Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገራዊ የዕርቅና ሰላም ፍለጋ በሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፍ

አገራዊ የዕርቅና ሰላም ፍለጋ በሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፍ

ቀን:

በዓባይነህ ግርማ

የአገራዊና ሕዝባዊ ሰላም ዕጦት መግለጫዎችን እንዘርዝር ብንል በአገር ደረጃ፣ ከትንሹ ከሠፈር ሠፈርና ከቀበሌ ቀበሌ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ክልላዊ አስተዳደር ደረጃ የሚታዩ፣ ከዚያም ሰፋ ሲል በአኅጉራዊ፣ በቀጣና በክልል አገሮች መካከል የሚከሰቱ ትንኮሳዎችን፣ ፀቦችን፣ ግጭቶችንና ጦር መማዘዞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእነዚህ መነሻዎች ደግሞ በሠፈርና በቀበሌ ደረጃ የሀብት ክፍፍል፣ የተጠቃሚነትና የይገባኛል ጥያቄዎች፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች፣ በክልልና በአገር ደረጃ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ፍላጎትና የብሔርተኝነት አስተሳሰብና ተቃርኖዎች ሲሆኑ፣ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትና የተፅኖ ፈጣሪነት ፍላጎቶች፣ ጣልቃ ገብነትና ተፅኖዎች፣ እነዚህም የሚፈጥሩት የሉዓላዊነት መብትና ሥጋት መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በአገራችን በኢትዮጵያ የተጠቀሱት የሰላም ዕጦት መገለጫዎችና ምክንያቶች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ የመጡና ዛሬ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱበት ወቅት ሆኗል፡፡ በውስጣዊ ተቃርኖዎችና በውጫዊ ጣልቃ ገብነትና ጫናዎች ምክንያት የሰላም ዕጦት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና ጦርነቱ ያስከተለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሥነ ልቦና ስብራት፣ የሀብትና የንብረት፣ የልማትና አገልግሎት መስጫዎች ውድመት ይህ ነው አይባልም፣ እጅግ አስከፊ ሊሆን በቅቷል፡፡ በአጠቃላይ አገራዊና ሕዝባዊ የህልውና ዘለቄታ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ያሠጋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሰላም ዕጦትና ለእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሚሆኑ ኃይሎች በርካታ ሲሆኑ በተለይ ብሔርተኛ ልሂቃን፣ ብሔርተኛ ድርጅቶች፣ ብሔርተኛ አክቲቪስቶች፣ ብሔርተኛ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ሙሰኞች፣ ጥቅመኞች፣ ጣልቃ ገቦች፣ ኢዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ አስተዳደር ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ማንነት በሚቀነቀንበት ኅብረተሰብ የእነዚህ ኃይሎች አፍራሽ ሚና የላቀ ነው፡፡ ስለሆነም ስለሰላም፣ ስለአገራዊና ሕዝባዊ አንድነትና ደኅንነት ሲታሰብ  እነዚህ ኃይሎች የችግሩ ምክንያት የመሆናቸውን ያህል የመፍትሔም ሚና ሊኖራቸው ይችላል ብሎ ለማሰብ የሚያስቸግር ቢሆንም እንኳ፣ ችግርን ከማባባስ መቆጠብ ራሱን የቻለ የመፍትሔ አካልነት ሆኖ ሊቆጠር ይችላል፡፡

በተለይ ራስን በራስ በማስተዳደርና በብሔር ብሔረሰብ መብት ጥያቄ ሰበብ የመገንጠል ዕሳቤ ያለው ማንኛውም ክልልና ሕዝብ ሊያጋጥመው የሚችለውን የህልውና አደጋ ቢሆኖችን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመገንጠል መንፈስና ዕሳቤ በግልጽ እየታወቀ፣ የመጣበትንና ለከፍተኛ ጦርነት የተዳረገውን የትግራይ ክልል አስተዳደርና ሕዝብ የመገንጠል ዕሳቤ ዕውን ይሁን ቢባል ወይም ቢሆን እንኳን ሊደርስበት የሚችለው አደጋ ከአጎራባች ክልሎችና ሕዝብ ጋር መቃቃር፣ መገለል፣ መገፋፋት፣ መናቆር፣ ብሎም ለሰላም ዕጦትና አለመረጋጋት ይዳረጋል፡፡ ከአጎራባች አገርና ከሕዝብም ጋር በጠላትነት ሊቆም ይችላል፡፡ በእነዚህም ምክንያቶች የሚታለመው ወይም የታለመው “ትግራያዊው አገርነት” ህልም ወይም ቅዠት፣ ዘላቂ ህልውናና ደኅንነት ከቶ ሊኖረው አይችልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የመገንጠል ዕሳቤ ያለው ወይም የሚኖረው ማንኛውም ሌላ ክልልና ሕዝብ ቢኖር ለተመሳሳይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የደኅንነት አደጋ ተጋላጭ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ክልሎች ከአጎራባች አገሮች ሊሰነዘሩ በሚችሉ ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በብሔርተኛ የፖለቲካ ወይም የማኅበራዊ ድርጅቶችና ቡድኖች የሚቀሰቀስና የሚካሄድ የመገንጠል ጥያቄና ጦርነት መዘዙና ውጤቱ፣ ለእያንዳንዱና ለሁሉም ብሔራዊ መንግሥታትና ሕዝቦች የህልውና  አደጋ ይሆናል፡፡

ስለሆነም በብሔር ማንነት ፖለቲካ የተቃኘ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል የሚል መርህን ተከትሎ በአንድ አገር ሕዝብ መካከል የሚካሄድ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት፣ በማንኛውም የዕርቅና የሰላም ምክክርና ድርድር መወገዝና መወገድ ያለበት ነው፡፡ ታዲያ የእዚህ ቁልፉ ጉዳይ የግጭትና የጦርነት ማስወገድና የዕርቅና ሰላም ፍለጋ (Quest for Reconciliation and Peace) ኃላፊነትና ባለቤትነት የማን ሊሆን ይገባል የሚለው ነው፡፡ ጉዳዩ ሕዝባዊና መንግሥታዊ የመሆኑን ያህል፣ ሕዝባዊና ሥነ መንግሥታዊ ሥልትና መንገድ ተከትሎ መከወን ያለበት ነው ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ መንፈስ የዕርቅና የሰላም ፍለጋ በግጭትና ጦርነት ኃይሎች ማለትም በመንግሥታቱና አብረዋቸው በቆሙ ኃይሎች መካከልና ባለቤትነት ሊፈጸም ይገባል ሊባል ነው፡፡ ክልላዊና ፌዴራላዊ መንግሥታት ቀዳሚ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ሊገመት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የግጭቱና የጦርነቱ ኃይሎች መንግሥታቱና አብረዋቸው የተሠለፉ ራሳቸው ሆነው ስለሚታዩና ስለሚቆጠሩ፣ ተዓማኒ የምክክርና የዕርቅ ፍለጋ የባለቤትነት ሚናና ቁርጠኝነት ሊሳናቸው ይችላልና በተሻለ አማራጭ ሥልትና ማዕቀፍ መደገፍ ይኖርበታል የሚያሰኝ ይሆናል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሕግንና አገራዊ ህልውናን ለማስከበር የተወሰደው ዕርምጃ ለጦርነት ዳርጓል፡፡ ይሁን እንጂ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከዚያ በፊት ዕርቅና ሰላም አፈላላጊና አሸማጋይ ተልዕኮዎችን በማዘጋጀት፣ የወሰንና የማንነት ጥናት ኮሚሽን በማቋቋም፣ በጦርነቱም ሒደት የጥሞና ዕድል ጊዜያት በመስጠት የዕርቅና የሰላም ፍለጋ ጥረት መደረጉ ይታወሳል፡፡ ሰብዓዊ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት በከፍተኛ መጠን ወደ ክልሉ እንዲገባ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ጥረቶች ተገቢ የነበሩ ቢሆንም፣ የተፈለገውን ሰላማዊ ሁኔታና ውጤት በማስገኘት ፈንታ ለጦረኛ ኃይሎች የልብ ልብ ሲሰጣቸው ተስተውሏል፡፡ አሁንም የዕርቅና የሰላም ፍለጋውን ጥረት በመቀጠል የአፍሪካ ኅብረትን ልዑክ አደራዳሪነት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡም የተሰየመው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የዕርቅና የሰላም ፍለጋ አካል እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡ በተለይ የአፍሪካ ኀብረት አደራዳሪነት የፌዴራል መንግሥቱ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝብ ለሕዝብ የዕርቅና የሰላም ፍለጋ ማዕቀፍና የሚፈጥሩና የሚያጠናክሩ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ተነሳሽነቶች የዕርቅና የሰላም ፍለጋውን በራሳቸው እንዲያካሂዱ የሚጠበቅ መሆኑ ቀርቶ፣ ከሥነ መንግሥታት መዋቅር ውጪ የሕዝብ ለሕዝብ የዕርቅና የሰላም ፍለጋ ማዕቀፍና ሒደት እንዲፈጠር ማመቻቸትና መሥራት አለባቸው፡፡

ይሁን እንጂ የተመለከተው የሕዝብ ለሕዝብ የዕርቅና ሰላም ፍለጋ ማዕቀፍ በመርህና በሐሳብ ደረጃ የሚፈለግና መሆን ያለበት ስትራቴጂ ቢሆንም፣ ትግበራው መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚጠይቅ ነው፡፡ አንደኛ የጦርነቱ ተዋናዮች ማለትም የትግራይ የሕወሓት መራሹ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት፣ እንዲሁም በሁለቱም በኩል በአጋርነት የቆሙ ኃይሎች ከራሳቸው ውጪ የሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፉን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡ ሁለተኛ በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ወገን የሚደረግ የውጊያና የጦርነት ዝግጅት በተኩስ አቁም ስምምነት (Hostility and Cease Fire) ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ ሦስተኛ የትግራይ የሕወሓት መራሽ መንግሥት ከፌዴራሉ የአገር ምክክር ኮሚሽን ጋር በአጋርነት የሚሠራ (Counterpart) ኮሚሽን መሰየም አለበት፡፡ ይህን ቅድመ ሁኔታ ለመፈጸም የትግራይ ሕወሓት መንግሥት ፈቃደኛና ዝግጁ ይሆናል ወይ የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ በጎነቱን አጥብቆ መፈተሸ ግን ያሻል፡፡ ሕዝቡ ዘንድ ሊደርስ የሚቻልበት ሥልት ሁሉ መታሰብና መሞከር ይኖርበታል፡፡

አራተኛ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነትና በሁለት በኩል የተሰየሙ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መዋቅሮች የሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፉን የማመቻቸት ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አምስተኛ በዕርቅና በሰላም ፍለጋ በመፍትሔ አካልነት የቆሙ የውስጥና የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም በጎ ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታት ለየሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ በይፋ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ስድስተኛ ሕግን ለማስከበር ሲባል የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ስትራቴጂካዊ የሆነውን የአገር ህልውና ለማስጠበቅ የሚደረጉትን የውይይት፣ የምክክርና የድርድር ጥረቶችን እንዳያውኩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰባተኛ የሕዝብ ለሕዝብ ማዕቀፍ ከበጎ አድራጎት ሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከወጣቶችና ከሴቶች ማኅበራት፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከመምህራንና ከሌሎች የሙያ ማኅበራት፣ ከሚዲያ፣ ወዘተ. በሚወከሉ አባላት እንዲቋቋም መደረግ አለበት፡፡

የዕርቅና የሰላም ፍለጋ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር በቀዳሚነት የሰሜኑን የጦርነት እንቅስቃሴ በሚመለከት ቢሆንም፣ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የሚፈጸሙ ግጭቶችን፣ ግድያዎችንና ሌሎች የሽብር ድርጊቶችን በሚመለከት ጭምር መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡ ስለሆነም የሕዝብ ለሕዝብ የዕርቅና የሰላም ፍለጋ በርዕሰ ጉዳይና በክልል ሳይወሰን/ሳይገደብ ሁለንተናዊ ፕሮግራምና ጥረት ሊደረግ ይገባል፡፡  

ዕርቅና ሰላም ለሁሉም!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...