Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ፌዘኝነት!

እነሆ ጉዞ ከሩፋኤል ወደ መርካቶ። ያለንበት ዘመን ሁካታ በዝቶበት ጭምድድ አድርጎ እየያዘ በጭንቀት ይንጣል። የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ለኑክሌር ፍጅት ይዳርገን ይሆን የሚለው በአንድ በኩል፣ የሰሜኑ የአገራችን ጦርነት እንደገና አገርሽቶ ሌላ ዕልቂትና ውድመት የሚለው ደግሞ በሌላ በኩል ይንጠናል። ይህች ነፍስ ተብዬ በሥጋ ውስጥ የተሸሸገች ታላቅ ሚስጥር ነች፡፡ የሁለመናን ሚዛን እየጠበቀች እስከ ፍጻሜ ትገሰግሳለች፡፡ ስለዚህም ሕይወት ምን ብትከብድ፣ ኑሮ ምን እያደር ፊቷ ቢጠቁር መኖር ይፈቀር ዘንድ ግድ ታስብላለች። ሥጋም ነፍስም ያሳሳሉና። በማግኘት ጎዳና ላይም ሆነ በማጣት መንገድ ላይ ወዲያ ወዲህ ስንል ቀናችንና ዘመናችን ከባድ ነው። እንቅፋቱ ሲበዛብን በነፍስ በኩል ለፈጣሪ፣ በሥጋ በኩል ለገዥዎቻችን እንናገር ዘንድ እንማስናለን። ጎዳናው መሀል ደግሞ ቆሞ የሚያስፈራራ ተውሳክ አይጠፋም፡፡ አሁንም የሚያስፈራራን እሱ ነው! 

ፈጣሪ በጊዜው ለሁላችንም እንደ ምግባራችን መልስ ሲሰጠን፣ የምድር ገዥ ግን ጉዳዩ በዝቶና ኔትወርክ ተጨናንቆበት አላዳምጥ ይለናል። ይህ ቢሆንም ቅሉ መኖር ይቀጥላል። ምን መከፋት ቢነግሥ፣ ምን መሰልቸት ቢያለፋን መኖር በሕይወት ጎዳና፣ መኖር በጉዞ ውስጥ መቀጠሉን ለመታዘብ ሁሌም በቦታው እንገኛለን። እንዳልነው ሥጋም ሆነ ነፍስ ያሳሳሉና፡፡ ታክሲ ውስጥ ገብቼ እንደ ተቀመጥኩ ዓይኔ አንዱ ጥቅስ ላይ ተተከለ። ‹ራስን ከመግዛት የበለጠ ትልቅ ሥልጣን የለም› ይላል። ከፊት መቀመጫ ደልደል ብሎ የተቀመጠ ተሳፋሪ እንደ እኔ ጥቅሱን በሙሉ ልቡ አጢኖ ሲያበቃ፣ ‹‹ባይሆን በዚህ እንኳ እንፅናና እንጂ…›› ብሎ ፈገግ አለ። በተናገረው ቃል ውስጥ ያለው ሥውር መልዕክት ቅድሚያ ለራሱ እንደ ተገለጠለት ሊጠቁመን የፈለገ ይመስላል። ካልመሰለስ ምን ይደረጋል!

‹‹በምኑ?›› በማለት ከኋላችን የተቀመጠ ጎልማሳ ጠየቀው። ‹‹‘ራስን ከመግዛት በላይ ሥልጣን የለም’ የሚለውን ጥቅስ አላየህም እንዴ? ባይሆን እንዲህ እያልን እንፅናና እንጂ፡፡ ይህ ራሱ ስላቅ አይደለምና ነው?›› ብሎ አሽሟጠጠ። አንድ ወጣት ተሳፋሪ ፈጠን ብሎ፣ ‹‹እንዴ? እንዴ? ምነው ዴሞክራሲ እየገነባን? በድምፃችን ራሳችንን ማስተዳደር እየቻልን ማሽሟጠጡን ምን አመጣው ወንድሜ?›› ብሎ በቀናነት የመሰለውን አስተያየት ጨምሮ ጠየቀው። መልሱን ከመስማታችን በፊት፣ ‹‹ከታክሲ ውስጥ የመናገር ነፃነትና ከፓርላማችን የትኛው የሚበልጥ ይመስልሃል?›› ብሎ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ ወዳጁን ሲጠይቀው ሰማን። መልሱ ተድበስብሶ አልሰማን ሲል፣ ‹ደጇን ዓይተህ ቤቷ ግባ፣ እናቷን ዓይተህ ልጅቷን አግባ› የሚሉት ምሳሌ በአዕምሮዬ ተመላለሰ። ተድበስብሶ ማድበስበስ የት ያደርሰን ይሆን? የዚህንም መልስ መስማት አማረን፡፡ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ጥያቄዎችን እንደ ሸቀጥ ማምረት ምን ይፈይድልን ይሆን? እንጃልህ አትሉም!

‹‹ምን ዋጋ አለው?›› አለ አሽሟጣጩ ተሳፋሪ ድንገት ጮክ ብሎ፣ ‹‹ድምፃችን የሚፈለገው ለምርጫ ብቻ ነው መሰለኝ፣ ለአቤቱታና ለአስተያየት ጊዜ የሚፀየፈን ግን አይጣል ነው…›› ሲለው ወጣቱ ዝም አለ። ተሳፋሪዎች እየገቡ ታክሲያችን እየሞላች ብትሆንም፣ ወያላው የያዘው ልማድ አለቅህ ብሎት ጠቅጥቄ ካልጫነ በቀላሉ የሚንቀሳቀስ አልመሰለንም። ‹‹ኧረ እንሂድ? ምናለበት ቢበቃህ?›› አለው አንድ ተሳፋሪ። መቸኮሉ ከመቁነጥነጡ ያስታውቃል። ‹‹ቀስ በላ፣ እንደ ፈለግኩት ጭኜ ነው የምሄደው…›› ብሎ በትዕቢት አነጋገር መለሰለት። ይኼ አልበቃው ብሎ ደግሞ፣ ‹‹ከፈለግክ መውረድ ትችላለህ…›› ብሎ ገላመጠው። ‹‹አይ ራስን መግዛት?› በማለት ቅድም ጥቅሱን እያየ ሲያሽሟጥጥ የነበረው ተሳፋሪ በሳቅ ፈነዳ። ‹‹ልጅ የአባቱን ይወርሳል ሆነና ለምንለጥፈው ጥቅስ፣ መርህ ታማኞች አልሆን አልን…›› ብሎ ሳቁን ካቋረጠበት ቀጠለው። ሌላው ደግሞ እኔ የምፈራው ሥራው በሌለበት ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተባለ የሚነገረው ነገር ተረት ተረት እንዳይሆን ነው…›› ብሎ አቀረቀረ። አንዳንዱ ሰው ክፉኛ ነገር ሲገባው አሳሳቅና አለቃቀስን አሳምሮ ይችላቸዋል። በአስመሳዮች ዘመን ሙዚቃው፣ ድራማው፣ ኮሜዲውና ለቅሶው እንደ ማኅበራዊ ተሰናድተው ሲቀርቡ ትወናውም የዚያኑ ያህል ቀጥሏል፡፡ ይቀጥል እንጂ!

የወያላው ነገረኝነት ያበሳጫቸው ተሳፋሪዎች አቤቱታቸውን ወደ ሾፌሩ ማቅረብ ጀመሩ። ‹‹ሾፌር? እንዴት እንዴት እንደሚናገር እያየህልን ነው? ገንዘባችን በእጥፍ ከፍለን ተንገላተን ለምንሄደውም ግልምጫ ይጨመርበት?›› አለ አንድ ቀጠን ያለ ተሳፋሪ። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ ዞር አለና ወያላውን አተኩሮ አየው። አስተያየቱ የ‹አበጀህ› ይሁን ወይም የ‹ተግሳጽ› አልገባንም፡፡ ‹‹የዛሬ ልጆች የዕውቀታችሁ ጥግ ይኼ ነው?›› አሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ። ‹‹ቆይ ግዴለም!›› አለ ሾፌሩ አሁንም በቁጭት ይሁን በደንታ ቢስነት ስሜት። ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ ተሳፋሪ፣ ‹‹እስከ መቼ እንዲህ ከሕዝብ እያናከሰህ ትኖራለህ አታባርረውም?›› ሲለው ጆሯችን ሰማ። ሾፌሩ፣ ‹‹ትንሽ  ቀን ነው ግድ የለም፣ ፓርላማ ሥራቸውን በአግባብ አላከናውን ያሉ ባለሥልጣናትን ማበረር ሲጀምር፣ የአንተና የእኔ ነገር ያከትማል…›› ሲለው ሁላችንም በመገረም ተያየን። ጉድ እኮ ነው!

‹‹ደግሞ እናንተንና ፓርላማን ምንና ምን ያገናኝችኋል?›› ሲለው ጎልማሳው፣ ‹‹እንዴ? ላይ ያለው ሹም ሥራውን በአግባቡ አላከናወነም ተብሎ የሚሻር ከሆነ፣ ሌላው ምን ቆርጦት ሥራ እያበላሸ ይኖራል? ግን መጀመርያ ከላይ መማር አለብን። የተወራው መተግበር አለበት። ማተኮር ያለብን ቅርንጫፉ ላይ ሳይሆን ግንዱ ላይ ይሁን ተብሎ የለ? ከዚያ እኛ፣ ከእኛ ደግሞ አዲሱ ትውልድ ይኼን አካሄድ እየተከተለ እውነተኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይሰፍናል…›› አለ ሾፌሩ እንደ ካድሬ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ! በቃ ሰው የአገሩን ጉዳይ እንዲህ በዓይነ ቁራኛ መከታተል ጀመረ ማለት ነው?›› አለኝ። እንዲህ ሲል የሰማው፣ ‹‹ታዲያስ? ሌላማ ምን አለን ብለህ ነው?›› አለው። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ሁሌም ታክሲ ውስጥ ስሳፈር የተሳፋሪዎች ግልጽነት ይገርመኛል። የእውነት ነው? ወይስ አጋጣሚ ነው?›› ብሎ ይጠይቃል። አንዱ እየሳቀ፣ ‹‹አይ አጋጣሚ ነው…›› ብሎ በምፀት ይመልሳል። ከምፀቱ ጀርባ ከባድ ምሬት ይታያል፡፡ በኑሮአችን ውስጥ መርህ እየተረሳ አጋጣሚ ሲበዛ ምን ይባላል ታዲያ!

ወያላው እንደለመደው ማጎር እንደማይችል ሲረዳው፣ ‹‹እንሂድ!›› ብሎ ሾፌሩን አዘዘው። ‹‹የበላዩ ታዛዥ የበታቹ አናዛዥ የሆነበት ዘመን…›› ይላል አንዱ። ‹‹እግዚኦ! ይኼንን የኑሮ ውድነት ፈጣሪ ወደ መጣበት ካልመለሰልን ዘንድሮ እንጃ…›› ብለው ከኋላ ጥግ ላይ የተቀመጡ አዛውንት ተናገሩ። ‹‹እውነት እኮ ነው! ነገር ግን እኛስ የሚጠበቅብንን መቼ አደረግን?›› ብሎ ጎልማሳው ጥያቄ አነሳ። ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹ለኑሮም የትራፊክ ፖሊስ ሳያስፈልግ አይቀርም…›› ብሎ በስስ ፈገግታ ፊቱን አብርቶ እያንዳንዳችንን ተመለከተን። ‹‹ማለት?›› አለው አጠገቡ ያለው ወጣት። ‹‹ጎመንና ቲማቲም ተክላችሁ ብሉ ሲባል መከፋት፣ እንትንን በእንትን ፈርሻችሁ ብሉ ሲባል መነጫነጭ…›› ሲል ነገሩ ገባን። ‹‹ስንቱ አውቆ ተኝቶ ሰበብ እንደሚያፈላልግ ስናውቅ ሐዘናቸን ብሔራዊ የማይሆንልን ለምን ይሆን?›› ይላሉ አዛውንቱ፡፡ ብሔራዊ ጉዳይ ከተረሳ እኮ ቆየ!

 አንዳንዱ የአንጀቱን ሲያወራ የአንዳንዱ ፌዙ አያልቅም። ይህን የተናገረውን ቀና ብለን አየነው። ሁኔታችንን ተረድቶ፣ ‹‹እኔም እኮ ከአንጀቴ ነው የመለስኩት። ዛሬ የምናየው ውኃ መቋረጡን ነው። በዚህ ዓይነት ስንት ሥራ መሰላችሁ በቅንጅት ጉድለት የሚስተጓጎለው?›› እያለ አስተያየቱ ከምር እንደሆነ አስረግጦ አብራራ። የአንዳንዱ ሰው አነጋገር ካልተብራራ ትርጉሙ ከባድ ነው። በትርጉም ስህተት ስንት ሰው ጠፍቶ ይሆን? ጉዞአችን ሊገባደድ ጥቂት መንገድ ሲቀረን ሾፌሩ የከፈተው ሬዲዮ በቴሌቪዥን ስለሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም ተናገረ፡፡ አዛውንቱ እየተቆጡ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው ከቁምነገሩ ፌዙ እያየለ ግራ ተጋባን እኮ?›› ሲሉ ድንግርግር ያልን በዛን፡፡ አንዱ ተሳፋሪ፣ ‹‹አንተም አልገባህም?›› አለኝ፡፡ እንዳልገባኝ አንገቴን በመወዝወዝ ገለጽኩለት፡፡ ‹‹በገዛ ቴሌቪዥናችን ቤታችን ድረስ ከቀልድ እስከ ብልግና እየተላከልን ነው ማለታቸው ነው…›› ሲለኝ ገባኝ፡፡ ወያላው መድረሻችንን ለማብሰር ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ተንጋግተን መውረድ ጀመርን፡፡ ያው ተሳፋሪ፣ ‹‹ከሁሉ ነገር በላይ ምን እንዳስደሰተኝ ታውቃለህ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ይሆን?›› አልኩት፡፡ ‹‹አንድ ችግራችን የገባው ፖለቲከኛ የማይረቡ ነገሮች ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ ረሃብና ጦርነት ለማስቆም እንታገል ያለው አንጀቴን አራሰው ለማለት ፈልጌ ነው…›› ሲለኝ፣ ከፌዝ ይልቅ ቁምነገር ላይ ማተኮሩ ገባኝ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት