Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከሳሾችና ፈራጆች!

ሰላም! ሰላም! ዓለም ሰላም አጥታ በእኛ ሰላም መባባል የሚቆጣ ይኖራል እኮ። ምን ይታወቃል? ምቀኛ አያሳጣን ነው መቼስ። የቅናት ዛር የሰፈረበት ሁላ እንኳን በሰው ሰላም በሰው ኪስ ይቃጠል የለ? አንዳንዴ እኮ አለመፈጠርን የሚያስመኘኝ ከተፈጠርኩ ጀምሮ ያየሁት ትርጉም የለሽ ክፋት ተቆጥሮ የማይልቅ ሲሆንብኝ ነው። ዘንድሮ ቆጥራችሁ አይደለም ገና ሳትጀምሩት የሚያልቀው ገንዘብ ብቻ ሆኗል። በተረፈ ሌላው ጉድ የሚያልቅ አይደለም። እናም ሰላም በራቀን ልክ እኛም የምንመፃደቀው እንደ ጉዳይ መቁጠር የጀመርነው ዕኩይ ዕኩዩን ሆነ። መቼ ዕለት አንድ ወዳጄ ከአንዱ ወደ አንዱ ድለላ ስከንፍ አግኝቶኝ ‹‹ጫረው!›› አለኝ። ‹ፀብ አጫሪ መንገዱን አጣቦና ዓለምን አስጨንቆ ይዟት ሳለ ሌላ ፀብ ጫር ነው የሚለኝ?› ብዬ ልሸሸው ስል፣ ‹‹የት ነው የምትሸሸው? አሁንማ እንዲህ በቀላሉ በዋዛ አንላቀቅም፣ ና ቢራ ልጋብዝህ…›› አለኝ። ‹‹አንተ የእኛ ሰው በሌላ ሰው ግላዊ ጉዳይ ቢዚ ሆኖ ከሳሽና ፈራጅ ሲሆን ብቻህን የምን መንጦልጦል ነው…››     ቢለኝ ክፉም ደግም ሳይወጣኝ አንገቴን ነቅንቄ ጥዬው ሄድኩ። ተኝቶ መታከም ያለበት ሰው ቁጥር ከኢኮኖሚ ዕድገት አኃዙ እጥፍ በእጥፍ እየጨመረ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኛለሁ። በዚህ የኑሮ ውድነት ዳቦ፣ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ እንጀራና ሌላው ቸግሮን በጓሮ እርሻ ራሳችሁን ደጉሙ ሲባል የሚያላግጥ ሁሉ የሰው ገመና ለማውራት ቢራ እናጋጭ ይባላል? ኧረ በስንቱ እንቃጠል? የምድር ፀሐዮች የሰማዩዋን ሊያስቀኗት ምን ቀራቸው እናንተ፡፡ ዘንድሮማ ለይቶልናል!

ወትሮም ‹‹እውነት የሚናገር ሰው ጓደኛ የለውም…›› ይላል የአፍሪካውያን አባባል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ዕድሜ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ እውነቴን ነው የምላችሁ ይህንን ጥቅስ እስከ ሰማሁበት ቀን ድረስ፣ እኛ አፍሪካውያን የመንጋነት እንጂ የመሪነት መንፈስ እንዳለን አላውቅም ነበር። ከነበር አፈንግጦ ‹‹የለም በዚያ አይደለም! ኑ በዚህ በኩል!› ያለ አፍሪካዊ ሶቅራጥስ እንዳለ ከድለላ በሚተርፈኝ ሰዓት መርምሬ ለማግኘት አንዳንድ መጻሕፍትን ሳገላብጥ ውዷ ማንጠግቦሽ ታዝባኝ፣ ‹‹አንበርብር ተው ብዙ አታንብብ ታብዳለህ፡፡ እኔ በኋላ በኅብረተሰቡ ወፈፌ ተብሎ የተገለለ ባል አልፈልግም። አርፈህ የሌሎችን ቅስቀሳ አዳምጥ። ‹አሸነፍን› ሲሉ ‹አበጃችሁ› በል። ‹አልተሸነፍንም› ሲሉ ‹እንዳላችሁ› ብለህ እለፍ። ነገር አታምጣብኝ…›› ብላ አስፈራራችኝ። ያነበበና የተመራመረ ሁሉ የሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ይገባል ያለው ማን እንደሆነ አላውቅም። ትንሽ ሰነባብታ ደግሞ፣ ‹‹እዚህ ቤት መጽሐፍ የሚባል ነገር ባይ የእኔና የአንተ ነገር አከተመ…›› አለችኝ። ማንጠግቦሽ እንደምትለው በዚህ ዘመን የሚያዋጣው ከማያልቀው የመጻሕፍት ዕውቀት ተጎንጭቶ በሚሰማውና በሚታየው ከመበሳጨት፣ ሌሎች የሚቀባጥሩትን እየሰሙ ፈገግ ማለት ይሻላል፡፡ ተማርን ባዩ ሁሉ ዩቲዩብ ከፍቶ የሰው ገመና እያሰሰ እንጀራ በሚጋግርበት ዘመን ተመልካች መሆን ያዋጣል ባይ ናት፡፡ አንዳንዴ እኮ ያሰኛል!

እንዲያው እርሜን በተጋመሰ ዘመኔ እውነትን ፍለጋ ቆርጨ ብነሳ ተቃውሞ ከቤቴ መጀመሩ አስገርሞኝ ገመናዬን ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሳዋየው፣ ‹‹ደግ አደረገች!›› አለኝ። ‹‹ምነው አንተ የተማርክ ሰው አይደለህ? እንዴት እንዲህ ይባላል?›› ስለው፣ በከፊል ይኼ የትምህርት ጥራት ጉድለት እንኳን በሚኒስትር ሹም ሽረትና በርዕየተ ዓለም ለውጥ በእንዶድ ቢያጥቡትም አይፀዳ እያልኩ ስቆናጠር፣ ‹‹መጻሕፍት ውስጥ ሐሳብ እንጂ እውነት ተገኝቶ አያውቅማ። ‹በተማረው ባሰ›፣ ‹ባነበበው ከረረ› ሲባል የምትሰማው እኮ ሐሳብ ሸምድደን በሐሳብ ስለምንለያይ ነው። እውነት ግን አብራህ የተፈጠረች ናት። ህሊናህን ስትጠይቀው እውነትን ይጠራልሃል…›› ብሎ  የሚገባኝን አሳንሶ ያልገባኝን አብዝቶ አብራራልኝ። ‹ሐሳብ የሌለበት እውነት እንዴት ያለው ይሆን?› ስል የሚያኖረኝን ደላላነት ትቼ የሚያስርበኝን ፍልስፍና ሙጥኝ ልለው ሆነና ነገሩን ተውኩት። በምሁሩ የባሻዬ ልጅ አስተያየት ግን ባይዘመርላቸውም ብዙ ሺሕ ሶቅራጥሶች አፍሪካ እንዳሉዋት አረጋገጥኩ። ማሰብና መናገር እየተከለከሉ አይመስላችሁም ያልዘመርንላቸው? አንዳንዴ ሳስበው እኮ በዚህ ዘመናችን አሳቢና አሰላሳይ ሳይሆን፣ በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ዘባራቂው መብዛቱ አያስፈራም ትላላችሁ? እኔ እፈራለሁ!

እናላችሁ እንደምታውቁኝ ሥራ ላይ ንብ ነኝ። ኦ! ለካ ጊዜው የፉክክር ነው? ፉክክሩ ቢደራም መብቴ እንደ ግለሰብ ይጠበቅልኝ አደራ። ደግሞ እንደሚገባኝ በላባችን እንደ ንብ ታትረን ማር መጋገር የከለከለን የለም። እና ደፋ ቀና ስል ባለሦስት ፎቅ ቪላ ላሻሽጥ፣ ከሻጩ ጋር አብሮ እንደኖረ ሰው ፍፁም ተግባባሁላችሁ። የእኛ ሰው ዝቅ ብላችሁ ጆሮ ከሰጣችሁት የጓዳ ታሪኩን ጨርሶ ዕትብቱ የተቀበረበትን አካባቢ ሁሉ ይጠቁማችኋል። ቪላውን ለማየት ቀጠሮ ይዘው ገዥዎች እስኪመጡ እንጫወታለን። ‹‹ይገርምሃል ባለቤቴ ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፏ ተነስታ ምን አማረኝ ብትለኝ ጥሩ ነው?›› አለኝ። ግምቴ ቀረብ እንዲል እርጉዝ መሆኗን ጠየቅኩት። ‹‹ኧረ መሀን ነች…›› አለኝ። አምልጦት አይደለም። እንደ ነገርኳችሁ ጆሮ ካገኘን ሚስጥር አንቋጥርም። ‹ሰው ሁሉ የልቡን እንዲህ የሚናዘዝልኝ ከሆነ በጆሮ ጠቢነት ተመዝግቤ ጥሩ አበል ልሸቅል ይሆን?› እያልኩ፣ ‹‹እርጉዝ ካልሆነችማ መገመት ይከብዳል…›› አልኩት። ልብ አድርጉ ‹መሀን ከሆነችማ’ አላልኩም። በተዋወቅን ልክ መናናቅን መሻር ከእኔ ተማሩ። በትምህርት ጥራት መላሸቅ ብቻ አታሳቡ፡፡ የትምህርታችን ነገርማ ገና ብዙ ጉድ አለበት፡፡ ዲግሪ እንደ ሽንኩርት መቸርቸር የተለመደ ሆኗል ሲባል፣ የለም ቸርቻሪዎቹን ለይታችሁ ጠይቁ የሚል ተቃውሞም ይሰማል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን በዘመነ ኩረጃ የሚገኝ ዲግሪም ሆነ ዲፕሎማ እንደገና ማጥለያ ቢደረግለት አይከፋም የሚሉ የዘርፉ አንጋፋ ባለሙያዎች አሉ መባሉን ሰምቻለሁ፡፡ ሁሉንም ነገር እያጠለልን ብንሰማ ጥሩ ነበር!

ደንበኛዬ ቀጠለ። ‹‹ገና ከእንቅልፏ እንደተነሳች ‹ናይጄሪያዊ መሆን አማረኝ› አትለኝ መሰለህ…›› ብሎ ወዲያው ተቆጣ። ‹‹ካልጠፋ ቦታ እነ ጀርመን ብትል አሜሪካ፣ ካናዳ ብትል ፈረንሣይ፣ ቻይና ብትል ሩሲያ እያሉ ናይጄሪያ ትለኛለች?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። ‹እኔ ያልኩት አስመሰለው እኮ› እያልኩ፣ ‹‹ምነው አለች?›› ስለው፣ ‹‹ምን እሷ ‹በሕይወቴ ዘመን የናይጄሪያ የፊልም አክተሮችን በአካል ሳታሳየን አትግደለኝ› ነው የዘወትር ፀሎቷ…›› ብሎ፣ ‹‹ካልጠፋ ፊልም የናይጄሪያ በዚያ ላይ ደግሞ ለምን እነዚያ አክተሮች እንደሚያምሯት ግራ ያጋባኛል፡፡ የእኛ አገር ሰው ባህሪ እኮ እንዲህ እየሆነ ነው የተቸገርነው…›› ብሎኝ በአንዲት ዘመዱ ላይ በተፈጸመ የስም ማጥፋት ዘመቻ የደረሰውን ቀውስ ሲነግረኝ ደነዘዝኩ። መላ ያጣ ነገር!

ሰውየው የቅርብ ዘመዱ የሆነች የተማረች ወጣት በንግድ ዓለሙ ውስጥ ገብታ ገበያው ውስጥ ፈላጊዋ በዝቶ የሀብት በረከት መቋደስ ስትጀምር፣ የቅርብና የሩቅ ተፎካካሪዎቿ ሊያጠፏት ሴራ ይጎነጉናሉ፡፡ አንድ ቀን ለሥራ ከተቀጣጠረችው ሰው ጋር ምሳ ለመብላት አንድ ታዋቂ ሬስቶራንት ይሄዳሉ፡፡ ያዘዙት ምግብ መጥቶላቸው እየተመገቡ ሳሉ ሰውየው በባህላችን መሠረት ብሎ ያጎርሳታል፣ እሷም እንደ እሱ አንዴ ታጎርሰዋለች፡፡ ምግባቸውን በልተውና ቡናቸውን ጠጥተው የተገናኙበትን የንግድ ሥራ ጉዳይ ተነጋግረው ሲለያዩ፣ ትከሻ ለትከሻ ተያይዘው ጉንጫቸውን ተሳስመው ይለያያሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ሌላ ቦታ ቢሆን ምንም ችግር የሌለበት ነው፡፡ ነገር ግን ሴረኞች ቀደም ብለው ባቀዱት መሠረት በካሜራ የተነሳው እንደገና በቅንብር ተሠርቶ በምሥልና በቪዲዮ በየፌስቡኩና በየዩቲዩቡ ሲለቀቅ፣ የእኛ ሰው ከየአቅጣጫው የእርግማን ናዳውን በሁለቱም ላይ ያወርዳል፡፡ ሰውየው ከትዳር አጋሩ እሷ ደግሞ ከአዲስ ፍቅረኛዋ ጋር ተቆራረጡ፡፡ በዚህ ሰይጣናዊ ሴራ ምክንያት ለአዕምሮ ሕመም ተዳርጋ ቤት ቀርታለች ሲለኝ ውስጤ ታወከ፡፡ ሴረኞች የስንቶችን ሕይወት ሲያመሰቃቅሉ እኛ ጅሎች ደግሞ አጉል ፈራጅ ሆነን የበለጠ ሰቆቃ እንፈጥራለን፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስን ፈሪሳውያን ሴቲቱ ዘማዊ ስለሆነች በድንጋይ ተወግራ መገደል አለባት ሲሉት፣ ከመሀላቸው ኃጢያተኛ ያልሆነ በድንጋይ ወግሮ ይግደላት ሲላቸው ማንም የደፈረ አልነበረም…›› ያለኝ ትዝ ሲለኝ የገዛ ኃጢያቴ ውል ብሎ ታየኝ፡፡ እናንተስ ይታያችሁ ይሆን!

ያልኳችሁን ቤት አሻሽጬ አንድ ሲኖትራክ ላከራይ ስንከራተት ስልኬ ባትሪውን ጨረሰ። እኛ ደላሎች ሳንቀጣጠር የምንገናኝባት የሰርክ መሰብሰቢያችን ወደ ሆነችው አሮጌ ካፌ ተጣደፍኩ። ስደርስ አንዱ ደላላ ወዳጄ ፈንጠር ብሎ ብቻውን ተቀምጦ ደብዳቤ ይጽፋል። ሌሎቹ ተሰብስበው ያሽካካሉ። ወደ የሚያሽካኩት ተጠግቼ በአንደኛው ሞባይል ወደ ቀጠርኩት ተከራይ እየደወልኩ፣ ‹‹ምን እየጻፈ ነው?›› አልኳቸው። ‹‹ለሞባይሉ ደብዳቤ እየጻፈ ነው፣ አትረብሽው…›› ብሎ አንደኛው ዕንባው እስኪያቀር ይስቃል። ‹‹ስልኩ በመጥፋቱ የስንት ሺሕ ብር ሥራ እንዳመለጠው ብታውቅ እንዲህ አታላግጥም…›› ይላል ከጎኑ ኮስተር ባዩ ወዳጃችን። ከደንበኛዬ ጋር ተቀጣጥሬ ‹ቻርጅ› እስካደርግ የሚጽፈውን ለማንበብ አጠገቡ ተቀመጥኩ። ‹‹ከኑሮ ፅዋ እኩል ተግተን፣ ሚሊየነር ሆኜ የደላላነት ጫማዬን ልሰቅል ስል ጥለሽኝ በመጥፋትሽ አዝኛለሁ…›› ሲል ይጀምራል። ‹‹… እነሆ ‹ወንዝ በሌለበት ድልድይ እንሠራለን› ማለት የለመደ ውሸታም ሲያስለቅሰኝ እንዲኖር ፈቅደሽ፣ ድህነቴን በሥራ ሳይሆን በርዕዮተ ዓለም ምርጫ አመልጠው ይመስል በወሳኜ ሰዓት ከዳሽኝ። መቼም ከዚህ አገር ባተሌ ጋር የዋለች ሞባይል መጥፋት እንጂ ሌላ ምንም ተምራ እንደማትመጣ የታወቀ ነው። ለሁሉም እንደ ሥራው ይሰጠዋል። ስንቱ በዘረፋ ሚሊየነር ተብሎ ታፍሮና ተከብሮ እየኖረ እኔ በላቤ ሳያልፍልኝ በድህነት እንድኖር ፈረድሽብኝ። ግን አንቺም? አብረን ብዙ ዓይተን ገና ለገና ሚሊየነር ሆኖ ‹አይፎን› ይደርብብኛል ብለሽ ጠርጥረሽ? ሳትነግሪኝ ገብቶኛል። ብደርብስ መደረብ በእኔ አልተጀመረ? ደግሞ በዚህ ጊዜ ማን ነው የማይደርበው? ግድ የለም…›› እያለ ይቀጥላል። እንግዲህ የሞባይል ቀፎ በጠፋ ቁጥር የአርባ ቀን ዕድልን በደብዳቤ መተቸት ከጀመርን፣ ከነዳጅ ዋጋ መጨመር በላይ ሊያሳስበን ነው እንዳልል ይህ ቅኔ የተዘረፈው ለሌላ ጉዳይ መስሎኝ ዳይ ወደ ሥራ አልኩ፡፡ ብዙ ሥራዎችን ሠርተን የገቢ አማራጮች መፍጠር ሲገባን፣ ወሬ ላይ ተጥደን መንግሥት የኑሮ ውድነቱን እንዲያቀልልን እንለማመጣለን፡፡ አይ ስንፍና!

በሉ እንሰነባበት። ‹ኮሚሽኔን› ተቀባብዬ ጥሜን ልቆርጥ ወደ ግሮሰሪያችን አመራሁ። ሰው እንደ ወትሮው ገደብ በጣሰ ብስጭትና ንዴት ይጨልጣል። ለምሁሩ የባሻዬን ልጅ ደወልኩለት። ጥቂት ቆያይቶ ከተፍ አለ። ቢራውን ጨለጥ ጨለጥ አድርጎ ሲደርስብኝ፣ ‹‹የእኛ ነገር እንዲህ በንዴትና በብስጭት ብርጭቆ ሥር ተጎልቶ ማምሸት ሆነ በቃ?›› ስለው፣ ‹‹ተወኝ የዛሬው ያስጠጣል…›› አለኝ። ‹‹አንተ ደግሞ ምን ሆንክ?›› አልኩት፡፡ ‹‹አባዬ ደከመ ብለውኝ ነፍሴን ሸጬ ቤት ስደርስ ሬዲዮ ጆሮው ሥር አስጠግቶ ይቁነጠነጣል። ደህና መሆኑን ስጠይቀው እሱ ከእኔ በልጦ ‹ዝም በላቸው ለምን አይሞትም ብለው ነው፡፡ ሟርተኛ ሁሉ…›› ብሎኝ፣ ‹‹በፊት ዘፋኝ፣ ቴአትረኛ፣ ታዋቂ ሰው ነበር እንዲህ ዓይነት ነገር የሚወራበት፡፡ አሁን ብሎ ብሎ አንድ አረጋዊ የሠፈር ሽማግሌ ላይ የምን ዘመቻ ነው…›› እያለ ሲበሳጭ፣ አዛውንቱ አባቱ አንድ ነገር ቢሆኑ ኮረንቲ ካልጨበጥኩ እንደሚል አረጋገጥኩ። እንዲያው ለመሆኑ ምን ነክቶን ነው እንዲህ ዓይነቱ ዝቅጠት ውስጥ የገባነው? ግራ ገባኝ እኮ!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ተናግሮ እንዳበቃ አንድ ጎልማሳ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ ‹‹እኔ ቤትህ ስለተቃጠለ ቶሎ ድረስ ብለው እግዜር ያሳያችሁ ሥራዬን ትቼ በድንጋጤ ሮጬ ስደርስ ሐሰት ነው አሉኝ። በድንጋጤ ስሮጥ አደጋ አጋጥሞኝ ብሞት ኖሮ ማን ነበር የሚጠቀመው?›› በማለት ተናግሮ ሳይጨርስ፣ ‹‹አንተም ሞኝ ነህ። ተቃጠለ ሲሉህ ምን ልታተርፍ ትሄዳለህ? ወይስ እንደ ደመራ ወዴት እንደሚወድቅ ልታይ ነው?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠ አጉል ቀልደኛ ነኝ ባይ፡፡ ሁለቱ በነገር ሲያያዙ ሌላው፣ ‹‹እኔ አለሁ አይደል? በእኔ ቤት ማንም አይሸውደኝም ብዬ እጮኛዬ የምሯን አረገዝኩ ስትለኝ ‹ሂጂና ሌላውን አታይ’ ብዬ የተቆራረጥኩት…›› አለ። ሌላ አንድ ሞቅ ያለው ተነስቶ ደግሞ፣ ‹‹ለማንኛውም ዛሬ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሲዋሽ የተገኘ ምላሱ ይቆረጣል ብሏል…›› ሲል ውሸቱ ያፈጠጠ ነበርና ከቁምነገር የቆጠረው አልነበረም። ሁካታው ሲያይል ለማርገብ የግሮሰሪው ባለቤት፣ ‹‹ፀጥታ! ዛሬ የፈለጋችሁትን ያህል ጠጡ ሒሳብ በእኔ ነው!›› አለ። ቤቱ በአንዴ ረጭ አለ። ሁሉም እውነት መስሎት ዓይን ዓይኑን አየው። ‹‹ቀልደኛ ሁሉ፣ እናንተን በነፃ አጠጥቼ ግብር ምን ልከፍል ነው?›› ብሎ ሳቀ። እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለዘመኑ ውሸትና ሥርጭቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከበስተጀርባው ስላለው ዘመቻ ግብ ስንጫወት አመሸን። በዚህ ምክንያት አንገታቸውን እንዲደፉ ስለሚደረጉ ምስኪኖች ዕጣ ፈንታ እያነሳን ብዙ ተነጋገርን፡፡ የአጉል ከሳሾችና ፈራጆች ጉዳይም ሌላው ርዕሳችን ነበር፡፡ መልካም ሰንበት

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት