Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዳግም ማገርሸት

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዳግም ማገርሸት

ቀን:

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም እየተንሰራፋ ከመምጣትና የዓለም የጤና ሥጋት ከመሆን ያገደው ነገር የለም፡፡ የዓለም አቀፍ ትንበያም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ እንደገና እያገረሸ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለፈው ጥር ከበድ ያለ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕበል ተከስቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማዕበሉ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የኮቪድ-19 ሕሙማን ቁጥር ቀንሶና በየጤና ተቋማተ ተዘጋጅተው የነበሩት አልጋዎች ባዶ ሆነው ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ የተሻሻለው መመርያ 882/2014 እንዲተገበር መደረጉን፣ ይህም ሆኖ ግን ኮቪድ ቀንሷል በማለት በማኅበረሰቡ፣ በባለድርሻ አካላትና በአመራሩ ዘንድ መዘናጋቶች መታየታቸውን፣ ይህ ዓይነቱ መዘናጋት ደግሞ ዋጋ ሊያስከፍል በሚችል ሁኔታ ኮቪድ-19 እንደደረሰ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 41,209 ሰዎች ተመርምረው 2,666 ሰዎች የኮቪድ-19 ቫይረስ እንደተገኘባቸው፣ ይህም ማለት ከ100 ሰዎች መካከል በሰባት ሰዎች ላይ ኮቪድ-19 እንደሚገኝ፣ ከዚህም ሌላ ላለፉት አራት ሳምንታት በተደረገው ክትትል በየሳምንቱ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣ አመልክተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ሰዓት 14 ሰዎች በጽኑ ሕመም ላይ ይገኛሉ፡፡ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችም እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ኮቪድ-19 እየጨመረ መጥቷል፡፡ የዓለም አቀፍ ትምበያም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ይህንኑ ለዓለም አገሮች እያሰሙ ነው፡፡ የኢትዮጵያም መረጃ የሚያሳየው ይህንን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኮቪድ-19 አሁንም ሥጋት እንደሆነና ሊጨምርም እንደሚችል ልንገነዘበው ይገባል፤ ያሉት ደረጀ (ዶ/ር)፣ በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከዚህ በፊት ሲደረግ በነበረው መንገድ ርብርቡን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ኮቪድ-19 ማዕከል ባደረገ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ዕውቅና ያላቸው ሰዎች ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰፊ ሥራ መሥራት፣ ጤና ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በተቀናጀ መንገድ የክትትል፣ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራን ማከናወን፣ የመንግሥት አመራርም በወረርሽኙ ዙሪያ የተለየ ትኩረት በመስጠት፣ ኅብረተሰቡም ከጤና ተቋማት፣ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚወጡትን መረጃዎች ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርግ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ መመርያ 822/2014 በአግባቡ እንዲተገበር ሁሉም ሰው መጣር እንዳለበት፣ በአሁኑ ጊዜ ሦስተኛው ዙር የኮቪድ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑንና ማኅበረሰቡ ክትባቱን በአግባቡ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡ ተጨማሪ 25 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ መታቀዱንም አክለዋል፡፡

ስለሆነም ከዚህ በፊት ክትባት ወስደው ስድስት ወርና ከዚያም በላይ የቆዩ ተጨማሪ የማጠናከሪያ ክትባትን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያልወሰዱ ሰዎች ደግሞ ክተባቱን መውሰድ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ475,000 በላይ ዜጎች በወረርሽኙ ተይዘዋል፡፡ 7515 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ወረርሽኝ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል በተካሄደው እንቅስቃሴ 25 ሚሊዮን ዜጎች የቫይረስ መከላከያ ክትባት ወስደዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሆስፒታል አልጋዎች ባዶ መቅረት፣ የሕሙማን ቁጥርና የሞት መጠን መቀነስ ትልቅ መዘናጋትን እንዳስከተለ ገልጸው፣ ከበሽታው የባህሪ መለዋወጥ አንጻር ሲታይ ግን ሥርጭቱ እየተስፋፋ መምጣቱን ወቅታዊ መረጃዎች ማመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡

የየሳምንቱ የቅኝት ሪፖርትም የሚያሳየው በተለይ በከተሞች አካባቢ የበሽታው ሥርጭት ከፍ እያለ መምጣቱን ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ ከዚህ በፊት ይተገበሩ የነበሩ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ አሁን ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...