Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትግፍና መከራ ምን መክሮ ምን አስተማረን?

ግፍና መከራ ምን መክሮ ምን አስተማረን?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

አገራዊ እውነታችን አስተማሪነቱ ሠልቷል፡፡ የኢትዮጵያን ምድርና ሰማይ ሰሌዳው፣ ያለፍንበትን መከራና ጭንቅ ጠመኔው አድርጎ ፍሬ ትምህርት ጽፎልናል፣ እየጻፈልንም ነው፡፡ ያሳለፍናቸው መከራዎች ብዙ መክረውናል፡፡ ይህ የእውነታችን ጽሑፍ አልታየውና አልነበብ ያለው ካለ ላግዘው፡፡ እነሆ!

የጎጆ ብሔርተኝነት ባለብዙ አዘቅት ነው፡፡ በደል ከነበረ ነበር ብሎ ማለት፣ በደል እየተካሄደ ካለ አለ ብሎ ማጋለጥ፣ ካለፈም በኋላ መዝግቦ ማስታወስ ጤናማ ነው፡፡ አውሮፓውያን ስለናዚዎች ፍጅት በየቀኑ ቢያወሱ፣ ኢትዮጵያውያን ስለፋሺስት ጣሊያን ፍጅት በየቀኑ ብናወራ የጤና አይሆንም፡፡ የአሜሪካ ጥቁሮች በጥቁሮች ላይ ስለሚፈጸም በደል ከጊዜ ጊዜ የሚያወሩት፣ የበደል ድርጊቱ ከጊዜ ጊዜ ስለሚፈጸም ነው፡፡ በደልን ማጋለጥ ለመፍትሔ ያግዛል፡፡ ማጋለጥ በራሱ ግን መፍትሔ አይሆንም፡፡ የነጭ ዘረኝነትን ጥቃት በጥቁር ዘረኝነት ልመክትህ ማለት መፍትሔ አይሆንም፡፡ ቀይ ህንዶች፣ ጥቁሮች፣ ሂስፓኒኮችና ሌሎች በደል ቀማሾች የየራሳችንን ዘረኝነት አዳብረንና አስተባብረን በነጭ ዘረኝነት ላይ እንነሳ ቢሉም፣ ጉዟቸው ጥላቻን በጥላቻ በደልን በበደል ለማሸነፍ የሚከጅል ነውና ቅራኔን አብሶ ይበልጥ ለመጠቃት ያጋልጣል፡፡ ጥቁሮች በአሜሪካ ውስጥ የጥቁር ክልል ቢጠይቁና ቢፈቀድላቸው በዚያ መንገድ የነጭ ዘረኝነትን ማሸነፍ አይችሉም፡፡ መፍትሔው ዘረኛ አድሏዊነትን የሻረ የእኩልነት ሥርዓት ማንገሥ ነው፡፡ ይህ መፍትሔ ደግሞ በጥቁሮች ጥረት ብቻ የማይገኝ የሁሉንም አሜሪካዊ ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡

በኢትዮጵያም በጎጆ ብሔርተኛነት ዕይታና ቡድድን ተከፋፍሎ ለበደሎች መፍትሔ አመጣለሁ ማለት መንገድ መሳት መሆኑ በማያደናግር ሁኔታ ታይቷል፡፡ በጎጆ ብሔርተኛነት የተከፋፈለ ዕይታና ቡድድን፣ የኢትዮጵያ ዝንጉርጉር ኅብረተሰብ አንድ ላይ ከመንቀሳቀስ የሚገኝ የትግል ኃይልን እንዳያገኝ ሲያውክ (ኃይል እየበተነ ለገዥዎች ጥቃት ሲያጋጥም) ኖሯል፡፡ ‹‹ብሔራዊ ክልል›› የሚል ሽንሻኖ ከብሔር ጭቆና እንደማይገላገል፣ እንዲያውም እንደሚያባዛ ማየት ከቻልን 30 ዓመታት ሞላን፡፡ መገንጠልም መፍትሔ እንዳልሆነ ከተገነጠሉ ልምድ እያየን ነው፡፡ የ1983 ዓ.ም. የግንቦት ‹‹ድል›› ያስከተለው በየብሔር ቡድን ተቧድኖ የአካባቢ ገዥ መሆን ራሱን የብሔር ጭቆናንና ምዝበራን አባዛ እንጂ አላስወገደም፡፡ የሕወሓት ዋና ገዥነት የትግራይ ሕዝብ ገዥነት እንዳልነበረ ሁሉ፣ አካባቢያዊ ብሔርተኛ ቡድኖች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ ወዘተ. ስለነገሡ ለየአካባቢው ‹‹ባለቤት›› የተባሉ ሕዝቦች ከጭቆናና ከምዝበራ አልተገላገሉም፡፡ በየብሔር/ጎጥ ቡድድን ሲካሄዱ የቆዩ የንግድ እሽቅድምድሞችም፣ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያላትም ጠንቅ ያረገዙና የረጩ የቡድኖች ሩጫዎች ናቸው፡፡ ያመነጩትም ‹‹ክልሌ ገብተህ ዘረፍከኝ! የብሔሬ ድርጅት ካልሆንክ ባዕድ ነህ…›› የሚሉ አድማዎችና ጥቃቶች ሁሉ ይህንኑ ጠቋሚ ናቸው፡፡

በኢትዮ ኤርትራ የ1991 እና 1992 ዓ.ም. ጦርነት ጊዜ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎቹን እንዲያሳስቅ ያደረገው፣ ‹‹ድል›› ተገኝቶ በ1992 ዓ.ም. ግንቦት ምርጫ ጊዜ ደግሞ ፊት ነስቷቸው ‹‹ፀረ ሰላሞች… ከቻላችሁ በምርጫ አሸንፉኝ›› እንዲል ያደረገው፣ የኢትዮጵያና የትግራይ ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የቡድኑ ዱርያዊ ሥልጣን ወዳድነት ነበር፡፡ ሃድያ ላይ፣ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ጭፍሮችን እምቢኝ ብሎ ሕዝብ ሌሎችን (ያመናቸውን) በመረጠ ጊዜ፣ አገዛዙ ወደ ድቆሳ መዞሩም የቡድኑ የሥልጣን ውጦሽ አንዲት ቀዳዳ መስጠት የማይሻ መሆኑን ከማሳየት በቀር ለሃድያ ሕዝብ ጥቅም ከማሰብ ጋር አንዳችም ግንኙነት አልነበረውም፡፡ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ከኢሕአዴግ ውስጥ በድምፅ ብልጫ የተሰየመው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከፓርላማዊ ሹመቱ አንስቶ የሕዝብ ድጋፍ እንዴት እንደሚታፈስ ባወቀ አካሄዱ ሰውዬው አሻንጉሊታቸው እንደማይሆን የሕወሓት ቁንጮች ሲገባቸው፣ ከሶማሌ ክልል አንስቶ እስከ ትግራይ ድረስ በተነጣጠረ ትልም ኢትዮጵያን ወደ ማፈራረስ መዞራቸው፣ የበቀል ጥማታቸውን ከማርካት በቀር ለየትኛውም ሕዝብ (የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ) ሰላምና ደኅንነት ደንታ የሌላቸው መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

በጥቅሉ በብሔርተኛ የተደራጀ ገዥነትን ይዞ የሚመጣና ገዥነቱን የጭቆና ‹‹መፍትሔ›› አድርጎ የሚያቀርብ ብሔርተኝነት፣ ቀጣፊ የቡድን ሩጫ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ሥልጣን ላይ ቢወጣም ጨቋኝነትና መዝባሪነት ውስጥ መርመጥመጡ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በአግላይ አተያዩና አደረጃጀቱ ውስጥ የአድሎና የበቀል አስኳል አለበት፡፡ የዴሞክራሲና የእኩልነት አማጭና ገንቢ ለመሆን የማያስችለውም ይኸው ባህሪ ነው፡፡ ቁልጭ ብሎ ከሚታይ ልምድ ትምህርት መውሰድ ያልፈቀዱ፣ በደል ሊባል የሚችል ነገር እየፈለጉ ከማላዘንና የሕዝብ ስሜትን ከመንዘር በቀር ምንም ነገር የሌላቸው፣ ወይም ብሔርተኛ ባለይዞታነትንም ሆነ መነጠልን መፍትሔ አድርጎ ማቅረብን ሙጥኝ ያሉ ብሔርተኞች፣ ማጠፊያ ሲያጥራቸው ማታለያ እየፈበረኩ ራሳቸውንም አለንልህ የሚሉትንም ማኅበረሰብ ሊያነክት የሚችል ጥላቻና በቀል ወደ ማደራጀት አዘቅት ማሽቆልቆል አይቀርላቸውም፡፡ የመሰከርነውም፣ የምንመሰክረውም ይህንኑ ነው፡፡

የትኛውም የጎጆ ብሔርተኛነት ቤቱን የሚሠራው የበደል ታሪክን ለጥላቻና ለቁርሾ እንዲመች አድርጎ በማጣመም፣ በማጋነንና ስሜትን በማንቀርቀብ ላይ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በአማራነት ውስጥ በተፈጠረው ብሔርተኛነት ውስጥ የቅርብ በደልን ማውሳት አንሶበት በረዥም ታሪክ ውስጥ አማራ በሰፋሪ ቅኝ የመያዝ፣ የመመናመንና ከመኖሪያው የመገፋት በደል ደርሶበታል የሚል ወፈፌነትም ብቅ ብሏል (ከ‹አብን› ውጪ)፡፡ በአዲስ በቀሉ ብሔርተኝነት ውስጥ ይህንን ካየን መማር እምቢኝ ያሉና የበደል ታሪክ ያረጀባቸው የቆዩ ብሔርተኞች ‹‹አምባገነንነት! ፋሺዝም ተቋቋመላችሁ! ብሔረሰቦችን ጨፍላቂ ሥርዓት መጣላችሁ!…›› በማለት መዳከራቸው በጣም ትንሹ ገመናቸው ነው፡፡ በሐሳብ መርታት የቸገረው ብዙ ነገር ያደርጋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደንን ‹‹ማርክሲስቱ! ኮሙዩኒስቱ! ግራ ክንፉ!›› በሚል ማስፈራሪያና ስም ልጠፋ ባዶነቱን ሊሞላ ሲፋጭር እንደነበረው ብሔርተኞችም ይፋጭራሉ፡፡ በስም ልጠፋ ማጭበርበርና ሕዝብን በስሜት አውሮ መጋለብ አልሠራ ሲል፣ ጥላቻንና ቂምን ሲያመነዥክ የኖረና ቡድናዊ ጥማትን በማርካት የተዋጠ ብሔርተኝነት ወደ ጭራቅነት እንደሚቀየር ለመገንዘብ፣ ኦነጋዊና ሕወሓታዊ ፅንፈኞች ከሌሎች ሎሌዎቻቸው ጋር ከኦሮሚያ እስከ ትግራይ ድረስ ያካሄዷቸው በጭካኔ የናጠጡ ጭፍጨፋዎች ምርጥ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

በጎጆ ባለቤትነት ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝት ከነፃነት ጉዞ ያሰናክላል፡፡ የብሔርተኛ ቡድኖች ገዥነት የበዳይነት ባህሪን ለማሳየት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ግፈኛ ጭካኔዎችም የተከሳሰቱት ገና በጧቱ ነበር፡፡ በአርሲ፣ በሐረርጌ፣ በወለጋ፣ በጋምቤላ፣ ወዘተ…፡፡ ለምን ግን ሕዝብ በቶሎ መንቃትና የብሔርተኛ ቡድኖች ገዥነትን መትፋት ተሳነው? ብሔርተኝነት፣ ‹‹ከየትኞቹም የማንነቴ ገጾች የብሔር ማንነቴ ይበልጣል (ከሁሉም በፊት የምታመነውና የማገለግለው ብሔሬን ነው)›› በሚል አስተሳሰብ አዕምሮን ያሟሻል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ አገር ልጅነት ውስጥ ያለ ብሔረ-ብዙ ግለሰብነት ተበጥብጧል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ የብሔር ናሙና ተደርጎ እንዲታይ ሆኗል፡፡ ከግለሰቦች ጋር ስንገናኝ የሚመጣብን ጥያቄ እንደ ግለሰብ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? የሚል ከመሆን ፈንታ የየትኛው ብሔር/ብሔረሰብ አባል ናቸው? የሚል እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከግለሰቦች ጋር የሚኖረን የመቀራረብም ሆነ የመራራቅ ዝንባሌ፣ አስተሳሰብና ፀባይ/ልማዳቸው ይስማማኛል ወይ? በሚል ግምገማ ከመለካት ፈንታ፣ በብሔር ታርጋቸው ወደ መለካት ዞሯል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ ስለመገኛ ብሔረሰቡ ለፈጠርነው ምሥል ወኪል ወይም ተሸካሚ ሆኖ ነው የሚታየን፡፡

በሌላ ገጽ የነገሥታትን የዘር ሐረግም ሆነ ጎጣዊ/ብሔረሰባዊ መገኛቸውን መጋራት፣ ነጋሢነታቸውንም መጋራት ሆኖ ኩራት ኩራት የሚላቸው፣ ከኑሮ ከልታማታነት ባሻገር የባዶ ኩራት እስረኝነት የሚደቁሳቸው ሰዎች አሉ፡፡ በሥልጣን ላይ በወጣም ሆነ ባልወጣ ብሔርተኝነት ዘንድም በዳዬ ተብሎ በተጠመደ ብሔር አባላት ላይ ጥቃት/በደል መሰንዘርን እንደ በደል ካሳ አድርጎ የማየት (የአካባቢ ባለቤትነትን መብት ማስመስከርያ አድርጎ የመውሰድ) ካቴና አለ፡፡ ብሔርተኝነት በይፋ ተናገረውም አልተናገረው “በዳይ” የተባለን ብሔር አባላት መበደልን የጭቆና ቁስልን እንደ ማሻሪያና ሒሳብን የማወራረጃ መብት አድርጎ ይገለገልበታል፣ ያጭበረብርበታል፡፡ የብሔር ቡድኖች የየብሔራቸውን ሕዝብ በገዥነት ስለተፈናጠጡ ብሔሮቹ የገዛ ወኪሎቻቸውን እንዳገኙ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን እንደተቀዳጁ አድርጎ ጎጆ ብሔርተኝነት ዓይንን ይጋርዳል፡፡ የብሔር ሕዝብና ከእዚያ የበቀለው ቡድን የማይነጣጠሉ (የቡድኑ መነቀፍ የብሔሩ መነቀፍ፣ የቡድኑ መወንጀልና መታሰርም በብሔሩ ላይ የሚካሄድ ጥቃት) ተደርጎ እንዲታይ አድርጎ አዕምሮን ያሳስታል፡፡ እናም ቡድኖችን በቡድንነታቸው፣ ግለሰቦችን በግለሰብነታቸው ወስዶ ለሠሩት ነገር መጠየቃቸውን ከማየትና ከመቀበል ፈንታ፣ ምንም ያድርጉ የብሔር ከረጢታቸውን መሠረት አድርጎ ለእነሱ ተገን መሆን (ጥቃታቸውን ጥቃቴ ማለት) የብሔር ግዴታ ሆኖ ያርፋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ ስሜት ላይ የሚያደራው በጥላቻ የተሞላ ቂምና በቀል አዕምሮን በማወር ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡

  የባለቤትነትና የባይተዋርነት መንታ ጥጎች ብቻ በሚታዩት የአስተሳሰብ ሽክርክሪት ውስጥ የሰመጠ ሰው፣ ሁለት ሦስት ዲግሪ የተሸከመ የሕግና የታሪክ ሰው ቢሆንም እንኳ፣ በመንታዊ (ባይነሪ) አመለካከቱ ታጥሮና ሚዛኑን አጥቶ ከእውነትና ከእውነታ ጋር ሊጣላ እንደሚችል የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች ልምዶቻችን በደንብ አሳይተውናል፡፡ እንዲህ ያለ በሽታ ወይም ልክፍት ውስጥ የገባ ሰው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 100 መሠረትና በተዛማጅ የዓለም አቀፋዊ ሲቪል ሰርቪስ ሕግና ደንቦች መሠረት፣ ተግባሬን ሳከናውን ከተቋሙ ውጪ ያለ የማንንም የመንግሥትም ሆነ የሌላ ቡድን ትዕዛዝና መመርያ በጭራሽ አልሻም፣ አልቀበልምም እያለ የመሃላ ቃል እየፈጸመ፣ እየማለና እየተገዘተ ወዲያውኑና እዚያውኑ የፓርቲ ትዕዛዝ ሲፈጽምና ሲያጽፈጽም ለማየት በቅተናል፡፡ በአጭሩ፣ የጨቆነኝን በጭቆና ልበቀለው ማለት ጭቆናን መርታት ሳይሆን ጨቋኝነት ውስጥ መንደባለል ነው፡፡ የብሔር ወገን ለሆነ ሰው/ቡድን ምንም ቢሠራና ቢያጠፉ በተገንነት መቆምን የብሔር ኃላፊነት፣ ይህንን አለማድረግ ብሔርን መካድ የሚል አመለካከት ውስጥ መኖርም የጨቋኞችና የመዝባሪዎች መጫወቻ መሆን ነው፡፡ ለጭቆና መጫወቻነት የሚዳርጉት ሁለቱም ወጥመዶች በጎጆ ብሔርተኝነት ውስጥ አሉ፡፡ ብሔርተኝነት ውስጥ ሆኖ ሁለቱን ወጥመዶች ማስተዋልና መጠንቀቅም በጣም ከባድ ነው፡፡ የጎጆ ብሔርተኝነት ይዞታዬ የሚለውን ምድር ለመቆጣጠር ሲታገል ወይም ተቆጣጥሮ ለመግዛት ዕድል ሲያገኝ፣ ሁለቱም ወጥመዶች አፋቸውን ከፍተው ሥራቸውን መሥራት ይጀምራሉ፡፡ በተለይ በገዥነት ጊዜ፣ ከፓርቲ እስከ መስተዳድር አመራር፣ ከፖሊስ እስከ ፍትሕ አውታራት ድረስ “ባለቤት” ብሔረሰብን በመጥቀም ሽፋን በደልና አድሎኛነት ሕጋዊ እስከ መምሰል ሊደርስ ይችላል፡፡ የመወራረስ/የመዛነቅ ሰነድ የሆኑ የማኅበረሰብ ገጽታዎችን የጎጆ ብሔርተኝነት እንደ ጥራት ብልሽት ያያልና ያንን ለማስወገድ በተለያየ ሥልት እያስደነበሩ/እያስመረሩ ማባረር፣ ዝንቅ ማንነትን “የጠራ” በሚባለው ባህልና ቋንቋ እየቀረፁ የማጥፋት ሥራ ሁሉ ሊያካሂድ ይችላል፡፡ ከዚህ አኳያ ጎጆኛ ብሔርተኝነት በአፍ “ብዝኃነት/ልዩ ልዩነት ውበት ነው!” እያለ ይጩህ እንጂ፣ ዝንጉርጉርነትን ውበቴ ብሎ በእኩልነት ማስተናገድ የማይችል ነው፡፡

 የአገረ ኢትዮጵያና የብሔረሰቦቿ የማንነት ሥሪት በብዙ ፈርጆች የተወሰወሰ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል በሁሉም ብሔረሰቦች ማኅበረሰባዊና ባህላዊ አስተናነፅ ታሪክ ውስጥ፣ የልዩ ልዩ ሕዝቦች ከቦታ ቦታ መነቃነቅና መወራረስ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ዛሬ በሚታዩ የብሔር/ብሔረሰብ ገጽታዎች ውስጥ ወደ ሦስት ሊጠቃለሉ የሚችሉ እውነታዎችን እናገኛለን፡፡ ቅሪቶች ቡራቡሬነት ፈጥረው ልናይ እንችላለን፡፡ ማኅበረሰቦች ከማኅበረሰቦች ጋር በተላላሱባቸው ሥፍራዎች ዲቃላ ገጽታዎች እናገኛለን፡፡ በከተሜነት ዕድገት ውስጥ ደግሞ፣ ውጥንቅጥነት ድምቀት እያገኘ መምጣቱንና ወደፊትም እንደሚገዝፍ እናያለን፡፡ ከእነዚህ ባህሪያት ጋር የተሰናሰለው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሥፍራ አያያዝ የተከተረ አለመሆን፣ የብሔረሰቦች ብርካቴ፣ ብሔረሰባዊ መጠናቸው ከትልቅ እስከ ሚጢጢዎች የሰፋ መሆኑ፣ የሥፍራ አያያዛቸው ከማኅበረሰባዊ ጥቅጥቃት ጋር የተሳላ አለመሆኑ፣ እንዲሁም ማኅበረሰቦች በልማት አቅም የተቀራረቡ አለመሆናቸው አንድ ላይ ተደምሮ ህልውናቸው፣ ግስጋሴያቸውና ሰላማቸው አንድ ላይ ድህነትን ከመታገል ጋር መሆኑን የሚናገር ነው፡፡

ይህንን የህልውና እውነታ መላ ኅብረተሰባችን በቅጡ መተማመኛው አድርጎ አንድ ላይ እንዳይተምም፣ ዛሬ በዋናነት እያወከ የሚገኘው የጎጆ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ከመነጠል በመለስ መላ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ በየሠፈር ባለቤትና ባይተዋር እያሉ በማሸካከር ሰላምንና አብሮ መሥራትን ምን ያህል ሲነሳ እንደቆየ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስታዋሽ አያሻውም፡፡ ምክንያቱም የጎጆ ብሔርተኛነት ከፋፋይነት ገና ከሥራ ውጪ ስላልሆነ፣ ለአገር ልጅነት ከመታመን ይበልጥ ለብሔር መታመን የአገር ልጅነትን በቀፎው የማስቀረት ያህል ቦርቡሯል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ብዙ ዜግነቶች ያሉ ያስመሰለ ብልሽት ፈጥሯል፡፡ “የአገር ልጅነት የዜግነት ማመልከቻ አስገብቶ በየትም አገር ሊገኝ የሚችል (ካርድ የመያዝ) ጉዳይ ነው፣ የብሔር ማንነት ግን አብሮ የተፈጠረ ነው፣ በተቀዳሚነት ለብሔር ማድላትና መሥራትም ተፈጥሯዊ ነው፤” ብለው በአደባባይ (በሚዲያ ጭምር) በኢትዮጵያ ምድር መቀስቀስም ተችሏል፡፡ የዚህ ዓይነት ደንቆሮ አመለካከት የአንድ “ክልል” ርዕዮተ ዓለም ሆነ ማለት አብሮ እየተመሙ ለመልማት የሚያስችሉ ድሮችን መበጣጠስ (ሳይነጠሉ መነጠልን ማከናወን) ነው፡፡ እዚህ ክንዋኔ ውስጥ ከተገባ ደግሞ ክንዋኔውን ይፋዊ አድርጎ ለማጠናቀቅ በሐሳብ ያፈነገጠ የገዛ ብሔር አባልን እንደ ከሃዲ ባንዳ የጠመደ፣ ማኅበራዊ ዝምድናና መተሳሰብን ሁሉ ትቢያ ያስገባና ለማንም ሰላምና ዕፎይታን የማያመጣ (የተለፋበትን ግንባታ ሁሉ ለዶጋ አመድነት የሚያጋልጥ) ወፈፌ ጥፋት ሊፈጸም ይችላል፡፡

እርግጥ ነው አንድ ግለሰብ ከጊዜ በኋላ የሆነ አገር አባል መሆን ሲሻ፣ ጉዳዩ ዜግነት ጠይቆ የማግኘት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በአንድ አገር ማኅበራዊ ማህፀን ውስጥ ባለ ባህልና ሥነ ልቦና ተኮትኩቶ ለተቀረፀ ግለሰብ ግን የአገር ልጅነቱ ከዜግነት ካርድ የትናየት የላቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አገርነት ከነመላ ኅብረተሰቡ የተገነባውም፣ በረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ  በተለያዩ ምክንያቶች የማኅበረሰቦች መታመስና መፈላለስ፣ መዳበልና መገፋፋት፣ መለዋወስና መወላለድ፣ ከብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት ወደ አንድ የጋራ ቋንቋ ተናጋሪነት፣ ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት ወደ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት መሸጋገር፣ ወዘተ. ሁሉ ባለበት አዝግሞት ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ግንባታ አዝግሞታዊ ሒደትም በመሠረቱ ከዚህ ዓይነቱ የአገር አገነባብ የተለየ አይደለም፡፡ ለእኛ ፅንፈኛ ጎጆኞች ግን ይህንን መረዳትና ማገናዘብ ከባድ ነገር ሆኖባቸዋል፡፡

የጎጆ ብሔርተኛነት ዳፋ በጎጆኛነት ላልተቀየደ ሰውም ይተርፋል፡፡ ኢትዮጵያ በረሃብ ቸነፈር በተመታችበት 1965/1966 ዓ.ም. እና ከዚያም በኋላ በተከታተለ የረሃብ ጥቃት ረሃብና ልመና የኢትዮጵያ መታወቂያ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት በየትም ዓለም ጥግ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በተናገሩ ቁጥር የረሃባቸው ነገር ይነሳባቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በረሃብና በልመና ከመታወቅ የሚያላቅቅ ለውጥ ባለማምጣታቸውም፣ የኢትዮጵያ መታወቂያ የሆነው ገመና በየደረሱበት እየተከተለ ሲያሳቅቃቸው ኖሯል፡፡ በብሔር የተቧደነ ትግልና ገዥነትም መሰል ዳፋ አለው፡፡ ጎጥን/ብሔርን መሠረት ያደረገ ቡድንና የፖለቲካ ትግል እስከ ተፈጠረ ድረስ አብረው ሁለት ነገሮች ይመጣሉ፡፡ የጎጥ/የብሔር ቡድን ጎጥና ብሔሩን መሠረት አድርጎ አባልና ደጋፊ የማባዛት ሥራ መሥራቱ አይቀርም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለ ኃይል ብሔርተኛ/ጎጠኛ ተቃዋሚ ሲገጥመው አባሎቹና ደጋፊዎቹ እነ ማን ይሆኑ በማለት የተቃውሞ ቆዳ የሆነውን ጎጥና ብሔር በጥርጣሬ ማየትና መበርበሩም አይቀርም፡፡ ደርግ በጊዜው ገንጣይ አስገንጣይ እያለ እንደ ኃይል ሚዛን መቅለልና መክበድ የኤርትራ ልጆችን፣ የትግራይ ልጆችንም ሆነ ኦሮሞን በጥያቄ ምልክት ውስጥ አስገብቶ ሲበረብር የመቆየቱ ጉዳይ ከደርግ ክፋት የመጣ ሳይሆን የኤርትራ ተወላጅነትን፣ የትግራይ ልጅነትንና ኦሮሞነትን መሠረት ካደረገ ትግል ጋር ተያይዞ የመጣ ነበር፡፡

በ1983 ዓ.ም. ግንቦት ደርግ ወድቆ ሕወሓት የኢትዮጵያን መንበረ-ሥልጣን ተቆጣጥሮ ጌታ ገዥ ሲሆን፣ በትግራዊነት በመሰባሰቡና የመግዣ አውታራቱን በተገዳላዮቹ በማቅለሙ ምክንያት አብሮም ዕብሪቱና የፖለቲካ ብልሹነቱም ገና በጧቱ የተጀመረ በመሆኑ፣ ቅሬታ የገባቸው ትግራዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ከትግራዊ ወገኖቻቸው ጋር የልባቸውን ለማውራት እንኳ መፍራት የጀመሩት (የሕወሓት አባላት ቢሆኑና መረጃ ቢሰጡብኝስ በሚል ጥርጣሬ) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡

በየብሔር ከመቦዳደን ጋር ሰዎችን በየብሔረሰብ ጎተራቸው ያጓተረ አመለካከት እየተስፋፋ፣ የፓርቲ አባላትን በየብሔር መስመር እያደራጀ ሄዶ በሕወሓት ዋና ዕልቅና ሥር አካባቢያዊ ገዥነቶች ሲዘረጉ፣ ሕወሓቶች ትግራዊ ቆዳን ለበላይ ገዥነት በመጠቀማቸው ምክንያት የበደል ዕዳቸው ለትግራዊነት በአሉታዊ ስሜት መታየትን እንደጎተተ ሁሉ፣ በዚያው ዓይነት ለአካባቢ ገዥነት ቆዳ የሆኑ የብሔረሰቦች ማንነቶች ሁሉ የቅሬታ ማረፊያ ሆነዋል፡፡ በአጠቃላይም በጥርጣሬና በቅያሜዎች መከፋፈል በየክልሉ ሁሉ ሊባዛ ችሏል፡፡ በየክልል “ባለቤትነት” ቆዳ ውስጥ ወደሚታይ ገዥነት ውስጥ ገባ ስንል ደግሞ፣ በሥልጣንና በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ድርሻ ተበለጥኩ/ተገለልኩ የሚሉ ጎጥና ማኅበረሰብ ነክ ሽኩቻዎችን ሁሉም ክልሎች ውስጥ እናገኛለን፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ደግሞ በባሰ ደረጃ “ትግራዋዊ” የሚል አንድ ብሔርነትን የመቅረፅ ምህንድስና ባለበት ትግራይ ውስጥ፣ ምርኮኛ ማኅበረሰብ ያለ የሚያስመስል አያያዝ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የወልቃይት ጠገዴና የራያ ብሶት ዋና ምንጭ ያለ ይሁንታቸው ወደ ትግራይ መካተታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በትግራይ አካልነት ውስጥ ፍትሐዊ ልማት አለማግኘታቸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር አለመታመናቸው፣ በቋንቋዎቻቸው ለመጠቀም/ለመማር ነፃ አለመሆናቸው፣ ባህሌ፣ ማንነቴ ያሉትን በድፍጠጣ ለማጠብ መደፈሩና ይህንን እምቢኝ ሲሉ የከፋ ድቆሳ መፈጸሙ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በትግራይ ክልል ውስጥ ሲተዳደሩ የነበሩ ራያዎችንና ወልቃይቴዎችን ልብ የማሸፈቱ ሙሉ ተጠያቂነት የሕወሓቶች አስተዳደር ነበር፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የአገዛዝ ፖለቲካው በየብሔር መስመር እንደ መሄዱም፣ ሁሉም ብሔርተኛ ገዥ የራሱን ብሔር ከሌላው ይበልጥ ለእሱ የሚቀርብና የሚታመን አድርጎ መመልከቱ፣ በዚያው ዓይነት ሕወሓቶች ከሌላው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ይበልጥ ትግራዊነትን የበለጠ ታማኛቸውና አለኝታቸው አድርገው ማየታቸው በኢትዮጵያ ላይ የተነጠፈ እውነታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ብሔርተኛ የአዕምሮ ሙሽትና አገዛዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የሳለው ሥዕል ይህንን መሳይ ነው፡፡

የሕወሓት ቁንጮዎች ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ዘወር ሲሉ፣ ለአንዳንዶቻችን ቀድሞ አልተገለጠልንም እንጂ በአዲስ አበባው ጠቅላይ ቢሯቸው ውስጥ የማይጥማቸው ሰው ከመግባቱ በቀር፣ የሥልጣን አውታሩ ከሞላ ጎደል ከእነሱ እጅ ባለመውጣቱ ከመቀሌ ሆነው ብዙ ነገር መዘወር ይቻላቸው ነበር፡፡ የሚቻላቸውን ያደርጉ እንደነበር ፍንጭ ሰጪ መረጃዎችና ሐሜቶች የነበሩ ቢሆንም፣ ብዙ ነገር የተገለጠው በኋላ (በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አማካይነት) ኅዳር 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ እነሱ በይፋ ከመቀሌ ሆነው ያካሂዱ የነበረው ሽፍንፍን ደባና የማናለብኝ ዕብሪት የፈለገውን ያህል አንጀት ቢያሳርርም፣ በእነሱ ፍላጎትና ፖለቲካዊ ባህሪ ትግራዊ ሁሉ እንዲታይ ለማድረግ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ አንድነት ጎን የቆመ ትግራዊ ትግል አንገቱን ቀና አድርጎና ከበፊት የተሻለ አንደበት አውጥቶ፣ የሕወሓቶችን ከፋፋይ ሸር መቃረን ይዞ ነበርና በሕወሓቶች ነገረ ሥራ ትግራዊነትን የመመዘን ጅምለኛነት የመክሳት ቁልቁለት ጀምሮ ነበር፡፡

በጊዜው የተኳሻነቱንና የአማሽነቱን የፊት ለፊት ሚና ይዞ የነበረው ኦነጋዊ ፅንፈኝነት እንደ መሆኑም፣ ዋናው አደጋና ግብግብ የኦሮሞ ፅንፈኞችን የሚመለከት መስሎ ነበር፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ መንግሥት ጠንካራ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ባለመቻላቸውም የኦሮሞ ፅንፈኞች አጀንዳ ሥውር አስፈጻሚ ሆነዋል፣ ወይም ፅንፈኞቹ እየቦረቦሩ አሽመድምደዋቸዋል የሚል ሐሜት በሰፊ ተረጭቶ ነበር፡፡ ፅንፈኞቹ በኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞ ባልሆኑ ላይ ያካሄዷቸው ጨካኝ ጥቃቶች (በሰኔ 20ዎች 2012 ዓ.ም. ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊትና በኋላ) ነውራቸውን ኦሮሞነት ላይ ያላክካሉና ድርጊቱን የሚፀየፉ ኦሮሞዎች ማፈርና መሳቀቅ አይቀርላቸውም፡፡ መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ፣ የፅንፈኞቹን የዳርና የመሀል ዘግናኝ አተራማሽነት ከሥራ ውጪ ለማድረግ አምርሮ በተንቀሳቀሰ ጊዜም፣ ጥፋተኛውን ከደህነኛው እየለዩ በመያዝና በማደን ተግባር ኦሮሞ መበራየቱ አይቀሬ ነበር፡፡

ሕወሓቶች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜን ዕዝን የማጥቃትና መሣሪያውን የመቆጣጠር ዕርምጃ ካደረጉ ጊዜ አንስቶ፣ ለኢትዮጵያ ህልውና ዋና አደገኝነታቸው ደረቱን ገልብጦ ፊት ለፊት መጣ፡፡ የእነሱ እንቅስቃሴ የቀውስ ሁሉ ዋና ማዕከልና ማስተናበሪያ ሆኖ ወጣ፡፡ ያን ጊዜ ላመንታ/ትንሽ ጊዜ ልውሰድ ሊባል የሚቻልበት ፋታ አልነበረም፡፡ እጅግ ፈጥኖ በፅንፈኞች እጅ የገባውን የትጥቅና የስንቅ ክምችት አገር ማጥቂያ እንዳይሆን የማኮላሸት፣ ለተጠቃው የወገን ኃይል ፈጥኖ የመድረስ፣ በፌዴራሉ የሥልጣን ማዕከል ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ ነውጥ የማቀጣጠል ዕድልን የማምከን፣ ጥቃት ፈጻሚዎች የሸሪክ ዕገዛ እንዳያገኙ የማድረግ ፈጣን እንቅስቃሴ ማካሄድ የሞት ሽረት ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የአየር ጥቃቱ፣ የምድር ከበባው፣ ሽሽግ የጥፋት መዋቅርን በነባርና በአዲስ መረጃ መበጣጠስ፣ እንደ ኦነግ-ሸኔ ባሉ የቃታና የፅንፍ ባልንጀሮቻቸው ላይ የምንጣሮ ዘመቻ አዳብሎ መክፈት ሁሉ ተገቢ ነበር፡፡ በጊዜው የተካሄዱ ፍተሻዎችና ለቀማዎች ከዚህ አገርና ሕዝብን የማዳን አጣዳፊ ተግባር አኳያ ነው መመዘን ያለባቸው፡፡

የብሔር ፖለቲካ ቡድኖች የድርጅትና የድጋፍ መረባቸውን የሚሠሩት የብሔር መስመርን ተከትለው መሆኑ እየታወቀ፣ ፅንፈኛ ብሔርተኞቹ አገር ለማፍረስ በተነቃነቁበት ሰዓት መንግሥት የደባ መረባቸውን ለመበታተን ብሔር ጠለቅ አሰሳ ባያደርግ ነፈዝነት ይሆንበት ነበር፡፡ በሰሜን ዕዝ ላይ የተካሄደው ጥቃት ከአዲስ አበባ እስከ ሰሜን ዕዝ በሕወሓታዊ የውስጥ ከሃዲዎች የተቀናበረና የተካሄደ ስለመሆኑ በኋላ የተገለጠው መረጃ አሳይቷል፡፡ በአሰሳም ከግለሰብ ቤት አንስቶ በግልና በፓርቲ ንግድ ተቋማት ውስጥ ጭምር የተገኘው የመሣሪያ ብዛት ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥርጠራና አሰሳ ባይወደድም ግድና ትክክል እንደነበር ያረጋገጠ ነው፡፡ እንደ አገር ገብተንበት የነበረ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ቅድሚያ መረጃ ከተገኘባቸው ባሻገር የትግራይ፣ የኦሮሞና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ብዙ ሰዎችን በጥርጣሬ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚጥል ነበር፡፡ በጥድፊያ ዘመቻ ሰዓት ከርቀት ደህነኛውን ከመሰሪው አጣርቶ የመለየት ዕድል የለም፡፡ የፍተሻ ትዕዛዝ ለማውጣት እንኳ ጊዜ ላይገኝ ይችላል፡፡ ፈትሼ ምንም ባላገኝ ዜጎቼን ቅር አሰኛለሁና ቅሬታ ከሚፈጠር ባይፈተሽ ይቅር የሚል አቋም መውሰድ ኃላፊነትን መሳት (በደኀነኞች ውስጥ ያለ አጥፊ ሥራውን ይሥራ ብሎ መፍቀድ) ይሆናል፡፡ የረባ መረጃ ባይኖርም ለደህንነት ስስ የሆነ የሥራ አካባቢን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል፣ ቢያንስ ከደመወዝ ጋር እረፍት ለመስጠት ጨከን አለማለትም፣ ንፁህ ሰው ስለምን ተጠርጥሬ ብሎ ከሚከፋው ተቋማት ለአደጋ ቢጋለጡ ይሻላል የሚል ምርጫ መውሰድ ይሆናል፡፡ ከእነዚህ ዓይነት ጅል ውሳኔዎች ፈንታ፣ ደህነኞች ላይ ጊዜያዊ ቅሬታ የሚፈጥር ድርጊት ፈፅሞም ቢሆን በቅድሚያ ካልታወቁ አጥፊዎችና አተራማሾች ሊመጣ የሚችልን የአደጋ ዕድል ማምከን ለሁላችንም (ለጊዜው ቅር ለተሰኙ ወገኖቻችንም ጭምር) ይሻላል፡፡ “በብሔሬ ተጠረጠርኩ! ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ ቤቴ ተፈተሸ! ከሥራ ተገለልኩ…” የሚል ቅሬታ የገባችሁ የአገር ልጆች የመንግሥትን ዕርምጃ አወሳሰድ አገርን (መላ ኅብረተሰባችንን) ከእሳት ከማዳን አኳያ ካያችሁት፣ እዚህ ዓይነት የቢቸግር መላ ውስጥ የከተተን ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካና አደረጃጀት መሆኑን ካስተዋላችሁ፣ ቅሬታችሁ ይቀላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በፍተሻና በመሳሰሉ ዕርምጃዎች አደጋን በማስወገድ ጊዜ፣ በሩጫ ሥራ፣ በስሜታዊነት፣ ባልተጣራ መረጃ፣ ጥላቻና በቀል በፈበረከው የጥቆማ “መረጃ” ምክንያት ስህተቶች ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ ለእነዚህ ስህተቶችና ጥፋቶች ምንም ማመካኛ መስጠት አይኖርብንም፡፡ ፈጣን የጥፋት ማረሚያ ሊካሄድ ይገባል፡፡ በዚሁ አግባብ መብትን ለማስከበር መጣርም ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ መድሎና መገለልን ለማጦዝ መሞከር ሁላችንም ደርሰንበት ከነበረው የመተላለቅ አፋፍ ጋር ሲነፃፀር እንደ መቀናጣት ወይም ሥውር የጥፋት ደጋፊ እንደ መሆንም ይመስላል፡፡

ከብዙ በጥቂቱ ከሰኔ 22 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በኦሮሚያ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች የተሰነዘሩ ዘግናኝ ጥቃቶች፣ በ2013 ዓ.ም. በጊምቢ አካባቢ ስብሰባ ተጠርቶ የተካሄደ ርሸና፣ በደቡብና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተካሄዱ ጨካኝ ግድያዎች፣ በትግራይ በማይካድራ ባተሌዎች ላይ የተካሄደው ጭራቃዊ ጭፍጨፋ፣ ወዘተ ባመዛኙ “አማራ” ተብለው በታሰቡ ሰዎች ላይ የተነጣጠሩ እንደ መሆናቸው፣ አማራ ትዕግሥቱ አልቆና ወደ ጭፍን በቀል ተንሸራቶ እንዲገባ፣ በዚህም ለሙሉ ፀረ አማራ ፍጅትና ለኢትዮጵያ መወራረድ ሰበብ እንዲሆን የመነዝነዝ ደም ግባት ነበራቸው፡፡ የማይካድራውን ጭፍጨፋ ነጥለን ብንመረምረው እንኳ የሴራውን ሙሉ ሥዕል አናጣውም፡፡ ትግራዊ ያልሆኑ የአካባቢውን ለፍቶ አዳሪዎች የበላውና ይበልጡን አማሮችና ወልቃይቴዎች ላይ ያተኮረው ጭፍጫፋ ከመከላከያ ኃይል ጋር በአካባቢው የዘመተውን የአማራ ሚሊሺያ ደም ፍላት ውስጥ ይከታል… ደም ፍላት ቃታ እየሳበ ትግራዊዎችን በነሲብ ይረፈርፋል… የትግራይ ልጆች መረፍረፍ ደግሞ በአጠቃላይ የአገሪቱ ፀጥታ ውስጥ ያለውን የትግራይን ልጅ በፀረ አማራነት አስቆጥቶና አሸፍቶ ገሃድ ከወጣው አገር ናጅ ኃይል ጋር ይቀላቀላል… ከዚያ በኋላ እየተሰነጣጠቁ መከታከት ቀላል ይሆናል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሸናፊ ከሌለበት የመተጫጨድ ሥሌት ጋር ሲተያይ አገርን በማትረፍ ሥራ ውስጥ የሚደርስ ባልተጣራ መረጃና ሕግን በተላለፈ አያያዝ የሚደርስ ጊዜያዊ መጉላላት ተመስገን የሚያሰኝ ነበር፡፡

በብሔር ጎጆዎች ውስጥ የተወሻሸቀ ፖለቲካና የፓርቲ አደረጃጀት አዕምሮን እየከታተፈ ከሰፊ ዕይታ እንደሚያርቅ፣ ኢቡድናዊና ኢፖለቲካዊ መሆን የሚገባቸውን የአገረ-መንግሥት ተቋማትን በጎጆ ፖለቲካና ወገናዊነት እንደሚቦረቡርና በጎጆኛ ሻጥር ለመጠቃት እንደሚያጋልጣቸው፣ የሕዝቦችን አንድነት፣ መተማመንና ሰላም እንደ ብል እንደሚበላ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ሥፍራ ውስጥ አገሬ ወገኔ ብሎ ያለ ሥጋት ሥራ መክፈትና ማስፋፋትን እንኳ እንደሚያውክ ዓይተናል ተምረናል፡፡ የጎጆ ፖለቲካ በትንንሽ ስስትና መመቀኛኘት ህሊናን ሊሰለቃቅጥ፣ የአገር ልጅነት ዝምድናን፣ አብሮ ማደግን፣ አብሮ መኖርንና የሙያ አጋርነትን ሁሉ በማያውቅ ጥላቻና በቀል ህሊናን ሊሰልብ እንደሚችል፣ ብሎም ከሰውነት ዳር አውጥቶ ሰው-በላ ጭራቅ ሊያደርግ እንደሚችል፣ በስለት ከመክተፍና ከመዘንጠል አንስቶ በመኪና እስከ መረምረም ድረስ ሕይወታችን ጉድ እያሳየ አስተምሮናል፡፡ በዚህ ትምህርት ውስጥም፣ ከእንግዲህ የጎጆ ፖለቲካ ጠንቀኛ ተብሎ መሻር አለበት የሚል መልዕክት በትልልቅ ፊደል ተጽፏል፡፡ አብሮም ወደ ሙሉ መበላላት ከመሄድ እስካሁን ምን እንዳዳነን ወደፊትም መዳኛችን ምን እንደሆነ ተጽፎልናል፡፡ ምን ምን አዳነን?

ዘመናችን፣ መነጣጠል አሮጌና መጠፋፊያ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ መቻሉ፣

በመራራና በደግ መንገዶች የተገነባ ረዥም ማኅበራዊ መዘማመድ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ውስጥ የፈጠረልን የአንድ አገር ልጅነት “ደመነፍስ”፣

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ በጥላቻና በበቀል ነዲድ በተደጋጋሚ የተተነኮሰ ቢሆንም፣ ቱግ ከማለት ቁጥብ መሆኑ፣

ጎጆኛነት አለመፈየዱንና ማጥፋቱን ከልምድ የቀሰመ አመለካከት ወደ ኢትዮጵያ መንግሥት ቢሮ ሾልኮ መግባቱ፣

ለአንድ ቡድን ታማኝ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀውን የታጠቀ የመንግሥት አውታር በማዘመን ብልኃት፣ አገራዊ ሙያዊና ኢፖለቲካዊ የተልዕኮ ቁመናውን የማፍካት ትግል ውስጥ በቶሎ መገባቱና የጎጆኞችን አደጋ ለመመከት የሚያስችል አቅም መጎልበቱ፣

በገዥነቱ ቅንብር ውስጥ የነበሩ የኢሕአዴግ አባልና አጋር የጎጆ ቡድኖች አገራዊ ውህድ ፓርቲ ፈጥረው፣ ኅብራዊ አተያይ ይፋ መንግሥታዊ ሥፍራውን ይዞ ከጎጆኞች ጋር ያለውን ትግል ማትጋቱና ያልቦተለከ አምደ-መንግሥት ለመገንባቱ ሒደት ወሳኝ የመለካትና የድርጅት ስንቅ ለመሆን መቻሉ፣ እንዲሁም፣

እነዚህን ሰበዞች አንድ ላይ ጉልበቱ አድርጎ የያዘ አመራር፣ የሞት ሽረቱን ፍልሚያ ድል ለማስገኘት በሚያስችል ጥንቁቅነትና ትዕግሥት መምራቱና መመራት ያለበት መሆኑ ናቸው፡፡

ወደፊትም ከመበላላት የምንድነው፣ መተላለቃችንን የደገሰልንን ዋናና መሠረታዊ ችግር መፍታት የምንችለው ለውጠንና ሽግግሩን ከክሽፈት ስናድን፣ የአገረ መንግሥቱን ተቋማት ከፓርቲያዊነት ከወገንተኝነትና ከፖለቲከኝነት የፀዱ አድርገን ስናቋቋም፣ የመንግሥትንና ወይም መንግሥት የያዘውን ፓርቲ/ ፓርቲዎች ጨምሮ የሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ትግል በሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሕጋዊ ትግል ክልል ውስጥ መግታትና እዚያ ውስጥ መኖር ስንችል፣ እንዲሁም ሕግ ማክበርን፣  በሕግ መገዛትን፣ በሕግ ውስጥ መኗኗርን የመንግሥት የሥልጣን አካላትና ባለሥልጣኖቻቸው ሁሉ ግዴታና ቀይ መስመር ስናደርግ ጭምር ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...