Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዕዳ ለያዛቸው መሬቶች ግብር ለመክፈል መስማማቱ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእርሻ ለተሰማሩ 114 ተበዳሪዎች የሰጠው ብድር ባለመከፈሉ፣ በዕዳ ከያዘው 69 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ይገኝ የነበረውን የምርት ግብር፣  የእርሻ መሬት ኪራይና ሌሎች ገቢዎች ለክልሉ መንግሥት ለመክፈል መስማማቱ ተገለጸ፡፡

የክልሉ መንግሥት ለባንኩ ባቀረበው መረጃ መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ከመሬቶቹ ሊገኝ ይችል የነበረው ገቢ 60 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን፣ ባንኩም ባለሀብቶቹ ክፍያውን ካቋረጡበት ጊዜ አንስቶ ለመክፈል መስማማቱን የክልሉ የገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከ2010 ዓ.ም. በፊት የክልሉ መንግሥት በሰፋፊ እርሻዎች ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ሲሰጥ ነበር፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ ባለሀብቶች ከክልሉ በነፃ የወሰዱትን መሬት አስይዘው ከልማትና ንግድ ባንኮች ብድር ከወሰዱ በኋላ፣ የተበደሩትን ገንዘብ ይዘው ጠፍተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ባለሀብቶች ብድሩን የወሰዱት የደን ምንጣሮ እንኳን ሳያካሂዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አመንቴ ጥቂቶቹ ሥራ ከጀመሩ በኋላ የመክፈል አቅም አጥተው ከስረው እንደወጡም አንስተዋል፡፡

ልማት ባንክ እነዚህ መሬቶች ማስያዣ አድርጎ ለባለሀብቶቹ የሰጠው ብድር ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡                         

‹‹ለልማት ይውላል ተብሎ የታሰበው መሬት ለግለሰቦች ዘረፋ ሁኖ ቀረ፡፡ በዚህ የተነሳ የክልሉ መንግሥት ከመሬትና እረሻ ግብር ያገኝ የነበረው 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢም ቀረ፤›› ያሉት ኃላፊው የክልሉ መንግሥት መሬቶቹን ወደ ልማት ሊያስገባ ሲል ባንኩ ‹‹የኔ ነው›› የሚል ሐሳብ ማንሳቱን አስታውሰዋል፡፡

አቶ አመንቴ እንደሚያስረዱት ልማት ባንክ የሰጠውን ብድር ለማካካስ በዕዳ የያዛቸውን እነዚህ መሬቶች አጫርቶ በሊዝ የመሸጥ ሐሳብ አለው፡፡ ይሁንና የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስተሮች መሬት በነፃ የሚሰጥ በመሆኑ እነዚህን መሬቶች ተጫርቶ የሚገዛ አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መሬቱ ባዶውን በመቅረቱ የክልሉ መንግሥት መፍትሔ ለማበጀት ከባንኩ ጋር ንግግር አድርጓል፡፡

በሁለቱ አካላት ንግግር፣ ባንኩ ክልሉ ከመሬቱ ያገኝ የነበረውን ገቢ እንዲከፍልና በሚሰጠው የጊዜ ገደብ መሬቱን አጫርቶ እንዲያስተላልፍ ካልሆነም ክልሉ ተቀብሎ ለአልሚዎች እንዲሰጠው የሚል መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ጋር በተደረገው ንግግር ባንኩ ክልሉ ከመሬቶቹ ያገኝ የነበረውን ገቢ ለመክፈል መስማማቱን አቶ አመንቴ ተናግረዋል፡፡ መጀመርያ ላይ ባንኩ ክልሉ ባመጣው 60 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ ላይ እንዳልተስማማ የገለጹት ኃላፊው ‹‹መጨረሻ ላይ ግን በ60 ሚሊየኑ ስንስማማ ኦዲት ተደርጎ የሚገኘውን በሙሉ ለመክፈል ተስማምተዋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አመንቴ ገለጻ ከተበዳሪቹ መካከል በቅርቡ ጥለው የወጡ ያሉ ሲሆን፣ ከጠፉ ሦስትና አራት ዓመት የሆናቸውም አሉ፡፡ ተበዳሪዎቹ ጥለው የወጡበት ጊዜ የተለያየ በመሆኑ የወጡበት ጊዜ ልክ ክልሉ ያጣው ገቢ ኦዲት ተደርጎ አጠቃላዩ ለባንኩ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡

የመሬቶች ዕጣ ፋንታ ምን ይሁን? የሚለው ላይ ግን ሁለቱ አካላት ሙሉ ለመሉ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን አቶ አመንቴ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእኛ አቋም መሬቱን በተሰጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ የማያስተላልፉ ከሆነ መውሰድ የሚል ነው፤›› ያሉት ኃላፊው ባንኩ ግን ክልሉ ያጣውን ገቢ የሚከፍለው መሬቱ ላይ ያለውን መብት ለማስጠበቅ እንደሆነ መግለጹን ተናግረዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ትላልቅ ካፒታል ያላቸው ዳያስፖራዎች በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ወደ ክልሉ ማስገባቱን ያስታወቁት ኃላፊው ይሄንን ለማድረግ ግን የመሬት እጥረት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ አክለውም ‹‹እነሱ ዛሬም ጀምሮ ማጫረት ላይ ችግር የለብንም ሰው አጣን እንጂ ነው የሚሉት እኛ ደግሞ በስድስት ወር ውስጥ ማስተላለፍ የማትችሉ ከሆነ ከፍተኛ የልማት ሥራ ነው የሚበላሸው ጥቅምም እናጣለን ብለናቸዋል፤›› ሲሉ የነበራቸውን ንግግር ጠቅሰዋል፡፡

ልማት ባንክና የክልሉ ገጠር መሬትና ኢንቨስትመንት ቢሮ ባደረጉት ንግግር፣ ልማት ባንክ በክልሉ አነስተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች ብድር የሚመቻችበት መንገድ ላይ ንግግር መደረጉንና ስምምነት ላይ መደረሱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ባንኩ ባህር ዳርና ነቀምት ከተሞች ላይ ሆኖ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ለማቅረብ አሶሳ ከተማ ላይ ቅርንጫፍ ለመክፈት ንግግር መደረጉን አቶ አመንቴ ገሺ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች