Monday, January 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለኢትዮጵያ ሰላም አስፈላጊው ዋጋ ይከፈል!

በሰሜን ኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አላባራ ያሉ ግጭቶች በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ያሉ ቁርሾዎችም አጣዳፊ መፍትሔ ይሻሉ፡፡ ጦርነት ከሚያስከትለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በተጨማሪ አገር ሊያፈርስ እንደሚችል፣ የተለያዩ አገሮችን ልምዶች በወፍ በረር መቃኘት ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አላባራ ያሉ ግጭቶችም አገር ለማፍረስ የሚያስችል ዕምቅ አቅማቸውን በሚገባ እያሳዩ ነው፡፡ ሰላም ለማስፈን ከሚረዱ ዓበይት ተግባራት መካከል ዋና ዋናዎቹን መጥቀስ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ጥያቄ ያለው ወገን በተቻለ መጠን ለሰላምና መረጋጋት መፈጠር የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ከሥልጣንና ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ አገር እንደምትቀድም፣ የሕዝብ ደኅንነትና የመኖር መብት መጣስ እንደሌለበት፣ ልዩነትን ከጠመንጃ አፈሙዝ ይልቅ በምክክርና በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆን፣ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ከሚጋብዙ ድርጊቶች ራስን ማራቅ፣ በሕዝብ ስም አለመነገድ፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ መገዛት፣ በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ሥጋት ሊፈጥሩ ከሚችሉ ድርጊቶች መቆጠብና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ተገኝቶ በኢትዮጵያ ሰላም ማስፈን የመላ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ 

የሰኔ ወር እየገባ ክረምቱ ሲቃረብ ከብሔራዊ ጉዳዮቻችን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ሰበዞች ይኖራሉ፡፡ ክረምቱ በሦስት የዝናብ ወራት ታጅቦ ሲመጣ በአብዛኛው የአገሪቱ የደጋ ክፍሎች እርሻ ይጀመራል፡፡ የአገራችን ገበሬ ትርፍ አምራች ባለመሆኑ በክረምት ወራት የምግብ እጥረት ስለሚኖርበት፣ ወደ ገበያ አውጥቶ ለከተሜው የሚያቃምሰው አይኖረውም፡፡ በመስኖ ከሚያመርቱ አካባቢዎች የሚገኘው የምግብ ምርት በቂ ባለመሆኑ፣ ከተሜው በአሁኑ ጊዜ ካለው የባሰ የኑሮ ውድነት እንደሚያጋጥመው ይታሰባል፡፡ ከሁሉም የምግብና ምግብ ነክ ምርቶች በተጨማሪ በተለያዩ ሸቀጦችና የመገልገያ ዕቃዎች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት፣ በክረምቱ ወራት ተባብሶ እንደሚቀጥል ጥርጥር አይኖርም፡፡ በግንባታ ዕቃዎችና በሌሎች ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረትም እንዲሁ፡፡ በክረምቱ ወራት ሌላው ተጠባቂ ጉዳይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ሲቃረብ በውጭ ኃይሎች አቀናባሪነት ግጭት ለመቀስቀስ እንቅስቃሴ ሊጀመር ይችላል፡፡ የውጭ ኃይሎች ከውስጥ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ጋር በመቀናጀት ሰላም የሚነሱ ግጭቶችን በየቦታው ለመቀስቀስም ይሞክራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰላማቸው እንዳይደፈርስ ይተባበሩ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልልና በኤርትራ መካከል የሚስተዋለው አደገኛ ሁኔታ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ታዛቢ ሆኖ የኢትዮጵያ አንድ ክልል ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው መዘዝ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህንን ጉዳይ በመጠኑ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ጉዳይ የምትወዛገበው ሱዳን፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ጥርሷን የነከሰችው ግብፅና ሌሎች በቅርብና በሩቅ ያሉ አገሮች በቀጥታና በእጅ አዙር እጃቸውን ማስገባታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አጋጣሚውን ለጥቅሞቻቸው መከበር የሚጠቀሙበት ኃይሎች በሙሉ፣ ከውስጥ ሸሪኮቻቸው ጋር በመናበብ በሚፈጥሩት ትርምስ ለሰላም የነበረው ተስፋ ይሟጠጣል፡፡ ክረምትና ጦርነት ከምግብ እጥረትና ከዋጋ ግሽበት ጋር ተሸራርቦ ሲመጣ፣ ሊደርስ ከሚችለው ቁሳዊና ሰብዓዊ ቀውስ በተጨማሪ ለአገር ህልውና አደገኛ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የዘለቀውን ጦርነት በማስቆም ፊትን ወደ ልማት ማዞር ካልተቻለ፣ መጪው ጊዜ ይዞት ሊመጣ የሚችለው አደጋ ከሚታሰበው በላይ ነው የሚሆነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለአገር በአንድነት መሠለፍ ያለባቸው ወገኖች እየተለያዩ ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ መንገድ መፍታት እየተቻለ፣ ጠላትነትን የሚያባብሱ ድርጊቶች እየተስፋፉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዙሪያ የጦር ነጋሪት እየተጎሰመበት ውስጣዊ ሰላም ማጣት ለማንም አይበጅም፡፡ በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶችን በማጦዝ መከፋፈል ለኢትዮጵያ ህልውና ጠንቅ ነው፡፡ የመንግሥት ሕግ የማስከበር ተግባር የብዙኃኑን ሕዝብ ቅቡልነት የሚያገኘው፣ ሰላም ለማስፈን ያለው ቁርጠኝነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ መቼም ቢሆን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ገደብ ሊጣልበት አይገባም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች የሚፈልጉትን ሐሳብ በነፃነት ማቅረባቸው፣ ለአንድ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦ ስለሚኖረው ነው፡፡ ሰዎች በነፃነት ሲነጋገሩና የሐሳብ ልውውጥ ሲያደርጉ፣ አምባገንነትና የአንድ ወገን የበላይነት እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡ በሰዎች መካከል ክብር፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሐዊነት እንዲኖር ያግዛል፡፡ በሥልጣኔ ከገሰገሱ አገሮች ብዙዎቹ እዚህ ደረጃ የደረሱት ለሐሳብ ነፃነት በከፈሉት ዋጋ ነው፡፡ ሰዎች ነፃ ሲሆኑ ዕምቅ የሆነ የፈጠራ ችሎታቸውን ለማውጣት አይቸገሩም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሲከበር ሰላም አስተማማኝ ሆኖ ይሰፍናል፡፡

ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ውስጥ የማውጣት አቅም ያላቸው ዜጎች በአገር ውስጥም በውጭም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ አቅም ጥበብን ከብልኃት ጋር አዛምደው ሲጠቀሙበት ውጤቱ ከሚጠበቀው በላይ ነው፡፡ በመጀመርያ አገር ለምትባለው የጋራ ቤት ማሰብ፣ አርዓያነት ያለው ሥነ ምግባር መላበስ፣ ለዴሞክራሲ መሠረታዊ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ ከአድልኦ አስተሳሰብ በመላቀቅ ሰብዓዊ ፍጡራንን እኩል ማስተናገድ፣ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እውነተኛውና ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ማግኛ ብቸኛ መንገድ መሆኑን ማመን፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ከልብ መሥራት፣ ከአመፃና ከውድመት ድርጊቶች መታቀብ፣ ሕዝብን ማክበርና ለፈቃዱ መታዘዝ ከተቻለ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ይህ ምኞት የሚሳካው ግን በዋዛ አይደለም፡፡ በበርካታ አደናቃፊ ችግሮች የተከበበ ነው፡፡ ሆኖም ለአገር ማሰብ ከተቻለ ከፀሐይ በታች የማይቻል ነገር የለም፡፡ መሰሪነትና ሴረኝነት በተፀናወተው ፖለቲካችን ለቅንነት አንድ ስንዝር ቢገኝለት ይኼ ከባድ ወቅት በጥበብ ይታለፋል፡፡ ቅንነት በስፋትና በጥልቀት ሲናኝ ደግሞ ኢትዮጵያ አገራችን አንገቷን ካስደፋት ቀውስ ውስጥ በፍጥነት ትወጣለች፡፡ ሰላሟም አስተማማኝ ይሆናል፡፡

ከኢትዮጵያ በላይ ምንም ነገር እንደሌለ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ምንም የሚቀድም እንደሌለ መግባባት ተገቢ ነው፡፡፡ ሕዝብ የሚደሰተው አገሩ ሰላም ስትሆንለትና በዕድገት ወደፊት ስትራመድለት ነው፡፡ ዴሞክራሲዊና ሰብዓዊ መብቶቹ ተከብረው በአገሩ ጉዳይ ዋነኛ ተሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ሰላሙ እየተናጋ፣ ደኅንነቱ አደጋ ውስጥ እየገባ፣ በስንት ትግል የሚያኖረው ሕይወቱ እየተመሰቃቀለና የአገሩ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ ሲሆንበት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ጊዜያዊና ኃላፊ እንዲሆኑ ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ዘመን ተሸጋሪ እሴቶች ሊከበሩ ይገባል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት፣ በቀቢፀ ተስፋ ወጣቶችን ለጥፋት ማሰማራት፣ ከመቀራረብ ይልቅ እልህ ውስጥ የሚከቱ አጉል ድርጊቶችን መፈጸምና አገርን የባሰ ቀውስ ውስጥ የሚዘፍቁ እኩይ ድርጊቶችን በፍጥነት ማቆም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለዓመታት ተሞክረው ያልተሳኩ ፍጥጫዎችንና ግጭቶችን በማበረታታት የተጠመዱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች፣ በዚህ መንገድ የሚፈልጉትን ዓላማ እናሳካለን ብለው ካሰቡ ተሳስተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሰላም አስፈላጊው ዋጋ ይከፈል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

አዲስ የፀደቀው የትርፍ ሰዓት ክፍያ መመርያ የመንግሥት ሾፌሮችን አበል በእጥፍ አሳደገ

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ያወጣው አዲስ የፌዴራል...

በጤናና ትምህርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ባለሀብት በአሜሪካ ኮንግረስ ተሸለሙ

ኑሮአቸውን በውጭ አገር ካደረጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...