Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለማዳበሪያ ግዥ የተለየ የግዥ ማዕቀፍ እንዲበጅ ምክረ ሐሳብ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ የሚያስገባው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከምርት ዘመን ጋር በተጣጣመ ጊዜ እንዲቀርብ ለማድረግ የተለየ የግዥ ማዕቀፍ ሥርዓት እንዲበጅለት ምክረ ሐሳብ ቀረበ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት መድረክ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የግብርና፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ የልማት ዘርፎችን ዋና ዋና አፈጻጸም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የግብርና ዘርፉን በተመለከተ በቀረበው ምክረ ሐሳብ ላይ እንደተመላከተው፣ የግብርና ምርት ወቅትና የበጀት ዓመቱ አቆጣጠር የሚጣጣም ባለመሆኑ፣ አገሪቱ ከፍጥነትና ከዋጋ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ባለማግኘቷ ለማዳበሪያ የተለየ የግዥ ማዕቀፍ ሥርዓት ሊኖር ይገባል ተብሏል፡፡

የበጀት ዓመት መጀመርያው ወር የሚባለው ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ ያለውን ጊዜ እንደሆነ ያስታወሱት ፍፁም (ዶ/ር)፣ ይህ ወር የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተዘግቶ ለአዲሱ የበጀት ዓመት ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የገንዘብ ፍሰት (ካሽ ፍሎው) ችግሮች የሚስተዋሉበት መሆኑን ሚንስትሯ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የማዳበሪያ ግዥ ሊደረግበት የሚገባው ወቅት የሐምሌ ወር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን የበጀት ዓመት አቆጣጠሩ ይህንን ለማከናወን ስለማይፈቅድ የግዥ ወቅት እንደሚዘገይና ይህም በፍጥነት ከመግዛት ሊገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም ማሳጣቱን በቀረበው ገለጻ ላይ ተገልጿል፡፡

የፕላን ሚኒስትሯ ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ ላይ እንደጠቆሙት፣ አገሪቱ ይህንን ጥቅም ለማግኘት ለማዳበሪያ ግዥ የተለየ የግዥ ማዕቀፍ ሥርዓት መኖር አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ስላሳየ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት እንዲያዘጋጅና ጥቅም ላይ እንዲያውል ክትትልና ድጋፍ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ዘርፍ የ2014 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከሁለት ሳምንት አስቀድሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ያቀረበ ሲሆን፣ በሪፖርቱ እንደተመላከተው፣ ለ2014/15 ምርት ዘመን በፍላጎት መሠረት ማዳበሪያ ማቅረብ አልተቻለም፡፡

አቅራቢዎችን በበቂ አለማግኘትና የዓለም የማዳበሪያ ዋጋ መጨመር፣ ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኋላ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱና ለግዥ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ማደጉ በአገሪቱ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ የተያዘው ዓመት የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮትነቱ ተገልጿል፡፡

የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል የግብርና ሚኒስቴር የመፍትሔ ሐሳቦች ያላቸውን ነጥቦች ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከዚያም ውስጥ ከውጭ የገባውን ማዳበሪያ ዋጋ መንግሥት የሚደጉምበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ አርሶ አደሩ 50 በመቶውን በቀጥታ ግዥና ቀሪውን በብድር የሚወስድበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንዲያዘጋጅና በመደገፍ ጥቅም ላይ ማዋል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በሌላ በኩል ከቀጣዩ ወር ሐምሌ እስከ መጪው የመስከረም ወር ድረስ የማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት ላይ አጠናክሮ በመሥራት ለሚቀጥለው የበጋ እርሻ ሥራ ዝግጅት ማድረግ ሌሎች በአማራጭ የመፍትሔ ሐሳብነት ቀርበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረበ ሲሆን፣ በመድረኩ ላይ የግብርና ሚንስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በተለይም የአፈር ማዳበሪያ የግዥና ሥርጭት ሒደትን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያው እንደተገለጸው፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የግል ድርጅቶች ከአርሶ አደሩ ጋር ማዳበሪያ እየጠቀራመቱ መኖር የለባቸውም ራሳቸውን ችለው ግብዓቶችን ከውጭ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ይህንን አሠራር የሚከተል ይሆናል ያሉት አቶ ኡመር፣ መንግሥት ሊደግፍ የሚገባው አነስተኛ አርሶ አደርን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የተሻለ ገቢና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ያላቸው ከአርሶ አደር እኩል ማዳበሪን መቀራመት እንደሌለባቸው ሚንስትሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ፍፁም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የግብርናው ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ፣ በተለይም የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ እንዲስገኝና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት እንዲችል የTEN IN TEN ስትራቴጂው በበጀትና በፖሊሲ በቂ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡ በተጨማሪም ለዘርፉ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖረው መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለበጋ ስንዴ ልማት የታየው የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመኸርና በበልግ ወቅት መድገም ከፍተኛ ለውጥ እንዲያመጣ መትጋት ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን፣ የመስኖ አጠቃቀምን እንዲሁ ውጤታማ ለማድረግ የመስኖ ኤክስቴንሺን ባለሙያዎች በጥራት ሠልጥነው ወደ ሥራ መግባት አለባቸው የሚል ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች