Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአፍሪካን ለምግብ ደጅ ያስጠናው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት

አፍሪካን ለምግብ ደጅ ያስጠናው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት

ቀን:

በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ጉዳቱ በአገሮቹ ብቻ ሳይገደብ መላ ዓለምን ነቅንቋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች እርስ በርስ አሊያም ከጎረቤት ጦር ሲገጥሙ ችግራቸው እዚያው በውስጣቸው ተቀብሮ ይቀራል እንጂ እንዲህ እንደ ዩክሬንና ሩሲያ ዓለምን አያናጉም፡፡

በአፍሪካ በተለይ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አንዳንድ አገሮች እንዲሁም በአፍጋኒስታን መቋጫ ያጡት የእርስ በርስና የውክልና ጦርነቶች ሕዝባቸው እንዲሰደድ፣ እንዲሞት፣ አካል ጉዳተኛ እንዲሆንና እንዲራብ አድርገዋል እንጂ የዓለምን ሕዝብ ለኑሮ ውድነት አልዳረጉም፣ ለኢኮኖሚ ቀውስ አላጋለጡም፣ ዓለም የምግብ እጥረት ይከሰታል ብሎ እንዲርበተበትም ምክንያት አልሆኑም፡፡ በዩክሬንና ሩሲያ መካከል የተነሳው ጦርነት ግን የተለየ ነው፡፡

በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ቀድሞ የጦርነት ነጋሪት ሲጎሰም፣ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲያስጠነቅቁ የነበረውም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት ከዚህ ቀደም በሌሎች አገሮች እንደታዩት አይደለም፣ የዓለምን ኢኮኖሚ ያሽመደምዳል፣ የምግብ እጥረት ይፈጠራል፣ የዋጋ ግሽበት ይከሰታልና ከጦርነት ታቀቡ በማለት ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህ ግን አልሆነም፡፡ የፖለቲካ ተንታኞችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደተነበዩትም፣ የጦርነት ቃታ ከተሳበበት ቀን ጀምሮ የዓለም ኢኮኖሚ ርዷል፣ ኑሮ ተወዷል፡፡ በሁሉም ምግብ ነክና ምግብ ነክ ባልሆኑ ምርቶች ላይ ዓለም ከ20 እና 30 ዓመታት ወዲህ አስተናግዶ የማያውቀው ዓይነት የኑሮ ውድነት ተከስቷል፡፡

ዛሬ ላይ በሀብታም ሆነ በደሃ አገሮች የኑሮ ውድነቱ ያላንኳኳው ቤት የለም፡፡ ችግሩ ደግሞ በደሃ አገሮች ሕዝቦች ጎልቷል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የዋጋ ንረትና እጥረት ብቻ ሳይሆን የምግብ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም ከአቅም በላይ የሆነ ግሽበት ተከስቷል፡፡

ቀድሞውንም ራሷን መመገብ ካልቻለችው፣ ለም መሬቷን አርሳ ላልተጠቀመችው፣ ዕርዳታና ግዥ ላይ ለተንጠለጠለችው፣ ለእርስ በርስ ጦርነትና ላልተረጋጋ ፖለቲካ ምኅዳር በሯን ለከፈተችው አፍሪካ ደግሞ ችግሩ ገዝፏል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራምም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተለይ በአፍሪካ ከባድ የምግብ ቀውስ ደቅኗል ብሏል፡፡

የግብርና ግብዓቶችንና ምርቶችን በዘላቂነት ለዓለም በማቅረብ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙት ዩክሬንና ሩሲያ፣ የአፍሪካም ቀዳሚ የግብርና ውጤት ላኪ ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2020 ብቻ የአፍሪካ አገሮች አራት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የግብርና ምርቶች ከሩሲያ አስገብተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶው ስንዴ ሲሆን፣ ስድስት በመቶው የሱፍ ዘይት ነው፡፡ አብዛኛው አስመጪ አገሮች ደግሞ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ዓመት ዩክሬን 2.9 ቢሊዮን ዶላር የግብርና ምርት ለአፍሪካ አገሮች የላከች ሲሆን፣ ከምርቶቹም 48 በመቶ ስንዴ፣ 31 በመቶ በቆሎ ቀሪዎቹ ደግሞ የሱፍ ዘይት፣ ገብስና ቦሎቄ ነበሩ፡፡

ከዓለም የስንዴ ፍላጎት ሩሲያ አሥር በመቶ እንዲሁም ዩክሬን አራት በመቶ በዓመት ያመርታሉ፡፡ ይህ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በአንድ ላይ ሆነው በዓመት የሚያመርቱትን ያህል ነው፡፡ ከዓለምም አንድ አራተኛውን የስንዴ ወጪ ንግድ የያዙት እነዚሁ ዛሬ ጦር የተማዘዙት ዩክሬንና ሩሲያ ናቸው፡፡

ዩክሬን በየዓመቱ ለአፍሪካ 40 በመቶ ያህል ስንዴና በቆሎ ትልካለች፡፡ ሩሲያ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ አፍሪካ ከሚያስፈልጋት የስንዴ ምርት 32 በመቶ ያህሉን ልካለች፡፡

በየዓመቱ በቋሚነት ከምግብ ዓይነቶች ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ እንዲሁም የግብርና ግብዓቶች ስታስገባ የከረመችው አፍሪካ፣ በዩክሬንና ሩሲያ መካከል በተጀመረው ጦርነት እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ፣ ድርቅና የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ዛሬ ላይ ለከፍተኛ የምግብ ቀውስ ተጋልጣለች፡፡

በተለይ ከሁለቱ አገሮች ወደ አፍሪካ የሚገባው ጥራ ጥሬና እህል መቋረጡ የአፍሪካ ኅብረት ሩሲያን እባክሽ ለምግብ ማለፊያ የሚሆን የማሪያም መንገድ ክፈችልን ብሎ እንዲማፀን አስገድዷል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር  የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ወደ ሩሲያ አቅንተው፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በምግብ ዋስትና ዙሪያ መክረዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ከፑቲን ጋር የመከሩት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የምግብ እጥረት፣ ከዩክሬን ወደቦች መንቀሳቀስ ስላልቻሉ የምግብ አቅርቦቶች እንዲሁም አፍሪካ ስለገጠማት የምግብ ቀውስ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ቀውሱና በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች በተለይ ደካማ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ላይ ቀውስ ፈጥሯል ማለታቸውን ኤስቢኤስ ዘግቧል፡፡

ፑቲን ከውይይቱ በኋላ ምዕራባውያን ሞስኮ ከዩክሬን እህል እንዳይላክ አግዳለች ማለታቸውንም ወቅሰዋል፡፡ ከዩክሬን ምግብ ቢላክ ምንም ችግር የለውም ያሉት ፑቲን፣ የተለያዩ የመላኪያ አማራጮችንም አቅርበዋል፡፡

ከዩክሬን የሚላኩ ምግቦች ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው የማሪፖልና በርድያኒስክ ወደቦች ወይም በኦዴሳ ወደብ ምግብ መላክ ይቻላል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ወደቦች ከጦርነቱ በኋላ በጊዜያዊነት በመዘጋታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ምግብና ነዳጅ ዘይት ዋጋ ጨምሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዳኒውብ ወንዝ አካባቢ አገሮች በሮማኒያና ሃንጋሪ ወይም በፖላንድ በኩል መላክ ሌላው ያቀረቡት አማራጭ ነው፡፡

ፑቲን በጣም ቀላልና ርካሽ ብለው ያቀረቡት ግን በቤላሩስ በኩል መላክ የሚለውን ነው፡፡ ከቤላሩስ ማንም ወደ ባልቲክ ወደቦች ከዚያም ባልቲክ ባህር በኋላም ወደ ማንኛውም የዓለም ክፍል ምግብ ሊሄድ ይችላል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም በቤላሩስ በኩል የሚላክ ምግብ ተግባራዊ የሚሆነው ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ሲያነሱ ይሆናል፡፡

ለሦስት ሰዓታት ያህል ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሳል ጋር ውይይት ያደረጉት ፑቲን፣ ከአፍሪካ ጋር አብሮ መሥራት ወሳኝ እንደሆነና ከማንኛውም ምግብ፣ እህልና ጥራጥሬ እንዲሁም ማዳበሪያ ጋር የተያያዘ ማዕቀብ እንደሌለ አውስተዋል፡፡

‹‹ሩሲያ ሁሌም ከአፍሪካ ወገን ናት›› ያሉት ፑቲን፣ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትሠራለች ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሳል በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ባለው ጦርነት እንዲሁም በምዕራባውያን ማዕቀብ ምክንያት የምግብ እጥረት መከሰቱን በመግለጽ አገሮች ምግብና ማዳበሪያ ላይ ማዕቀብ እንዳይጣል እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል፡፡

ፑቲን በበኩላቸው፣ ለዚህ ሁሉ ቀውስ ምዕራባውያንን ወቅሰው፣ ሩሲያ ከዩክሬን ለሚላኩ ምግቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንደምትከፍት ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሰላማዊ´ መንገድ  እናመቻቻለን፡፡ ከወደቦቹ ምግብ ጭነው ለሚሄዱና ከውጭ ለሚገቡ መርከቦች የእንቅስቃሴ ደኅንነት ዋስትና እንሰጣለን ›› ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...