Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ላለፉት ሦስት ዓመታት ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄደው ንግድ ምክር ቤት የምሥረታ በዓሉን ሊያከብር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሕገ ደንቡ ውጭ ከሦስት ዓመታት በላይ የዘገየውን ጠቅላላ ጉባዔውን ሳያካሂድ የምሥረታ በዓሉን ለማክበር እየተሰናዳ ነው። ከምሥረታ በዓሉ ክብረ በዓል በኋላ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድና የአዳዲስ አመራሮች ምርጫ ለማከናወን አቅዷል።

 ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ያስታወቀው የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት በማስመልከት ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ ከንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብና ከተቋቋመበት አዋጅ ድንጋጌ ውጭ ጠቅላላ ጉባዔ ሳይጠራና ምርጫ ሳያካሂድ መቆየቱ ከአባላት ጭምር ትችት ሲቀርብበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ግን ይህንን ለመቋጨት መወሰኑንና ለዚህም ቀን መቁረጡን በዚሁ መግለጫው ላይ ገልጿል፡፡  

ንግድ ምክር ቤቱ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በጠቅላላ ጉባዔ አከናውኖ አመራሮቹን እንዳልመረጠ እየታወቀ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ለማክበር መዘጋጀቱ ተገቢነት ላይ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አመራሮች ክፍተቱ የተፈጠረው አስገዳጅ በሆኑ ምክንያቶች እንደሆነ የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዘገየው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ጋር በተያያዘ በተለይ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ በሰጡት ምላሽ የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራሮች ምርጫ ያልተካሄደው በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችና በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ምክንያት የማይቀበሉ ወገኖች ደግሞ ብዙ ተቋማት ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ተከናውኖ ሳለ ንግድ ምክር ቤቱ የሚሰጣቸውን ምክንያቶች ተቀባይነት የላቸውም ይላሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዓውን ለማካሄድና አዲስ አመራሮችን ለመምረጥ አሁን ላይ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።

የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም እንደገለጹትም ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔ በመጪው መስከረም 2015 ዓ.ም. የሚያካሂድ ይሆናል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫውን ወደ መስከረም የተገፉበት ዋናው ምክንያት 2014 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት ተሠርቶ መቅረብ እንዳለበት በመታመኑ ነው፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ካለማካሄዱ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኦዲት ሪፖርት ያልቀረበ በመሆኑ በቀጣዩ ጉባዔ የኦዲት ሪፖርት እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

‹‹የጠቅላላ ጉባዔን በተመለከተ ትክክለኛና መሠረታዊ ጥያቄ ነው፤›› ያሉት የንግድ ምክር ቤቱ ምክልት ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንን በበኩላቸው ንግድ ምክር ቤታቸው ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ውሳኔ በተላለፈባቸው በተለያዩ ወቅቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ እንዲሁም የሰሜኑ ጦርነት መቀስቀሱና ሌሎች ገፊ ምክንያቶች ጉባዔውን እንዳይካሄድ እክል እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ። ወ/ሮ መሰንበት ደግሞ በንግድ ምክር ቤቱ በአመራር ደረጃ መቀመጥ የሚያስገኘው ምንም ጥቅም የለም ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ያለመካሄዱና ምርጫ ተደርጎ ለአዲስ አመራር ቦታ ያለመልቀቃቸውም በቦታው ላይ መቆየት ፈልገው ሳይሆን አስገዳጅ ሁኔታዎች የፈጠሩት ችግር መሆኑን ያስገነዝባሉ።

የንግድ ምክር ቤቱ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ከቀደመው አንፃር ሲታይ የተዳከመ ስለመሆኑ፣ ለዓብነትም በተለያዩ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ድምፁ እየተሰማ አለመሆኑ ለትችት ዳርጎታል። ይህንን ትችት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ መሰንበት የንግድ ምክር ቤቱ የቀድሞና የአሁን እንቅስቃሴዎቹ እጅግ በጣም የተለያዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የንግድ ምክር ቤት አባሎችን ጥቅም የማስጠበቁ ሥራ ተጠንክሮ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት በአሥር ዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ለግል ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ዕገዛ እንደሚያደርግ ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም ቀድሞ ከነበረው ሁኔታ በተሻለ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን በመጠቆም፣ የንግድ ምክር ቤቱ ሚና ደብዝዟል የሚለውን ትችት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡ እንደውም ከቀድሞ በተሻለ ሁኔታ እየተራመደ መሆኑን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቷ ንግድ ምክር ቤታቸው በተሻለ እየሠራ ስለመሆኑ አስረጂ ይሆነኛል ያሉትን ምሳሌዎች አቅርበዋል፡፡ ከነዘህም ውስጥ አንዱ ከዋጋ ንረትና አጠቃላይ ሁኔታዎችን በተመለከተ በንግድ ምክር ቤቱ የፖሊሲ ንድፈ ሐሳብ ቡድን አማካይነት ለመንግሥት የቀበረውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በመሬት አቅርቦት፣ በግብርና እንዲሁም በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። እነዚህ ምክረ ሐሳቦችም በመንግሥት እየወጡ ባሉ ፖሊሲዎች ላይ እየታዩ መሆናቸውንም ፕሬዚዳንቷ ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ንግድ ምክር ቤቱ በተሻለ እየሠራ እንደሆነ በመጥቀስ የተሰነዘረውን ትችት እንደማይቀበሉ አመልክተዋል፡፡ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሺበሺ ደግሞ ንግድ ምክር ቤታቸው የተለየ አካሄድ እየተከተለ በመሆኑ ተፅዕኖው ላይስተዋል ይችላል ነገር ግን ሥራውን በአግባቡ እየሠራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

‹‹በአገራችን የተፈጠሩ ችግሮች በንግዱ ኅብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ቀውስና ችግር ፈጥሯል፡፡ የንግድ ኅብረተሰብ የተለያዩ ቀውሶች ገጥመውታል፤›› ያሉት አቶ ሺበሺ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ግን በድሮው የጩኸት ዘዴ አለመሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህ በፍፁም አይሆንም፡፡ ከእንግዲህ ንግድ ምክር ቤቱ የሚመራው በዕውቀት ነው፤›› በማለት የቀረበው ትችት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

‹‹መሪዎቻችን የቢሮክራሲው አካል፣ ተቋሞች የኢንቨስትመንትና የንግድን ችግር ሊሞላ የሚችል ዕውቀት አላቸው ብለን አናምንም፤›› ያሉት ዋና ጸሐፊው ነገር ግን እዚያ ላይ ተረባርበውና ተጋግዘው መሥራት የሚፈልጉ በመሆኑ በዚሁ ዕሳቤ ከመንግሥት ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ 

አገር የሚገነባውም በመተጋገዝ ጭምር በመሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ግልጽ የሆነ አቋም በመያዝ በትብብር በመሥራት አገር የመገንባት ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ‹‹መንግሥት ይቆያል ብዬ ነው ዛሬ ኢንቨስት የማደርገው፡፡ ከዚህ አኳያ የግሉ ዘርፍ በተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር እየሠራ ነው፤›› ያሉት አቶ ስለሺ በተለይ በአዲስ የኢንቨስትመንት ሕግጋት ላይ ሁሉ ከመንግሥት ጋር እየሠሩ መሆኑን ይህም ትልቅ ዕርምጃ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንግድ ምክር ቤቱ 75ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በተለያዩ ክንውኖች እንደሚያከብር ገልጿል፡፡ ቀደምት ከሚባሉ አገራዊ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንዱ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሰንበት የተለያዩ ታሪካዊ ምዕራፎች አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ርዕዮተ ዓለማዊ አንድምታዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያሳረፈ ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 በተለይ ከመንግሥት ጋር አገናኝ ድልድይ እንደመሆኑ በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ የአሠራር ማነቆዎችን ለማቃለል የንግድ ሥራዎችን ለማሻሻልና አገሪቱን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ጉምቱ ሥራዎች መሠራታቸውንም ወ/ሮ መሰንበት አስታውሰዋል፡፡ 

አሁንም የግሉን ዘርፍ ዕድገት ለማስቀጠልና የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን ምክር ቤቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል የአገናኝ ድልድይነቱን ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ 75ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በማስመልክት ይፋ ባደረገው መረጃ በዓሉ ከሰኔ 21 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህ ክብረ በዓል የተለያዩ ክዋኔዎች የሚካሂዱ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል ለንግድ ምክር ቤቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወገኖች ዕውቅና የሚሰጥ ሲሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሲምፖዚየምና ፓናሎች ይካሄዳሉ፡፡  

ከዋና ጸሐፊው ገለጻ መረዳት እንደተቻለው ደግሞ ‹‹በዓሉ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የገባችበትን ከጦርነት በኋላ የተፈጠረን በክራይሲስና በሪሴሽን ጊዜ መገለጫ የሆኑ የቢዝነስ ድክመቶችን በመጠኑ ለማስወገድ የመነሳሳት መንፈስን ለመፍጠር የተዘጋጀንበት ነው፤›› ይላሉ፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቶች የግሉ ዘርፍ ተወካይ በመሆናቸው የግል ዘርፉ አገር ገንቢ መሆኑን ለማስገንዘብና ለዚህም ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል የሚለውንም አመለካከት ለማንፀባረቅ ይህ በዓል ያግዘናል ብለው ያምናሉ፡፡

ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለይ ከኑሮ ውድነት ጋር ያሉ ችግሮችን ከመታደግና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ላይ ይፋ የሚያደርገው ፕሮጀክት እንዳለም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ 

እንደ ከተማ ንግድ ምክር ቤት በከተማ ውስጥ የሚደርሰውን የኑሮ ችግር በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እየመጣ በመሆኑ ከዚህ አንፃር ንግድ ምክር ቤቱ ሦስት አቅጣጫ ያሉት ፕሮግራም በማውጣት በሚቀጥሉት ሁለት የክረምት ወሮች የሚተገበረው ይሆናል፡፡ 

ይህም በከተማ ውስጥ ያሉ እስከ 70 ሺሕ ለሚደርሱ ችግረኞች የሁለት ወር የምገባና አስቤዛ ድጋፍ  የሚያደርግበት ይሆናል፡፡ 180 የሚሆኑ በዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታና መኮሮኒና የመሳሰሉ የንግድ ምክር ቤት አባል ኩባንያዎችን በማስተባበር የሚከናወን ነው ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ መቶ የሚሆኑ የንግድ ምክር ቤቱ አባል ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው የሁለት ወር ቀለባቸውን በአነስተኛ ክፍያና በብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮጀክት ተዘርግቷል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በረዥም ጊዜ የደወመዝ ብድር ክፍያ ቀለባቸው እንዲቀርብላቸው የሚያስችል አሠራር ሲሆን ይህንን አሠራር ንግድ ምክር ቤቱም በራሱ የሚተገብረው እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ደግሞ የቀን ቀለብ የሌላቸው በልመና ላይ ያሉትን ዜጎች የበሰለ ምግብ የመመገብ ፕሮግራም ተቀርጿል፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት አስተዳደርና የግሉን ዘርፍ በአንድነት በማጣመር የሚሠራ ነው፡፡ ይህም ‹‹የግሉ ዘርፍ ጥምረት በኑሮ ውድነት ላይ›› በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ሲሆን፣ አገልግሎቱን የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን በመጠቀም የሚካሄድ እንደሆነም ከዋና ጸሐፊው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች