፡ በመገዳደል አዙሪትም ችግር ይፈታል ብዬ የማስብም አይደለሁም፡፡ ሀቀኛ በሆነና ሰጥቶ በመቀበል አምናለሁ፡፡ አገር ለልጆቹ እንደሚያወርስ ሰው በልዩነቶቻችን ላይ ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን፡፡ አገሮች በየዘመናቱ ይሠራሉ  ይታደሳሉ፡፡ ዝም ብለው አይቀጥሉም፡፡ ሁል ጊዜም የዘመኑ ልሂቃን ይመጣሉ፣ ለዘመኑ በሚመች ሁኔታ እያስተካከሉ ይሄዳሉ፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ፣ ጂኦፖለቲክስና ኢኮኖሚ ጋር በሚመች ሁኔታ እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ መነጋገር ወንጀል አይደለም፡፡ የሁላችንም ተስፋ ዕውን የሚሆንባትን አገር እንዴት እናድርጋት ብሎ መነጋገር የዘመኑ ልሂቃን የቤት ሥራ መሆን አለበት፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ በጠመንጃ አፈሙዝ አይሆንም፡፡ አፈሙዝ ያጠፋል እንጂ አያለማም፡፡ በአፈሙዝ ሰላም መጥቶ አያውቅም፡፡ ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በመነጋገርና በመወያየት ብቻ ነው፡፡ የጥፋት ጩኸት አለመኖር ማለት ሰላም አለ ማለት አይደለም፡፡ በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ (የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ) መወያየትና መነጋገር አለበት፡፡ እስካሁን ብዙ መቶ ሺሕ ወጣቶችን አጥተናል፡፡ እያንዳንዱ አዋጊ መኮንን የራሱን ልጆች በእነዚያ ውስጥ አድርጎ ያስብ፣ ይበቃል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የነበራት ተሰሚነት ምን ያህል እንዳሽቆለቆለ፣ ዲፕሎማሲያችን ምን ያህል እንደዘቀጠ፣ እንደ አገር ያለን ክብር በከፍተኛ ሁኔታ በሌሎች ጫማ ሥር የወደቀበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንን እያየን በዕብሪት ‹‹እንደመስሳቸዋለን፣ እናጠፋቸዋለን›› የሚለው ጨዋታ ለሕዝብ አይጠቅምም፡፡ ለመገዳደል ያለንን ቁርጠኝነት ያህል ለመነጋገርና ለመቀራረብ እናድርገው፡፡

ሪፖርተር፡- ጦርነቱ ከሁለቱም በኩል ባሉ ሥልጣን ፈላጊዎች መካከል የሚደረግ እንጂ የሕዝብ ፍላጎት አለመሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- የሥልጣን ሚዛን ወይም የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ከጨዋታ ውጭ የምታደርገው ነገር አይደለም፡፡ ደግሞም በደምሳሳው ብቻ ነገሩን ማስቀመጥም ፍትሕ መስጠት አይደለም፡፡ ለምሳሌ እንዳነሳሁልህ ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን በምንም ሁኔታ ‹‹በጎ ነገር አስቦ ይሆናል›› ብዬ ላስተባብለው የምችለው ነገር የለም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስቦ፣ ለትግራይ ሕዝብ አስቦ ‹‹ሺዎችን ገደለ›› ብለን ማሰብ አይቻልም፡፡ ይህ ሥልጣንን ለማግኘት ብቻ አይመስለኝም፡፡ ከሥልጣን ጋር ብቻ ማያያዙ ትክክል አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በአንድ ወቅት ሲናገሩ ምንም ይሁን ማንም ቢመጣ ከኢሕአዴግ የባሰ ስለማይመጣ፣ በማንኛውም ሁኔታ ኢሕአዴግ (ሕወሓት) ከሥልጣን ማስወገድ ያስፈልጋል ብለው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ለቆ ብልፅግና ተተክቷል፡፡ የብልፅግናን አመራር ወይም ገዥው የብልፅግናን መንግሥት እንዴት አገኙት?

አቶ አንዱዓለም፡- በትክክል እንደዚያ ማለቴን አላስታውስም፡፡ ግን ኢሕአዴግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ መውረድ አለበት የሚለው ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ልዩነት የለም፡፡ ከቀመሩ የወጣው ሕወሓት ብቻ ነው፡፡ ሕወሓት ሲወጣ አጋር የነበሩ ድርጅቶች ገቡ፡፡ ከዚያም ኢሕአዴግ የሚባለው ስያሜ ቀርቶ ብልፅግና ተባለ፡፡ ኦሕዴድ ወደ የኦሮሞ ብልፅግና፣ ብአዴን የነበረው ወደ አማራ ብልፅግና፣ ወዘተ ሆኖ ብሔር ተኮር የሆነው የውስጥ አሠላለፍ እንዳለ ቀጠለ፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሕወሓት ሲከተለው የነበረው የብሔር አስተሳሰብ አሁንም አለ፡፡ በብልፅግና በኢሕአዴግ (ሕወሓት) መካከል ያለው ልዩነት ምን ያህል መከራ እንዳመጣብን ሁሉ፣ በብልፅግና ውስጥ ባሉት ድርጀቶች ውስጥ ያለው ዘር ተኮር መገፋፋት አሁንም እንዳለ ነው፡፡  ሌላ መከራ እንዳያመጣብን እሠጋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ስለሆነው ነገር ብልፅግና ብቻ ‹‹ኃላፊነት ይወስዳል ወይ?›› እሱን አላውቅም፡፡ ሕወሓትም ተጠያቂ ነው፡፡ ምክንያቱም አጠቃላይ የግጭቱ ጠንሳሽና ማን ይደፍረኛል ባዩ እሱ በመሆኑ፡፡ በመንግሥትም አጠቃላይ የጦርነቱን አስከፊ ሁኔታ ቀድሞ አስቦና አስልቶ የመሄድ ውስንነት በመኖሩ እሱም ተጠያቂ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ በሁሉም ላይ ከትናንቱ አለመማር አለ፡፡ ደርግ ከንጉሡ፣ ሕወሓት ከደርግ፣ ብልፅግና ደግሞ ከሕወሓት ውድቀት መማር አልቻሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ብልፅግና ከኢሕአዴግ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ ቢኖርም፣ በኑሮ ውድነት፣ በመፈናቀል፣ በስደት፣ ወዘተ የባሰ ሆኗል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡- ሁሉንም በአንድ ብርድ ልብስ መጠቅለሉ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ቢያንስ በመጀመርያው ዓመት ላይ የነበረው በጎ ፈቃደኝነት፣ ለመወያየት የነበረውን ተነሳሽነት አለማድነቅ አይቻልም፡፡ የነበረውም ነፃነት በጎ የሚባልና የሚያስመሠግን ነበር፡፡ ነገሮች የተበላሹት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመጣ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ከኢትዮጵያ ውጥንቅጥ አንፃር ሲታይ በጎ የሚባል ነበር፡፡ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መምጣት ጋር ተያይዞ የምርጫ መራዘም መጣ፡፡ ከምርጫ መራዘሙ ጋር የተፈጠሩ ውዝገቦች ብዙ ነገር አበላሹ፡፡ ቀጥሎም ጦርነት መጣ፡፡ በሰው ሕይወት፣ በኢኮኖሚና በብዙ ነገር ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ ቀጠሉ፡፡ እንደ ነጋ አስበነው የነበረ ነገር ሁሉ ጠፍቶ በፊት ወደ ነበርንበት የተመለስን ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመቶ ሺሕ በላይ ወገኖች መሞታቸው ይነገራል፡፡  ለእነዚህ ወገኖች ዕልቂት ምክንያት የሆነው ደግሞ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ሕግን መሠረት ያደረገ የድንበር አከላለል ባመኖሩ፣ በሁለት ሰዎች ስምምነት ብቻ በመፈጸሙና ግጭት ሲፈጠር መዳኛ የሚሆን ሕግ ባለመኖሩ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ ከሃያ ዓመታት ጦርነት ወይም ሰላም በሌለበት ሁኔታ የቆዩት ሁለቱ አገሮች በለውጡ ማግሥት ሰላም አውርደዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የተፈጠረው ግንኙነት የሕግ መሠረት ስለሌለው (በግልጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተነገረ)፣ ቀድሞ የተፈጠረው ነገር ሊደገም ይችላል የሚል ሥጋት አለ፡፡ እንደ ኢዜማ በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ያላችሁ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- አለመታደል ሆኖ የኤርትራ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማለት በቅተናል፡፡ ነገር ግን የኤርትራ ሕዝብ ደምና ሥጋችን ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ የራሱን መንግሥት መሥርቷል፡፡ ይህንን አለማክበር አንችልም፣ እናከብራለን፡፡ ነገር ግን ሁለት አገር እስከሆንን ድረስ ነገሮች በሕግና በሥርዓት መመራት አለባቸው፡፡ አቶ መለስ ስለኤርትራ ዜጎች፣ ‹‹የኤርትራ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተገባ ጥቅም እያገኙ ነው፡፡ የውጭ አገር ዜጋ ከሆኑ እንደ ውጭ አገር ዜጋ መታየት የለባቸውም ወይ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹ጠይም ዘለግ ያለ መልከ መልካም ዓይቻለሁ ከሆነ ኢሳያስ አፈወርቂ አይደለም›› ብለው ሲሳለቁ ትዝ ይለኛል፡፡ ሕዝቡ ቀደም ብሎ ይህ ነገር አያዋጣም ብሎ ነበር፡፡ እንደተባለው በሁለቱ መሪዎች መካከል ወዳጅነት ነበር፡፡ መጨረሻም ላይ ሁለቱ መሪዎች አልተዋጉም፡፡ ‹‹ትክክል አይደለም›› ሲል የነበረው ሕዝብ ነው ደም መፋሰስ ውስጥ የገባው፡፡ ወንድም ወንድሙን የሚገልጽበት ክፉ ዘመን ተፈጥሮ ዓይተናል፡፡ ከዚያ በኋላም እንዳልከው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት መጥፎ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ተዓምር በሚመስል ሁኔታ ስምምነት ፈጥረው ሕዝቡ እጅግ ተደስቷል፡፡ ነገር ግን ‹‹ኢትዮጵያ ከዚህ ግንኙነት ምን ታተርፋለች? ለኤርትራ ሕዝብ የምንሰጠው ምንድነው? ቀጣይ ሁኔታችን በምን ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነው? ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ግንኙነታችን ምን ይመስላል?›› ተብሎ ተተንትኖና ሕዝቡ በሚገባው ሁኔታ የተሠራ ሕጋዊ ነገር የለም፡፡ በጎ ሁኔታው ጥሩ ቢሆንም ልክ በአቶ መለስና አቶ ኢሳያስ መካከል የነበረውን ግንኙነት የሚመስል ነገር ነው ያለው፡፡ ተቀራርቦ መሥራቱ አይደለም ከኤርትራ ጋር ቀርቶ ከቀጣናው አገሮች ጋር አብሮ መሥራት ጥሩና መሆን ያለበት ነገር ነው፡፡ ያ ግን በሕግና በሥርዓት ሆኖ በግልጽ በተቀመጡ ፍላጎቶች ላይ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያዊነት ለእርስዎ ዜግነት ነው ወይስ የማንነት መገለጫ?

አቶ አንዱዓለም፡- ለእኔ ሁለቱንም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይህ የተትረፈረፈው መልካም ነገር ብቻ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከውድቀት፣ ከድህነትና ከጦርነት ጋር አያይዘን እናየዋለን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ድህነቱ፣ ሥቃዩ፣ አብረን ያሳለፍነው መልካም ነገር፣ ጋብቻው፣ ፌሽታው፣ ቀብሩ፣ እምነቱ፣ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ወዘተ ውስጥ የምታየው ነው፡፡ ይህንን ከመቀበል ዜግነት ይመጣል፡፡ ስለዚህ ለእኔ ሁለቱም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ በተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች ሲፈጠሩ ወይም ጉዳት ሲደርስ መግለጫ ከማውጣት ባለፈ፣ እንደ ፓርቲ ጥልቅ ጥናት አድርጎ አገሪቱ ከችግር የምትወጣበትን የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርብ አይታይም፡፡ አገራዊ ፓርቲ እንደ መሆኑ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር ምን እየሠራ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ተንትኖ ማስረዳት ያስቸግራል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተወሳሰበ ችግር ነው ያለው፡፡ እንዳልከው ለዚህ ውስብስብ ችግር ከፖለቲከኞች መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ እንደተባለው የተለያዩ መግለጫዎችን አውጥተናል፡፡ ይህንን ያደረግነው ግን መንግሥት ዝም ብሎ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዲያልፈው አይደለም፡፡ ከመግለጫው ግብዓት የሚሆነውን እየወሰደ ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ይሠራል ብለን በማመን ነው፡፡ ዳግሞም እየወሰደ ሲተገብርም ዓይተናል፡፡ መንግሥት ሲሳሳት፣ እንደፈለገው ሲሠራ፣ አገር ቁም ስቅሏን ስታይ ከመግለጫ ባለፈ ምንድነው የምናደርገው? የሚለው ያስጨንቃል፡፡ አገር ስትጎዳና ወጣቶች ሲያልቁ አቅመ ቢስ መሆን ያማል፡፡ ምንም ማድረግ ሳይቻል ሲቀር አንዳንድ ጊዜ ፖለቲከኛነት ትርጉም ያጣል፡፡ ኢዜማ ገና ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ ከመግለጫ ባለፈ ለመሥራት በደንብ የተደራጀና ዓይነ ግቡ የሆነ ፓርቲ መሆን አለበት፡፡ አሁን ግን ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ድርጅቱ በእግሩ ሲቆምና ጉልበት ሲኖረው ከመግለጫ ባለፈ ወደ ድርድር ይመጣል ማለት ነው፡፡ እስከዚያ ድረስም ሕጉ በሚፈቅደው ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዜማ ትይዩ ካቢኔ (ሻዶ ካቢኔ) አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እስካሁን በሠራቸው ተግባራት ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል? በመንግሥት በኩል ምን ገጠመው? ተቃውሞ ወይስ ድጋፍ?

አቶ አንዱዓለም፡- የፓርቲያችን አወቃቀር የተለያየ ነው፡፡ በአንድ ክንፍ በኩል በዋና መሪው ይመራል፡፡ በሌላው ክንፍ በኩል ደግሞ በሊቀመንሩ ይመራል፡፡ በሊቀመንበሩ የሚመራው የፓርቲው መዋቅር ሲሆን፣ የፖለቲካው መዋቅር ደግሞ በመሪው ይመራል፡፡ ለክልል የሚመረጡ ሰዎች የፖለቲካን ክንፍ ይመራሉ፡፡ ለምሳሌ በአገራዊ ምርጫው ብንመረጥ ኖሮ የተለያዩ የሚኒስትር ቦታዎችን የሚይዙ ሰዎችን አዘጋጅተን ነበር፡፡ ካልተመረጥን ወይም ምርጫውን ከተነጠቅን ደግሞ በፓርቲያችን በተቀመጠው በመዋቅራችን መሠረት የጥላ (ሻዶ) ካቢኔ ማደራጀትና በየዘርፉ ተሰማርተን በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉ ችግሮችን እያጣራን እንድንሠራ ማድረግ ነበር፡፡ ከተቋቋመ ቅርብ ጊዜ በመሆኑ ገና ብዙ አልሠራንም፡፡ እስካሁን ባለው በኑሮ ውድነት ላይ ጥናት አቅርበው በሕዝብ ግንኙነት በኩል ለሕዝብ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ሌላም እየተሠራ ነው፡፡ ገና እየተሠራ እንጂ ለሕዝብ የደረሰ ነገር የለም፡፡ ግን መንገዱን ይዘነዋል፡፡ እያስተካከልንና እየሠራን እንሄዳለን፡፡ ከመንግሥት የመጣብን ተፅዕኖ የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ በጎ አቀባበል አድርገውልናል፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ አገራዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ አገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚረዳ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስለመቋቋሙና የኮሚሽነሮች ስያሜ ላይ ኢዜማ ያለው አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ሁልጊዜም ስንፈልገው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንዲያሰራራ፣ የዜግነት ሐሳብ በሰማያችን እንዲሞላ፣ ዜጎች ሁሉ እኩል እንዲታዩባት፣ ሳይሸማቀቁ ተከብረው እንዲኖሩባት አገር እንድትኖረን ነው ስንታገል የቆየነው፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ግን የዜግነት ፖለቲካ ተደፍቋል፡፡ የዘር ፖለቲካ ገዝፏል፡፡ ሰው በአስተሳሰቡ ጥራትና በብቃቱ የማይመዘንበት፣ በስሙና በዘር ሐረጉ የሚመዘንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ ያሳዝነኛል፡፡ እንደ አንድ አገር ልጆች የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ በሐሳብ ከመሸናነፍ ይልቅ፣ በአፈሙዝ መሸናነፍ የባህላችን ምሰሶ ሆኗል፡፡ የፈለግነው የሰላም አስተሳሰብ ባህል እየተቀበረ፣ የጦረኝነት ባህል እንደገና እየገዘፈ መጥቷል፡፡ ይህ ዘመን ጠገብ የሆነ ክፉ ደዌ እንዲላቀቀን ቢያንስ ለ50 ዓመታት ያህል የዕርቅ ፖለቲካ ያስፈልጋል የሚለውን ነገር በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በተደጋጋሚ መሪዎቻችን ዕርቅ አያስፈልግም፣ ውይይትም አያስፈልግም የሚሉ ምላሾች ሲሰጡም ቆይተዋል፡፡ በብልፅግና መንግሥት ‹‹እንወያይ፣ ይህንን አገር ወደፊት ልንወስደው የምንችለው በመወያየት ነው›› ከተባለ ጥሩ ነው፡፡ የብሔራዊ ዕርቅ አጀንዳም እኛ ተቃዋሚዎች ለዓመታት ስናቀርበው የነበረ ነው፡፡ እሱንም ተቀበሉ፡፡ ይህ ጥሩ ነው፡፡ ግን ያ የዕርቅ ኮሚሽን ምንም ሳይሠራ ተበተነ፡፡ የድንበርና የማንነት ኮሚሽንም ተቋቁሞ ትንሽ ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ ግን ቆሟል፡፡ አሁን ደግሞ አገራዊ ምክክር ወደሚለው ደርሰናል፡፡ አጀንዳ መንጠቅ ችግር የለውም፡፡ ወስዶ ማበላሸት ግን ክፋት ነው፡፡ አሁን የተጀመረው የአገራዊ ምክክር ሐሳብ አጀንዳ ከመንጠቅ ማለፍ አለበት፡፡ ከሆነና ከተሳካ የኢትዮጵያ ዕድል የተንጠለጠለው እዚህ ላይ ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ አንዱ የአገር ባለቤት፣ ሌላው ባይተዋር የሚሆንበት ሁኔታ የትም አያደርሰንም፡፡ ለመወያየት ከመንግሥት በኩል ድፍረት መታየቱን አደንቃለሁ፡፡ ለውይይትና ለመመካከር ቦታ ለሚሰጡት ሁሉ ትልቅ አክብሮት አለኝ፡፡ ወደ ዕርቅና ሰላም መምጣት የመሠልጠን ጥግ ነው፡፡ አሁንም የያዝነው መንገድ ከኮሚሽኑ መቋቋም ጀምሮ የመጣደፍ ሁኔታ አለ፡፡ ረጋ ብሎ በሰከነ ሁኔታ ሁሉንም የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት መሆን አለበት፡፡ ኢዜማ በጣም የሚደግፈው ነው፡፡ እውነተኛ የሆነ ምክክር፣ ውይይትና ሰጥቶ የመቀበልና ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ መሪዎች፣ ዘመኑን የሚመጥኑ ልሂቃን ተሰባስበው የሚወያዩበት ሁኔታ እንዲመጣ ትልቁና ዋናው  ምኞታችን ነው፡፡ ግን አሁን እንደሚታየው ሁሉንም በሕጋዊነት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ እንቅስቃሴ ስለሆነ፣ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ  እንዳይሆን ሁሉንም ማካተት አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ፈውስ ስለሚሆን ይህንን ዕድል ተጠንቅቀን ማካሄድ አለብን፡፡ ሁሉም የፈለገውን ሙሉ በሙሉ እንዲያገኝ ሳይሆን፣ ከሁሉም የተወሰነ የተወሰነውን ወስዶ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን፡፡ አሸናፊዋ አገር ነችና ሁላችንም በቀናነት መሳተፍ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ በመነሳት ልትፈርስ ዳር የደረሰች አገር ሆናለች የሚሉ ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ  ትፈተን ይሆናል እንጂ መቼም አትፈርስም የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አገር በመፈክር አይፈርስም፣ በመፈክርም አይቀጥልም፡፡ ቀደም ብለን እንደተነጋገርነው መሥራት ያለብንን በአግባቡና በደንብ ከሠራን አገር ይቀጥላል፡፡ ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ፣ አመራርና ልሂቃን ካለን አገር ይቀጥላል፡፡ ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ ባለቤት የሆነ ሕዝብ፣ ምሁራን፣ ልሂቃንና መሪዎች ከጠፉ አገር ይፈርሳል፡፡  ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለውና እስካሁንም ያቆየን በልሂቃኑ ብስለት አይደለም፡፡ ልሂቃን እንዲያውም የችግር ምንጭ ናቸው፡፡ ግን ኢትዮጵያ የተገመደችበት ቋንቋው፣ አመጋገቡ፣ አኗኗሩ፣ ወዘተ መቼም አይነካም፡፡ መሠረቱ ጠንካራ ነው፡፡ ግን ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድግ አለብን፡፡ ካለበለዚያ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ የሚችሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ለቀጣይነቷ ደግሞ የሚሞቱና የሚሰው እንዳሉ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በማፍረስ ማንም አይጠቀምም፡፡ አንድ ብሔር ሲጠቃ የሁሉም ሕመም ነው፡፡ ወይ አብረን እንነሳለን ወይም አብረን እንጠፋለን፡፡ አጠፋፋችን ግን በጣም አስቀያሚ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመጎዳቱ ዜጎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚውን ለመታደግና የዜጎችን ችግር ለማቃለል ኢዜማ ምን እየሠራ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- አጠቃላይ ችግር የሚጀምረው ከፖለቲካው ነው፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋት የኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡ የማኅበራዊ ቀውስም ያመጣል፡፡ የፖለቲካ መብቶች ባልተከበሩበት ሁኔታ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን ማስተካከል ከባድ ነው፡፡ የተረጋጋ ፖለቲካ በሌበት አገር ውስጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ መረጋጋት አለበት፡፡ በሰው መብት ላይ ቆሞ ዳቦ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ሰላም ከተፈጠረ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ገብተው ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ የአገር ውስጥ ምርታማነትንም ማሳደግ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ለኢኮኖሚው መረጋጋት የፖለቲካው ሒደት ሰላማዊና የተረጋጋ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ውዝግቦች ይነሳሉ፡፡ አዲስ አበባ ትልቋን ኢትዮጵያ ማሳያ ትንሿ ኢትዮጵያ ነች የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አይ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ነች የሚሉ አሉ፡፡ የኢዜማ አቋም ምንድነው? 

አቶ አንዱዓለም፡- ኢዜማ የሚያራምደው የዜግነት ፖለቲካ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለእኛ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ሁሉም ዜጎች በነፃነት በፈለጉበት ቦታ የዕውቀትና የገንዘብ አቅማቸውን ተጠቅመው ማልማትና መኖር መብታቸው ነው፡፡ በሕግና በሥርዓት ተከባብረን የምንኖርበት ሁኔታ መጠፈር አለበት፡፡ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንኳን ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ የአገሩ ዜጋ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጉ እየኖሩ ነው፡፡ በአገርህ ላይ ደግሞ የበለጠ ክብር፣ በራስ መተማመንና ምቾት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ስለዚህ በእኛ እምነት ኢትዮጵያውያን በአራቱም አቅጣጫ የሚመሩበት ሕግ ኖሮ መመራት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ አዲስ አበባም በዚሁ በትልቁ ማዕቀፍ ውስጥ ናት፡፡ መንገድ ላይ እንኳን ወጥቶ ትንሿን ኢትዮጵያ ማየት ይቻላል፡፡ ሁሉም ብሔር የሚኖርባት ከተማ ነች፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ የኦሮማ ሕዝብ ተጋብቶና ተዋልዶ በፍቅር የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ ይኼ ሕዝቡን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚፈልጉ ልሂቃን ፍላጎት ነው፡፡ የምቀኝነትና የዘረኝነት ፖለቲካ ለማንም አይጠቅምም፡፡

ሪፖርተር፡- በጦርነትና በድርቅ ምክንያት በተለይም ከአማራ፣ አፋርና ከኦሮሚያ ክልሎች በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ዜጎች ከመታደግ አንፃር ኢዜማ ምን እየሠራ ነው?

አቶ አንዱዓለም፡- ኢዜማ እንደሚታወቀው ከመንግሥት የሚያገኘው ሀብት (ሪሶርስ) የለውም፡፡ የአቅማችንን ለመርዳት ግን የተለያዩ ጥረቶችን እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን መንግሥት በቅድሚያ ጦርነቱ ቆሞ ወደ ውይይት የሚመጣበትን ሁኔታ እንደ ፖሊሲ ይዞ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ሕዝቡን ማወያየትና በጋራ መፍትሔዎችን መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ከሆነ መልሶ ማቋቋም ቀላል ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ባለፉት ሳምንታት ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ጋዜጠኞችን፣ አክቲቪስቶችንና የተለያዩ ግለሰቦችን እያፈኑና እያሰሩ መሆናቸው በርካቶችን አሳስቧል፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው? የሚል ጥያቄም እያነሱ ይገኛሉ፡፡ በእዚህ ላይ እርስዎ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- እንደ ኢዜማ እኛ ቀደም ብለን የክልሎችን ልዩ ኃይል መቋቋምን ስንቃወም ቆይተናል፡፡ አገር ያጠፋል፡፡ በየክልሉ ልዩ ኃይል እየተባለ ትንንሽ አገሮች እየተፈጠሩ ነው ብለን ስንቃወም ነበር፡፡ ትግራይ ውስጥ ምን እንደተፈጠረ ዓይተናል፡፡ በመከላከያ ወይም በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ እንዲካተቱም አሳስበን ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ከመቶ ዓመታት በፊት የነበረው ሁኔታ ልክ የአሁኑን ይመስል እንደነበር ሪቻርድ ፓንክረስት በመጽሐፋቸው አስፍረውት ይገኛል፡፡ በዚያን ወቅት መሣሪያን እንደ ልዩ ሀብት የማየት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁንም የተፈጠረው ይኸው ነው፡፡ ግን ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል የሚቻለው በፖሊሲ ደረጃ ታስቦበት በሥርዓትና በሕግ እንጂ አሳዶ በማሰር አይደለም፡፡ ማሰር መሸነፍ ነው፡፡ ጋዜጠኛንም ሆነ ታጣቂን ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው በማፈን ሳይሆን፣ ማስረጃ ይዞና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሚያስተምር ሁኔታ መሆን አለበት፡፡ ማፈንና ማሰር አያስተምርም፡፡ ሌላ ቂም በቀል ማትረፍ ነው፡፡ የሚያዋጣው ሕግና ሕግን መከተል ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ አገሮች ጋር ያላት ቀጣይ ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡- በጣም እየተወሳሰበ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡ አዲስ አሠላለፍም ሊመጣ ይችላል፡፡ አካባቢው በቀንዱ አካባቢ የሚገኙት አገሮች ብቻ ሳይሆን የትልልቅ አገሮችም ፍላጎት ያለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ግንባር ቀደም አገር ተብላ የምትጠራ ነበረች፡፡ ያ ትልቅነቷ ግን አሁን ላይ እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል፡፡ ሱዳን ከግብፅ ጋር ባላት ወዳጅነት ኢትዮጵያን እንደ ጠላት ማየት ጀምራለች፡፡ በተወሰነ ሁኔታ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ግንኙነት በጎ ይመስላል፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ከጦርነት ይልቅ ወደ ሰላም የመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ከጂቡቲ ጋር ያለን ግንኙነት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያለበት ነው፡፡ ከሶማሊያ ጋር አሁን ያለንበትን ሁኔታ ብዙም አላውቀውም፡፡ ምንም ይሁን ምንም ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን የተሰሚነት ቦታ ለማስመለስ መሥራት አለባት፡፡ ከኤርትራ ጋር ሕግን መሠረት ያደረገ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ከሁሉም ጋር ሕግን መሠረት ያደረገና የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ትስስሩ የፖለቲካ ትብብር ሊያመጣ ስለሚችል የመሪነትን ብልኃት በመጠቀም ውጥረቶችን አርግቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ጂኦፖለቲካውን ተረድቶ ለኢትዮጵያ በሚጠቅም ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በፌዴራል መንግሥትና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እንዲቆም፣ በተለይ አሜሪካ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረገች መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ሕግ በማርቀቅ ጭምር እያደረገችው ያለው ተፅዕኖ ላይ የኢዜማ አቋምና አስተያየት ምንድነው?

አቶ አንዱዓለም፡- የሚለምን ሰው በድሎት ከሚኖር ሰው ጋር በሰውነት ደረጃ ተመሳሳይ ቢሆንም እኩል ግን አይደለም፡፡ ምክንያቱም በድሎት የሚኖረው በመኪና እየሄደ፣ ደሃው ከእሱ ቁራሽ ይለምናልና፡፡ በሕግም ባይሆን የሚያጎበድድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ህልውናውን ለማቆየት ቁራሽ ለመለመን ይገደዳል፡፡ ከኃያላን አገሮችም ጋር ያለው ይኸው ነው፡፡ የኢኮኖሚ አቅማችን እስከተዳከመ ድረስ በእነሱ ፍላጎት እንድንገዛ የሚፈጠርበት ሁኔታ አለ፡፡ ያለ እነሱ ዕርዳታ ኢኮኖሚያችንን ማስቀጠል አንችልም፡፡ ይህ ሲታይ ግን ኢሰብዓዊ ነው፡፡ በአንድ አገር ሉዓላዊነቱ ላይ ሳትደርስበት፣ ብዙ ሺሕ ማይልስ አቋርጦ መጥቶ ‹‹አንተ በዚህ ግባ፣ አንተ በዚህ ውጣ›› ሲልህ ክብርን የሚነካ  ነው፡፡ ብዙ የተወሳሰበ ነገር ቢኖርም ተገቢ አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ ያመጣብን የአገራችን የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው፡፡ ክብራችንን ያጣነው በራሳችን ነው፡፡ መመለስ ያለብን ራሳችን ነን፡፡ ትናንት ሕዝብ ረግጠው ሲገዙ የነበሩ፣ ዛሬ እዚያ ሄደው ስለሰብዓዊነት ይሰብካሉ፡፡ ይህ አዙሪት እስካልተገታ ድረስ ላልተገባ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ እንሆናለን፡፡ በጋራ ከቆምንና ቀዳዳችንን ከዘጋን ሁሉም ያከብረናል፡፡ ጣልቃ ገብነትን የሚያስፋፉ ነገሮችን ማጥፋት የምንችለው ራሳችን በራሳችን የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታት ስንችል ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሩሲያና ዩክሬን በጦርነት ውስጥ ናቸው፡፡ በሁለቱ አገሮች ጦርነት ምክንያት አገሮች ውግንናቸውን ለሁለቱም አገሮች እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ከዲፕሎማሲ አንፃር የኢትዮጵያ አቋም ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡- የሁለቱ አገሮች ጦርነት በሌሎች አገሮች ላይ እያደረሰ የሚገኘው የኢኮኖሚ ችግር በኢትዮጵያም ላይ እየታየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ከዲፕሎማሲ አንፃር የምትከተለው የገለልተኝነት ፖሊሲ ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮችም ወገን ለይታ መቆም አይገባትም፡፡ ትክክለኛ አቋም ላይ ነች የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ ወገንተኝነት ከሰላም ጋር መሆን አለበት፡፡ ከጦርነት ምንም የሚገኝ ነገር የለምና፡፡ አንዳንድ ጊዜ የራስህን ችግር ሳትፈታ ስለሰላም ስታወራ አሳፋሪ ቢሆንም፣ አባቶቻችን ከኮሪያ ዘመቻ ጀምሮ ሲሠሩት የነበረ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰላም ነውና ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ጥሩ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና...

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበች በሰፊው ሲወራ ሰንብቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት የቅርቡ...

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...