በመታሰቢያ መላከ ሕይወት
በአንድ አገር ጤነኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት መኖሩን ብዙ ሳይደክሙ ለማየት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ምን ያህል ቱሪስቶችንና ኢንቨስትመንትን ታስተናግዳለች ብሎ በማየት ብቻ ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡
ቱሪስቶች ወደ አንድ አገር ሄደው ጉብኝት ለማድረግ፣ በመሠረቱ ሁለት ነገሮች ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡ የመጀመርያው የፀጥታ ሥጋት የሌለበት አገር መሆኑን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቀልብ የሚስብ የሚጎበኝ ነገር መኖር አለበት፡፡
ቱሪስቶች ዴሞክራሲ ኖረም አልኖረም አገሪቱ በአምባገነናዊ ሥርዓት የምትገዛ ብትሆንም፣ ሰላምዋ አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ ሌላ አገር ሄደው ጊዜያቸውን ከማሳለፍ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ኢንቨስተሮች ግን ዘለቄታዊ ሥርዓት ያላትና የሕግ የበላይነት የተከበረባት፣ የሚያፈሱትን ሀብት ለረዥም ዓመታት ያለ ችግር መሥራት የሚያስችላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንድ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ውጤት ማምጣት የሚጀምሩት ከብዙ ዓመታት በኋላ በመሆኑ፣ ኢንቨስተሮች ጠንካራ የመንግሥት ሥርዓት መኖሩን ሳያረጋግጡ ሀብታቸውን ይዘው ወደ ሌላ አገር አይሄዱም፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያለ፣ ገና የተጠናከረና የበለፀገ ፖለቲካና ኢኮኖሚ በሌለበት አገር ምዕራባውያን የሚያደርሱትን ጫና ለመቋቋም የሚቻለው፣ የአገሪቱን ሀብት ወደ ጥቅም መለወጥ የሚቻለው፣ ምዕራባውያን ከፍተኛ ሀብት አገራችን ውስጥ እንዲያፈሱ በማድረግ፣ ያ ሀብታቸው ችግር እንዳይገጥመው ለሰላማችን ምዕራባውያንም ጭምር አብረው እንዲሠሩ በማድረግ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ምዕራባውያን ብዙ ቢሊዮኖች የሚያወጣ ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌላቸው ስለ ኢትዮጵያ ግድ የላቸውም፡፡ በሌላ አነጋገር እንደ ኢትዮጵያ ባለ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች አገር፣ ያላትን ሀብት አልምታ የዜጎችን ሕይወት መለወጥ ያልቻለች አገር ውስጥ፣ ጠላትን በወታደራዊ ኃይል በመዋጋት ብቻ መቋቋም በእጅጉ አዳጋች ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ሁሉም እንደ ፍላጎቱ ሥራው ድርሻውን ማግኘት የሚችልባት አገር መፍጠር ከቻልን ያለ ምንም ወታደራዊ ግጭት አገራችንን ሰላማዊ ማድረግ ይቻላል፡፡
ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ምዕራባውያንን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለማድረጋችን አሁን ላይ ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ በዱር እንስሳት አኗኗር አንበሳ የበላይ እንደሆነው ሁሉ፣ በአሁኑ ወቅት (አቅማቸው እስኪሟሽሽ ድረስ) ምዕራባውያን በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ የአንበሳውን ያህል ድርሻ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነ ኮሪያና እነ ጃፓን አድገው እዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት በሁሉም የኢኮኖሚ ተግባር ውስጥ ምዕራባውያንን ተጠቃሚ በማድረግ ነው ለውጤት የበቁት፡፡ እኛም አገር በቢራና በወይን ምርት ዘርፍ ምዕራባውያን በመሳተፋቸው ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም፡፡ በማዕድን፣ በእርሻ፣ በቱሪዝም፣ በፋይናንስና በአገልግሎት ዘርፍ በበቂ ሁኔታ እጃቸው እንዲኖር በማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ሰፊ ዕድል ይፈጠራል፡፡
በአሁኑ ዘመን ሦስቱ ኃያላን አገሮች ማለትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እንዲሁም የአውሮፓ አገሮች ከአፍሪካ ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት የድርሻቸውን ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ እየሠሩ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን የጀመርነው የብሔር መንግሥት የመፍጠር ቅዠት አቁመን፣ ለአገራዊ አጀንዳ ብቻ በመሥራት ሀብታም አገሮች የደረሱበት ለመድረስ መትጋት ነው ያለብን፡፡
በአንድ አገር ሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ሊያራምድ ዕቅድ ማዘጋጀት ቢያቅተውና ሰላምን ግን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ ከቻለ ሰላም በመኖሩ ምክንያት ብቻ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ አሁን በአገራችን በአመፅ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ሠርቶ ማደር ከቻሉ ወደ ግጭትና ጦርነት የመሄድ ፍላጎት አይኖራቸውም፡፡ ልማትና ሰላም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሲሆኑ፣ ኢንቨስትመንት አለመኖርና የፖለቲካ ችግር፣ ግጭትና ጦርነት ደግሞ የሌላ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በተጋ ቁጥር ሰላም የመኖሩ ሁኔታ አስተማማኝ እየሆነ ይመጣል፡፡ ሰላም ካለ ኢንቨስትመንት ይኖራል፣ ሰላም ከሌለ ጦርነት ይኖራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ በአዕምሯቸው ያለው ዕቅድ ፓርክ መገንባትና የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ ሰጥተው ተንቀሳቀሱ እንጂ፣ ወጣቱን በሥራ ሊይዙ የሚችሉ ተግባራትን በተፋጠነ መልኩ አከናውነው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የምናያቸው ችግሮች ባልተከሰቱ ነበር፡፡
የአፍሪካ መሪዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ባህሪያቸው፣ በሥልጣን ላይ እያሉ ለአገር ለወገን የሚበጅ ሥራ ሠርተው፣ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ እንኳን ለራሳቸው የሚጠብቃቸው ሥርዓት መፍጠር አለመቻላቸው ነው፡፡ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ተከብረው መኖር የሚችሉት በሥልጣን ላይ እያሉ በሠሩት በጎ ተግባር ነው፡፡ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ መለስ ዜናዊ ያሉ መሪዎች ለዚህ አልታደሉም፡፡
በቅርቡ የተከሰተውን በሶማሌ ክልልና በቦረና የደረሰው በውኃ ጥም ምክንያት የሞቱ ከብቶች ሁኔታን ብንመለከት አገራችንን ‹የአፍሪካ የውኃ ማማ› እያልን እየጠራናት በውኃ ጥም ይህን ያህል ከብት መሞቱ መሪዎቻችንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደማይተጉ በግልጽ ያሳያል፡፡ እንኳን ኢንቨስትመንትን የሚስብ ተግባር ሊፈጸሙ ይቅርና፣ ቱሪዝምን የሚያስፋፋ ተግባር ሊፈጸሙ ይቅርና በባህላዊ መንገድ ከብት የሚያረቡ ዜጎቻችንን ንብረት ከአደጋ መታደግ አለመቻላቸውም ምን ላይ እንዳሉ በግልጽ ያሳያል፡፡
መቶ አሥር ሚሊዮን ሕዝብን ማስተዳደር እጅግ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ ለከባድ ኃላፊነት ደግሞ ትልቅ ብቃት፣ የተጠራቀመ ዕውቀት፣ የረዥም ዕድሜ ከማንበብና ከሥራ ልምድ፣ የሚገኝ ዕውቀት ባለቤት መሆንን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያን ማስተዳደር እጅግ ከባድ የሚያደርገው በመጀመርያ መሠረታዊ ፍጆታዎችን በአግባቡ ማቅረብ ግድ ይላል፡፡ ሁለተኛ አገሪቱን ከተበላሸ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት በማውጣት ወደ ትክክለኛ ሥርዓት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛ የአገር ሰላምን ከውጭና ከውስጥ ኃይሎች መጠበቅ የግድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ኃላፊነቶችን ተረክቦ በብቃት መሥራት እጅግ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ጥበብን ይጠይቃል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሰፊ የቆዳ ሥፋት ካላቸው አገሮች የምንመደብ ነን፡፡ ከእኛ በቀር ሌሎቹ ሰፊ አገሮች ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል ያዳረሰ ልማት ማካሄድ በመቻላቸው የብሔር ፖለቲካ እንኳን ሊስተናገድ ስለብሔር ማውራት በራሱ ነውር የሆነ ተግባር ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡