Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ታክስን በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ለማሳወቅና ለመክፈል የተጀመረው አዝጋሚ ጉዞ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ዕቃን በዕቃ ግብይት ይደረግበት ከነበረበት ጥንታዊው ዘመን አንስቶ እስከዛሬ ድረስ ዜጎች ለሚኖሩበትና ርስትና ለተለዋወጡት ዕቃ ተገቢውን ክፍያ ለአገር ጥቅም የማዋልን ፅንሰ ሐሳብ ወደ መሬት አውርደው ይሠሩ ከነበሩ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ጸሐፍት የከተቧቸው ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

እንደ አገሪቱ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታም ሆነ የግዛት አስተዳደሮች ልዩ የሥርዓት ባህሪ ዜጎች ከቀደሙት ጊዚያቶች አንስቶ እንዲከፍሉ የተበየነባቸውን የግብር ውሳኔ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ ዛሬም በዘመነ ዲጂታል ይህንን ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ምንም እንኳን አገሪቱ የግብር ወይም የታክስ አሰባሰብ ሥርዓትን ከጥንት አንስቶ ተግባራዊ ስታደርግ ብትቆይም፣ ወጥነት የሌለው፣ አስፈላጊውን ቅርፅ ያልተከተለ፣ በቂ ትኩረት ያልተሰጠው፣ ከዘመኑ እኩል ዘመናዊነትን (ዲጂታላዊነትን) ያልተላበሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአገሪቱ የመሠረት ልማቶች ልማትና ከዚያም ለሚገኘው አበርክቶት ታክስ የነበረው ድርሻ በሚጠበቀው ልክ የተሠራበት እንዳልሆነ ዘርፉን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛ ተርታ በተቀመጠችው ኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የግብር ከፋይ ቁጥርና ከዘርፉ የሚገኘው አገራዊ አስተዋጽኦ ከሌሎች አገሮች በተለይም ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ጋር ሲነጻጸር አንሶ እንደሚገኝ በዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ተመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና የቀረጥ አጀማመር ከመንግሥት አመሠራረት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፣ በዚህም በአገሪቱ ውስጥ መንግሥት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ግብር ተብለው ሊጠሩ የሚችሉ የተለያዩ ዓይነት መንግሥት የጣላቸው ግዴታዎች እንደነበሩ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ቢኖሩም የጽሑፍ ማስረጃ የተገኘው በ15ኛው ክፍለ ዘመን መንግሥት ነበር ይባላል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ግብር ይከፈል የነበረው በአብዛኛው በዓይነትና በጉልበት ሥራ ወይም በአገልግሎት ሆኖ አልፎ አልፎ በገንዘብ መልኩ ይከፈል እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ባለንበት ዘመን በሕግ ሳይፈቀድ ማናቸውም ዓይነት ግብር የማይሰበሰብ ሲሆን፣ እነዚህን ሕጎች የተፈጻሚነታቸውን ወሰን፣ ግብር ከፋዩ ማን እንደሆነ፣ መቼና እንዴት መክፈል እንዳለበት፣ የግብሩ መሠረት ምን እንደሆነ፣ ግብሩ በምን መጣኔ እንደሚከፈልና ሌሎች የግብሩን አስተዳደር የተመለከቱ ጉዳዮችን ያካተቱ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓላማዎችን ለመፈጸም የምታደርገውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችላትን ገቢ ከአገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢና ከውጭ ዕርዳታና ብድር እንደምታገኝ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪና አበዳሪ አካላት የሚገኘው ገቢ በየጊዜው በሚኖረው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ በመሆኑና በተለይ ብድርን በተመለከተም ከሕዝቡ ከሚሰበሰብ ገቢ ተመልሶ የሚከፈል በመሆኑ አስተማማኝና ተመራጭ ስላልሆነ የመንግሥት ትኩረት ሊሆን የሚገባው አገር ውስጥ የሚሰበሰበው መደበኛ ገቢ መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች አበክረው ያስረዳሉ፡፡

ግብርን በሚመለከት በሥራ ላይ የነበሩት ሕጎቹ ረዥም ጊዜ የቆዩና ወቅታዊ ሁኔታን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ከኢኮኖሚ ዕድገት ከሚገኘው ገቢ መሰብሰብ የነበረበት ግብር ወይም ታክስ ላለመሰብሰቡ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉ የሕግ ባለሙያ አስታውቀዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገራዊ የታክስ አስተዳዳር ሥርዓትን የመገንባት፣ ምቹ፣ ቀላልና ፍትሐዊ አገልግሎት የመገንባት፣ ግብር በፍቃደኝነት የመክፈል ባህል እንዲዳብር፣ የታክስና የጉምሩክ ሕግጋትን በማስከበርና ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን የታክስ ገቢ መሰብሰብ ዋነኛ ተልዕኮው እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ 

ተቋሙ ከአጋር አካላት ጋር ማለትም ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከተቆጣጣሪና ተባባሪ አካላት ጋር የተጠናከረ የሥራ ግኙነት በመፍጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ እንደሚገኝ በተዳጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2014 በጀት ዓመት የአሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባደመጠበት ስብሰባ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እንዳስረዱት፣ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት 303.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ282.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል፡፡

የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ በመደገፍ የአገልግሎት አሰጣጡ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በሆነ መንገድ መስጠት ዋናው የተቋሙ ተልዕኮ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ የግብር ሥርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን የፋይናንስ ተቋማት ከመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚስተካከል ሚና እንዳለባቸውም ይናገራሉ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጸጸሙ ላይ እንዳመላከተው፣ መንግሥት የታክስ ከፋዩን እንግልትና ወጪ ለመቀነስ የዘረጋው የኤሌክትሮኒክ ታክስ ማስታወቅና ክፍያ ሥርዓት ከታክስ ከፋዩ ዕይታ (Perception) አንጻር ያስገኘውን ጠቀሜታ በመዳሰስ ችግሮቹን ለመለየትና ችግሮቹ የሚፈቱበትን የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም የኤሌክትሮኒክ ታክስ ማስታወቅና ክፍያ ሥርዓት ትግበራ ዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው፣ የኤሌክትሮኒክ ታክስ ሥርዓት እየተተገበረ በሚገኝባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ካሉት 27,184 ታክስ ከፋዮች መካከል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 23,899 ታክስ ከፋዮች የኤሌክትሮኒክ ታክስ ማስታወቅ ሥርዓት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል 6,762 ወይም 24.87 በመቶ የሚሆኑት ታክስ ከፋዮች በኤሌክትሪክስ የክፍያ ዘዴን ተጠቅመው ያለባቸውን ታክስ በመክፈል ላይ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል። ለዓብነትም እነዚህ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ ታክስ መክፈል ከጀመሩት ግብር ከፋዮች በ2013 በጀት ዓመት 25.3 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው የአገር ውስጥ ታክስ ገቢ አንጻር ሲታይ 16.60 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው ነው። 

የአገሪቱ አፈጻጸም እንደ ሩዋንዳ ካሉ አገሮች አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ሁለቱም አገሮች የኢ-ታክስ ሥርዓትን መተግበር የጀመሩት ሩዋንዳ በ2011 እና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2013 ቢሆንም፣ በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ2019/20 በኤሌክትሮኒክ ማስታወቅ 100 ፐርሰንት የደረሰ ሲሆን፣ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት መክፈል ደግሞ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች 96.2 በመቶና በመካከለኛ/አነስተኛ ግብር ከፋዮች 92.6 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የሩዋንዳ አፈጻጸምና ተሞክሮ እንደሚያስረዳው፣ በኢትዮጵያ የኢ-ታክስ ሥርዓት በሚፈለገው ፍጥነት እየተራመደ አለመሆኑን ሲሆን፣ በቀጣይ በሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ሥርዓቱን ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ራሱ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል።

ያም ሆኖ ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው፣ ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው የኤሌክትሮኒክስ ቁስን በመጠቀም ግብራቸውን በሚያውቁበትና በሚከፍሉበት የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ማስታወቂያና የመክፈል ዘዴን (ኢ-ታክስ) በመጠቀም ከ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከተያዘው ዓመት መጋቢት ወር ድረስ 57.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ (የኢ-ፔይመንት) ሥርዓት አተገባበር አፈጻጸም ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በኤሌክትሮኒክ መንገድ የግብር ግዴታቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ ለማድረግ ቀደም ሲል ጀምሮ እየተሠራ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ ውስጥ ባሉ አምስትና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ሦስት ቅርንጫፎች በአጠቃላይ 12,279 ግብር ከፋዮች ወደ ኢ-ክፍያ ሥርዓት የገቡ ሲሆን፣ በዚህም አገልግሎቱ ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ እስከ መጋቢት ወር 2014 ዓም ድረስ 123,631 ትራንዛክሽኖች ተደርገው የ57.2 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሞበታል።

ታክስን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለማሳወቅ ወደ ተዘረጋው ሥርዓት የገቡ ግብር ከፋዮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 27,039 መድረሳቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ 4,229 የሚሆኑት ግብር ከፋዮች በዘንድሮው ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ሥርዓቱ የገቡ ናቸው። 

በዘንድሮው ዓመት ወደ ኢ-ፋይሊንግ ወይም ታክስን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ የማሳወቅ ሥርዓት የገቡ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ብዛት ግን 662 ብቻ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

ታክስን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ መክፈል ከጀመሩት 12,279 ግብር ከፋዮች ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ሥርዓቱ የገቡት 5,514 ግብር ከፋዮች መሆናቸውንም መረጃው ያመለክታል። 

በኤሌክትሮኒክስ መንገድ መክፈል ከጀመሩት ታክስ ከፋዮች ውስጥ 11,063 የሚሆኑት በ2014 ዓም ዘጠኝ ወራት ውስጥ 17.1 ቢሊዮን ብር መክፈላቸውም ታውቋል።

ከአዲስ አበባ የሚገኘውን ገቢ ሰብሳቢ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ ካለፈው ዓመት አንስቶ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ በተለይም የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዩ የሚጠበቅባቸውን ክፍያ በአጭር የመልዕክት መላኪያ በመላ ገብር ከፋዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ተገቢውን ክፍያ የሚፈጽሙበትን ሥርዓት መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣  የግብር ከፋዩን ኅብረተሰብ ጊዜና  ድካም  ለመቀነስ በማለም ሥራ ላይ የዋለው የኢ-ታክስ አገልግሎት የግብር ሰብሳቢውን ቢሮ የሥራ  ጫና  በመቀነስም ሆነ የተገልጋዮችን የቆይታ  ጊዜ  በእጅጉ  ከማሳጠር አኳያ፣ የላቀ ጠቀሜታ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ግብር ከፋዮች ማንኛውንም አገልግሎት ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲጠቀሙ “ደራሽ” የተሰኘ መተግበሪያ አልምቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ መተግበሪያው ግብር ከፋዮች በኦንላይን አማራጭ አስፈላጊውን ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው ነው፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን የገቢዎች ቢሮ ባለፈው ዓመት የጀመረውን ለደረጃ ግብር ከፋዮች ግብርን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አማራጭ የማቅረብ ሒደት በማሻሻል በተያዘው ዓመት ደግሞ የማዘጋጃ ቤታዊ ግብር ዓይነት በሆኑት የቦታና ቤት ግብር ከፋዮች ላይ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የዕቅድና በጀት ዝግጅት ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፈው ዓመት የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮችን በስልካቸው በሚላክ መልዕክት የሚከፍሉትን የግብር መጠን እንዲያውቁ ተደርጓል፡፡ ዘንድሮ በተመሳሳይ የማዘጋጃዊ የግብር ዓይነት የሆነውን የቦታና ቤት ግብር ከፋዮች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የፓይለት ሥራ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም በቅርቡ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የአዲስ አበባ ወረዳዎች ላይ የቦታና ቤት ግብር የሚከፍል ግብር ከፋይ የገቢዎች ቅርንጫፍ ቢሮ ሳይመጣ በሚላክለት መልዕክት መሠረት ከፍያውን በባንኮች የሚከፍልበት ሁኔታ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ይህ መሆኑ ለግብር ከፋዩ ወጪን ጊዜን የሚቆጥብለት ሲሆን ለገቢዎች ቢሮ ደግሞ የሥራ ጫና የሚቀንስለት ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ዘመናዊ የኢ-ታክስ አገልግሎትን በአገር አቀፍም ሆነ በከተማ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ የግብር ከፋዮችን ወጪ ከመቀነስ እና ቀላል አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ የታክስ ሕግ ተገዥነትን ለማሳደግ፣ የታክስ መረጃ አሰባሰብ ሥርዓትን ለማሻሻልና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ማስገኘት የሚችል መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ 

ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የገቢው ዘርፍ ተቋማት ጋር በ2014 በጀት ዓመት የመልካም የሥራ ግንኙነት ላይ በግዮን ሆቴል ለሁለት ቀናት በቆየ ውይይት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ላቀ አያሌው እንዳስረዱት፣ እንደ አገር ሲታይ በኮንትሮባንድ፣ በሕገ-ወጥ ንግድ፣ በሐሰተኛ ደረሰኝ፣ በግብር ስወራ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን፣ በበጀት ዓመቱ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል ተብሎ ቢታቀድም ባልተሻሻሉ የታክስ ፖሊሲዎች፣ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ባለመደገፋቸውና በሌሎች መሰል ብዙ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ግብር እየተሰበሰበ አይደለም፡፡

እስካሁን እየተሰበሰበ ያለው ባህርን በጭልፋ ሊባል የሚችል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በውይይት መድረክ ላይ ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች በፍጥነት ወደ ተግባር በመቀየር፣ አሠራሮችን በመፈተሽ፣ ያለማቋረጥ ኅብረተሰቡን ስለታክስ ምንነት በማንቃትና በማስተማር እንዲሁም የታክስ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ታክስ ለመሰብሰብ መሥራት ይገባል ብለው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች