የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በምሥራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ጨዋታ ግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል፡፡ በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ዛንዚባር ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ የምድባቸውን ሁለት ጨዋታ አሸንፈውና አንድ አቻ በመውጣት በሰባት ነጥብ ወደ ግማሽ ፍጻሜው መድረሳቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከቀናት በፊት 23 የቡድን አባላትን ይዞ የተጓዘው የሉሲዎቹ አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ስብስብ፣ የምድቡን ሁለት ጨዋታ ክፍተኛ ግብ በማስቆጠር ጭምር ተጋጣሚዎቹን መርታት ችሏል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ የዛንዚባርን ብሔራዊ ቡድን የገጠሙት ሉሲዎቹ፣ 5 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲረቱ፣ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከታንዛኒያ 2 ለ 2 ሲያጠናቅቁ፣ ደቡብ ሱዳንን 4 ለ 0 በመርታት ወደ ግማሽ ፍጻሜው መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በግማሽ ፍጻሜው ኢትዮጵያ ዑጋንዳን ስትገጥም፣ ታንዛኒያ ብሩንዲን ትገጥማለች፡፡ የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች ቅዳሜ ሰኔ 4 ቀን የፍጻሜ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1986 በዛንዚባር አስተናጋጅነት የጀመረውና ለሠላሳ ዓመታት የተቋረጠው የሴካፋ ውድድሩ፣ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ በዑጋንዳ የተሰናዳ ሲሆን ሉሲዎቹ ለአራተኛ ጊዜ መሳተፍ ችለዋል፡፡
ሉሲዎቹ እ.ኤ.አ. 2016 እና 2018 ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ ታንዛኒያ ሁለት ጊዜ ሻምፒዮና በመሆን ቀዳሚዋ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ናት፡፡ ኬንያ የ2019 የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታ አሸናፊ ብትሆንም ፊፋ መንግሥት በእግር ኳሱ ጣልቃ ገብቷል በሚል አገሪቷን ከየትኛውም እግር ኳስ ጨዋታ ማገዱን ተከትሎ በዘንድሮ ውድድር ላይ መካፈል አልቻለችም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአኅጉራዊ ሻምፒዮናዎች የተለያዩ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖችን እየፈተነ የመጣው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ በዘንድሮው የሴካፋ ዋንጫ ጨዋታ ያሸንፋሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱ አይዘነጋም፡፡