አንድ ዝንጀሮ ያገባት ሚስት ‹‹ምን ሀብት አለህ? ብላ ስትጠይቀው ‹‹በየሜዳው ያለው እርሻ ሁሉ የማን ይመስልሻል? የእኔ እኮ ነው›› አላት፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለቱም ተጋብተው ወደ እየርሻው ከምር ለመዘንጠል ሲሄዱ ገበሬ በወንጭ ድንጋይ ያካልባቸው ጀመር፡፡ ሚስቱም አዝና ‹‹ምነው ይህ ሁሉ ማሳ የእኔ ነው ብለኸኝ አልነበረም እንዴ? በምን ምክንያት ነው ገበሬው ሁሉ በጠላትነት የተነሳብን?›› ስትለው ‹‹እንግዲህ እኛም የእኛ ነው እንላለን፤ እነርሱም የእኛ ነው ይላሉ፡፡ ቀስ ብለን በዘዴ እየተሹለከለክን አበላሉን ለማወቅ ብልሃት ሊኖረን ይገባል፡፡ የወንጭፍ ድንጋይ ሲመጣ ይህን ሳንቃ የመሰለ ደረትሽን ገልጠሽ በማሳየት ፈንታ፤ ጎንበስ ብለሽ የማሳለፍ ብልሃትና ጥበብ ይኑርሽ›› ሲል መከራትና በዚሁ ተስማሙ ይባላል፡፡
- መክብብ አጥናው ‹‹ሁለገብ የአእምሮ ማዝናኛ›› (2005)