Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የጤና አገልግሎት ስብራት እስካልታከመ ውጤት ማምጣት አይታሰብም›› v

‹‹የጤና አገልግሎት ስብራት እስካልታከመ ውጤት ማምጣት አይታሰብም›› v

ቀን:

ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ በጤና ሴክተሩ ላይ እየተፈተነች መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት የጤና ዘርፉን ጎድቶታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመቀልበስና የጤና ሴክተሩን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የጤና ሚኒስቴር በዓመቱ በተሠሩ ሥራዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ዓርብ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በኢንተር ሌግዥሪ ሆቴል ተወያይቷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠትና የማኅበረሰቡን ፍላጎት በተገቢው መንገድ ለማጣጣም ተቋሙ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የጤና ሴክተሩ አገልግሎትን በጥራት መስጠቱ ላይ ጉድለት በመኖሩ መፈተኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህንንም ክፍተት ለመሙላትና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ቢወጣም አሁንም ቢሆን ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም በማለት ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ከመሠረተ ልማት አቅርቦት ጋር ተያይዞም ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ በየጊዜው የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እያደገ ቢመጣም ይሁን እንጂ ሴክተሩ ላይ ግን የተሻለ ለውጥ መጥቷል ብሎ ደፍሮ መናገር አዳጋች ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፈን በፖሊሲ ደረጃ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ሴክተሩን በከፍተኛ ሁኔታ ፈትኖታል ሲሉ አክለዋል፡፡

ለሁለት ቀኖች የተደረገው ውይይት አንድም የጤና ዘርፉን ተግዳሮቶች ያሳየ በሌላ መልኩ ደግሞ የተሠሩ ጥሩ ጎኖችን ያመላከተ እንደነበር ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተደረገው ጦርነት የጤና ሴክተሩ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን፣ በተጎዱት ቦታዎች ላይ መንግሥት መዋለ ንዋይ በማፍሰስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ምላሽ መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ የጤና ተቋማትን በአሁኑ ወቅት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ግንባታ በማጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መደረጉን ገልጸው፣ በቀጣይም ይህንን አሠራር አጠናክሮ በመቀጠል ዘርፉን መታደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማት ላይ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ የሥነ ልቦና ጉዳት ያጋጠማቸው መሆኑን፣ ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ወደ ሥራቸው እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘም የሚነሱ ችግሮች ከፍተኛ እንደሆነ በተለይም ደግሞ ከግዥ ጀምሮ ለበሽተኛው እስከሚደርስበት ድረስ ያለው ሰንሰለት ስብራት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የግዥው ሰንሰለቱ በተለያዩ ቦታዎች የሚቆራረጥባቸው የውጭና የውስጥ ችግሮች እንዳሉ፣ ይህም በጎረቤት አገሮችም ጭምር እንዳለ ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት ከተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም፣ የሕክምና መስጫ ተቋማት መሣሪያዎች ቢሟሉላቸው በሰው ኃይልም የተደራጁ ቢሆኑም የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ስብራት እስካልታከመ ድረስ ውጤት ማምጣት አይታሰብ ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የጤና ሥርዓቱን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት እንደ አዲስ ፖሊሲዎችን በመከለስ የማኅበረሰቡን ፍላጎት በተገቢው መንገድ መስጠት እንዳለበት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የጤና ጥራትና ተደራሽነት ቡድን አስተባባሪ አቶ ደረጀ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመድኃኒት ዋጋ ጭማሪ ማኅበረሰቡን እያማረረ መሆኑን አቶ ደረጀ ገልጸዋል፡፡ የጤና ቢሮው ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ያለውን ችግር ለመፍታት እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ማጠናቀቂያ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...