Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከላይ እስከ ታች ባለ ሹመኛ ላይ ፀረ ሌብነት ዘመቻ ለምን አይከፈትም?

ከላይ እስከ ታች ባለ ሹመኛ ላይ ፀረ ሌብነት ዘመቻ ለምን አይከፈትም?

ቀን:

በእስክንድር ዳንኤል

ሥልጣንና የሕዝብ ሀብት ያላግባብ መቆጣጣር ምን ያህል እንደሚያባልግ ማሳያው፣ በተለይ በአዲስ አባባ የሚስተዋለው የመሬትና የገቢዎች አሠራር ይመስለኛል፡፡ እንደ ዜጋ መቼም በየዕለቱ የሚገጥመውን በተገናኙበት ዓውድ መነጋገሩ ያለና የተለመደ ነው፡፡ እናም እኔም በምኖርበት፣ በምሠራበትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቴ ሁሉ ስነጋገር ከለውጥ በኋላም ሙስና የደራባቸውን ዘርፎች እያየሁና እየሰማሁ ዝም ለማለት አልቻልኩም፡፡ በእርግጥ አሁን ከላይ እስከ ታች የተሳሰረ ሙስና፣ በኔትወርክ የተሰናሰለ ሌብነትና አሳፋሪ በሚባል ደረጃ በዕርዳታውና በብድሩ ላይ ሳይቀር የሚካሄድ ሌብነት ላይኖር ይችላል፡፡ አለ ቢባልም መረጃ ማቅረብ ያዳግታል፡፡

አሁንም ግን ሰዎች ቢቀያየሩም አሠራራቸው ባለመሻሻሉ የሌብነት ዘዴያቸው ያልተነቃባቸው መስኮች እንዳሉ መሆናቸው፣ አገርና ሕዝብ ዘርፈው እንዲከብሩ የተፈለጉ ሰዎች ይኖሩ ይሆን ያስብላል፡፡ በቅርብ እንደ ሰማሁት ብዙ ሰዎችን ከነበሩበት ቦታ ለመቀያየር ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፣ አሁንም በአዲስ አባባ የመሬት ጉዳይን ለማስጨረስ በመቶ ሺዎች ጉቦ መክፈል የተለመደ ሆኗል፡፡ ካርታ ማስቆረጥ፣ ሰነድ አልባን ወደ ካርታ ማስገባትና የካርታ ስምን መቀየር ይቅርና የግንባታ ፈቃድ ማውጣት፣ የሊዝ ክፍያ መክፈልና ተራ የመረጃ ሕጋዊነትን ማረጋገጥ ያለ እጅ መንሻ ሊታሰብ እንደማይቻል ቦሌ፣ የካ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ አቃቂ ቃሊቲና የመሳሰሉ ማስፋፋያ ክፍላተ ከተሞች በመሬት ዘርፍ ያለን ተገልጋይ ብቻ ማናገር ብዙ ጉድ ያሰማል፡፡

እውነት ለመናገር አሁን ባለው የመሬት ጉዳይ አገልግሎት ለማግኘት ሲኬድ ከባለፈው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በባሰ ደረጃ የሚታየው ግድፈት፣ መዋቅሩ በጉዳይ አስፈጻሚዎችና ደላሎች መከበቡ ነው፡፡ በተለይ በአርሶ አደር ስም የመሬት ከበርቴነት ዕድል በተከፈተላቸው፣ ሕጋዊም ሆኑ ሕገወጥ ሰዎች አማካይነት መሬት በተፈለገው ጊዜ ይታጠራል፣ ካርታ ይወጣል፣ በተፈለገው ፍጥነት ጉዳይ ይፈጸማል፣ ይዘገያል፡፡ አንዳንዶቹማ በየክፍለ ከተማው ሰውና ተባባሪ ብቻ ሳይሆን፣ ቢሮና ወንበር ያላቸው ይመስል እንዳሻቸው ገብተው እየወጡ የሙስናና የአሻጥር በሩን እየበረገዱት ነው፡፡ እውነት ግን መንግሥት በተለይ የከተማ አስተዳደሩ ይህን ብልሽት አያውቀውምን? ወይስ ሌላ ነው ጉዳዩ?

በእርግጥ መሬት የሙስና ዋነኛ ምንጭ የሆነበት ምክንያት በውድነቱ ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥት ራሱ እንደ ፖለቲካ መሣሪያ የሚያየው፣ መዋቅሩም እየተቧደነ እንደ ግሪሳ የሚዘምትበትና የሚበለፅግበት ስለሆነ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተቀየረው ሥርዓት ያን ያህል የዲሞግራፊ ለውጥና የመደብ መቀየር እንዲመጣ ያደረገውም ይኼው አሠራር እንደነበር ይታወቃል፡፡ አደጋው ግን ይህን ብልሽት ባለሙያው እስከ ቀራኒዮ ወስዶ ሕዝብን እያስለቀሰና እየመዘበረበት መሆኑ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የከተማ መሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ ላይ ያለውን ችግር እንዲመለከት የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሥራው አጋጣሚ የሲቪል ሰርቪስ ተገልጋዮችን ዕርካታና ቅሬታ የሚያረጋግጥ ኮሚቴ ውስጥ የመሳተፍ ዕድል ገጥሞት ነበር፡፡ በብዛትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክፍላተ ከተሞች በመገኘት ያለውን ሁኔታ የማጤን ዕድል አግኝቶ ነበር፡፡

ትናንትም ሆነ ዛሬ ግን ከመሬትና መሬት ነክ መረጃና አወሳሰን ጋር ያለው ችግር ታጥቦ የማይጠራ፣ ቀዳዳው ተደፍኖ የማያልቅ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም፡፡ ተገልጋዩም ጉቦ ሳይሰጥ የመሬት ጉዳይን እንደማይጨርስ ውስጡን አሳምኖ፣ በአብዛኛው በሕጋዊ መንገድ ለሚያልቀው መብት ሁሉ በአሥር ሺዎች እየገፈገፈ መስተናገድን መምረጡ ካልተቀየረ ፍትሕ ማንገሥ ከቶም አይቻልም፡፡ ለውጡንም የሚያቀጭጭ ሰንካላ ምክንያት ነው፡፡

እዚህ ላይ በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የታዘብኩት ሁኔታ ይህን አባባል ያጠናክርልኛል፡፡ በክፍለ ከተማው አንዳንድ ወረዳዎች የአየር ካርታ ላይ የለም፡፡ መሬቱ በሕገወጥ የተያዘ ነው የተባሉት ቦታዎች ላይ ካርታና ስም ወጥቶባቸዋል (በተለይ በሁለት ወረዳዎች)፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ የካርታና የግንባታ ፈቃድ ሲጠይቁ ግን ሊስተናገዱ አልቻሉም (ተገልጋዮች እንደሚሉት በመቶ ሺሕና በሚሊዮኖች ጉቦ ተጠይቀዋል)፡፡ የሚያሳዝነው ራሳቸው ፈጻሚዎቹ ሕጉ የፈቀዳላቸውን ክፍተት ተጠቅመው ዋነኞቹ መሬት ያዥና ሻጭ ነጋዴ ሆነዋል፡፡

በማኅበር በጋራ በወጣ የግንባታ መሠረት ላይ አንዳንድ ጉልበተኞችና ‹‹ጉቦ አቀባዮች›› ከፕላን ውጪ ወለል ጨምረው ፎቅ ሲሠሩ ከልካይ አልነበራቸውም፡፡ ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይኖር በገንዘብ ካርታ ማስቆረጥ፣ በአንድ ሌሊት ካርታ ማሠራት፣ በስንት ለቅሶ መሀል መሥሪያ ቤቱን እንኳን ሳያውቁ ጉዳይ ማስፈጸም ካለ ጉቦና አሻጥር እንዴት ይቀላል? እጅግ ያስገረመኝ ደግሞ  በመንገድና በመልሶ ማልማት ዓይነት ሥራዎች ‹‹ይፈርሳል›› በሚል ማስፈራሪያ ነባር ይዞታን በእጅ አዙር በማሸጥ፣ የጥቅም ተጋሪ እየተሆነበት ያለው የወሮበላ አካሄድ ነው፣ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

በፊት ከነበረው አንፃር ሲታይ በጉምሩክ በኩል መሻሻል ቢታይም፣ በገቢዎች ረገድ ያለው ማጭበርበርና የሕዝብ ሀብት ዝርፊያም ከልካይ ያለው አይደለም፡፡ ዜጎች ሕግን ተከትለው ኦዲት ቢያስደርጉ፣ ወይም በአግባቡ የመንግሥት ግብርን ለመክፈል በሚያደርጉት ጥረት ግድፈት ቢያጋጥማቸው ባለዕዳነታቸው እጥፍ ድርብ፣ ይቅርታ የሌለበትና የጭካኔ ዕርምጃ የሚያስከትል ነው፡፡ ወሳኝ ከሚባሉ ባለሙያዎች ጋር መደራደር ግን ዕዳን በጉቦ አካፍሎም ቢሆን 50 በመቶውን ለማዳን እየረዳቸው መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ በተለይ የዕዳ ዕገዳ ክፍሎች በመቶ ሺዎች የቅጣት፣ የወለድና መሰል ክፍያዎችን በሥውር እየሰረዙ ከፍተኛ ሀብት እየሰበሰቡ ያሉ ፈጻሚዎችን ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ እስከ ማዕከል ድረስ ቅሬታ የሚሰማ ኃላፊ አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ግብር ከፋዩን በማስተማር ሳይሆን በማስፈራራትና በመቅጣት ስም እየዞሩ ደረሰኝ አልተቆረጠም፣ በሚል ማስፈራሪያ ጉቦ ሲለቅሙ የሚውሉስ የሉምን? አስገራሚው ነገር ደግሞ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ (አብነትና መርካቶ)፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቄራና ጎፋ)ን በመሳሰሉ አካባቢዎች አብዛኛው ባለ ጋራዥ፣ የመኪና ዕቃ ቸርቻሪ፣ ባለአነስተኛ መለዋወጫ ወዘተ፣ በየቀኑ በመቶ ሚሊዮን እያንቀሳቀሰ እንኳንስ ደረሰኝ ሊጠየቅ፣ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ባልወጣበት ሁኔታ የሚያሳድዱት ያንኑ ሕጋዊውን አነስተኛ የአገልግሎት ነጋዴ መሆኑ ነው፡፡

ሌላው ይቅር እውነት በመሬትና ገቢ ዘርፎች ብሎም በሌሎች መንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ የተሰማሩ አንዳንድ ስግብግቦች ካልዘረፉ በምን ሥሌት በሚሊዮን ብር የሚገዛ ባለመኪና ሆኑ? እንዴትስ ሆኖ ባለትልቅ መኖሪያ ቤትና ባለሕንፃ መሆን ተቻለ? እውነት አሁን ይህንን ሊቆጣጣር የሚችል ሳይሆን ፍላጎቱስ ያለው መንግሥታዊ መዋቅር አለን? ግርም ድንቅ የሚል ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳን የምንገኝበት ጊዜ የምርጫ ወቅት ቢሆንም፣ ይህን በኋላቀር አሠራር የተተበተበና ዜጎችን ለብዝበዛ ማጋለጥ የሙስና መፈንጫ መዋቅር ለመቀየር አለመነሳት በታሪክም የሚያስጠይቅ ነው፡፡

በእርግጥ ሙስና ያልሠሩበትን የመሻት ዓለም አቀፍ ችግር ነው ሊባል ይችላል፡፡ ከትናንት ተምሮ ማሻሻል የማይቻልበት ነገር ግን አልነበረም፡፡ ባደጉትም ሆነ ባላደጉት አገሮች የሚከሰት የሕዝብ ተጠቃሚነትና የአገር መለወጥ እንቅፋት መሆኑ እየታወቀ፣ ችግሩን ለመቅረፍ አለመትጋትም ከዳተኝነትም በላይ ከፍተኛ ልግመኝነት ነው፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት ባህላቸው ዝቅተኛ በሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ከልብ እየገነቡ ባልሆኑ፣ የሕግ የበላይነት ጥርስ በወለቀባቸው አገሮች ሙስና አንበሳ ሆኖ ሲታይ መማር ካልተቻለም በእኛ ላይ የባሰ ነው የሚደርሰው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 4 ቀን 2000 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ሙስና በአገሮች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ጥረት ጀምሮ ነበር፡፡ ይኼውም የዓለም አገሮችን የሚያሳትፍ ዝርዝርና ሁሉን አቀፍ የፀረ ሙስና ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን በመደንገግ ውሳኔ ቁጥር 55161 ይፋ ማድረጉ፣ በቀጣይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንን ለማፅደቅ መሠረት ጥሎ ነበር፡፡ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት የተመከረበት ስምምነትም እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 31 ቀን 2003 በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ቁጥር 5814 መፅደቁ ይታወቃል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ሁኔታም ስንመጣ በአሁኑ ወቅት 178 የዓለም አገሮች ያፀደቁትን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን ተቀብላ ወደ ሥራ ከገባች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ መሠረት በአገሪቱ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ ተቋቁመው ወንጀሉን ለመከላከል የሚረዱ ልዩ ልዩ ተግባራት እያከናወኑ ቢቆዩም፣ መሥሪያ ቤቱ ከፖለቲካ መሣሪያነት የተላቀቀ አልነበረም፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍረውም በአገሪቱ የራሱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናትና ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል የሕዝብ መሬት፣ የባንክ ሀብት፣ የብድርና ዕርዳታ ገንዘብ… ሳይቀር እየዘረፈ ባዶ ካዝና ሲያስቀር ኮሚሽኑ በከፍተኛ ሰመመን ውስጥ እንደተደበተ መቆየቱ ነው፡፡ አሁንማ ከእነ መኖሩም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ሙስናን ለመቀነስም ሆነ ለመግታት የመንግሥታት ቁርጠኝነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ከለውጥ ወዲህ ያለው መንግሥትም ካጋጠሙት አገር የማረጋጋት ፈተናዎች አንፃር፣ ሙስናን ለመከላከል ቅድሚያ ባለመስጠቱ ላይወቀስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ካለፈው ታሪክ በመማርም ሆነ በብዙዎቹ ችግሮቻችን ላይ የሚርከፈከፈውን ቤንዚን ለማስቆም፣ ሙስናን ከወዲሁ መቀነስ ካልተቻለ የረጋ መንግሥትና አስተዳደር ሊፈጠር አይችልም፡፡ ሁሉም ሥልጣን ጨብጦ ዘርፎ ወደ መብላት ተስፋ ቆራጭነት ይገባልና፡፡

በእርግጥ ሙስና በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ የመጨመር እንጂ የመቀነስ ምልክት አልታየበትም፡፡ ለምሳሌ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው በሙስና ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም፣ አፍሮ ሜትር ተብሎ ከሚጠራው ተቋም ጋር በቅንጅት ባካሄደው ጥናት እ.ኤ.አ. በ2018 ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ከ96 ሚሊዮን የሚልቁ ሰዎች ጉቦ መስጠታቸውን አረጋግጧል፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ድሆችና ሀብት ያልተረፋቸው ናቸው፡፡

ይህ ግርድፍ ጥናት የአፍሪካ አኅጉር ሕዝቦች ጉቦ የሚሰጡበትንና የሙስና ወንጀልን የሚያበረታቱበትን መሠረታዊ ምክንያትንም አስቀምጧል፡፡ በቀዳሚነት ወንጀል ሠርተው ለማምለጥና የቅጣት ጊዜያቸውን ለማሳጠር ለትራፊኮች፣ ለፖሊስና ለፍርድ ቤቶች (ዳኞችና ዓቃቤያነ ሕግ) የሚከፍሉት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎት (መብራት፣ ውኃ፣ መሬት፣ ስልክ  ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች እንደ ቤት፣ ምግብና የመሳሰሉትን) ለማግኘት የሚከፈል ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ አገልግሎቶችና ምርቶች ለማግኘትም ከፍትሐዊ ግብይት ይልቅ ሙስናና አጭበርባሪነትን ማለፍ ግድ ብሏል፡፡

አገራችን ያለችበት ሁኔታም ከዚህ የተለየ ነው ሊባል አይችልም፡፡ እርግጥ በእኛ አገር እንደ ደቡብ አፍሪካና ላይቤሪያ ባሉት አገሮች ሙስና ዓይን ያወጣ  ነው ላይባል ይችላል፡፡ ካለፈው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት አንፃርም ረገብ ያለ መስሏል፡፡ ግን ቀስ በቀስ የኔትወርክና የመሳሳብ ምልክት እያቆጠቆጠ፣ አደጋው አፈሩን እየገለጠ፣ ጥቂቶችን እያደለበ፣ ብዙኃንን እያማረረና እያንገላታ መሆኑን ደጋግሞ ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ ምንም ተባለ ምንም ሙስና አጥፊና አገር በታኝ ነውና፡፡ አሁን ያለው የለውጥ መንግሥት ደግሞ የችግሩን መጠን ለሕዝቡ አሳውቆ፣ ‹‹የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስናን ለማስተካከል እሠራለሁ፤›› ብሎ መነሳቱንም መዘንጋት የለበትም፡፡ ሌላው ይቅር ሥራ በገንዘብና በዘመድ እቀጠራለሁ የሚል ዜጋ ከበዛ፣ የሕግ ጥሰትን በብር እወጣዋለሁ ባዩ ካየለ፣ በሕጋዊ መንገድና በአሠራሩ መሠረት አገልግሎት ማግኘት ከተሳነ ለውጡ እምኑ ላይ ነው ያስብላል፡፡ ‹‹ተረሳሽ ወይ …›› የሚለውን ሙዚቃ ለመጋበዝም ያስገድዳል፡፡

ሙስናን መፈክር ስለደረደርን፣ ሌላው ቀርቶ ራሱ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን በተቆጣጣሪ ብዛት ስላጥለቀለቅነው አናስወግደውም፡፡ ይልቁንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በቅልጥፍና ላይ የተመሠረተ አሠራር በመዘርጋት ለማዳከም ይቻላል፡፡ ከሁሉ በላይ ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ ሕዝብን በዜግነቱ በማሳተፍ ቀዳዳውን ማጥበብ ይቻላል፡፡ ለዚህ ሲባልም ገና ከበፊት አንስቶ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሥነ ምግባር መርሆች ተነድፈዋል፡፡ እንደ ቢፒአር፣ ቢኤስሲ፣ የለውጥ ሥራ አመራርና የካይዘን ዘዴን የመሳሰሉ የማሻሻያ ሥራዎች በየጊዜው እየመጡ ሊተገበሩ ተሞክረዋል፡፡ በአንዳንዱ አካባቢም ተለፍቶባቸውና ብዙ ሀብት ወጥቶባቸው በጎንዮሽ አልፈዋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የለውጥና የዘመናዊነት አቅጣጫዎች የትኞቹ መሥሪያ ቤቶችና ባለሙያዎች ተቀይረዋል? እንዴት ያሉ የሥራ መሪዎች ተፈጥረዋል? ብሎ መመርመር ብቻ ሳይሆን እንደገና መቀስቀስና መተግበር ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡

በአንዳንዱ መሥሪያ ቤት እኮ ዛሬም መፈራራት ጠፍቷል፣ ሙስና ደርቷል የሚያስብለው በየመስኮቱ ተቀምጠው አገልግሎት የሚሰጡ አንዳንድ ወጣቶችና ወዲያ ወዲህ  የሚሉት ሠራተኞች ‹‹ይህን አምጣ›› ሲሉ ይሉኝታ እንኳን አለመታየቱ ነው፡፡ ማን ነው? ምንድነው? እንኳን ሳይሉ ወደ ተቋሙ የመጣውን ተገልጋይ እንደ ልጥ ይሞሸልቁት ይዘዋል፡፡ ሁል ጊዜ የሚያስገርመኝ ነገር ግን እጅግ ኋላ ቀር በሆነ የፋይል አያያዝ በመዝገብ ቤት የተደረደረው የክላሰር ፋይል ለማግኘት (ለማውጣት ብቻ) ገንዘብ ወይም ልመናና ምልጃ የሚያስፈልጋቸው የመሬት፣ የገቢዎችና የመንገድ ትራንስፖርት ብቻ ሳይሆን ብዙ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም፣ ለውጥ ያለው ውልና ማስረጃ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዘወትር አድሮ ጥሬ ከመሆን ይህን መቀየርስ ለምን አልተቻለም ነው ጥያቄው፡፡

ብዙዎቹ ወንጀሎች የሚሠሩት በዋናነት መረጃን በማጥፋት፣ በመደበቅና ተገልጋይን በማጉላላት መሆኑንስ አለማጤን እንዴት ይቻላል  (ባለቀ ጉዳይ ላይ ገንዘብ ለመቀበል ብቻ ለወራት የሚያመላልሱ አሁንም የሉም ማለት ይቻላልን? ቅሬታ የሚሰማውስ አመራር ስንቱ ነው)? ይኼም ባይሆን ባለጉዳይ ተበደልኩ ብሎ በመረጃ አስደግፎ፣ ለኃላፊዎች ቅሬታ ሲያቀርብ እንዴት ሊፈታ የሚችል አመራር ቀርቶ እንዴት ሠራተኛ ይጠፋል? ስለዚህ ወይ የጥቅም ተጋሪነት አለ፣ ወይም ፍርኃቱ በርትቷል ያስብላል፡፡ የመጪው ጊዜ የብልፅግና ፈተና ይኼ ለመሆኑም ጥርጥር የለውም፡፡ ከእነዚህ ማሳያዎች አንፃር በሁሉም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አሠራር፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና መመርያ የሚባሉት ነቁጦች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ቢሆኑ በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ በቅልጥፍናና በፍትሐዊነት እንዲመሩ ማድረግ ካልተቻለ ያለ ጥርጥር ሙስና ፈቀቅ ሊል አይችልም፡፡

በእርግጥ ሙስናን ለማስወገድ የመንግሥት መዋቅር ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡም የአመለካከት ለውጥና ንቃተ ህሊናውን ወይም የሞራል ልዕልናውን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ የትም ቢሆን ሰው ሲበዛ መሬት/የተፈጥሮ ሀብት ይጠባል/ያንሳል፡፡ አገልግሎትና አቅርቦትም ይቀንሳል፡፡ በዚያው ልክ ሠርቶ አካባቢን መቀየር ካልተቻለ በስተቀር በዚህ ላይ ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነት ሲበረታ ሽሚያ፣ ንጥቂያና የሌላውን ድርሻ መብላት ይበረታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን በሃይማኖቶቻችንና በባህሎቻችን ፈሪኃ ፈጣሪና ሞራላዊ ማንነት ያለን ቢሆንም፣ በተለይ በከተሞች ከወያኔ/ኢሕአዴግ ዘመን ወዲህ እያቆጠቆጠ የመጣው በአቋራጭ የመክበርና ሕግና ሥርዓትን በገንዘብ የመጠምዘዝ ድርጊት ፈር እያሳተን ነው፡፡ ድሮ የነበረውን ‹‹ሲሾም ያልበላን…›› ከማበረታታም በላይ የሄደ ሆኖም እየታየ ነው፡፡

ከትንሿ የአሽከርካሪ ቅጣት አንስቶ፣ ከላይ ባነሳናቸው የመሬትና ገቢ፣ የመንገድ ትራንስፖርትና ማዕድን እስከ ትልልቅ ድርጅቶች የታክስና የጉምሩክ ሥራዎች ድረስ በጉቦ ለማስፈጸም የማይቋምጥ እስኪ ማነው? በእርግጥ አንዳንዱ ባለሥልጣን (ባለሙያ) ዓይኑን እያስለመለመ የ‹‹ስጡኝ›› ጥያቄውን በእጅ አዙር ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እኛ ግን አገሩን እንደሚወድ ዜጋ ስንቶቻችን ነን ‹‹ይኼ መብቴ ስለሆነ በዚህ ጊዜ ሠርተህ ስጠኝ፤›› ብለን በድፍረት የምንታገለው? ሌብነትና ሙስና እንዲገታስ ከመንግሥት ጋር የምንተባበረው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

አንዳንዱ ስግብግብና ጥገኛ እኮ ትናንት የፈጸመው ዘረፋና ሕዝብ መበደል አንሶት አሁንም እየቀጠለበት ነው፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ጊዜ ‹‹የፓራሹት ቱጃር›› ስለሆኑ ሰዎች ከወዳጆቼ ጋር እየተጨዋወትን ነበር፡፡ ጉዳዩን በአርምሞ የሚታዘብ አንድ ወዳጄ የነገረኝ ትዝብት ግን ‹‹እንዴት አይከበር›› እንድል ነው ያደረገኝ፡፡ ሰዎቹ አሁንም ድረስ  በገቢዎች፣ በውልና ማስረጃ፣ በባንኮችና በመሬት አስተዳደር፣ ወዘተ ሁሉ በየጊዜው እንደ ወር ደመወዝ ጉቦ ተቆራጭ የሚያደርጉላቸው፣ ቤትና መኪና የሚያበረክቱላቸው ሠራተኞችና ኃላፊዎችን ‹‹ቅጥረኞች›› አድርገዋል፡፡ ወደ ሥልጣንና መዋቅር ሳይጠጉ የሕዝብ ሀብት ማግበስበስ አይቻልምና፡፡

እንግዲህ የቱባ ጉቦኞችን አንድ ገመና ጠቀስን እንጂ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ ጉቦ የመስጠት ልክፍት በምን ያህል ደረጃ አለ? የሚለውን ነው መመርመር የሚያስፈልገው፡፡ ስንቶቻችንን መብትና ግዴታችንን አውቀን እንወጣለን ብሎ መጠየቅ ነው የሚጠቅመው፡፡ ሌላው ይቅር ጉቦ በመጠየቅ ያልሠሩበትን ለመዝረፍ መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጡን የመንግሥት ሌቦችን ደፍረን ለማስደንገጥና በፖሊስ ለማስያዝ አስበን እናውቃለን? ወደ ሁላችንም አዕምሮ መምጣት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሙስና ወንጀል ጎጂነት ላይ የምንስማማውን ያህል በጋራ መታገሉ ላይ ካልበረታን፣ ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ልናስተላልፍ አንችልም፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ በላቀ ሞራልና ሥነ ምግባር፣ በታታሪነትና ትጋት፣ እንዲሁም በፀረ ሌብነትና በፀረ ሙስና ባህል ውስጥ ሆነን ቤታችንን እንሥራ፡፡ ከላይ እስከ ታች በተዘረጋው መዋቅር ውስጥ ያለውን ሹመኛም በፀረ ሌብነት ዘመቻ አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...