Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሁለት ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በሁለት ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል፣ ምርጥ ዘር ለማባዛትና የኤክስፖርት ሰብሎችን ለማምረት አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ጠየቀ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ባካሄደው የአዋጭነት ጥናት መሠረት በመስኖ ከሚያለማው አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ በስድስት ሺሕ ሔክታሩ ላይ ኤክስፖርት የሚደረጉ ማሾ፣ አኩሪ አተር፣ ቦለቄና ሰሊጥ ለማምረት አቅዷል፡፡ በቀሪው አራት ሺሕ ሔክታር ደግሞ ለኤክስፖርት የታሰቡ ሰብሎች ጨምሮ የበቆሎ፣ የሩዝና የማሽላ ምርጥ ዘር ለማብዛት ማሰቡን፣ የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች በሳምንቱ መጀመሪያ በቦንጋ ከተማ ከክልሉ አመራሮች ጋር ንግግር ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ጋሻው፣ ከክልሉ መንግሥት በኩል ፈቃደኝነት መታየቱንና የአዋጭነት ጥናቱን እየተመለከቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ እንዲሰጠው የጠየቀው መሬት በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከተፈቀደለት በአራት ዓመት ውስጥ አጠቃላይ መሬቱን ለግብርና ልማት ዝግጁ ለማድረግ አቅዷል፡፡ ፈቃዱ በተገኘ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 2,500 ሔክታር የሚሆነውን መሬት ለማልማት እንደታሰበም አቶ ጋሻው አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ አሁን የጠየቀው  አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ከተፈቀደለት በአዲሱ ደቡብ ምዕራብ ክልል የሚቀበለው ሦስተኛ መሬት ይሆናል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ከቦንጋ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታማሻሎ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ለምርጥ ዘር ሰብሎች የሚውል 1,070 ሔክታር መሬት ወስዷል፡፡ 

በቦንጋ ከተማ ደግሞ በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን ማዕከል እየገነባ ነው፡፡ ማዕከሉ ባለአራት ፎቅ ሕንፃና ትልልቅ መጋዘኖች የሚገነቡበት ሲሆን፣ ግንባታው ከ14 ወራት በኋላ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ150 ሺሕ ኩንታል በላይ ዘር ማዘጋጀት የሚችል የዘር ማበጠሪያ ማሽን መትከያ ቦታ፣ 120 ሺሕ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘኖች፣ እንዲሁም የላብራቶሪና የቢሮ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቦንጋ እየገነባ ያለው ማዕከል ወደ ተለያዩ አከባቢዎች ምርጥ ዘር፣ የእርሻ መሣሪያዎችና ማዳበሪያ ለማሰራጨት አማካይ ቦታ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቶ ጋሻው እንደሚያስረዱት፣ ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ በተለይ ቆላማ አካባቢዎች ላይ መሬት እየተቀበለ በመስኖ የኤክስፖርት ሰብሎችን የማልማት ዕቅድ አለው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአንድ ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ለምርጥ ዘር ማብዣ እንደተፈቀደለት የተናገሩት ኃላፊው፣ የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ቡድን ከተቋቋመ በኋላ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለጥናት ሳይሰማራ መዘግየቱን አስረድተዋል፡፡

ከጋምቤላ ክልል አመራሮች ጋር የተደረገው ንግግር ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ ንግግር ለማድረግ ማቀዱን አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች