Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

አስተማማኝ የተባይ መከላከያና መቆጣጠሪያ የሚያስፈልገው የግብርና ዘርፍ    

አቶ ሃደራ ገብረመድኅን ከፍተኛ ትምህርታቸውን ከቀድሞ ጂማ እርሻ ቴክኒክ እንዲሁም ከሐረማያ ኮሌጅ በዕፀዋት ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ ከአሜሪካ ዊስኮንሰን ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም በሩሲያና ፊሊፒንስ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ በሥራው ዓለምም ለ25 ዓመታት በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በግብርናና በጤና ማለትም በግብርና የአንበጣ መከላከያ ቴክኒሻን፣ ተመራማሪ፣ ከፍተኛ ባለሙያ፣ የዘርፍ መሪ በመሆንና፣ በጤና ዘርፍ የወባ ማጥፊያ ድርጅት የጅማ ዓብይ ጣቢያ ሥራ መሪ፣ የፕላን ቀጣና ኮሚሽን የስታትስቲክስና የምርምር መምርያ ኃላፊ (ደሴ)፣ በቀድሞ የመንግሥት ምክር ቤት  የሶሻል፣ ኢኮኖሚክስና የአስተዳደር ጉዳዮች ዋና ኢንስፔክተር በመሆን  አገልግለዋል፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሞያው ለደቡብና ትግራይ ክልሎች ሁለት ማንዋሎች በማዘጋጀት፣ ሁለት ፕሮግራሞች ለሰሜን ወሎና ለአፋር፣ ሦስት ፕሮጀክቶች  ለሴቭ ዘ ችልድረን ሰሜን ወሎ ላይ፣ አነስተኛ መስኖ በአርጡሜ ጅሎ ወረዳ ከሚሴ ዞን ላይና በሑመራ የተባይ መከላከያ ፕሮጀክት በማማከር ሥራ ለዘጠኝ ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ስለምስጥ በቤንሻንጉል አሶሳ፣ የዲዲቲ ሁኔታ በአምስት ክልሎች፣ በአገር አቀፍ የፀረ ተባይ ክምችት ማስወገድና የማሽላ ጢንዚዛ ላይ፣ ሸዋ ሮቢትና አፋር ውስጥ ጥናቶች ሠርተዋል፡፡ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመሆን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በማቋቋምም በኦሮሚያ በአዳማና በአፋር አሚባራ ዱቡቲ በቀበሌ ደረጃ ስለ ፀረ ተባይ አጠቃቀምና ደኅንነት ለእርሻ ወኪሎችና  ለገበሬዎች ሥልጠና በመስጠት ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡  በተባይ  መከላከያና መቆጣጠሪያ የሥራ ዘርፍ ሁለት በአማርኛና  አንድ በእንግሊዝኛ  ሦስት  መጽሐፍት አሳትመዋል፡፡ ባላቸው የሥራ ተሞክሮ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-  እንስሳትና ዕፅዋትን የሚያጠቁ ተባዮች የምንላቸውን ቢገልጹልን?

አቶ ሃደራ፡- በኢትዮጵያ እስካሁን ከቫይረስ እስከ ትልልቅ እንስሳት እንደ ዝንጀሮና ጃርት የመሳሰሉትን ጨመሮ 40 የሚሆኑ የታወቁ ተባዮች አሉ፡፡ እነዚህም የኢንሴክት ተባይ፣ የዕፀዋት በሽታ/ፓተጂንስ፣ አረም፣ አይጥና መሰሎቻቸውና ወፍ ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ሌላ ተባይ ከውጪ እንዳይገባና በአገር ውስጥም ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይዛመት የፀረ ተባይ ምዝገባ፣ ምርመራና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መከላከያው ምንድን ነው?

አቶ ሃደራ፡- መከላከያው በሁለት ይከፈላል፡፡ ባህላዊ/አገር በቀል በአገር ውስጥ የተሻሻለ ዘር መጠቀም፣ በራሱ ያለምንም ድጋፍ ፍሬ የሚሰጥ ዘርና የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም፣ የተፈጥሮ ጠላት መጠቀም፣ ተባይ የሚቋቋም ዘር መጠቀም፣ ሕጋዊ የእርሻ ዘዴ አያያዝን ከኤክስተንሽን አጣምሮ መጠቀም ነው፡፡ የዚህ ጥቅም  ለተጨማሪ ወጪና ለብከላ አለማጋለጡ ነው፡፡ ተጓዳኝ ጉዳት አያስከትልም፡፡ ጉዳቱ ደግሞ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ይፈልጋል ፣ሙሉ መከላከል አይሰጥም ፣መከላከያው ቅጽበታዊ አይደለም፣ ለመገምገምም አይመችም፡፡ ሌላኛው ዘመናዊው ነው፡፡ ዘመናዊ መጤ የቴክኖሎጂ ፓኬጅ  ነው፡፡ ያለ ድጋፍ በራሱ ምርት የማይሰጠውን የተዳቀለ ዘር መጠቀም ነው፡፡ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይና ኤክስቴንሽን የሚጠቀም ሆኖ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና አካባቢያዊ ተጓዳኝ ተፅዕኖ የሚፈጥርና ዘላቂነት የሌለው ሒደት ነው፡፡ ጥቅሙ አስተማማኝ፣ ለሁሉም አካባቢ የሚመች፣ ለወረርሽኝ ተስማሚ መሆኑ ሲሆን፣ አደገኛ ቅሪት መተው፣ የተባዮች መቋቋም መፍጠሩ፣ አካባቢን መበከሉ፣ ዘላቂነት የሌለው መሆኑ ከጉዳቱ ይመደባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ምን አይነት ቁጥጥር ያስፈልገዋል? ከዚህ ቀደም የነበረውን አሰራር ቢያስታውሱን?

አቶ ሃደራ፡- ሕጋዊ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ የዕፀዋት ኳራንቲን አንዱ ነው፡፡ ተባይ ከውጪ እንዳይገባ፣ በአገር ውስጥ የሚገኝም ከቦታ ቦታ እንዳይዛመት መገደብ እንደዚሁም የፀረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉ የሚገኝበት ግብርና ሚኒስቴር የሰብል ምርት፣ ጥጥ፣ ሸንኮራ አገዳ፣ የግጦሽ ሳር፣ ቋሚ ተክል (ቡና፣ ሻይ፣ ትምባሆና ጫት) ደን፣ ፓርክና መናፈሻና ፓርክ፣ በስፋት የሚተከለውን ችግኝ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌ የሽቦ ተሸካሚ ፖሎችና ሌሎች ለሰው ኑሮ የሚጠቅሙ ቁሳቁሶች ሁሉ ከተባይ መከላከል አለበት፡፡ ዘርፉ ከግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ሆኖ አፈጻጸሙ ሲነሳና ሲወድቅ ነበር፡፡ በ1971 ዓ.ም. አካባቢ የእርሻ ሚኒስቴር እየተባለ ይጠራ የነበረው ለሥራው ጥራትና ቅልጥፍና በሚል ሰበብ የመዋቅር ለውጥ ተካሂዶ በሦስት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ማለትም የአሁኑ ግብርና ሚኒስቴር፣ የመንግሥት እርሻ ልማት ሚኒስቴርና የቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር ተብሎ ተዋቅሮ ነበር፡፡  በዚህን ጊዜ የአዝርዕት ምርት ልማት፣ ጥበቃና ቁጥጥር መምሪያ የሚባል ከለውጥ በፊት የነበረ ቢሆንም፣ ያለበቂ ምክንያት ትኩረት ተነፈገው፡፡ ለዚህ የውስጥና የውጪ ባለድርሻ ረዥም ሥውር እጆችን  አልነበረም ለማለት አይቻልም፡፡ ይኸውም የሁለቱን አዲሶች የመንግሥት እርሻ ልማት ሚኒስቴርና የቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴርን በር በርግዶ ከፍተኛ የፀረ ተባይ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ለነጋዴዎቹም ጥሩ ዕድል  ፈጥሮላቸው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ኤክስቴንሽን ፕሮጀክት ኢንፕልመንቴሽን ደፓርትመንት በሚባል አውቶኖመስ ድርጅት/ኤፒድ የተባይ መከላከያ በክፍል ደረጃ በዝቅተኛ ቦታ ተዋቀረ፡፡ ቀሪው አካል በሁለቱ ሚኒስቴሮች ተሰባጥሮ ወፍ ዘራሽና ሸባ ሆኖ ቀረ፡፡ የነበረው ክፍል በሒደት ዋና ክፍል ሆኖ አጠቃላይ የግብርና ሚኒስቴር የተባይ መከላከያና ቁጥጥር ተጠሪ ሆኖ ተገቢውን ግልጋሎት ማቅረብ ባለመቻሉ በጊዜያዊ ጥገና የአዝርዕት ልማት፣ ጥበቃና ሬጉላቶሪና ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ተብሎ በዋና ክፍል ተወሰኖ ቆየ፡፡ እንደገና እ.ኤ.አ. ከ1973 እስከ 1983 እየወደቀ እየተነሳ እስከ መምሪያ ደርሷል፡፡ በመቀጠል እስከ 1992 የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ሬጉላቶሪ ቴክኖሎጂ መምሪያ ወደ ዋና ክፍል ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ እ.ኤ.አ. 2008 በተደረገው አጠቃላይ የግብርና ሚኒስቴር የመዋቅር ለውጥ የዋና ክፍሉ አንዱ አካል ወደ እንስሳትና የዕፀዋት ጤና ሲመደብ ሌላኛው ደግሞ ወደ ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ተመድቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ምን ያሳያል?

አቶ ሃደራ፡- ይህ የሚያሳየው የላይኛውና የመካከለኛው የፖለቲካ አካል ሹመኞች ያልተገደበ ሥልጣን ሙያው ከሚጠይቀው ሐሳብ ውጪ ጣልቃ እንደሚገቡ ነው፡፡ ሳይጠናና ያለተጠያቂነት ውሳኔ መሰጠቱ የሥራ ዘርፉን ጎድቶታል፡፡ ይህ የሥራ ዘርፍ በአዝርዕት ልማት ምርትና ማሻሻያ ማኔጅመንትና ኤክስቴንሽን ተውጦ ትኩረት ሳይሰጠው ተጠሪነቱ ለሰብል ልማት፣ ለሰብል ማሻሻያ እንዲሆንና እነሱ ለሚፈጥሩት ችግር ሽፋን እንዲሰጥ የታሰበ ይመስላል፡፡ በተለይ ደግሞ ከዘርፉ መሻሻል ግንኙነት የሌላቸው በየወቅቱ በአጠቃላይና በተናጠል የሚካሄዱ ቢፒአርና ካይዘን የሥራ ዘርፉን አቀንጭረውታል፡፡ በብዙ ዓመታት ጥረት የተገነባ የሾላ አዝርዕት ጥበቃ ላቦራቶሪ ከነሙሉ ዝግጅቱ በድንገት መዘጋትና ቢሮው ደግሞ ለሌላ ድርጅት ተላልፎ መሰጠቱ እስካሁን ትልቅ እንቆቅልሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ተባይ ቁጥጥሩ  ላይ ምን አስከተለ?

አቶ ሃደራ፡- የተወሰኑ ተባዮች ከውጭ የገቡና ከግብርና ሚኒስቴር አቅምና ችሎታ በላይ ሆነው ያስቸገሩም ነበሩ፡፡ የማሽላ ጢንዚዛ በሸዋ ሮቢት አካባቢ፣ ቱታ አብሶሉታ በቲማቲም ላይ በመቂና ዝዋይ አካባቢ፣ ሚሊ ባግ በጥጥ ላይ በመልካ  ወረር አካባቢ፣ አርሚወርም ፎል በበቆሎ ላይ በደቡብ አካባቢ፣ ከነበረው የመከላከል እንቅስቃሴ ከግብርናም ከአገር ውስጥና ከውጪ ለጋሽና ባለድርሻ አካላት፣ ከፀረ ተባይ ነጋዴዎችም አቅምና ችሎታ በላይ በመሆን ያወደሙትን አውድመው የተፈጥሮ ሒደታቸውን ጨርሰው ማለፋቸው የሚታወስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንበጣን በተመለከተስ?

አቶ ሃደራ፡- አንበጣን በተመለከተ በ1972 ዓ.ም. በኬንያ ስለምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ለ21 ቀናት የተካሄደ ስብሰባ መነሻነት የቀረበ ሪፖርት የድርጅቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በመገምገም የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅን በሚመለከት ለግብርና ሚኒስቴር መቅርቡ ይታወሳል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ሚኒስቴሩ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማስታወሻ ጽፏል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በምላሹ ለግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የተባይ መከላከያ ድርጅት የርጭት አውሮፕላኖች ያሉት ዝርዝር ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ ይታዘዛል፡፡ በወቅቱ የነበሩት ቋሚ ተጠሪ አጋጣሚውን በመጠቀም ጥናቱ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ እርሻ ልማት መምሪያን ያዛሉ፡፡ መምሪያውም በጥቅምት ወር 1973 ዓ.ም. በትዕዛዙ መሠረት ጥናቱን አዘጋጅቶ እንዳቀረበ የቀረበው ጥናት በድርጅትና ሥራ አመራር በኩል እንዲታይ በድጋሚ በማዘዛቸው ጥናቱ በመካሄድ ላይ እንዳለ ደግመው በጥር ወር 1973 ዓ.ም. ጥናቱ እንዲዘገይ በማለት በእንጥልጥል እንዲቀር ተደረገ፡፡ አዲሱ ቋሚ ተጠሪ በ1974 ዓ.ም. መጨረሻ ገደማ አሁንም በድጋሚ ድርጅትና ሥራ አመራር በእንጥልጥል የቀረውን ጥናት እንዲያየው ታዘዘ፡፡ ድርጅትና የሥራ አመራር አይቶ ቢያቀርበውም ለመጨረሻ ውሳኔ ለአፈጻጸሙ የተሻለ እንዲሆን የሚኒስትሩ የማኔጅመንት ኮሚቴ እንዲወያይበት በማሰብ የድርጅትና ሥራ አመራር አገልግሎት አቅርበዋል በሚል በ2/9/75 ዓ.ም. ተዘግቶ ቀረ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን መደረግ ስላለበት ያለዎትን ምክረ ሐሳብ  ቢነግሩን?

አቶ ሃደራ፡- ተባይ መከላከል በወቅት ሳይታጠር የዓመት ሙሉ ቀጣይነት ያለው የሥራ ዘርፍ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ሥራው በይዘት፣ በቦታና በጊዜ በካላንደርና በእርከን ተከፍሎ መታቀድ ይኖርበታል፡፡ ይኸውም ተባዩን መለየት፣ ስለተባዩ አሰሳ ማካሄድ የጉዳትን መጠን ማወቅ፣ የተባይና የፀረ ተባይ ቁጥጥር በተጓዳኝ ማካሄድ፣ የሥልጠናና ተግባራዊ የምርምር ግብዓቶችን ተጠቅሞ በመጨረሻ ተባይ ሲከሰት መከላከልና የዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ በሪፖርት መልክ በየዓመቱ እየሰነዱ ለቀጣይ ዓመት ማጣቀሻ አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ግን እንደተጠቀሰው ሳይሆን ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ በሁሉም ደረጃ ቦታና ጊዜ ለረዥም ጊዜ በዚህ የሥራ ዘርፍ የተካሄደው ተግባራዊ ጥናት እንደሚያሳየውና እንደተገኘው ውጤት ሥራው በዚህ መልክ እንደማይካሄድ ታውቋል፡፡ ስለዚህ ይህን ሥራ ሊያሠራ የሚያስችል አጠቃላይ የፖሊሲ አቅጣጫ፣ ተቋም፣ በጀት፣ በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ተግባራዊ ሥልጠናና ምርምር የሚያበረታታ ሆኖ ተጠያቂነትና ግልጽነት መኖር አለበት፡፡ በብዙ ድካምና ጥረት የተገነባ የሾላ አዝርዕት ጥበቃ ላቦራቶር እንዴትና ለምን እንደተዘጋና ቢሮውም ለሌላ አካል ተላልፎ እንደተሰጠ መርምሮ ሊያሠራ የሚያስችል አቅም መገንባት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በትምህርት ዘርፍስ?

አቶ ሃደራ፡- ምንም እንኳን ወደ 45 የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎችና ከ15 በላይ ቲቪቲ ኮሌጆች ቢኖሩም አዳቸውም በተባይ መከላከያና መቆጣጠሪያ የሥራ ዘርፍ ራሱ የቻለ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ፣ በሰርተፍኬት፣ በዲፕሎማና የመጀመርያ ዲግሪ ሲሰጡ አልታየም፡፡ በዚህ ሙያና በዚህ ደረጃ የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም፡፡ ታዲያ በዚህ የሥራ ዘርፍ ችግሩ እንዴት ይሸፈናል ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ በምርምር ማዕከል በብሔራዊ የግብርና ምርምርና በብዙ ቅርንጫፍ ማዕከላቱና አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ተመራማሪዎች የሚሠሩት ከፀረ ተባይ ፍቱንነትና ጥራት (Pesticide Screening) እና ከሰብል ማዳቀል (Germ Plasma) የዘለለ አይደለም፡፡ ሁለቱን ባህላዊና ዘመናዊውን አጣምሮ ወይም በምክንያት አንዱን አብልጦ ተግባራዊ ተባይ ነክ ምርምር አይካሄድም፡፡ እንዲያውም ሁለት የከፍተኛ ትምህርት ቤቶችና ሦስት የምርምር ማዕከላት የፀረ ተባይ አያያዛቸው ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ሆኖ ተገኝቷል፡፡  በተባይ መከላከያና መቆጣጠሪያ የሥራ ዘርፍ የሠለጠነ የሰው ኃይል ስለሌለ በሰብል ልማት ወይም በሌላ እንደ ሶሻል ሳይንስ የሠለጠኑትን በመመደብ ግብርና ሚኒስቴርም እየተሠራ ነው ብሎ አምኖ መቀበሉ ስለሙያው ያለውን ግንዛቤ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም የተባይ መከላከያና መቆጣጠሪያ የሥራ ዘርፍ በሰብል ልማት ይመራል፣ ይሠራል፡፡ ከሁለቱ የተባይ መከላከያ ዘዴው ባህላዊውን በመጣል በዘመናዊው በፀረ ተባይ ብቻ ስለተንጠለጠለ በፍፁም ዘላቂነት የለውም፡፡ ፀረ ተባይ በአየር ወይም በየብስ ሲረጭ ከአሥር እስከ 15 በመቶ ወይም አንድ በመቶ ብቻ ዒላማውን እንደሚመታ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡ ይኸውም 85 እስከ 90  በመቶ እና 99 በመቶ የሚሆነው የአገር ሀብት የወጣበት እንደ ቆሻሻ ወደ አካባቢ  ይገባል፡፡ በአንፃሩ ምግብን፣ አየርን፣ ውኃና መሬትን ይበክላል፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ውድመት ከማስከተሉም ሌላ ዘላቂነት ስለሌለው ቆም  ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ከ1971 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ለ33 ዓመታት የዘርፉ በግብርና ውስጥ መውደቅና መነሳትን የቅርብና የሩቅ ፕሮግራም በመቀየስ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቅርብና የሩቅ ፕሮግራም የሚሏቸውን ቢገልጹልን?

አቶ ሃደራ፡- የቅርብ ፕሮግራም ሁለንተናዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ማድረግና የቅርቡ ምን ይሁን ሲባል ከሙያው ጋር የፖሊሲ አቅጣጫ ማስቀመጥና ምናልባት ለመፈንጠቅ ያህል፣ በዚህ ሥራ ጥሬ ዕውቀት ያለው ብቻ ሳይሆን የመስክ ልምድ ታክሎበት የተለያዩ ዕውቀቶችን ያቀፈ ቡድን ማቋቋም፣ በየዕርከኑ ተመድበው የሚገኙትን  በመስኩ ፕሮግራም አውጥቶ ተግባራዊነቱን የሚገመገም ሥልጠና መስጠት፣ ይህንንም ግብርና ሚኒስቴር በጀት መድቦ መከታተል ሊሆን ይችላል፡፡ የሩቅ ፕሮግራም በፖሊሲው ተመርኩዞ በዚህ የሥራ ዘርፍ ዘላቂ ትምህርት፣ ሥልጠናና ተግባራዊ ምርምር ሊያካሂድ የሚችል ተቋም ማቋቋም፣ ተቋሙ የተባይ መከላከያ ባለሙያ በሠርቲፊኬት፣ በዲፕሎማና በመጀመርያ ዲግሪ በማሠልጠን ለአገሪቱ አስተማማኝ የሆነ ብሔራዊ የተባይ መከላከያና መቆጣጠሪያ የሥራ ዘርፍ መገንባት ይኖርበታል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...