Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተፈጥሮ ጋዝን በመጠቀም የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ለማቋቋም የአዋጭነት ጥናት ጨረታ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ ጋዝ ሀብትን በመጠቀም፣ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የአዋጭ ጥናት የሚያደርጉ ድርጅቶችን የሚጋብዝ ዓለም አቀፍ ጨረታ አወጣ፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጣው የፍላጎት ማሳወቂያ መንግሥት በአገር ውስጥ ለማቋቋም ላሰባቸው የማዳበሪያ ፋብሪካዎች የአዋጭነት ጥናት ተፈላጊውን መሥፈርት የሚያሟሉ፣ ፍላጎቱ፣ ብቃቱና ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተናጠልም ሆነ ኅብረት ፈጥረው መሳተፍ እንዲችሉ የሚጋብዝ  ነው፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው የማዳበሪያ ዓይነቶች ዳፕና ዩሪያ ናቸው፡፡ እነዚህን የማዳበሪያ ዓይነቶች ለማምረት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወይም ሀብቶች ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ ይጠቀሳል፡፡ አሞኒያ፣ ፖታሽና ፎስፌት ከተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው ብለው፣ ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በፍለጋ ላይ የሚገኙና ተፈልገው የተገኙ አሉበት ሲሉ አስረድተው ነበር፡፡

አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣባቸውን ማዳበሪያ፣ ነዳጅና ብረት በአገር ወስጥ ለመተካት መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠቱን፣ ማዳበሪያና ብረት አገር ውስጥ ለማምረት የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ አቅጣጫ ማስቀመጡን የማዕድን ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡

የፍላጎት ማሳወቂያ ጨረታውን አሸንፎ የአዋጭ ጥናት የሚያደርገው ኩባንያ የዘርፉን ገበያ፣ የማዕድን ቦታ ልየታ፣ ኢትዮጵያ ማዳበሪያን አምርታ ከራሷ አልፋ ለሌሎች አገሮች እንድትሸጥ የሚያበቃትን እንቅስቃሴ የሚያጠና ነው ተብሏል፡፡

ታከለ (ኢንጂነር) ጨምረው እንዳስረዱት፣ ጨረታውን የሚያሸንፍ ኩባንያ የሚያደርገው ጥናት የኢትዮጵያ መንግሥት ማዳበሪያን በራሱ ወይም ከኩባንያዎቸ ጋር በተናጠልም ሆነ በጋራ ቢያመርት፣ በአገር ደረጃ ይህን ያህል ያዋጣዋል፣ ከዚህ ባሻገር ወደ ውጭ ቢሸጥ አዋጭ ነው የሚለውን በዝርዝር ያቀርባል፡፡

ተወዳዳሪ ኩባንያዎች የሚያደርጉት ጥናት ሦስት ጉዳዮችን የሚሸፍን መሆኑን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበው መሥፈርት ያስረዳል፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ቴክኒካዊ አዋጭነትን ማጥናት ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊና የፋይናንስ ግምገማ ማድረግ፣ እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማና ቅነሳ ግምገማዎች ሌሎች በጥናቱ የሚሸፈኑ ናቸው፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የአማካሪ ኩባንያዎቹ ምርጫ ሒደት የሚመራው በኢትዮጵያ ባሉት ሕጎች ነው፡፡ ይህም የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001፣ እንዲሁም በ2002 ዓ.ም. የወጡ የፌዴራል የመንግሥት ግዥ መመርያዎች ናቸው፡፡

የአዋጭ ጥናት ጨረታ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች በሁለት ሳምንት ውስጥ መልሳቸውን እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ደቡብ ምሥራቅ ክፍል በኦጋዴን ቤዚን በጥናትና በቁፋሮ የተገኘውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ለኢንቨስትመንት ጥቅም ለማዋል የሚያግዝ የማማከርና የጥናት ሥራ ለማከናወን፣ የአሜሪካ ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሼትስ ኢንክ ኩባንያ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡

ኩባንያው የሚያካሂደው ጥናት ውጤት በኦጋዴን የሚገኘውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ለማዳበሪያና ለኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች ጥቅም ላይ እንዲውል፣ እንዲሁም ከጋዝ ወደ ፈሳሽ ነዳጅ ለመቀየር ነው ተብሏል፡፡

ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሼትስ ኢንክ ኩባንያ በሶማሌ ክልል አጋዴን ቤዚን 3,500 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተከናወኑ የፍለጋና የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ፣ በቤዚኑ ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት መጠን የሚያሳውቅና ኢኮኖሚያዊ ግምገማ የሚያሳይ ጥናት የሚያከናውን እንደሆነ ከዚህ ቀደም ተገልጿል፡፡

የቱርክ የማዕድን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዳበሪያ ፋብሪካ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን፣ ሪፖርተር ከማዕድን ሚነስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች