- የዘንድሮ ክረምት ከበድ ብሎ የመጣ ይመስላል አይደል?
- እንዴት አወቅህ?
- ይኸው ገና ሰኔ ሳይገባ ጎርፍ እያስቸገረን አይደለም እንዴ?
- ቦዮቹ በቆሻሻ ስለተደፈኑ ይሆናላ?
- እንጂ ክረምቱ ከባድ ስለሆነ አይደለም እያልሽ ነው?
- እሱንማ እንዴት አውቃለሁ?
- በከባዱ እየዘነበ እያየሽ አይደለም እንዴ?
- ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑንማ እያየሁ ነው።
- ታዲያ ምንድነው የምትይው?
- መለየት አልቻልኩም ማለቴ ነው።
- ዝናብ መሆኑን መለየት አልቻልሽም?
- እሱማ እንዴት ይጠፋኛል?
- እና ምኑን ነው መለየት ያልቻልሽው?
- የማን እንደሆነ።
- ምኑ?
- ዝናቡን ነዋ፡፡
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው፣ ባለፈው የእኛ ዝናብ ነው ስትሉን አልነበረም እንዴ?
- እህ… የዝናቡን ባለቤት ነው መለየት የተቸገርሽው?
- ታዲያ… የብልፅግና ዝናብ ይሁን የክረምት ዝናብ መለየት ተቸገረን እኮ?
- አይ አንቺ… እና እንዴት ነው የዝናቡን ባለቤት የምትለይው?
- እኔ እንኳን ባልችልም በቀላሉ ይለያል ሲባል ሰምቻለሁ።
- እንዴት ነው በቀላሉ የሚለየው?
- በኪሎ በቀላሉ ይለያል አሉ።
- በኪሎ?
- አዎ። እንደዚያ ሲባል ሰምቻለሁ።
- ዝናብ በኪሎ?
- አዎ። ለምሳሌ የእናንተ አራት ኪሎ ነው የሚባለው አሉ።
- አራት ኪሎ? ለምን?
- እዚያ ስለማይጥል።
[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊው ዝናብ ዙሪያ ከባለቤታቸው እየተጨዋወቱ ቴሌቪዥኑን ሲከፍቱ ቃል አቀባይዋ የሰጡት መግለጫ እየተላለፈ ዓይተው ከባለቤታቸው ጋር መከታተል ጀመሩ]
- ሰማህ… ሰማህ?
- ምንድን? ቃል አቀባይዋ ያሉት ነው?
- አዎ። አሁን ነው ክረምቱ ከባድ ማለት!
- ምንድነው ያሉት?
- ክረምቱን ተገን አድርገው ጥቃት ለመክፈት ዝግጅት ላይ ናቸው እያሉ ነው።
- አያደርጉትም?
- ለምን?
- አይሆንም ስልሽ?
- እኮ ለምን?
- የቀጣዩ ዓመት በጀት ለፓርላማ ሲቀርብ የተገለጸው ያንን የሚያመለክት አይደለም።
- በጀቱ ሲቀርብ ምንድነው የተባለው?
- ጦርነት ቆሞ ሰላም እንደሚሰፍንና በቀጣዩ ዓመትም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ታሳቢ የተደረገው።
- እንደዚያ ከሆነስ ጥሩ ነው ግን ….
- ግን ምን?
- ለምንድነው ከአንድ መንግሥት ሁለት የሚጣረሱ መረጃዎች የሚወጡት?
- ምን ተጣረሰ?
- አንዱ በክረምቱ ጥቃት ለመክፈት ዝግጅት እያደረጉ ነው ይላል።
- እሺ…
- ሌላው ደግሞ በቀጣዩ ዘመን ሰላም ሰፍኖ ለመልሶ ግንባታ ትኩረት የሰጠ በጀት አጽድቁልኝ ይላል። ግራ እኮ አጋባችሁን?
- አይዞሽ አትስጊ ሰላም ይሆናል።
- የቀረበው በጀት ግን ያንን የሚያመላክት ነው?
- አዎ። ትልቅ በጀት ነው እንዲጸድቅ የተጠየቀው።
- ትልቅ በጀት መጠየቁ ሰላም እንደሚሆን ያሳያል ብለህ ነው?
- እንደ እኔ እንደ እኔ ትልቅ በጀት መጠየቁ ፊታችንን ወደ ልማት ማዞራችንን ይጠቁማል ባይ ነኝ።
- ስንት ተጠየቀ?
- 6 ቢሊዮን ብር።
- አጠቃላዩ ማለት ነው?
- አዎ። አጠቃላይ ነው።
- ከዚህ ውስጥ ለመከላከያ ስንት ተያዘ?
- መቶ ቢሊዮን።
- ምን…?
- ምነው ደነገጥሽ?
- በጀቱ ወደ ልማት መዞራችንን ይጠቁማል ስትል አልነበረም እንዴ?
- አዎ። ብያለሁ፡፡
- ይኼ ልማትን ይጠቁማል?
- እኔ ግን አላልኩማ፡፡
- ምንድነው ያልከው ታዲያ?
- ልማት ሳይሆን ወደ ልማት መዞራቸንን ይጠቁማል ነው ያልኩት።