Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ሲሚንቶ ዶላር ሆኗል››

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዓመታት የዘለቀው የሲሚንቶ ችግር አሁን ላይ ብሶበታል፣ ከዚህም አልፎ ለብዙ ለሕገወጥ ተግባራት ሁሉ በር እየከፈተ መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ኮንትራክተር ይገልጻሉ፡፡ እኝህ ኮንትራክተር እንደሚሉት ‹‹ሲሚንቶ ዶላር ሆኗል›› በሲሚንቶ ግብይት ውስጥ ያለው ሥር የሰደደ ችግር ካልተቀረፈ ለኢንዱስትሪው ውድቀት ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ይሠጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ከፍተኛ አበርክቶ አለው፡፡ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ትልቅ ዘርፍ ስለመሆኑም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሶሴሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ ለዓመታት ባልተቀረፉለት ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች መወደድና እጥረት ለብዙ ፕሮጀክቶች ግንባታ መስተጓጎል ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል፡፡

በተለይ የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ንረት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ አሁንም ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እየተፈተነ ነው፡፡

አሁን ላይ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ እስከ 1,300 ብር እየገዙ መሆናቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ኮንትራክተር ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ዋጋ ተገዝቶም እንኳን ትክክለኛ ደረሰኝ ማግኘት እንደማይቻል በመግለጽ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ብልሽት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በ1,300 ብር ለገዛነው ሲሚንቶ ደረሰኝ ሲጠየቅ ሻጮቹ የ480 ብር ወይም 520 ብር ደረሰኝ ነው የምንቆርጠው እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ስለዚህ የሲሚንቶ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢና መፍትሔ የጠፋለት ጉዳይ ሆኖብናል›› ይላሉ፡፡ የእኚህን ኮንትራክተር ሐሳብ የሚጋሩት የኢትዮጵያ የኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ኃብተ ማርያም፣ ዘርፉ ድርብርብ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የሲሚንቶ ዋጋን መቆጣጠርና ግብይቱን ማስተካከል አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡ የሲሚንቶና የሌሎች ግብዓቶች ዋጋ ንረት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እየጎዳና ነገሮች ሁሉ ከአቅማቸው በላይ እየወጡ መሆናቸውን በምሬት ይናገራሉ፡፡ ከሲሚንቶ ዋጋ ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ችግር በምሳሌነት ያቀረቡት አቶ ግርማ፣ ሰሜን ጎንደር ያለ አንድ ፕሮጀክታቸውን ለመጨረስ ከፋብሪካ ሲሚንቶ ማግኘት ባለመቻላቸው በ1,300 ብር ሲሚንቶ ገዝተው የማጠናቀቅ ሥራቸውን እየሠሩ ነው፡፡ የጎንደሩን ፕሮጀክት ሲዋዋሉ ሲሚንቶ በ400 ብር ከገበያ አገኛለሁ በሚል ነበር፤ አሁን ግን ሁለትና ሦስት እጥፍ ዋጋ እያስከፈላቸው ሲሆን በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱን ዘግይተው ለመጨረስ ተገደዋል፡፡ ሲሚንቶ ገበያ እንዲህ መበላሸት ኮንትራክተሩን፣ ሠራተኞችንና ተያያዥ ቢዝነሶችን በአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚውን እየጎዳ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ ከፋብሪካ ከ500 ብር ያልበለጠ ዋጋ ያለው የሲሚንቶ ገበያ ላይ እስከ 1,300 ብር ሲሸጥ ይህንን የሚያስተካክል ተቆጣጣሪ አካል መጥፋቱ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ያሰምሩበታል፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ ይህ ጉዳይ አገር እንዳያፈርስ የሚል ሥጋት እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ግርማ፣ የሲሚንቶ እጥረት በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውሉ እንደጠፋበት ይገልጻሉ፡፡

‹‹ከአንድ ዓመት በፊት ከ500 እስከ 700 ብር ሲሸጥ ጉድ እንዳላልን አሁን ጭራሽ እስከ 1,300 ብር ድረስ ዋጋ እየተጠየቀበት መሆኑ ሳያንስ፣ በፋብሪካ የለም የተባለ ሲሚንቶ በጥቁር ገበያ ያለ ምንም ችግር ሲቸበቸብ ማየት ሕግና ሥርዓት መፋለሱን ያሳያል፤›› ሲሉ አቶ ግርማ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ግንባታዎች መቆማቸውንና በሠራተኞች የሥራ ዋስትና ላይም አደጋ ይዞ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዘገየ ሀብተ ሥላሴ በበኩላቸው በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ግንባታዎች እየቆሙ መሆኑ በሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ላይ ጫና አሳድሯል ብለዋል፡፡  

ከአነስተኛ እስከ ትላልቅ ግንባታዎች በሲሚንቶ እጥረት እየተፈተኑ በመሆኑ ሠራተኞች ሠርቶ ለማደር ችግር እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ የብሎኬትና የትቦ ማምረቻዎች የሲሚንቶ እጥረቱ በፈጠረባቸው ችግር ሥራ እንዲያቆሙ እያስገደዳቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘገየ አንዳንዶቹ ጊዜያዊ ሠራተኞቻቸውን እያሰናበቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ሲሚንቶ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሲሚንቶን በግብዓት የሚጠቀሙ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾች ላይም ትልቅ ሳንካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለኮንስትራክሽን ዋነኛ ግብዓት የሚባሉት ሲሚንቶ፣ ብሎኬትና የመሳሰሉት ምርቶች ሳይኖሩ ግንባታ ማድረግ ስለማይቻል አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

ችግሩ በዚህ ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ዘገየ ለምሳሌ ግንባታዎች አካባቢ ሻይ፣ ቡናና ምግብ ከሚያቀርቡት ጀምሮ ሌሎች የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በመንተራስ የሚቀርቡ ንግዶች በሙሉ ጉዳት እንደሚገጥማቸው ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ የግብይት ችግር ዛሬ የተፈጠረ አለመሆኑን የሚገልጹት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች የግብይት ሒደቱን መስመር ለማስያዝ ያልተሞከሩ ነገሮች እንደሌሉ ነገር ግን ትክክለኛው መፍትሔ እስካሁን እንዳልተገኘ ጠቁመዋል፡፡ በሲሚንቶ ምርትና አጠቃላይ የግብይት ሒደቱን በተመለከተ አሉ የሚባሉ ችግሮች ከዛሬ 20 እና 25 ዓመታት በፊትም ሲነገሩ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በሲሚንቶ ግብይትና ዋጋ ዙሪያ ያሉ ችግሮች ሳይገለጹ የታለፈበት ዓመት የለም፡፡ ችግሩ በፓርላማ ጭምር ቀርቦ ብዙ ያወያየም ነው፡፡ መፍትሔ ይሆናል የተባሉ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ ቢባልም ውጤታቸው አልታየም፡፡ በተለይ ቢዝነሱ ፖለቲከኞች ጭምር ያሉበት በመሆኑ ሁኔታውን እንዳወሳሰበው ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ደግሞ ለችግሩ መባባስ የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦችን ካለመቀበል የመነጨ ነው፡፡ ‹‹የበዛ ሙስና የሚካሄድበት፣ ባለሥልጣን ለእከሌ ይህንን ያህል ሲሚንቶ ስጥ ብሎ የሚያዝበት በመሆኑ እንዲህ ያለው ሁኔታ ካልተቀየረ ከችግሩ አንወጣም፤›› ብለዋል፡፡

ቀደም ባሉ ጊዜያት የሲሚንቶ ገበያን ለማረጋጋት እጥረቱን ለመቀነስ፣ እንዲሁም በግብይት ውስጥ ያለውን ረዥም ሰንሰለት ለመበጠስና በየጊዜው እንደ ችግር ለሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ይሆናል የተባሉ ዕርምጃዎች በመንግሥት ቢወሰዱም ምንም ለውጥ ሊያመጣ ያልቻለበት ምክንያትም ይኸው የፖለቲካ ሰዎች እጃቸውን ማስገባታቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ካነጋገርናቸው የኮንስትራክሽን ባለቤቶች መረዳት እንደሚቻለው ለመፍትሔ የከበደው የሲሚንቶ ገበያ አሁን ላለበት የባሰ ችግር የገባው የምርት እጥረት ተፈጥሮ ሳይሆን ግብይቱን በአግባቡ ካለመምራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሲሚንቶ ግብይት ዙሪያ በቅርቡ በተደረገ የምክክር መድረክ ላይ የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ አሰግዴ እንደገለጹት የአገሪቱን የሲሚንቶ ፍላጎት ለመሙላት አራቱ ትላልቅ ፋብሪካዎች ብቻ በቂ ነበሩ፡፡ ከአሥር ሚሊዮን ኩንታል በላይ ያመርታሉ ማለታቸው በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡

በሲሚንቶ አምራቾች ዘንድ ችግሩ የማምረቻ ወጪ መጨመር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ችግር መሆኑን ቢገልጹም ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ከአቅም በታች ማምረታቸው ችግሩን እንዳባባሰው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡ አሁን ላይ ግን ችግሩን ለመቅረፍ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ሲሚንቶ አከፋፋይ ኤጀንቶች ከገበያ በማስወጣት ገበያውን ማረጋጋት ይችላል የሚል አቋም በመንግሥት ተወስዷል፡፡

ከሰሞኑም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ሆኖ በሰጠው መግለጫ ከዚህ በኋላ በክልሉ ሲሚንቶ የሚከፋፈለውና የሚሸጠው ሦስት ሺሕ አባላት ኖሯቸው በተዋቀሩ 300 ማኅበራት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ማኅበራቱን ያደራጀው ራሱ ክልሉ እንደሆነና በእነዚህ ማኅበራት በኩል ሥርጭቱ መደረጉ ገበያውን ያረጋጋል ብሏል፡፡

ደላሎችን በመቁረጥ የተጋነነውን ዋጋ የሚሸጥበትን አሠራር ለማስቀረት ክልሉ የደረሰበት ውሳኔ በአዲሱ የሲሚንቶ ሥርጭት ፋብሪካዎች ከሚሸጡበት ዋጋ አሥር በመቶ ብቻ ዋጋ አክለው የሚሸጡ በመሆኑ የተሰቀለው ዋጋ ይወርዳል፣ ገበያውም ይረጋጋል የሚል ውጥን ተይዟል፡፡

ይህ ውሳኔ ምን ያህል ተፈጻሚ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ግን አሁንም ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ‹‹ሲሚንቶ ዶላር ሆኗል›› ያሉት ኮንትራክተር ሰሞኑን በማዕድን ሚኒስቴርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በኩል ሊወሰድ የታሰበው ዕርምጃ መፍትሔ ያመጣል ብለው አያምኑም፡፡ ገበያው ከፖለቲካ ንክኪ መውጣት አለበት፣ እንደውም መንግሥት ከዚህ ወጥቶ ገበያውን ነፃ ቢያደርገው ገበያው ይስተካከላል የሚል እምነት እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ግርማ በበኩላቸው ‹‹እስካሁን የማከፋፈሉን ሥራ ይዘው የቆዩት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ዘመዶች ናቸው፡፡ እነዚህን አነሳን ብለው ጥቃቅንና አነስተኛ አደራጁ፡፡ እነዚህ ተደራጅተው የመጡት ማኅበራት እስካሁን ሲደረግ የነበረውን ሥራ ላለማድረጋቸው ምን ዋስትና አለ? ከጀርባቸውስ ባለሥልጣናት ስላለመኖራቸው እንዴት ማወቅ ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ አሁንም ችግሩ ላይፈታ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን የገለጹበት ዋነኛ ምክንያት በዚህ ገበያ ቱባ የሚባሉ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ያሉበት በመሆኑ እነሱ እስካሉ ችግሩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

አከፋፋዮችን አውጥተናል ተብሎ የፖለቲካ ድጋፍ ያላቸው ወጣቶችን ማስገባት  መፍትሔ አያመጣም የሚሉት አቶ ግርማ መፍትሔው አጠቃላይ ሲስተሙን መቀየር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት የኮንስትራክሽን ግብዓትን በተመለከተ ዕርምጃ መውሰድ ከፈለገ ሥራው ቀላል እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ፋብሪካዎቹ ምን ያህል ሲሚንቶ እንደሚያመርቱ ይታወቃልና ማን ምን ያህል ሲሚንቶ ወሰደ? በማለት በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመሠራቱ ለግንባታ የተሰጠውን ሲሚንቶ መርካቶና መገናኛ ወስዶ መሸጥ ተለምዷል፣ ይህም ሙስና መኖሩን ያሳያል ይላሉ፡፡ አቶ ግርማ በበኩላቸው አንዳንድ ሙሰኛ ሕግ አስከባሪዎች በሕገወጥ መንገድ የሚሸጠውን የሲሚንቶ ምርት እያዩ ዕርምጃ እንደማይወስዱ፣ ከዚያ ይልቅ የሚቀበሉትን ተቀብለው ዝም እንደሚሉ ገልጸዋል፡፡ ነገሮች እንዲህ ዝም ተብለው ከቀጠሉ ሲሚንቶ አሥር ሺሕ ብር ሊገባ ይችላል ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ መናገር እንደሰለቻቸው የሚገልጹት አቶ ግርማ እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚፈተነውን ኮንትራክተር እንዴት ግንባታውን በጊዜ አልጨረስክም ብሎ መሞገት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ ኮንትራክተሮች በሲሚንቶና በሌሎች የግንባታ ግብዓቶች ግብይት ዙሪያ በምሬት የሚናገሩ ሲሆን፣ በመንገድ ግንባታ ላይ ያሉ ኮንትራክተሮች ግን ይህ ችግር ብዙም እንደሌለባቸው ይገልጻሉ፡፡ በመንገድ ሥራ ላይ ያሉ ኮንትራክተሮች ሲሚንቶ በቀጥታ ከፋብሪካ የሚያገኙ በመሆኑ በመንገድ ግንባታ ሥራ ብዙም እንዳልተቸገሩ ያነጋገርናቸው ኮንትራክተሮች ይገልጻሉ፡፡

አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔው መንግሥት እጅ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ ፕሮጀክት ያላቸው ኮንትራክተሮች በቀጥታ ከፋብሪካዎች ምርትን እንዲያገኙ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ ኮንትራክተሩ የፕሮጀክት ውሉን እያሳየ ከፋብሪካ እንዲገዛ የማይደረግ ከሆነ የግንባታ ዘርፉ አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዋል፡፡

ይህ እንዲሆን በተደጋጋሚ በደብዳቤ ጭምር መጠየቃቸውን የገለጹት አቶ ግርማ ነገር ግን እናደርጋለን የሚል ምላሽ እንጂ በተግባር የተየቀረ ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በነፃ ገበያ ስም ብዙ ችግር እየተፈጠረ ነውና ይህንን በመመልከት መንግሥት ዕርምጃ ይውሰድ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ሲሚንቶ ሻጮች በ1,300 የተገዛን ሲሚንቶ በ520 ብር ነው ደረሰኝ የምንቆርጠው እያሉ መሆናቸውን መንግሥት አያውቅም አንልም ያሉ ኮንትራክተሮች ከዚህ በላይ ሕገወጥነት ምን ሊኖር ይችላል? በማለት አሁንም የመንግሥት ቁርጥ ውሳኔ የሚጠብቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች