Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያዊያን አምራቾች ተመርተው ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ወጥነት ባለው መንገድ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ተጠየቀ።

ኢትዮጵያ ሠራሽ የሆኑ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ባለመተዋወቃቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸው እንዳይጨምር አድርጓል ያሉት የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ፣ ለዚህም ወጥ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ መከናወን አለበት ብለዋል።

ኢንቨስትመንት ምርቶችን ለማስተዋወቅ ራሱን የቻለ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በተጨማሪም ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ የተውጣጣ አካል ከማስተዋወቅ ጀምሮ ገዥዎችንም ሆነ ኢንቨስተሮች እስከ መጨረሻው በመከታተል የሚጠይቋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ያስፈልጋል ብለዋል። አሁን ያለው የተበታተነ አሠራር ግን ወጥነት የሌለውና ውጤትም እያስገኘ እንዳልሆነ አክለዋል።

በአገር ውስጥ የአገርን ምርት የመጠቀም ባህል አነስተኛ መሆኑን፣ ይህንን ለማሻሻልም አምራቹ ከውጭ ከሚመጡ ምርቶች ጋር የሚስተካከል ጥራት ያለው ምርት ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ተጠቃሚውም የራስን ምርት በመጠቀም የአገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ እንዳለበት አስረድተዋል።

ለአምራቾች የሚሰጡ ማበረታቻዎችን አሁን ካለው በላይ ማሻሻል፣ እንዲሁም የተሰጡ የአምራች ማበረታቻዎች በትክክል መተግበራቸውን መከታተል ላይ ያለውን ክፍተት ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል።

የወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሽያጭ መሐንዲስ አቶ ብሩክ አድባሩ በአብዛኛው የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ አገሮች እንደሚልኩ ገልጸው፣ ነገር ግን ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በርካታ መሻሻል ያልባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል። በተለይም ለውጭ አገር የሚላኩ ምርቶች ታሳቢ አድርጎ ማምረት የተለመደ እንዳልሆነ፣ ለዚህም አርሶ አደሮች በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የምርቶቹን ዓይነት የውጭ ገበያን ታሳቢ አድርጎ ከመሥራት በተጨማሪ፣ ምርቶቹ ለገበያ የሚቀርቡበት ወቅትም ከተቀባዮች ፍላጎት ጋር የተጣጣመ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የግብርና ምርቶች ጥራት የጎደላቸውና ተቀባይነታቸው አነስተኛ በመሆኑ፣ ገዥዎች ባላቸው የመቀበል አቅም ልክ እንዳያቀርቡ እንዳደረጋቸው አክለዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅና ተቀባይነታቸውን ለማሳደግ በአገር ውስጥ ካለው አምራች ጀምሮ መሠራት እንዳለበት አስረድተዋል። የምርት ጥራትን ከማሳደግ ጎን ለጎንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ምርቶች ተቀባይነት ለማሻሻል፣ ባልተቆራረጠና በተለያዩ አማራጮች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

 የቤል ባልትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ በለጥሻቸው ነጋሽ በበኩላቸው ወደ ውጭ የሚልኳቸውን የባልትና ምርቶች ለውጭ ገዥዎች የሚያስተዋውቁበት መንገድ እንደሌለ ገልጸው፣ ለማስተዋወቅ ሲፈለግም በደላሎች አማካይነት መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የሚገኘውን ገቢ ለበለጠ ወጪ የሚዳርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ምርቶች የሚተዋወቁበትና ላኪዎች ከተቀባዮች ጋር የሚገናኙበትን ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች