Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹‹ኢትዮጵያዊያን የአንድ እናት ልጆች ነን››

‹‹ኢትዮጵያዊያን የአንድ እናት ልጆች ነን››

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው  

ዕውቁ የሥነ ጽሑፍ፣ የቴአትርና የፍልስፍና አዋቂና የሥነ ፍጥረት ሊቁ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን (ነፍሳቸውን ይማረውና) በነሐሴ ወር 1997 ዓ.ም. ከጦቢያ መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ሰፊ የታሪክና ወቅታዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ሀቲታቸው የጊዜ፣ የቦታና የሁኔታ መቀያየር እንጂ ኢትዮጵያዊያን የአንድ እናት ልጆች እንደሆንን ያወሱበትን ጭብጥ የጽሑፌ መግቢያ ለማድረግ ወድጃለሁ፡፡ የትኩረቴ ማጠንጠኛም ቢሆን የአገራችን ሕዝብ በገዥዎች አለማወቅ፣ ጥፋትም ይባል ሴራ፣ እንዲሁም በዘመናዊው የፖለቲካ ትውልድ ጥገኝነት እንዲለያዩ መገፋታቸው እንጂ፣ ለአብሮነትና ለወንድማማችነት የቀረበ መሆኑን ለማመሳከር ነው፡፡ በእውነቱ አሁን በምንገኝበት አሳዛኝ ወቅት በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በሁሉም አቅጣጫ በማንነታቸው ብቻ በድንጋይና በእንጨት ሳይቀር መገዳደላቸውን በምንሰማበት አገር እንዲህ ያለ ጭብጥን ከማንሳት ውጪ ምን ሌላ አጀንዳ ለመያዝስ ይቻላል?

እንዲህ ይላሉ ሎሬት፣ ”የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአይሁዳዊያንና ከሮማዊያን በፊት ጀምሮ ከግሪኮችና ከፈርኦኖች በፊት ጀምሮ ከልቡ ሃቅ የሚያከብር ነው፡፡ ከልቡም ክህደትን ይጠላል፡፡ ሕዝብ በታሪክ ከጂዎች እየተጠለፈ እንጂ፣ ሁላችንም ከኩሽና ከሴም  የተቀየጥን የአንድ እናት ልጆች መሆናችንና ከሰማይም አለመውረዳችንን ያውቃል፡፡ አስተዳደጋችን ግን በመቻቻል ላይ ሳይሆን፣ በመበላለጥና በመሸናነፍ ላይ ስለተመሠረተ፣ በሃይማኖቶችና በቋንቋዎች አጥር ታግዶ፣ በባላባቶች ዝርፊያ ስለተካረረ፣ ወዘተ የዛሬዎቹም እንደ በቀደሞቹ የማንተማመን ጎደሎዎች ሆነናል፡፡

“ፈተናችን የሚመነጨውም ከዚሁ የመንፈስ ጎዶሎነት ነው፡፡ ሰሜነኛውም ሆነ ደቡበኛው፣ የሱማሌው ቤት ሆነ የገዳ ቤት፣ ክርስቲያኑም ሆነ እስላሙ፣ ምሁሩም ሆነ ማይሙ፣ ፍም የመሰለው ቀይ ሰውም ሆነ ኑግ የመሰለው ሻንቅላ በተለይ ትንሽ ሥልጣን በቀመሰ ማግሥት  ቶሎ የመካድና በትምክህት የመወጠር አዚም ይጠናበታል እንጂ፣ በዘር ግንድ አመጣጡ ሁሉም የአንድ እናት ልጅ ነው፡፡

“ሰልስቱ ታላላቅ ሴኮች የምላቸው ታላቁ ሳይንቲስትና አንትሮፖሎጂስት ሼክ አንታ ዲዮጵ፣ ታላቁ ባለቅኔ ሼክስፒር፣ ታላቁ ንግርተኛ (Oraculation) ሼክ ሁሴን ጅብሪል በጥልቀት ቢያስተምሩንም እኛ ከትምክህትና ከክህደት አዚም መላቀቅና መገላገል አልቻልንም እንጂ፣ ኢትዮጵያውያንና ሱማሊያዊያን፣ ኪስዋሊሃያዊንና ኤርትራውያን የአንድ እናት ልጆች ነን፡፡”

ለዚህ ጽሑፍ መግቢያ እንደ መንደርደሪያ ይህን ዘለግ ያለ ሐሳብ የወሰድኩት ወድጄ አይደለም፡፡ በመላምት ሳይሆን በአንትሮፖሎጂና በታሪክ ጥናት እንደተረጋጋጠው፣ እንኳንስ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ያለነው ቀርቶ በዙሪያችን (በቀጣናው) ያሉ ሕዝቦችም የኩሽና የሴም ዘር ግንድ ውስጥ የተፈጠሩ መሆናቸውን ለማስታወስ  ነው፡፡ ታዲያ የዘር፣ የማንነትና የቋንቋ ልዩነትን በማራገብ ከተለያየ ባህር እንደተጨለፍን እንቁራሪቶች ስለምን ጩኸትና ጫጫታ እናበዛለን ነው ጥያቄው፡፡

በእርግጥ የአገራችን ሕዝቦች በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በውዝግብና ቁርቁስ ነው ያሳለፉት፡፡ በዚህም ለረዥም ዘመናት ብዙ የሰው ሕይወት፣ የአገር ንብረትና መልካም ገጽታ ወድሟል፡፡ ውዝግቡም በአገር ዕድገት ላይም ደንቃራ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቢያንስ ከዚህ በኋላ ግን የሚያስፈልገን በልዮነት መነታረክና በታሪክ መወናበድ ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝሙን በማጠናከር አብሮነትና ሁለንተናዊ ትብብርን ማሳደግና ፍትሐዊነት አገራችንን መገንባት ሊሆን ይገባል ለማለትም ነው። ምንም ቢሆን ግን በአዲስ ትውልድና በተቀየረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ትናንት በነበረ ትርክት ላይ ተመሥርቶ የተዘራን የተሳሳተ የጥላቻ ፖለቲካ እያጋነኑና እያመነዥኩ፣ ሕዝቦች አብረው የማይኖሩበትን የቂም በቀል ዘር ከውጭ ባላንጣ ወርሶ ማላዘን መቆም አለበት። እንኳንስ የአንድ እናት ልጆች ለሆንነው ለእኛ ይቅርና ለሌውም ዓለም ቢሆን ወቅቱን የዋጀ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ያፋጀን እንደሆን እንጂ የሚያስገኝልን ቅንጣት ጥቅም እንደሌለ እየታወቀ ነው፡፡

 ከሁሉ በላይ “እኔ እበልጥ”፣ “እኔ እበልጥ“ ፉክክርና የእኛና የእነሱ ጨቅጭቁ የለየለት የጥገኝነት መስገብገብ የወለደው ኋላቀርነት እንጂ፣ ሩቅ የሚወስድ መንገድ እንዳልሆነ ግንዛቤ መያዝ አለበት። ትናንት በሴራ ሕዝቦችን ለማቃቃር የተቀነበበን የወሰንና የማንነት ጥያቄ በግብታዊነት እየመዘዙ፣ በሕግና ሥርዓት ከማስተካከል ይልቅ በፀብና በግጭት ለመፍታት መሞከርም ራስን እንደመካድ ነው መቆጠር ያለበት። እናም ክቡር ሎሬት እንዳሉት የተጫነን አዚም አሸንቀጥሮ ስለመጣል ነው መጨነቅ የሚያስፈልገን፡፡

መንግሥትም ሆነ አብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን መጠላለፍና መገፋፋትን ትተው መቀራረብን ማስቀደም ያለባቸው፣ የአንድ እናት ልጆች በመሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ብቸኛው ሥልጡን መፍትሔ መነጋጋርና መቀራራብ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ሁሉም አወዛጋቢ ወይም አከራካሪ ጉዳዮች ከአገርና ከሕግ በታች እንደ መሆናቸው እውነታውን እየተጋፈጡ፣ የሕዝቡን ውሳኔ እያዳመጡ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ነው የሚጠቅመው፣ ከጥፋት የሚያድነውም።

በመሠረቱ ምንም ያህል የሴራ መጠላለፍና የመነጣጣል አዚም ቢበረታ፣ ከቀደሙት ዘመናት የተሻለ ወይም ከአባቶቻችን የላቀ አገር ወዳድነትና አንድነት ለማምጣት ነበር መትጋት ያለብን፡፡ እንደ ሕዝብ ስክነትና ምክንያታዊነት እንዲያብብ፣ ከወደቅንበት አገራዊ መራቆት በመውጣት ቢያንስ አፈርነታችንን ሸፍነን በመደማማጥ ፈተናዎቻችን ለማለፍ መነሳትም ነበረብን፡፡ ቆም ብሎ  ከልብ ምን እናድርግ መባል ያለበትም ለዚሁ ነው፡፡

እንጂማ በውጭ ባላንጣዎቻችን የተሸረቡትን የሃይማኖት አክራሪነትና ፅንፍ የረገጡ የብሔርተኝነት አካሄዶችን በማቀጣጠል፣ የዛገውን አስተሳሳብ በማቀንቀን ከውድቀት መዳን አይቻልም፡፡ እርግጥ ውዝግቦችን እናስወግድ ሲባል በጥንቱ የአንድ እናት ልጆች ታሪካችን ላይ ብቻ ተመሥርተን ሳይሆን፣ በመሀል በተፈጠሩ ሽኩቻዎቻችንና ግጭቶቻችን ላይም ተግባብቶና መጪውን ጊዜ አስታርቆ ሊሆን ይገባል፡፡

     ስለሆነም አገራዊ አንድነትና አብሮነታችንን በማስቀደም፣ የብሔረሰቦችን የየራሳቸው ማንነትና ታሪክ እየገነቡ፣ የየትኛውም መብትና ጥቅም ሳይገፈፍ በአብሮነት ጠንካራ የጋራ አገር በሚገነባበት አኳኋን መሆን ነው ያለበት። ለዚህ ደግሞ አገራዊ የምክክር ምድረኮችን በቅንነትና በአገር ወዳድነት መንፈስ መሳተፍ ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ መንግሥትም ከገባንበት አገራዊ ቀውስ ለመውጣት ከዚህ የበለጠ ዕድል እንደሌለ መረዳት አለበት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሕዝብ ችግሮችን መፍታትም እንዲሁ፡፡

በጥቅሉ አሁን እንደ አገር በተጀመረው ሥርዓትና ሕግ የማስከበር፣ ብሎም አገር አደናቃፊነትን በማረም ሒደቱ ውጤት ሳንኩራራ፣ ከፈተና ማግሥትም በሚገኘውና በተገኘው ድል ሳንሻማ፣ በኅብረ ብሔራዊ አገር ግንባታ ሒደት ላይ ማተኮር የውዴታ ግዴታችን ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ በእኛ አገር መሆን ያለበት ብቻ ሳይሆን፣ እኛን በመሰለ መቋሰል ውስጥ በነበሩት እነ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ወዘተ ጥቅም ላይ የዋለ ነው፡፡

አሁን አገራችን የምትከተለውን ፌደራሊዝም ጉድለቶች መሙላትና ዝንፈቶቹን ማረም ከተቻለ ራስን በራስ ለማስተዳዳር፣ ለመዳኛትና ለመጠበቅ የሚያስችልና ትውልድን በራስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያግዝ፣ የአናሳውንም ሆነ የብዙኃኑን ባህል፣ ታሪክና ማንነት ለማጎልበትና ለማሳደግ የሚረዳ ሥርዓት ነው፡፡ ጠንካራ የአንድነት መስተጋብርን መፍጠር የምንችልበት የአስተዳዳር ሥልት ከሆነም ይበጀናል እንጂ አይጎዳም፡፡ ዘርና ጎሳን ለክልል አጥር ግድግዳና ማገር አድርጎ በሰፊው ዓለም ለመኖር መመኘት ግን ፈፅሞ የሚቻል አይሆንም፡፡ በተጨባጭ እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡

ሥርዓቱ ሌላው ቀርቶ የሃይማኖት፣ የባህልና የማኅበረሰብ ልማዶችን ለይቶ ለማጉላትና ለማሳደግ የሚያመች፣ የታሪክና የቅርስ ፀጋዎችን ለላቀ ጥቅም ለማብቃት የሚያግዝም መሆኑ ላይ ልዩነት የለም፡፡ ሁኔታው ዋስትና ባለው ዴሞክራሲና በጠንካራ ሰላማዊ ጉዞ ከታጀበ ደግሞ የዕድገትና የብልፅግና መሠረት መሆኑም  ተደጋግሞ የተባለ ነው፡፡ ታዲያ ይህን መልካም ጅምር በጠንካራ አብሮነትና አንድነት፣ ብሎም በመደማመጥ ማጠናከር ለምን የሚከብድ ሆነ ነው መባል ያለበት፡፡

ፌደራሊዝሙን አጠናክሮ ለመቀጠልም ሆነ አገራዊ አንድነቱን ለማሳደግ የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን፣ የትኛውም ክልል ማዕከላዊነትን መጠበቅና የራስ ነፃነትን ማፅናት መቻል አለበት፡፡ የዚህ መሠረቱ ደግሞ ሕገ መንግሥትን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ሕግና ሥርዓት ሳይሸራርፉ መተግበር፣ ልማትና ብልፅግናን ለማሳደግ መትጋት ነው፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው በማይበጀው የፉክክርና የእልህ መንገድ ለመንጎድ መሞከርና በሥልጣንም ሆነ በሀብት ቅርምት ውስጥ መመላለስ፣ ከከሰረው መንገድ ሊያወጣን አይችልም፡፡ በሕዝብ ደም ፖለቲካ የመሸቀጡ ቆሻሻ ድርጊትም ሊወገዝ ይገባዋል፡፡

እዚህ ላይ በሁሉም ወገኖች በኩል መታመን ያለበት ቁምነገር፣ ፌደራሊዝም የአብሮነትና የአንድነት ፀረ አለመሆኑ ላይ መግባባትን ማስቀደም ይገባል የሚለው ነው፡፡ ለአብነት ያህል በፌዴራላዚም የዳበረ ሥርዓት ተጠቃሽ የሆነችው ጀርመንን ብንወስድ፣ ከተበታተነ የመሣፍንት አገዛዝ ታላቅ ማዕከላዊ መንግሥት የሚያቋቁም ሕገ መንግሥት የተቀረፀላት እ.ኤ.አ. በ1871 ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን በፊት በአገሪቱ ውስጥ ከ30 በላይ የየራሳቸውን አስተዳደር ዘርግተው የነበሩ የአካባቢ ንጉሦች ነበሩ፡፡ እናም ፌደራሊዝሙ ይህንን የተበታተነ አስተዳደራዊ ሥርዓት ነው በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር የጠቀለለው፡፡ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውሮፓ አገሮች፣ እንዲሁም  እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ፣ ብሎም ህንድና ብራዚልን በመሳሰሉትም ቢሆን እውነቱ ከዚህ ውጪ አልነበረም፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘመናት ከዘለቀው የአሀዳዊ ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዞች በፊትም ሆነ በኋላ የየራሳቸው አስተዳደር፣ ሕዝብና ወሰን ያላቸው ነገሥታትና መሪዎች ያሏቸው ቦታዎች ስብስብ ነበረች፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘመነ መሣፍንትን የመበላላት ክስተት ብንመረምር፣ አንዱ ሌላውን ለማስገበርና ለመጠቅለል ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዷል፡፡ አሀዳዊ ሥርዓት ከ125 ዓመታት ወዲህ ተጠናክሮ የአሁኗን ኢትዮጵያ ቅርፅ አካቶ እንደ አዲስ ሲዋቀርም፣ በኃይልና በጦር በመጨፍለቅ ጭምር መሆኑም ከታሪከ ሊፋቅ አይችልም፡፡ እነዚህ የሥርዓትና የጊዜ ክፍተቶች ግን ምንጩ አንድ የሆነን ሕዝብ ሊለያዩት አይችልም፣ እንዲያውም ክፍተቶቹ ታርመው ሊያጠናክሩት እንጂ፡፡

  በእርግጥ አሁን ባለው የፌደራል ሥርዓት ውስጥ ለመለያየትና ለቁርሾ ፖለቲካ በር የሚከፍተው የታሪክ ዝንፈቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም አብሮ ለዘመናት የኖረው ሕዝብ ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ በዘር፣ በቋንቋና በማንነት የተከፋፋለ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ በተለይ  ክልሎች ቋንቋና ብሔር ተኮር መሆናቸው፣ ‹‹በአስተዳደር የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣንና መዋቅር ያላቸው ክልሎች በጋራ የሰየሙት አንድ ፌዴራላዊ መንግሥት ይኖራቸዋል›› ከሚለውና ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመምጣት ዕሳቤ ጋር የሚጋጭ በመሆኑም ነው፡፡

እንዲያውም አንዳንዱ ክልል ማዕከላዊውን መንግሥት በማዳከም፣ ራሱን የቻለ መንግሥት ለመሆን የሚያደርገው መውተርተር እያስከተለ ያለውን ዳፋ እየተመለከትን ነው፡፡ በተለይ የአስተዳዳር አወቃቀርንም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣንን ለጥቂት ጥገኛ ኃይሎች የመጠቀሙ አባዜ ከሥልጣን፣ ከሀብትና ከመሬት ዕይታ አንፃር በጋራ ማደግና መበልፀግን እንደ ነውር ሲመለከት እየታዘብን ነው፡፡ አካሄዱ ሌላው ይቅርና ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባይተዋር እያደረገው መሆኑንና አገርን ለአደጋ እያጋለጠ መምጣቱን አለመገንዘብ እንዴት ይቻላል?

በእውነቱ እንኳንስ እኛ ለሺሕ ዘመናት ተሳስረን አብረን የኖርነው ሕዝቦች ቀርተን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፈቃዳቸውም ያለ ፈቃድም ወደ አንድ አገረ መንግሥት  የተሰባሰቡ አገሮች እንኳን ከመነጣጠል ይልቅ አብሮነትና የጋራ ህልውናን ነው የሚያስቀድሙት፡፡ ለዚህም ነው ችግሮቻቸውን በመነጋጋርና በመደማመጥ ከመፍታት ባሻገር ለወል ተቋማቶቻቸው መጠናከር ሳያሰልሱ በመሥራት፣ በሠለጠነ መንገድ ወደፊት ለመሄድ የሚረባረቡት፡፡ ይህም በታሪካቸው ላይ ተመሥርቶ፣ ነገንም አማትሮ ለመስፈንጠር የሚረዳቸው ትዕምርት እየሆነ ነው (በእኛ አገር የምዕራብና ደቡብ ምዕራብ፣ እንዲሁም የትግራይ ሁኔታ በጥንቃቄ ታይቶ ሥር ነቀል ለውጥ ካጀበው ፈተናው ቀላል አይሆንም!!)፡፡

ለነገሩ በሁሉም አካባቢ ቢሆን አሁን እየተፈጠረ ያለው የዜጎች የመኖር ዋስትና ማጣት ችግር የሁላችንም ጭንቀት ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በታሪክ አጋጣሚ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተበትነው፣ ተዋልደውና ተጋብተው ኑሯቸውን የመሠረቱ ዜጎችና  ወገኖች፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች በዘርና በእምነታቸው ምክንያት ብቻ የሚጠቁበት ወንጀል በሕግም ሆነ ፖለቲካ አግባብ መስተካከል አለበት፡፡

    በእርግጥም ባለፉት አራት ዓመታት በ“ለውጥ“ ስም በተለያዩ አካባቢዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ላይ ይህን ሁሉ ግፍና ጥፋት እስከ ማድረስ የሚያስጨክነውን በሽታ ለይቶ ማከም ካልተቻለ “የአንድ እናት ልጆች  ነበርን“ በማለት ብቻ የሚድን የለም፡፡ በብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች የሚኖሩ አናሳዎች ይገፋሉ፣ በቂ የሕግ ከለላና የፖለቲካ መብት አጠቃቀም የላቸውም፡፡ ይህንን ዜጎች በገዛ አገራቸው ባዕድ የሚያደርግ ራስ ምታት ማስተካካል ሳይቻል ስለአገር ግንባታ ማውራትም ከንቱ መሸነጋገል መሆኑ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡

       በአገራችን የዘውግ ፌደራሊዝሙ የተዘራበት መንገድ የተንሸዋረረና ሆን ተብሎ ጥቂቶችን በኢፍትሐዊነት ለመጥቀም ተብሎ ነው፡፡  በአገር ላይ ኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመፍጠር  ታስቦ ቢዘጋጅ ኖሮ ከአንድ ሰው ዕድሜ በኋላ ነገሩ ሁሉ ተባብሶ ወደ ብተና ጫፍ ባልደረሰ ነበር፡፡ አገራዊ አንድነትና የሕዝቦችን አብሮነት ዕውን ለማድረግ ሥራ ሲከናወን ነበር ቢባል እንኳን፣ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አለማምጣቱ ዛሬ ምስክር ነው፡፡

በእርግጥ  በዚች አገር የተጀመረው ፌዴራላዊ ሥርዓት በሽታው ዘውግ ተኮር ከመሆኑ የሚመነጭ ነው ብቻ እንዳይባል፣ ክልሎችን ሲያደራጅ ግልጽና የማያሻማ መሥፈርት አለመኖሩም እያደር ራስ ምታት እንደሆነ አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች ተዳፍነው ባደሩ የክልልነት ጥያቄዎች ማየት ይገባል፡፡ የክልልነት መሥፈርቱ በጎሳ ወይም በብሔረሰብ ብቻ ነው እንዳይባል፣ ሁሉንም ብሔረሰቦች በክልል ደረጃ ዕውቅና አለመስጠቱም የሚታይ ነው፡፡ ሁሉንም በ11 ቋቶች ውስጥ ከቷልና፡፡ በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ክልል አይደለም ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ፣ ወይም ወረዳ ለመመሥረት ሕዝብን ቀስቅሶ በራሱ ሀብት ላይ ጥቃት እስከማድረስ መድፈር ተጀምሯል (የደቡብ ምዕራብን ሁኔታ ይመለከቷል!!)፡፡

በአጠቃላይ  የአገራችን ዜጎች ማንነታቸውንም  ሆነ የግል እምነታቸውን ፈቅደውና ወስነው እንዳልመረጡ ይታወቃል፡፡ የዘር ሐረጋቸው ፈጣሪ በቀደደለት ቦይ እየፈሰሰ ነው እዚህ ያደረሳቸው፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ ክፉም ደግም ታሪክ እያለፉ የትውልድ ሽግግር ለመፈጸሙ መጠራጠር አይቻልም፡፡ የዓለም ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የጊዜው መርዘምና፣ የቆጠራው አድካሚነት ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያውያን ሎሬት ፀጋዬ እንዳሉት “የአንድ ቤተሰብ ልጆች“ ናቸው፡፡ ይህም በጥናት ተረጋግጦ ያደረ እውነት ነው፡፡ እናም ተስማምቶና ተከባብሮ ከመኖር ውጪ በመጠቃቃትና በመዋጋት፣ እርስ በርስ በመሳደድና በመገዳደል ምን ሊገኝ ይችል ይሆን? በአንድ እግር ቆመን መልስ ልንፈልግላቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...