Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከ40 ዓመት በላይ የሠፈራችን ነዋሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አንዲት አዛውንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩን፡፡ እኚህ በጉልት ንግድ የሚተዳደሩ እናት በአንዲት ጠባብ ክፍል የቀበሌ ቤት ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ሲሆን፣ ልጅ የላቸውም፡፡ በአለፍ ገደም ሊጠይቃቸው የሚመጣ ‹‹ዘመድ›› እንደሆነ የሚነገርለት አንድ ሰው ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣ ይኼ ነው የሚባል የቅርብ ሰው የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ብቻቸውን ኖረው ነው ለዘለዓለሙ ያሸለቡት፡፡ ዘመድ አልባ ብቸኛ ምስኪን፡፡

የአካባቢው ሰዎች ተሰባስበን የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማስፈጸም ወዲያ ወዲህ ስንል፣ አምስት ያህል ሰዎች ተመርጠን ያላቸውን ንብረት እንድናስከብር ተወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት አስከሬናቸውን አስገንዘን ሁሉም ነገር በወጉ መሠረት ከተፈጸመ በኋላ ወደ ቀብር ስንንቀሳቀስ፣ በሰብሳቢነት የመረጥናቸው አዛውንት ቤቱን ቆለፉት፡፡ ከደጅ ጠባቂም መደቡለት፡፡ የአዛውንቷን ቀብር ፈጽመን ለሦስት ቀናት ድንኳን ውስጥ ብንከርምም፣ ‹‹ዘመድ›› ተብሎ የሚታወቀውን ሰው ግን ማግኘት አልቻልንም ነበር፡፡ የት እንደሚኖር አይታወቅምና፡፡

ያም ሆኖ ሰነባብተን አምስታችን የኮሚቴ አባላት በሩን አስከፍተን የአዛውንቷን ንብረት አደራጅተን ለማሳወቅ ሥራ ጀመርን፡፡ በመጀመሪያ ለዓመታት ይተኙበት የነበረውን የሽቦ አልጋ ለማውጣት ፍራሹን ስናነሳ ለማመን የሚያዳግት ነገር ገጠመን፡፡ በፍራሹና ከሥሩ በተነጠፈው አሮጌ ብርድ ልብስ መካከል ከዳር እስከ ዳር ገንዘብ እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል ተጎዝጉዟል፡፡ መሬት ላይ ጋቢ አንጥፈን ገንዘቡን ላዩ ላይ መልክ መልክ እያስያዝን አስቀመጥን፡፡ እጅ በእጅ በተደረገ ቆጠራ 41,557 ብር ተገኘ፡፡ ጉድ አልን፡፡ በጉልት ንግድ እየተቆራመዱ ይኖሩ የነበሩ እናት በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ ቆሎ ወይም ቂጣ እየበሉ፣ አንጀታቸውን አስረው ይህንን ሁሉ ገንዘብ ማከማቸታቸው ገረመን፡፡ አልጋቸውን አውጥተን ሌሎች ትርኪ ምርኪ ዕቃዎችን ማየት ጀመርን፡፡

አሁን ደግሞ የባሰ ነገር ገጠመን፡፡ የበርበሬ ዕቃቸውን ስንከፍተው ገንዘብ፣ የሽሮ ዕቃቸው ሲከፈት ገንዘብ፣ የጥጥ አገልግላቸው ሲከፈት ገንዘብ፣ የሲኒ ረከቦት መሳቢያ ውስጥ ገንዘብ፣ አንደኛው ጥግ ላይ የተቀመጠ አሮጌ አነስተኛ የብረት ሳጥን ውስጥ ገንዘብ፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ቤቱ ውስጥ ያለ ዕቃ ውስጥ ሁሉ ገንዘብ አለ፡፡ ሁሉንም ቦታ አበጥረን ፈትሸን ሲቆጠር ተጨማሪ 24,241 ብር ተገኘ፡፡

እማማ ግን አንድም ቀን ጎናቸውን አሳርፈው የረባ ነገር በልተው አያውቁም፡፡ ይልቁንም ጎረቤት አንዳንዴ ከሚያጎርሳቸው የተሻለ ነገር ዓይተው የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ በጣም አሳዘኑኝ፡፡ ዕቃቸውን በሙሉ ፈትሸን ጨርሰን ካስተካከልን በኋላ ጣሪያ ላይ የተንጠለጠሉ ቅሎችን አየን፡፡ አውርደን ስንፈትሽ ሌላ 6,427 ብር አገኘን፡፡ አይ እማማ ማን እንደሚበላው የማይታወቅ ለዓመታት የተጠራቀመ በጠቅላላው ከ72 ሺሕ ብር በላይ ጥለው አልፈዋል፡፡ አንድ ቀን እንኳ ሳይደላቸው፡፡

‹‹ዘመድ›› የሚባለው ሰው እስካሁን ብቅ አላለም፡፡ ጎረቤቱ ደግሞ ምንም ቢሆን ስኳርና ቡና፣ ሙዝና ብርቱካን እየያዘ የሚጠይቃቸው ስለነበረ ወራሻቸው እሱ መሆን አለበት ብሎ ስለወሰነ እየተጠበቀ ነው፡፡ አንድ ቀን ብቅ ሲል ከሞታቸው ይልቅ ትተውለት ያለፉት ድንገተኛ ሀብት እንደሚያስደነግጠው አይጠረጠርም፡፡ አንዱ ያከማቸውን ሌላው መብላቱ የተለመደ በሆነባት ዓለም ውስጥ፣ በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል በውርስ ምክንያት በየቦታው የሚፈጠረውን ጦርነት ላየ ይኼ ላይደንቅ ይችላል፡፡ በየፍርድ ቤቱ ወራሾች የኑዛዜ ወረቀት ‹‹ፎርጅድ›› እያሠሩ ሲካሰሱ ብዙ ጊዜ ስላየሁ፣ ሟች በሕይወት እያለ ላይ ታች ወርዶ ጥሎት ያለፈ ሀብት ቋሚዎችን እንዳይሆኑ ሲያደርጋቸው የማየት ዕድል ቢኖረው ኖሮ እንዴት ይሆን ነበር እላለሁ፡፡

የአዛውንቷን ወራሽ እየጠበቅን ባለንበት ወቅት ከዓመታት በፊት የተከሰተ አንድ ገጠመኝ ትዝ አለኝ፡፡ ድሮ ፒያሳ ሆስቴል ውስጥ ስኖር አንድ ሰው ነበር፡፡ ይህ እንግሊዝ አገር ማስተርሱን ሠርቶ ለበርካታ ዓመታት በመንግሥትና በተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ውስጥ ያገለገለ ሰው ለምን ሆስቴል ውስጥ እንደሚኖር ይከነክነኝ ነበር፡፡ እኔና መሰሎቼ ቤት አጥተን ነው እዚያ የምንኖረው፡፡ ይህ ሰው ግን በዘመኑ ከፍተኛ ተከፋይ የነበረ ከመሆኑም በላይ የራሱ ፔጆ መኪና ነበረው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምግብ የሚበላው በጣም ርካሽ የተባለ ቦታ ነው፡፡ ቁርሱን ሻይና ዳቦ አነስተኛ ሻይ ቤት ገብቶ ይበላል፡፡ ምሳውን ደግሞ በአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሽሮ በቃሪያ ይበላል፡፡ ከዚያ ውጪ ሕይወት የለውም፡፡ በእግሩ ፒያሳን እያካለለ ቢራ እንኳ ጠጥቶ አያውቅም፡፡ ኬክም በልቶ አያውቅም፡፡ ተቆራምዶ ኖሮ ድንገት ሳይታሰብ ይታመማል፡፡

ሆስቴሉ ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ትልልቅ ሰዎችን አስጠርቶ አንድ ሰው ዘንድ እንዲደውሉለት ያስደርጋል፡፡ ‹‹ወንድሜ›› የሚለው ያ የሚያውቀው ሰው ይመጣል፡፡ የማይታወቀው ሰው በመልክም ሆነ በግብርም አይመስለውም፡፡ በቃ ባዕድ መሆኑ በደንብ ያስታውቃል፡፡ ለስላሳ መጠጥና ቀለል ያሉ ምግቦች እያመጣ ቢሞክረው ሰውየው መብላት አልቻለም፡፡ ሆስፒታል ልውሰድህ ሲለው ገንዘብ ማውጣት ስላልፈለገ እንቢ አለ፡፡ ሞት አይቀርምና ሞተ፡፡ ይህ ‹‹ወንድም›› የተባለ ሰው ቀብሩን ካስፈጸመ በኋላ የሰውየውን ክፍል ከፍቶ ሰነዶችን ሲበረብር ባንክ ውስጥ የተከማቸ በብዙ ሺሕዎች የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘቱን ሰማን፡፡ ጊዜ ሳያጠፋ ፍርድ ቤት አሳውጆ ወረሰ፡፡ ቤት ውስጥ ያገኘውን ገንዘብና መኪናም ወሰደ፡፡ የሆስቴሉን ክፍል ለአንድ የገዛ ዘመዱ በስጦታ ሰጠ፡፡

ያ ወራሽ ዛሬ እኔ ነኝ ያለ ሀብታም ነው፡፡ በአንዴ ከዜሮ ወደ ሚሊየነርነት የሚቀይረውን ዕድል ያገኘ ሀብታም፡፡ አንዳንዴ ልፋታችንና ውጣ ውረዳችን እኛን ካልጠቀመን የሕይወት ትርጉሙ ግራ ያጋባል፡፡ መጀመሪያ ለራስ በኋላ ለሌሎች ብንኖርስ? ጠቢቡ ሰለሞን ከፀሐይ በታች ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ሲገልጽ የመከረን፣ ልፋታችንን በመደሰት እንድናካክስ ነበረ፡፡ በዚህች ኃላፊ ዓለም ምን አቆራመደን? ላባችንን አንጠፍጥፈን ያፈራነውን በየሥርቻው እየሸጎጥን ለሌሎች ሲሳይ ከማድረግ፣ በሕይወት እያለን ብንሠራበትና የሥራ ዕድል ብንከፍትበት ለአገርና ለወገን አይጠቅምም? ለህሊናስ ደስ አይልም? በዚህ ዘመን ደግሞ ለተቸገሩ ወገኖቻችን ብንደርስላቸው በምድርም በሰማይም መልካም ሥራ ይሆናል፡፡

(ሳሙኤል ተፈሪ፣ ከአዲሱ ገበያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...