Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕገወጥ የሜትርና የኤሌክትሮኒክስ ታክሲዎች መኖራቸው በመረጋገጡ እንደገና ምዝገባ እንዲደረግ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚኒ ባስና በሚድ ባሶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል

በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ የሜትርና ኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች በመኖራቸው፣ እንደገና ምዝገባ እንዲደረግ መወሰኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የሜትርና የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራትና ድርጅቶችን ለመቆጣጠር በሚያስችል መንገድ ማሻሻያ መደረጉንና በዚህ መሠረት አገልግሎት ሰጪዎቹን እንደ አዲስ መመዝገብ ማስፈለጉን፣ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብና ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የስምሪት ዳይሬክተር አቶ አልዓዛር ይርዳው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ 53 የሜትር ታክሲ ማኅበራት መኖራቸውን ገልጸው በእነዚህ ማኅበራት ውስጥም 2,800 ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ ብለዋል። ከእነዚህ ውስጥም ፈቃዳቸውን በወቅቱ ያላደሱ በርካታ ማኅበራት በመኖራቸው ለቁጥጥር እንዲያመች በድጋሚ ምዝገባ ሊደረግ መሆኑን አክለዋል።

በተጨማሪም እስካሁን በቢሮው ዕውቅና ያገኙት የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች 17 ብቻ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውጪ ፈቃድ ሳያወጡ የሚሠሩ መኖራቸውን ገልጸዋል። ፈቃድ ካወጡት ውስጥም አብዛኞቹ በወቅቱ ሳያድሱ እየሠሩ በመሆናቸው እንደገና ምዝገባ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል።

በሌላ በኩል ቢሮው በነዳጅ ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ ተከትሎ በሚኒ ባስና በሚዲ ባስ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ላይ ከረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል።

የትራንስፖርት ዋጋ ላይ በአጠቃላይ ከ0.50 ሳንቲም እስከ 3 ብር ከ50 ሳንቲም ጭማሪ ማድረጉን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ይርጋለም ብርሃኔ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በሚድ ባስ (ሃይገርና ቅጥቅጥ) ተሽከርካሪዎች ታሪፍ ላይ ከ0.50 ሳንቲም እስከ 2.00 ብር ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣  በሚኒ ባስ ታክሲዎች ላይ ደግሞ ከ0.50 ሳንቲም እስከ 3.50 ብር መጨመሩን አብራርተዋል።

የታሪፍ አዘገጃጀቱም ከዚህ በፊት በኪሎ ሜትር የነበረ ሲሆን፣ እንደ አዲስ የትራንስፖርት መስመሮችን መሠረት አድርጎ እንደሚተገበር ተገልጿል። ከተፈቀደው ታሪፍ ውጪ የሚጭኑ አሽከርካሪዎችን በተመለከተ ደግሞ በከተማዋ በአጠቃላይ 486 የታክሲ አገልግሎት መስመሮች መኖራቸውን፣ በእነዚህም መስመሮች የቁጥጥር ሥራ የሚሠሩ ከ400 በላይ ባለሙያዎች እንዳሉ በቢሮው የትራንስፖርት ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ገልጸዋል።

ነገር ግን የቁጥጥር ሒደቱ ቅሬታ የሚነሳበት በመሆኑና በተቆጣጣሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት የሚፈተሩ ክፍተቶች በመኖራቸው፣ ይህንን ለማሻሻል የባለሙያዎቹን ጥቅማ ትቅም ከማስተካከል ጀምሮ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉ  ነው ብለዋል። ነገር ግን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በወጣው ታሪፍ መገልገል መብቱ መሆኑን አውቆ፣ መብቱን ለማስከበር ተባባሪ መሆን አለበት ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች