በኢትዮጵያ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት እንዲወገድ ለማድረግ የአስታራቂነት ሚናዋን ለመወጣት እንድትችል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በይፋ ጠየቀች፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን ጥያቄ ለፌዴራል መንግሥት መላኳን ያስታወቁት ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ሳምንት ያካሄደውን ጉባዔ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡
ፓትርያርኩ ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ሲኖዶሱ ለአገርና ለሕዝብ ሰላም መገኘት፣ ለተሰደዱና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ መረጋጋትና ወደ ቀዬአቸው መመለስ ጦርነትና የሰላም ዕጦት በሚወገድበት ሁኔታ በመምከርና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ውሳኔዎችን ማሳለፉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መንገድ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ ቤተ ክርስቲያናችን የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከሰተው የሰላም ዕጦት ምክንያት በቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በካህናትና በምዕመናን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትን በአሳሳቢነቱ የዘረዘሩት ፓትርያርኩ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች መነጠቅ አስመልክቶ ጉባዔው መነጋገሩን፣ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥት አካላት ጥያቄው እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል፡፡
አክለው በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የደረሰውን ችግር በዓይነትና በቁጥር ተለይቶ ለመንግሥት አካላት መቅረቡንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባዔውን የሚያካሂደው ቅዱስ ሲኖዶስ ሁለተኛውን ጉባዔ ከግንቦት 9 እስከ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ማከናወኑ ታውቋል፡፡