Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቅባት እህሎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዳይከፈል የተሰጠው ውሳኔ አለመተግበሩ ቅሬታ አስነሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ገንዘብ ሚኒስቴር በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ መሠረት ለቅባት እህሎች ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዳይከፈል ቢወሰንም፣ የተሰጠው ውሳኔ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ አልተደረገልንም ሲሉ ዘይት አምራቾች ቅሬታ አሰሙ።

 የኢትዮጵያ ምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሴ ጋርካቦ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማኅበሩ በጳጉሜን 2013 ዓ.ም. ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ ለዘይት ምርት የሚሆኑ የቅባት እህሎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ ተጠይቋል።

በጥያቄው መሠረት ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ኑግ፣ ሱፍ፣ ጎመን ዘርና የመሳሰሉ የቅባት እህሎችና ተረፈ ምርቶቻቸው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ ገንዘብ ሚኒስቴር  ወስኗል ብለዋል። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ይህ ውሳኔ ተፈጻሚ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት በኩል ግን ተፈጻሚ እንዳልሆነ አቶ አዲሴ ገልጸዋል።

ይህም በምግብ ዘይት ላይ የሚጠበቀው የዋጋ ቅናሽ እንዳይኖርና አምራቾችም ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን አክለዋል። በተጨማሪም ተጨማሪ እሴት ታክስ ተቀናሽ የተደረገው ለአምራቾች ቢሆንም፣ ድርጅቱ ግን ነጋዴዎችንም በተመሳሳይ መንገድ እያስተናገደ በመሆኑ አምራቾች መቸገራቸውን አብራርተዋል።

የሊዮስ ምግብ ዘይት ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይለ ማሪያም ጉተኒ፣ ለአምራቾች የተሰጠው የተጨማሪ እሴት ታክስ ቅናሽ ለነጋዴዎችም እኩል በመሰጠቱ በምርቶቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ምርቶቹ ለጨረታ በሚቀርቡበት ወቅትም ነጋዴዎች ከቀረጥ ነፃ ጥቅማ ጥቅም ተጠቃሚ በመሆናቸው፣ አምራቾችም ከነጋዴዎች ጋር ተወዳድረው መግዛት ባለመቻላቸው ተጎጂ መሆናቸውን አብራርተዋል። ነጋዴዎች የምርቱን ዋጋ ከፍ በማድረጋቸው አምራቾቹ የሚያስፈልጋቸውን ያህል የቅባት እህል ገዝተው መጠቀም አለመቻላቸውን የገለጹት አቶ ኃይለ ማሪያም፣ ፋብሪካቸው በቀን 1500 ኩንታል የቅባት እህል የመጠቀም አቅም ቢኖረውም እየተጠቀመ ያለው ግን 200 ኩንታል ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ድርጅት በቅባት እህሎች ላይ የተነሳውን ተጨማሪ እሴት ታክስ ተፈጻሚነት በተመለከተ ሪፖርተር ለድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አሽኔ ቦጋለ (ዶ/ር) ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አምራቾችና ነጋዴዎች በተመሳሳይ እየተስተናገዱ ናቸው ብለዋል።

ለዚህ በምክንያት ያቀረቡት ገንዘብ ሚኒስቴር ከቅባት እህሎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ቢያነሳም፣ ለነጋዴዎች ይሁን ወይስ ለአምራቾች የሚለው በግልጽ አልታወቀም ሲሉ ገለጸዋል፡፡ ‹‹በምርቶቹ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚነሳው ለየትኛው አካል እንደሆነ በግልጽ ሲቀመጥ ብቻ ማስተካከያ እናደርጋለን፣ ለዚህም ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች