በየዕለቱ እያሻቀበ የሚሄደው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡ ፈተና ከሆነ ቢሰነብትም፣ የኑሮ ውድነቱን ለመግታት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎች የዋጋ ውድነቱን ሊቀንሱት አሊያም ባለበት ሊያረጋጉት አልቻሉም፡፡ ይልቁንም ከለት ዕለት በእያንዳንዱ ዋጋ ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ እየተለመደ መጥቷል፡፡
በተለይ መሠረታዊ የሚባሉት የምግብ ሸቀጦች ከዕለት ዕለት የዋጋ ጭማሪ እየታባቸው ነው፡፡ በማከፋፈያና ቸርቻሪ ሱቆች እንደየዓይነቱ ከ880 ብር ጀምሮ እስከ 950 ብር ድረስ ይሸጥ የነበረ አምስት ሊትር የሱፍ ፈሳሽ ዘይት አሁን ላይ መነሻ ዋጋው 980 ሆኗል፡፡ የስንዴ ዱቄት፣ ጥራጥሬና እህሎች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ዋጋቸው በእጅጉ ንሯል፡፡
ለኑሮ ውድነቱ በኢትዮጵያ ያለው ሰላም መደፍረስ፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ተፅዕኖ፣ የምርትና ፍላጎት አለመጣጣም፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የነጋዴዎች አሻጥርና ሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የሚደረደሩለት ቢሆንም፣ መንግሥት እየሠራሁበት ነው ያለው አካሄድ የኑሮ ውድነቱ ይበልጡኑ እንዳይብስ አድርጎ ይሆናል እንጂ፣ አሁን ሕዝቡ እየተፈተነበት ያለውን የገቢና ወጪ አለመመጣጠን ችግር አልፈታም፡፡
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ቀድሞ ይመገባቸው የነበሩ ምግቦችን ለመተው አልያም ለመቀነስ ተገዷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከገንቢ ምግቦች የሚመደቡትና የጤናም ሆነ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ከዕለት ምግብ ውስጥ እንዲካተት የሚመክሩት ወተትና የወተት ተዋፅዖ እንዲሁም እንቁላል ይገኙበታል፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንስሳት ተዋፅዖ የሆኑት ወተት፣ ቅቤ፣ ዓይብና ሌሎች ምርቶች እንዲሁም የእንቁላል ዋጋ ጣሪያ እየነካ ይገኛል፡፡ በተለይም ከሰሞኑ የወተት ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱ ሸማቾችን ከማማረርም አልፎ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከኢንዱስትሪው እንዲወጡ አድርጓል፡፡
በዘርፉ ላይ የሚታየው የአቅርቦት ችግርና የማኅበረሰቡ ፍላጎት ባለመጣጣሙም የአንድ ሊትር ወተት ዋጋ ከ40 ብር ወደ 60 ብር እንዲንር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም የወተት ነጋዴዎችንም ሆነ ተጠቃሚውን የማኅበረሰብ ክፍል ፈተና ውስጥ ከቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል አቶ ደምሴ ኃይሉ ይገኙበታል፡፡
ከተለያዩ ቦታዎች ወተት በመሰብሰብ ለማኅበረሰቡ እያከፋፈሉ የሚገኙት አቶ ደምሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ዘርፉን ጎድቶታል፡፡
ከዚህ በፊት ወተት በቀጥታ ከገበሬዎች እንደሚረከቡ፣ አሁን ግን ዘርፉ ላይ ደላሎች በመግባታቸው በቀጥታ ከገበሬዎች እየገዙ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በቀን አምስት የ25 ሊትር ጀሪካን እንደሚሸጡ፣ አብዛኛውን ጊዜም ወተት የሚያመጡት ከቢሾፍቱና ከአዳማ እንደነበረ አሁን ላይ ወተት ጭራሽኑ እያገኙ እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡
በዚህ ሥራ ከተሰማሩ ሰባት ዓመታት ማስቆጠራቸውን የሚያስታውሱት አቶ ደምሴ፣ የከብቶች መኖ ዋጋ በመናሩና አብዛኛው አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውን እየሸጡ በመሆኑ የወተት፣ የዓይብና የቅቤ ዋጋ ሊጨምር እንደቻለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አንድ ሊትር ወተት ከ55 ብር እስከ 60 ብር ድረስ እየሸጡ መሆኑን፣ ከዚህ በፊት አንድ ሊትር የሚወስዱ አብዛኛው ሸማቾች ግማሽ ሊትር እየወሰዱ እንደሆነ ገልጸው፣ የወተት ጭማሪው ከታየ በኋላም ጭራሽኑ ያቆሙ ደንበኞች እንዳሉዋቸው ተናግረዋል፡፡
የወተት ንግድ ሥራ በአሁኑ ወቅት አዋጭ እንዳልሆነ የትራንስፖርትና የቤት ኪራይ ሲደመር ምንም ዓይነት ትርፍ እንደማያገኝም አክለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም አንድ ሊትር ወተት ከ30 ብር እስከ 40 ብር ይሸጡ እንደነበር፣ ከአርሶ አደሮች የሚቀበሉበት ዋጋና አሁን ላይ እየሸጡበት የሚገኘው ዋጋ ባለመመጣጠኑ ንግዱን ማቆምን አማራጭ እንዳደረጉት አስረድተዋል፡፡
በርካታ ወላጀች ለልጆቻቸው ለመስጠት የማይሳሱለትን ወተት ማጣት ከባድ መሆኑንና የኑሮ ውድነት እንደዚህ በከፋበት ወቅት ልጅ ማሳደግ ፈተና መሆኑን የነገሩን ደግሞ ወ/ሮ ብዙነሽ ደስታ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ብዙነሽ የአራት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ሦስት ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ሠፈራቸው አካባቢ ከሚገኝ የወተት አከራይ አንድ ሊትር ወተት በወር ከ600 ብር እስከ 800 ብር በመከራየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹አሁን ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደርሰናል? ወተት ተከራይቼ ልጅን ማሳደግ አይደለም የዕለት ጉርስን መሙላት ዳገት ሆኖብኛል፤›› ያሉት ወ/ሮ ብዙነሽ፣ አራተኛ ልጃቸውንም አንድ ሊትር ወተት በወር አንድ ሺሕ ብር በመኮናተር እያሳደጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአንድ ሊትር ወተት ዋጋ ጣሪያ መንካቱንና ይከራዩት የነበረበት ቦታ በአንድ ሊትር ላይ 20 ብር በመጨመሩ ለማቋረጥ መገደዳቸውን ገልጸው፣ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ በተለያዩ ግብዓቶች ላይ እየጨመረ የሚሄደውን ዋጋ ማረጋጋትና የንግድ ሥርዓቱ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ በዘፈቀደ ዋጋ ይጨምራል የሚሉት ወ/ሮ ብዙነሽ፣ በዚህም የተነሳ ከቤት ኪራይና አሁን እየታየ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ልጆቻቸውን ማሳደግ እንደከበዳቸውና ምግባቸውን እየቀነሱ መሆኑን፣ አንዳንዴም ለልጆቻቸው ብቻ አብልተው ለራሳቸው የሚተውበት ጊዜ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ወተት ተከራይተው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቀርቶ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሙላት እንደከበዳቸው፣ የኅብረተሰቡን በልቶ የማደር ችግር በመረዳት ለችግሩ ቅድሚያ ሰጥቶ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የሀፒ ወተት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ፋንቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከታች ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የሚሰበሰበው ወተት ውኃ የሚደባለቅበት በመሆኑ ለወተት አቀናባሪዎች ፈተና ሆኗል፡፡ ዘርፉ ላይ ደላሎች በመግባታቸውና የወተት ዋጋ እንዲንር በማድረጋቸው አብዛኛው የወተት ማቀናበሪያ ፋብሪካዎች ድርጅታቸውን እንዲዘጉ አድርጓል፡፡
መንግሥት በዘርፉ ላይ አስገዳጅ የሆነ ሕግ ባለመዘርጋቱና ምንም ዓይነት ትኩረት ባለመሰጠቱ ዘርፉ ሊጎዳ እንደቻለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ይህም ምርትና አቅርቦቱ ላይ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል፡፡
ፋብሪካው በሚቋቋምበት ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር እንዳመቻቸላቸው ገልጸው፣ ለተመቻቸላቸው ብድር በየወሩ ከ500 ሺሕ እስከ 600 ሺሕ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ በመሆኑ ብድሩንም መክፈል ባለመቻላቸው ፋብሪካው ሊዘጋ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ከመዘጋቱ በፊት በቀን ከ10 እስከ 15 ሺሕ ሊትር ወተት ማቀናበር ይችል እንደነበር፣ የወተት አቅርቦት ችግር በመኖሩ ምክንያት ግን ፋብሪካው ማምረት ከሚችለው በታች ሲያመርት መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በአካባቢውም ከተለያዩ ቦታዎች የሚሰበሰበው ወተት በቀን 30 ሺሕ ሊትር ነው ቢባልም፣ ድርጅቱ የሚያገኘው የወተት አቅርቦት ማምረት ከሚችለው በታች እንደነበር አቶ ሰለሞን አክለዋል፡፡
በአጠቃላይ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለ በተለይም በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩ ደላሎች ዘርፉ ከፍተኛ ማጥ ውስጥ እንዲገባና ማኅበረሰቡን ለተለያየ እንግልት እንዲጋለጡ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
‹‹የዚህ ሁሉ ተጠያቂ መንግሥት ነው›› የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ የወተት ፋብሪካ ባለቤቶች ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር መንግሥት እንዲቀርፍላቸው በር ቢያንኳኩም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የከብቶች የመኖ ውድነትና በሕገ ወጥ መንገድ የተሰማሩ የዘርፉ ተዋናዮች መበራከት እንዲሁም መንግሥት ለወተት ፋብሪካ ባለቤቶች ምቹ ሁኔታዎች አለማዘጋጀቱ ዘርፉ እንዲጎዳ አድርጎታል የሚሉት የአልሚ ወተት ፋብሪካ ባለቤትና የኢትዮጵያ የወተት አቀናባሪዎች ማኅበር መሥራችና የቦርድ አባል አቶ አስማማው ታፈሰ ናቸው፡፡
በሲዳማ ክልል (በሐዋሳ) በ1997 ዓ.ም. የተቋቋመው የአልሚ ወተት ፋብሪካ፣ 780 ያህል ገበሬዎች ጋር በመድረስና ወተት በመሰብሰብ አቀናብሮ በመሸጥ ይታወቅ እንደነበር አቶ አስማማው ተናግረዋል፡፡
በቀን 20 ሺሕ ሊትር ወተት የማቀናበር አቅም እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ አስማማው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘርፉ ላይ ደላላ በመግባቱና ማሽኑ የሚጠበቅበትን ያክል ወተት ባለማግኘቱ ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ ሊዘጋ እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡
አንዳንድ ገበሬዎች ሆኑ አቀናባሪዎች ውኃ ይቀላቅላሉ የሚሉት አቶ አስማማው መንግሥት ይህንን ለማስተካከል ያወጣው ፖሊሲ የፋብሪካ ባለቤቶችን ብቻ ስለሚመለከት በሕገ ወጥ መንገድ የሚሠሩ ነጋዴዎች ዘርፉ ላይ እንደፈለጉ እንዲፈነጩ አድርጓልም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ድርጅታቸው የተበደረውን ብድር ሊከፍል ባለመቻሉ በሀራጅ ሊሸጥ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት መንግሥት ዘርፉ ላይ ትኩረት ባለመስጠቱ እንደሆነ አክለዋል፡፡
የአልሚ ወተት ፋብሪካ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደገጠመው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ተቋሙ አገልግሎት ሲሰጥ በነበረበት ወቅት ሥራ ላይ የነበሩ ወገኖች ከሥራ ገበታቸው መፈናቀላቸ አሳዛኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በየቦታው የሚገኙ የወተት ፋብሪካዎች መዘጋታቸው ችግሩን ቢያባብሰውም፣ እጥረቱን ተጠቅመው ያልተገባ ዋጋ እየጫኑ የሚገኙ ነጋዴዎችን መንግሥት መቆጣጠር አለበት፡፡ በኩዊንስ ሱፐር ማርኬቶች 21 ብር ከ80 ሳንቲም አካባቢ የሚሸጠው ግማሽ ሊትር ፓስቾራይዝድ ሾላ ወተት በየሠፈሩ በሚገኙ ሱቆች ከ30 ብር እስከ 32 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ አንድ የፈረንጅ እንቁላል አዲስ አበባ ላይ ከሰባት እስከ ሰባት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ይሸጥ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ እስከ ዘጠኝ ብር ገብቷል፡፡ የሐበሻ እንቁላል ደግሞ አንዱ 11 ብር፡፡
ቅቤ ከባህር ዳር አሁን ላይ በኪሎ እስከ 400 ብር ድረስ፣ ከሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን በኪሎ 800 ብር እየተጠየቀበት ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ እንደየቅቤው ዓይነት በኪሎ እስከ 790 ብር ይሸጣል፡፡
ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ ትያዛለች፡፡ በዓለም ከ10 አገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡ ሆኖም ከወተት ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም፡፡ በሌላ በኩልም ሌላው ዓለም ባለው የእንስሳት ቁጥር ልክ ወተትን በየገበታው በተለያየ መልኩ ሲጠቀም፣ በኢትዮጵያ ግን ባሉት እንስሳት ልክ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ የወተትና ወተት ምርቶች ወጪ ንግድን የሚያደናቅፉ ምክንያቶች በሚል እ.ኤ.አ. በ2019 አፕሮችስ ኢን ፖሊውተሪ፣ ዳየሪ ኤንድ ቨትርነሪ ሳይንስ ጆርናል ላይ የሰፈረው ዳሰሳ፣ በኢትዮጵያ ዓመታዊ የወተት ምርት 5.2 ቢሊዮን ሊትር እንደሆነ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከኢህ ቀደም እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ ለአንድ ሰው በዓመት በአማካይ የሚደርሰው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ነው፡፡ ለችግሩ ከሚጠቀሡት ምክንያቶች አንዱ ያሉት የወተት ላሞች እንደብዛታቸው ወተት የሚሰጡ አለመሆናቸው ነው፡፡ የወተት ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ደረጃ ዕድገት አለማሳየቱና ግብይቱም ጤናማ አለመሆኑም ከችግሮቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡