የምሥራቅ አፍሪካና አገሮች በባህልና በጥበብ ለማስተሳሰር ያለመው ክፍለ አኅጉራዊው የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ከሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፣ በፌስቲቫሉ አሥራ አንድ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመሰናዶውም ባህላዊ ክዋኔዎች የሰርከስና የጎዳና ላይ ትርዒቶች፣ ሲምፖዚየም፣ ባህላዊ የምግብና የመጠጥ ዓውደ ርዕይ፣ የፊልም ዝግጅት እንዲሁም የሙዚቃና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይቀርቡበታል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በሰኔ መባቻ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ፌስቲቫሉን ማዘጋጀት ስታስብ በመሠረታዊነት የቀጣናው ሕዝቦች መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር ዕድል መፍጠርን ታሳቢ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ጥበባትና ባህል ለቀጣናዊ ትስስር›› በሚል መሪ ቃል ፌስቲቫሉ በወዳጅነት አደባባይ ሰኔ 7 ቀን እንደሚከፈት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ዝግጅቱን አስመልክቶ ከቀጣናው አገሮች ዲፕሎማቶች ጋር ተከታታይ ውይይቶች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ምን ያህል አገሮች ለመካፈል ማረጋገጫ ሰጥተዋል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፣ ከቀጣናው አገሮች መካከል እስካሁን ኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ የባህል ቡድን እንደሚልኩ አስታውቀዋል ብለዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ዝግጅት ከሦስት ወራት በፊት መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቱሪዝምና የሰላም ሚኒስቴሮች የፌዴራል ፖሊስና ከኪነጥበብ ቤተሰቡ ጋር በመሆንም ሥራው እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ፌስቲቫሉ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ እያካሄዱት ካለው የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል (ጃማፌስት) ጋር ግንኙነት እንዳለው የተጠየቁት ሚኒስትሩ፣ ስለጃማፌትስ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ ፌስቲቫሉ የባህል ዲፕሎማሲ አካል አድርጎ ከመጠቀም አንፃር ጥሩ ዕድል እንሆነና የፐብሊክ ዲፕሎማሲንም እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የኪነጥበብና ሥነጥበብ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማሃዲ፣ ፌስቲቫሉ ዓምና የተካሄደው የኢትዮጵያ ሳምንት ቅጥያ መሆኑንና ወደ ክፍለ አኅጉር ደረጃ የተሻገረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በየክልሉ የባህል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን በአዲስ አበባው መሰናዶም ከክልሎች የሚመጡ እንደሚሳተፉበት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ሚዲያው ፌስቲቫሉን በተከታታይ እንዲያስተዋውቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፌስቲቫሉ ይዘት
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ባሠራጨው ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፣ ፌስቲቫሉ አራት ዋና ዋና መርሐ ግብሮች አሉት፡፡ እነርሱም ዓውደ ጥናት፣ ዓውደ ርዕይ፣ ኪነታዊና ባህላዊ እንዲሁም ስፖርታዊ ዝግጅቶች ናቸው፡፡
ዓውደ ጥናቱ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካን ትስስር ማጠናከር›› በሚል ስያሜ የሚከናወን ሲሆን፣ የዕደ ጥበባት ዓውደ ርዕይ፡ የባህል መገለጫ የሆኑ ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ሌሎች የሚቀርቡበት መሰናዶ፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካውያን የባህል ምልክት መግለጫ›› በሚል መሪ ቃል፣ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ፡ ‹‹ምሥራቅ አፍሪካ ታንብብ››፣ የሙዚቃ ፌስቲቫል፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ሙዚቃ ቃና›› በሚል ስያሜዎች፣ ሌሎች ደግሞ የፊልም ፌስቲቫል፡ ‹‹አገሮችን ማስተዋወቅና ማገናኘት››፣ የሥዕልና ቅርፃ ቅርፅ ፌስቲቫል፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ቀለም›› በሚል ሰያሜ የቀጣናው ሠዓሊዎች ሥራ የሚያቀርቡበት ይሆናል ተብሏል፡፡