Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ተንቀሳቃሽ ንብረትን በማስያዣነት ለሚያቀርቡ ብድር ካልሰጡ ገንዘቡ ለኢኖቬሽን ፈንድ እንዲውል ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚገኙ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ሕግ መሠረት በዓመቱ ከሚሰጡት ብድር ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆነውን ተንቀሳቃሽ ንብረትን ዋስትና አድርገው ለሚያቀርቡ ተበዳሪዎች ካልሰጡ፣ በዚህ መንገድ መቅረብ የነበረበት ገንዘብ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባና ለኢኖቬሽን ፈንድ እንዲውል ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በእንዲህ ዓይነት አሠራር ለአዕምሯዊ ንብረቶች የሚቀርበው ብድር እንዲጨምር የማድረግ ሐሳብ ያለው ሲሆን፣ ጥያቄውን ያቀረበው ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመሆን እንደሆነ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በ2012 ዓ.ም. ያወጣው በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድርን የሚመለከት መመርያ፣ ባንኮች ከሚሰጡት አጠቃላይ ብድር ውስጥ አምስት በመቶ የተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣ አድርገው እንዲሰጡ ያዛል፡፡ በዚህ መመርያ ውስጥ ተንቀሳቃሽ ንብረት ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ አዕምሮአዊ ንብረት አንዱ ሲሆን፣ ዓላማው የፈጠራ ሥራ ሐሳብ ኖሯቸው የኢንቨስትመንት ካፒታል ላጡ ግለሰቦችና ተቋማት ብድር ማቅረብ ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ አሠራር ቢዘረጋም ባንኮች አሁንም ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፣ በተለይም አዕምሮአዊ ንብረቶችን ማስያዣ በማድረግ የሚሰጡት ብድር አነስተኛ መሆኑን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኃላፊ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ መመርያው ቢወጣም አስገዳጅነት የሌለው መሆኑን በዋነኛ ምክንያትነት ያወሱት አብዮት (ዶ/ር)፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴሩ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንና ብሔራዊ ባንክ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

‹‹ባንኮች [በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ዋስትናነት] ሳይበደሩ ሲቀሩ ገንዘቡን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡና ለኢኖቬሽን ፈንድ እንዲውል ማድረግ የሚል ሐሳብ አቅርበናል፣ የእነሱን ምላሽ እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በጥያቄው ላይ የተጠቀሰው ‹‹የብሔራዊ ኢኖቬሽን ፈንድ›› በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በቀረበው የስታርት አፕ (ጀማሪ ቢዝነሶች) ረቂቅ አዋጅ ላይ የሠፈረ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመረጡ አባላት ያሉበት ካውንስል እንደሚቋቋም የሚደነግግ ሲሆን፣ ካውንስሉ የተለያዩ ጀማሪ ቢዝነሶችን አዋጪነት እየገመገመ በብድር፣ በድጋፍና በኢንቨስትመንት ለጀማሪ ቢዝነሶች የኢንቨስትመንት ገንዘብ ይሰጣል፡፡ ገንዘቡም የሚሰጠው የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ ከሚቋቋመው የብሔራዊ ኢኖቬሽን ፈንድ ነው፡፡

ሚኒስቴሩ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣንና ብሔራዊ ባንክ በሚያደርጉት ንግግር ለመመርያው አስገዳጅ ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ፣ ከቀረቡት ሌሎች አማራጮች ውስጥ የተሻለውን ተግባራዊ ለማደረግ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አብዮት (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ከበጀታቸው ውስጥ ሁለት በመቶውን ለሥልጠና እንዲያውሉ ያደረገበት ተመሳሳይ አሠራር እንዳለ የጠቀሱት ኃላፊው፣ ባንኮች ሁለት በመቶ በጀታቸውን ሥልጠና ካላዋሉ ብሔራዊ ባንክ እንደሚወስደው ገልጸዋል፡፡  አሠራሩ ተለምዶ ባንኮች ጥቅሙን እስኪረዱት ድረስ አስገዳጅነቱን መተግበር አማራጭ ሆኖ መቅረቡን አክለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በቅርቡ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ባፀደቀው የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ፖሊሲ ላይም ሥራ ፈጣሪዎች የአዕምሯዊ ንብረትን በማስያዝ ብድር የሚያገኙበትን መንገድ ትኩረት ሰጥቶታል፡፡ ፖሊሲው ግለሰቦችና ተቋማት በአዕምሯዊ ንብረታቸው ብድር እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር፣ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ላገኙ ቴክኖሎጂዎች የዋጋ ትመና ሥርዓት ለመዘርጋት አቅዷል፡፡

አብዮት (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ያላቸው ግለሰቦች ኢንቨስት የሚያደርግላቸው አካል ሲፈልጉ፣ ከሚቸገሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የቴክኖሎጂ ፈጠራው ምን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ አለመታወቁ ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ፈጠራው ዋጋ የማይታወቅ መሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ከኢንቨስተሮች ጋር ሲዋዋሉ ትክክለኛውን ድርሻ እንደማያገኙ አስረድተዋል፡፡

ፖሊሲው በሚዘረጋው ሥርዓት መንግሥት ይህንን ዓይነት የዋጋ ትመና የሚያካሂዱ የግል ተቋማት እንዲቋቋሙ እንደሚያደርግ፣ ተቋማቱ የፈጠራ ሥራ ትመና የሚደረግባቸው ዓለም አቀፋዊ መለኪያዎችን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች