ተጠርጣሪዎቹም አዋጅን የተመለከተ የይግባኝ አቤቱታ ለሰበር አቅርበዋል
ከግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በዋስ እንዲለቀቁ የፈቀደ ቢሆንም፣ ይግባኝ ተብሎባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ10,000 ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፈቅዶ የነበረው ለፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፣ ለሮሃ ሚዲያ ባለቤት መዓዛ መሐመድና ለገበያኑ ቢዝነስ ፕሮፌሽንና ኮሙዩኒኬሽን (ሠርገኛ ወጎች) ባለቤት አቶ ሰለሞን ሹምዬ ሲሆኑ፣ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው መርማሪ ፖሊስ ይግባኙን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ማቅረቡን፣ የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ይግባኝ ያለ ቢሆንም በዕለቱ የሚሰየም ዳኛ ባለመኖሩ፣ ፋይል ከፍቶ ለዛሬ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ማስቀጠሩንም አክለዋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር፣ ‹‹ተጠርጥራችኋል›› የተባሉበት ወንጀል እንደማያሳስራቸው አስረድተው፣ የሚያስጠይቃቸው የሚሆን ቢሆን እንኳ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 አንቀጽ 86(1) ድንጋጌ መሠረት መሆን እንደነበረበት መከራከራቸውን አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡
ክራክራቸውን ሰምቶ የሥር ፍርድ ቤት ውድቅ ስላደረገው፣ ጉዳዩ የሕግ ትርጉም እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ ማቅረባቸውንም አቶ ሔኖክ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስና መምህርት መስከረም አበራም ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ፖሊስ ከመምህርት መስከረም ቤት በብርበራ የያዘው የውጭ አገር ገንዘብ ሕጋዊነትን (ሁለት የኬንያ ሽልንግ) ለማጣራት ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ በጋዜጠኛ ያየሰው ደግሞ ላይ ማስረጃዎችን ከድረ ገጾች ማውረዱንና ማስተርጎም እንደሚቀረው፣ እንዲሁም የያዛቸው በርካታ ኤሌክትሮኒክሶችን ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተልኮ እያስመረመረ መሆኑን ተናግሮ፣ ውጤቱን ለመጠባበቅ በሁለቱም ተጠርጣሪዎች ላይ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን በሁለቱም ተጠርጣሪዎች ላይ ከተጠየቀው 14 ቀናት ስድስት ቀናትን ፈቅዷል፡፡