Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ችግር ፈቺ መፍትሔዎች ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያን ከገባችበት ውጥንቅጥ ውስጥ ለማውጣት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን በየፈርጁ የሚያቀርቡ ትጉኃን ያሉትን ያህል፣ ለችግር ፈቺ ጉዳዮች ጀርባቸውን የሰጡና ትርምስ ላይ የሚያተኩሩ እየበዙ ነው፡፡ አገር ለገጠማት ፈተና ነባራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ያገናዘበ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሰዎች ተሞክረው መፍትሔ ያላገኙ ንትርኮች ላይ ጊዜ መግደል ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው በሁሉም አቅጣጫዎች ሰላምና መረጋጋት ሲፈጠር ነው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ሰላም ለማስፈን ተመሳሳይ አቋም መኖር አለበት፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የጠመንጃ ላንቃ መዘጋት ይኖርበታል፡፡ በየቦታው ኩርፊያና ንጭንጭ እየታየ መረጋጋት ሊኖር አይችልም፡፡ ከሰላም ቀጥሎ ሕዝቡ የሚበላው ምግብ፣ ልብስ፣ የሚጠለልበት ታዛ፣ የጤና ክብካቤ፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርትና የመሳሰሉትን ማግኘት አለበት፡፡ ሥርዓተ ምግቡ ያልተስተካከለውና እጅግ ዘግናኝ በሆነ ድህነት ውስጥ እየማቀቀ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ችግር ፈቺ መላዎችን ወዲህ በሉ እያለ ነው፡፡ በግጭቶችና በጦርነቶች ምክንያት ሰላሙ ተናግቶ በፍርኃትና በጭንቀት ውስጥ ሆኖ፣ ከተደራራቢ ቀውሶች ውስጥ የሚያወጡት መፍትሔዎች ላይ ይተኮር እያለ ነው፡፡

ከችግር መፍቻ ዘዴዎች አንዱ ግጭትን ወይም ጦርነትን ተባብሮ ማስቆም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታሪኳ አብዛኛው ክፍል የጦርነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከዚህ ቀደም የውጭ ወራሪዎችን ለመመከትም ሆነ በእርስ በርስ የሥልጣን ትግል በርካታ ጦርነቶች ተደርገዋል፡፡ ዘመነ መሣፍንትን እንዲያበቃ ካደረጉት አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች በርካቶች አልቀዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ጦርነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያተረፈው ነገር ቢኖር ከመጠን ያለፈ የመረረ ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ከግጭትም ሆነ ከጦርነት አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይበጃል፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበትን የዕብሪት መንገድ መተው ይሻላል፡፡ ማንም በማንም ላይ የበላይ መሆን አይቻለውም፡፡ ይህ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ሥሩ ተነቅሎ መጣል አለበት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር እንዴት እንደምትገነባ የበሰሉ ሐሳቦችን ማቅረብ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብቻ የበላይ ሆነው አገር ስትታመስና ሕዝብ ተስፋው ሲደበዝዝ፣ ለምን ብሎ የሚነሳ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ማፍራትም ሌላው የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋ የሚለመልመው ልጆቿ ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡ ይህ ስምምነት መጠራጠርንና ቁርሾን ማስወገድ ይገባዋል፡፡ በሐሰት ከመሸነጋገል በመውጣት ለአገር ቁምነገር መሥራት የሚቻለው፣ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር እንደሌለ መተማመን ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ስም ለመስማት የሚፀየፉ ቢኖሩ እንኳ ችግራችሁ ምንድነው መባል አለበት፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙ አጓጉል ድርጊቶች የበርካቶችን አዕምሮ አበላሽተዋል፡፡ የተበላሹ አዕምሮዎችን ለማስተካከል ከፍተኛ ትዕግሥትና ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱን የመረዙት አጓጉል ነገሮችንም ማስተካከል እንዲሁ፡፡ ማንነትንና እምነትን መዝለፍና ማዋረድ የተዘራው መርዝ ውጤት ነው፡፡ በግራም ሆነ በቀኝ ተሠልፈው አፀያፊ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩትን ማረም ይገባል፡፡ የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ አመለካከቶች፣ ፍላጎቶች፣ ወዘተ ባሉባት አገር ውስጥ መቀንቀን ያለበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አንድነት ነው ኢትዮጵያውያንን በዓለም አቀፋዊ ደረጃ አንቱታ ያተረፈ ስም ያስገኘላቸው፡፡ ብዝኃነትን ሳይቀበሉ የኢትዮጵያዊነትን ፕሮጀክት ማሳካት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነትን በማናናቅና በማዋረድ የተሰማሩም የተያያዙት መንገድ አያዋጣም፣ አያዛልቅም፡፡

የሆድ ነገር ጊዜ አይሰጥምና ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡ እንቶ ፈንቶ ወሬዎችን አስወግዶ የተትረፈረፈ የምግብ ምርት የሚገኝበትን ዘዴ የሚያመላክቱ ሐሳቦች ላይ ይተኮር፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከውጭ የሚገቡ የምግብ ምርቶችንና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን፣ በአገር ውስጥ በብዛትና በጥራት እንዴት ማምረት እንደሚቻል የሚያግዙ ሐሳቦች ይፍለቁ፡፡ ኮቪድ-19፣ የተለያዩ ግጭቶች፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና ድርቅ ተባብረው ያደቀቁት ኢኮኖሚ በዘላቂነት እንዴት እንደሚያገግም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ በኑሮ ውድነት እየተደቆሰ ያለው ሕዝብ በምን ዓይነት ዘዴ መሠረታዊ ፍላጎቶቹ ከሞላ ጎደል እንደሚሟሉ መፍትሔ ይፈለግ፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ወገኖች ሐሳብ እንዲያካፍሉ፣ የተጣመመ ነገር ካለ እንዲያስተካክሉ ዕድል ይሰጣቸው፡፡ ዘመኑ በቴክኖሎጂ ግስጋሴ ወደር የሌለው ነውና የሙያው ባለቤቶች ይጋበዙ፡፡ የተለያዩ አገሮች ከመሰል ችግሮች ውስጥ እንዴት ሊወጡ እንደቻሉ በባለሙያዎች ጥናት ይደረግ፡፡ በጥናቱ ውጤት መሠረትም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚስማማ የፖሊሲ ውሳኔ ላይ ይደረስ፡፡

ይህ ወቅት ለኢትዮጵያም ሆነ ለኢትዮጵያውያን ከባድ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በፍጥነት ሰላም ማስፈን ካልተቻለ፣ ለአፍሪካ ቀንድ የሚተርፍ አደገኛ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚለው ብዙዎችን ያስማማል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተሰማ ያለው የሕወሓት ኃይሎችና የኤርትራ መንግሥት ግጭት፣ በአካባቢው የብዙ አገሮች ተሳትፎ የሚኖርበት ጦርነት የማስነሳት አቅም አለው፡፡ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላት የድንበር ውዝግብና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማይዋጥላት ግብፅ ጉዳይ፣ እንዲህ በቀላሉ የሚገላገሉት ሳይሆን ከብዙ ነገሮች ጋር የሚወሳሰብ ነው፡፡ በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሰቀሰው አልሸባብ ጉዳይም እንዲሁ፡፡ ጦርነትና የምግብ እጥረት ሲቀናጁ ደግሞ ከባድ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ በሥልጣንም ሆነ በሌላ ምክንያት የከረረ ቅራኔ ውስጥ እየገቡ ያሉ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ሌሎች አካላት፣ ከገቡበት አደገኛ ጎዳና ወጥተው ለሰላማዊ ንግግርና ድርድር ራሳቸውን ካላዘጋጁ መጪው ጊዜ በጣም ከባድ ነው፡፡ ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የሆቴል አገልግሎት፣ የኮንስትራክሽንና መሰል ዘርፎች እንቅስቃሴ ሲስተጓጎል ኢኮኖሚው ሙሉ ለሙሉ ሊቆም ይችላል፡፡ ስለዚህ የመፍትሔ ያለህ ይባል፡፡

ወደ መራሩ እውነታ ስንቃረብ ደግሞ የመጪው ዓመት በጀት ወጪ ቅነሳ ላይ እንደሚያተኩር ነው የተሰማው፡፡ በዚህም መሠረት አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች አይኖሩም፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከሌሉ ደግሞ በርካታ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችና በሥራቸው የሚገኙ ሠራተኞች ሥራ አይኖራቸውም፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማ የተመራው 781.6 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ላይ ማብራሪያ ሲሰጥ፣ ከውጭ በብድርና በዕርዳታ ሊገኝ የሚችለው አስተማማኝ ስለማይሆን ወጪ ቁጠባ ላይ ማተኮር የግድ ነው ተብሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉትሬስ፣ ሀብታም አገሮች ለደሃ አገሮች ከሰብዓዊ ዕርዳታ በስተቀር የልማት ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ያሳስባል ሲሉ ሰሞኑን ማስታወቃቸው የችግሩን መጠን ያሳያል፡፡ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ዳፋና በሌሎች አጣብቂኞች ሳቢያ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ፣ ሰላም በማስፈን ከችግሮች የመውጫ ቀዳዳ አለመፈለግ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የከበቧትን ችግሮች በዘዴ ተሻግሮ ለውጤት መብቃት የሚቻለው፣ ችግር መፍቻ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ሲቻል ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...