Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የጥበብ አገር በፍቅር›› ዓውደ ርዕይ

‹‹የጥበብ አገር በፍቅር›› ዓውደ ርዕይ

ቀን:

የብዝኃ ባህል ባለፀጋ የሆነችው ኢትዮጵያ በብርቅዬ የዕይታ ጥበባት ትውፊቶችም ታድላለች፡፡ ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ ወደ ብራና ሥነ ጽሑፍ እመርታ ሲያሳይ፣ ከአለት ውቅር ላይ ሲሣል የነበረው ሥነ ሥዕልም ወደ ብራናዎችና ለሥርዓተ አምልኮ በሚያመች መልኩ በየቤተ እምነቱ ግድግዳና ራስጌ መሣሉ ቀጥሎበታል፡፡

እነዚህ የጥበባት ውጤቶች ናቸው ለኢትዮጵያ ጥንታዊነት ከሚቆሙት በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ተርታ የሚሠለፉት፡፡

የሥዕል ጥበብ ከጥንታዊው የአክሱም ሥርወ መንግሥት ዘመን፣ በተለይ ከኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን በአመዛኙ የሚቀዳ ነው፡፡ ዘመናትን ተሻግሮ የመጣው ትውፊታዊው ሥዕል ከ19ኛው ምዕት ዓመት ወዲህ ካቆጠቆጠው ዘመናዊ ሥዕል ጋር መሳ ለመሳ መጓዙ አልቀረም፡፡ ዘመናዊው የሥዕል አስተምህሮ ቀደምቱ በብሉይነታቸው ተጠብቀው እንዲኖሩ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ቢሆንም ምሉዕነት ይጎድለዋ ይበልጥ ትኩረት ያሻዋል የሚሉም አልታጡም፡፡

ጥንታዊው የሥዕል ጥበብ አብርሃማዊ እምነቶች (አይሁድና ክርስትና እስልምናም) ከመከሠታቸው በፊት እጅግ በራቀ ዘመን ውስጥ በኢትዮጵያ ምድር ከአለት ላይ ጀምሮ ህልው መሆኑም አይዘነጋም፡፡ አብርሃማዊ እምነቶች እምነታቸውን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረፅ ከሚጠቀሙባቸው ቅዱሳት መጽሐፎቻቸው በተጨማሪ ሥነ ጥበብን እንደ መሣርያ መጠቀማቸውም አልቀረም፡፡

ይህንኑ በመገንዘብ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ (ባኪቱ) ከሥዕልና ቀራፂያን ማኅበር ጋር በመተባበር ጥንታዊውን የኢትዮጵያ የሥዕል ጥበብ የሚያስተዋውቅ ዓውደ ርዕይ ረቡዕ ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከፍቷል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የተከፈተው ዓውደ ርዕዩ መሪ ቃሉ ‹‹አንድ የጥበብ አገር በፍቅር›› ይሰኛል፡፡

‹‹የትምህርት ራስ ፊደል የምግብ ራስ ጨው›› እንዲሉ በተለያዩ ከያንያን የተዘጋጀው የጥበቡ ትሩፋት መነሻውን ያደረገው ኢትዮጵያን ልዩ ከሚያደርጋት አንዱ በሆነው የፊደል ገበታን በሥነ ጥበብ በማስተዋወቅ ነው፡፡

የግእዙን  የሀለሐመ እና የአቡጊዳ የፊደል ተርታ እንዲሁም የዓረብኛው አሊፍ ባት … በኪነ ቅብ ተቀናብረው ቀርበውበታል፡፡

የፊደላት ቊጥር (ኈልቈ ፊደላት) እና የግእዝ አኃዝ መሠረታዊ ምልክቶች ፩፣ ፪፣ ፫፣ ፬፣ ፭፣ ፮፣ ፯፣ ፰፣ ፱፣ ፲፣ ፳፣ ፴፣ ፵፣ ፶፣ ፷፣ ፸፣ ፹፣ ፺፣ ፻  ተሰድረው መቅረባቸው ለዓውደ ርዕዩ ፈርጥ ሆነውታል፡፡

የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ ባለቤቷን ኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመቱን (የዓመቱ መነሻ ዋናው ዕለት) መስከረም 1 ቀንን የሚያበስረው በየትም የሌለው አደይ አበባን ከፊደል ገበታው ጋር ተሳስሮና በለምለሙ ምድር ላይ ተያይዞ የቀረበውም ቀልብን ይስባል፡፡

‹‹አመርን እኛ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው በሚዶ መሣርያነት የቀረበው ማበጠርያውን ባለሰባት ሰበዝ አድርጎ መታየቱ ፊደሉ ከለ ግእዝ (1) እስከ ሎ ሳብዕ (7) ድረስ ባለተርታ መሆኑ ሲያመሠጥረው ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ሠዓሊው [ስሙ አልተጻፈበትም] እኛ አማርን ያለው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚያንፀባርቁ ቅዱሳት ሥዕላትም በየዘርፉ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡ ለጥንታዊው ጥበብ አስተዋጽኦ ካደጉት መካከል ቤተ እስራኤላውያን የሚገኙ ሲሆን በዓውደ ርዕዩ ለምን አልተካተቱም ጥያቄ ሆኖ አልፏል፡፡

ኢትዮጵያ ጥንታዊ የአሣሣል ጥበብ በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስጊድ ያላት አገር መሆኗን የገለጹት፣ ዓውደ ርዕዩን የከፈቱት የአዲስ አበባ ባኪቱ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ናቸው፡፡

በአሁን ዘመን ይህን ነባር ጥበብ ለማስታወስ ዓውደ ርዕዩ መዘጋጀቱን የጠቆሙ ሲሆን ቢሯቸው ለዕይታዊ ጥበባት ትኩረት በመስጠት በጥበቡ ከተሰማሩ ጋራ በመሠራት ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ዓውደ ርዕዩ ለሰባት ቀናት ክፍት ይሆናልም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...