Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሁንስ በዛ!

ሰላም! ሰላም! ከሰላም የበለጠ ምንም ነገር ስለሌለን ሰላም ስንባባል ከልባችን ይሁን፡፡ የሰላምን ዋጋ ለማወቅ እንደ ኢራቅ፣ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ… ሰዎች የግድ ማለቅ ወይም መሰደድ የለብንም፡፡ ግና ብዙኃኑ ስለሰላም ምህላ በየእምነታቸው ይዘው፣ ልባቸው የታበየ ጥቂቶች ግን በጊዜያዊ ተረኛ ጉልበተኝነት ሰክረው የሚሠራቸውን አሳጥቷቸዋል፡፡ አንዳንዱ ወናፍ ዘንድሮ ምን እንደ በላ ወይም ምን እንዳበሉት አላውቅም የጥጋብ ስካር አናቱ ላይ ወጥቷል። እባካችሁ ተብሎ ምክር በልመና በሆነበት አገር፣ ጥጋበኞችን ለመምከር የሚያዘው ሠልፍ የዳቦ ሠልፍን ያስንቃል። እውነቴን ነው የምላችሁ። አንድ ጊዜ አዛውንቱ ባሻዬ እንዲህ አሉኝ፡፡ ‹‹ሰማህ አንበርብር ፈጣሪን የረሳ ራሱን እንደ ፈጣሪ ያያል፡፡ ለፈጣሪ ምሥጋና ማድረስ የሚገባው ፍጡር ራሱ ተመሥጋኝ መሆን ይፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለው የታበየ ፍጡር ነው በጊዜያዊ ድል እየተኩራራ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል ከርሞ የተያዘ ዕለት የሚዝለፈለፈው…›› ሲሉኝ ልቤ በአነጋገራቸው ተነካ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ምንም እንኳ የሥነ ልቦና ባለሙያ ለመሆን የትምህርት ደረጃዬ ባይፈቅድልኝም፣ ከብዙ ሰዎች ጋር ሥራዬ ስለሚያገናኘኝ የሰው ልጅ ምን ያህል ደካማ ፍጡር እንደሆነ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ያለ እኔ ማን አለ እያለ ሲፎክር የነበረ አውደልዳይ ሁሉ ጥጉን ይዞ የሰው ዓይን ሲሸሽ ስንቱን ታዝቤያለሁ፡፡ ‹ማወቁንስ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን› የተባለው እኮ እንዲሁ አይደለም፡፡ እውነት ነው!

እናላችሁ በቀደም አንዱ፣ ‹‹አንበርብር ለምን ለራስህ አታውቅም?›› አለኝ። ይኼውላችሁ ነገር ፍለጋ ሲጀመር። ‹‹እሺ ምን ብዬ ልወቅ?›› ስለው፣ ‹‹አለ የተባለ ሁሉ ገንዘቡን ወደ ውጭ አገር እያሸሸ በዶላርና በዩሮ እያስቀመጠ አንተ ለምንድነው ዝም ብለህ የምታየው? ይኼ አገር ተስፋ አለው ብለህ ነው?›› ብሎ ገና ምንም ሳልለው በአገሬና በእኔ ላይ እኩል ሳቀ። ‹‹አይ ምን መሰለህ. . .›› ምናምን እያልኩ ገና መናገር ስጀምር፣ ‹‹ዝም ብለህ እኔን ብትሰማኝ ይሻልሃል። ከአንተ የበለጠ ስለገንዘብ የሚያውቅ የለም። ምን አለፋህ ይኼን አገር አምነህ ደክመህ ያገኘኸውን ለማንም ከምትበትነው አሽሸው…›› ሲለኝ ቀስ ብዬ እንደ ምንም በሰበብ ሹልክ ብዬ ሄድኩ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ዘንድሮ ልክፍት ነው አፍ አፍ አፋችንን እያለ አላስቀምጥ የሚለን? እንግዲህ ሁኔታችንን ዝም ብዬ በማይም ጭንቅላቴ ሳጤነው አንድ የተበላሸብን ነገር እንዳለ ይገባኝ ጀምሯል፡፡ የአገር ሰላም የሚያምሰው አጉል ደፋር በዚህ በኩል፣ በአጉል ወሬ የወገን ቀልብ የሚመነትፈው አሉባልተኛ በዚያ በኩል ሲራወጡብን መረማመጃው እየጠፋብን ተቸግረናል፡፡ በዚህ ላይ ሳያጣሩ የሚለቀቅላቸውን እንደ ቱቦ የሚያስተላልፉ ጅሎች መብዛታቸው ደግሞ ያናድዳል፡፡ ወይ መቃጠል!

መቼም ይኼ ጨዋታ ብዙ ሳያስወራን አይቀርም። ጊዜው ቆይቷል አሉ፡፡ ሰው ራሱን ከክፉ ነገር መጠበቅ እንዳለበትና ይህም ለጤናማ ማኅበረሰብ መፈጠር ጥሩ መሆኑ ተነገረ፡፡ በዚህ መሀል አንድ ዕድሜ የጠገቡ አዛውንት እስቲ አዳምጡኝ በሚል ድምፀት ካጨበጩ በኋላ፣ ‹‹ፈጣሪን አትርሱ፡፡ ፈጣሪን የረሳ መመፃደቅ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የዱር እንስሳት እንኳ ለፈጣሪያቸው ምሥጋና ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ የሚሆን አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ አንድ ቀን ጨለማው ተገፎ ብርሃን ሲወጣ አንበሳ ‹ተመሥገን አምላኬ በሰላም ያሳደርከኝ፣ ቁርሴን ደግሞ አንተው ዕርዳኝ› ብሎ ለአደን ሲሰማራ፣ ልክ እንደ እሱ ለፈጣሪዋ ምሥጋና አቅርባ የተነሳች ሚዳቆ ወደ መስኩ ለግጦሽ ስታመራ ከአንበሳው ጋር ተገናኝታ ያሳድዳት ጀመረ፡፡ ሁለቱ በጫካው ውስጥ ሲሳደዱ ከእንቅልፉ ነቅቶ እያዛጋ ሲገላበጥ የነበረ ከርከሮ ጋ ሲደርሱ፣ አንበሳው ድንገት እጁ ላይ የገባለትን ሲሳይ ሲያይ ሚዳቆዋን ማባረር ትቶ ከርከሮው ላይ ጉብ ብሎ ፈጣሪውን እያመሠገነ ቁርሱን ማወራረድ ጀመረ፡፡ ሚዳቆዋም ከመስኩ ጨሌ እየጋጠች ለፈጣሪዋ ምሥጋና አቀረበች፡፡ ይህን ጊዜ ‹አውጣኝ ያለ ወጣ አብላኝ ያለ በላ፣ ፈጣሪን የረሳ ከርከሮ ተበላ› ተብሎ ተተረተ…›› ሲሉን በመገረም ሰማናቸው፡፡ የሰው ልጅ ከዚህ በላይ ምክር ከየት ያገኝ እንደሆነ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው!    

እኔም እንደ አቅሚቲ አንድ ጉዳይ አውቃለሁ፡፡ የሰው ልጅ ደካማ ፍጡር መሆኑን ብዙ ጊዜ ዓይቻለሁ ብያችሁ የለ፡፡ አንድ ጊዜ አንዱ ወዳጃችን ድለላው ደርቶለት ከዚህም ከዚያም ብሎ ረብጣ በረብጣ ሆነ፡፡ እኔንና መሰል ወዳጆቹን ትቶ ‹አራዶች› ከሚባሉ አጭልጎች ጋር መዋል ጀመረ፡፡ እናላችሁ ውድ ቪላዎች ውስጥ ከቆነጃጅት ጋር ጫት መቃም፣ ሺሻ ማቡነን፣ የእኩለ ሌሊት መጠጥ ማዘውተር፣ እንዲሁም ማመንዘር ለመደ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ዕፅ እንደሚወስድ ሁሉ ተወራበት፡፡ ሁኔታው ስላላማረኝና በወዳጅነት ኃላፊነቴንም ልወጣ በሚል ዕሳቤ ለመምከር ጥረት ባደርግም፣ እኔን እንደ ኋላቀርና ተራ ደላላ በማመናጨቅ አባረረኝ፡፡ የፈራሁት አልቀረም አጅሬው ከድለላ ሥራው ርቆ ሌላ ወንጀል ውስጥ ተዘፍቆ ኖሮ ፖሊስ አስሮት፣ ፍርድ ቤት ገትሮት ካስመሰከረበት በኋላ ቂሊንጦ ለአሥር ዓመታት ተላከ፡፡ ታስሮ ልጠይቀው ስሄድ ጠቁሮና ከስቶ አንገቱን ደፍቶ ዓይኔን ማየት አቃተው፡፡ ሳናግረው እንባው ይታየኛል እንጂ፣ ድምፁን መስማት አቅቶኝ እግዜሩ ይሁንህ ብዬ ተሰናበትኩት፡፡ ምናለ በሉኝ አገር የሚያምሱ የጊዜያችን ነውጠኞችም እንዲህ እንደ ወዳጄ አንገታቸውን ይደፋሉ፡፡ ይህ ለፈጣሪ የማይሳነው ትንሹ ነገር ነውና፡፡ አይደለም እንዴ!

ቅድም የነገርኩዋችሁ ገንዘብን በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ስለማሸሽ ነገር ሰሞኑን ብዙ ስሰማ ነበር። ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር የምንሸጋገረው እንግዲህ በዚህ አያያዛችን መሆኑ ነው። ‹‹እኔን የሚገርመኝ ግን በቃ ሁሉም ሰው የሚያስበው አንድ ዓይነት ነገር ነው ማለት ነው?›› አለኝ በቀደም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነገሩን አንስቼለት። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹ለፍተን ሠርተን ሲጠራቀምልን ለምንድነው ከትልቅ ቤት፣ ከቅንጡ አውቶሞቢልና ከውስኪ ቤት ሌላ ማሰብ የማንችለው?›› ሲለኝ፣ ‹‹ነገር አታምጣ!›› ብዬ እንዳልሰማ ሆንኩበት። ነገር ፈርቼ እንጂ በውስጤ የሚብላላው መዓት ነው። በተለይ ስለ እኛ የምናወራቸውንና የምናደርጋቸውን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ነገሮችን ሳይ ሳቄም እንባዬም እኩል ይመጣሉ። ለምሳሌ ብዬ ላስቆጥራችሁ። ለምሳሌ አገር አገር እያሉ ለመጮህና ለመተማማት አንደኞች ነን። ከዚያስ አትሉም? ከዚያማ በአቋሯጭ ከአገር ላይ የሚዘረፍ ስናገኝ ወይም ደግሞ ከዘራፊዎች ጋር ሆነን የአገራችንን መሬት እየወረርን ስንይዝና ስንቸበችብ፣ አገር የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ጠፍቶ ‹ከራስ በላይ ንፋስ› ማለት ይጀመራል፡፡ አገር የሚዘርፈውም ሆነ የሚያምሰው ዋናው ዓላማቸው በዚህ ምስኪን ሕዝብ ላይ መቆመር ነው፡፡ ቁማርተኞች ደግሞ ህሊናም ሆነ ፈሪኃ እግዚአብሔር የላቸውም፡፡ ህሊና የሌለውና ያልተጠረበ ድንጋይ አንድ ናቸው!

በሌላ በኩል የማሰብና የማሰላሰል ተሰጥኦ የሌለን ዘወር ተደርገን ስንታይ ተውት ሌላውን፣ ለህሊናችን መታመን ግድ የማይሰጠን ሆነን እንገኛለን። ‹እከሌ ሀብታም ነው ግን አይሰጥም። ተሸክሞት ሊሞት ነው እንዴ? ወይስ መቃብር ቤት ሲወርድ ሊንተራሰው ነው?› እያልን ለፍቶ ያገኘውን ባለሀብት ስናማ ላየን፣ ከእኛ በላይ መፅዋችና የተቸገረ የሚረዳ ያለ አይመስልም። ነገር ግን እንዲያ ከምንለው ውስጥ እንደ አቅሚቲ የምናከራያት ቤት ያለችን ሰዎች የተከራይ ለቅሶና ብሶት አልታወቀን ብሎ በወር በወር ኪራይ የምንጨምር ሆነን እንገኛለን። እንዲያው እሱን ትታችሁት የቤት ውስጥ ሠራተኞቻችንን በትህትናና በወንድም በእህትነት ስሜት የምንከባከባቸውስ ስንቶቻችን ነን? ሰብዓዊነት ከውስጣችን ነጥፎ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተሟጋች ነን ብለን የምንኩራራ መብዛታችንም ይገርማል፡፡ ‹‹የሴቶች መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ዘመናይ ሴቶች እኮ ለቅጠል ለቃሚዋና ለጭቁኗ አርሶ አደር መብት ሳይሆን፣ ፈረንጅ ለሚፈልገው አጀንዳ መሳካት ብቻ ነው የሚውረገረጉት፡፡ አጀንዳው የፈረንጅ፣ በጀቱ የፈረንጅ፣ ተጠቃሚዎቹ እነሱ፣ ጭቁኖቹን ግን የሚያስታውሳቸው የለም፡፡ በሕዝብ ስም የሚጮሁ ወረበላ አክቲቪስቶችንም ብታይ ለሕዝብ ኑሮ፣ ሕይወትና ተስፋ ደንታ የላቸውም፡፡ እነሱ በሕዝብ ስም የሚቆምሩት ከፋዮቻቸው ለሚፈልጉት ዓላማ መሳካት ብቻ ነው…›› እያለ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከዓመታት በፊት የነገረኝን ሳስታውስ ራስ ምታቴ ይነሳል፡፡ ዘንድሮ እንጃልን!

አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ፣ ሁለት ጓደኛሞች አንዲት ገጠር ውስጥ ሲኖሩ መጠጥ ይለምዳሉ፡፡ መጠጡም ሱስ ይሆንባቸውና ሌብነት ይጀምራሉ፡፡ አንድ ቀን በጠዋት ተነስተው የአንዱን ታታሪ ገበሬ አህያ ይሰርቃሉ፡፡ አንደኛው አህያውን ገበያ ወስዶ እንዲሸጥ፣ ሌላው ደግሞ መንደር ውስጥ ሆኖ የሚባለውን እየሰማና እያስተባበለ እንዲቆይ ተስማምተው ይለያያሉ፡፡ አህያውን እየነዳ ከተማ ገበያ ወስዶ ለመሸጥ የተላከው ገዥ እየተጠባበቀና የገበያውን ሁካታ በተመስጦ እየተመለከተ ሳለ፣ ሌላ ሌባ አህያውን ካሰረበት ፈቶ ይወስድበታል፡፡ አጅሬው ዓይኖቹን ከገበያው ሁካታ አህያውን ወደ አሰረበት ሲያዞር አህያው የለም፡፡ ወዲህ ቢል ወዲያ ቢል የሰረቀው አህያ ሊገኝ አልቻለም፡፡ አንዴ ወደ ላይ ሌላ ጊዜ ወደ ታች እየተመላለሰ አህያውን ቢፈልግም ማግኘት ሳይቻለው ቀረ፡፡ ገበያው እስኪበተን ቢጠብቅም አህያው የከተማ ሌባ ሲሳይ ሆኗል፡፡ ‹‹ሌባን ሌባ ቢሰርቀው እንዴት ይደንቀው›› ሆኖበት፣ በመጨረሻ ወደ መንደሩ ፀጉሩን እየነጨ ይመለሳል፡፡ መንደሩ ሲደርስ የሰረቁት አህያ ተሽጦ የሚያገኘውን ገንዘብ እያሰላሰለ በጉጉት የሚጠብቀው ጓደኛው፣ ‹‹ተሸጠ እንዴ?›› ብሎ በደስታ ተውጦ ሲጠይቀው፣ ‹‹አዎ ተሸጧል…›› ሲለው፣ ‹‹ስንት ተሸጠ እባክህ?›› በማለት እንደገና ሲጠይቀው፣ ‹‹ጠዋት ባመጣንበት…›› ብሎ መለሰለት ተባለ፡፡ የሌብነታቸው ዋጋ ማለት ነው፡፡ የእኛም ጉዳይ እንዲያ እየሆነ ይመስላል!

ያው እንግዲህ ለማይሞላው ኑሮ ታዲያ ተፍ ተፍ እንዳልን ነው። ሕይወታችን በምን ይመሰላል ቢባል አንዱ “በገብረ ጉንዳን” ብሎ መለሰ አሉ። “የትኛው ግብራችን ነው አንተ ካልጠፋ ነገር ከጉንዳን ያመሳሰለን?›› ሲባል፣ “ሠልፋችን!” ብሎ አረፈው። የትራንስፖርት ችግር ያማረረው መሆን አለበት መቼም። ‹‹አይ! በባቡር አይሄድም?›› ብዬ ነበር እኔም እንደ እናንተ። ‹‹ዘመኑ እኮ የ‘ኮምፒቲሽን’ ነው የ‘ፒቲሽን’ ማሰባሰቢያ አይደለም…›› አለኝ ሌላው፡፡ “እንዴት?” ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አታየውም እንዴ ፍጥነቱን? እንኳን እኛ ኤሊም በአቅሟ ለዘመናት የተጫናት ድንጋይ እንዲቀልላት ከሆነም እንዲነሳላት የት ሄጄ ልለምን በምትልበት የጥንቸሎች ዘመን፣ የባቡራችን ፍጥነት ፊርማ ለማሰባሰብ ካልሆነ ገንዘብ ለመሰብሰብ መቼ ይሆናል?›› አይሉኝ መሰላችሁ። ለነገሩ ባቡሩ አሁን መገስገስ ጀምሯል እኮ፡፡ እኔ ደግሞ ለተንኮሌ፣ “የምን ፊርማ?” ብዬ ነገር መጠምዘዝ። “የብሶት!” መቀጠል እነሱ። “ማነው የባሰው?” እኔ። “የባሰበት ነዋ!” እነሱ። “እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም” አለች ስትዘፍን ውላ ብታድር የማትሰለቸዋ። ለነገሩ መሰልቸትን ምን አመጣው አሁን!

ፊቴን ወደ ሥራ አዙሬ ሁለት ሲኖትራኮች ላሻሽጥ ገሰገስኩ። መቼ ዕለት ነው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ድድ ማስጫዎች ከመንደራዊነት ወደ ‘ዲጂታል’ ማኅበረሰባዊ ድረ ገጽነት የተለወጡለት የፌስቡክ ትውልድ፣ የሚለጥፋቸውን ፎቶዎች ሲያሳየኝ ነበር። ይኼው ‘ሲኖትራክ’ የተባለ ጦሰኛ ከባድ መኪና የኋሊት ተገልብጦና ፊቱን ወደ ሰማይ ቀስሮ፣ “አውሮፕላን መግጨት አማረኝ” ተብሎ ተጽፎበት አየሁና ሳቅ ሳቅ አለኝ። ልብ አድርጉልኝ። ሳቅ ሳቅ አለኝ እንጂ አልሳቅኩም። ‹‹ግዑዝ አፍ የለውም ብሎ የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ጥፋት ታዛዡን አዛዥ፣ አገልጋዩን ጌታ የሚያደርግበት ሥልቱ ሳቅ ሳቅ ያስብላል እንጂ ያስቃል?›› ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ፣ ‹‹ወደፊት ሕግና ሕግ አስከባሪውን አላፍር አልፈራ ላለው ‘ሲኖትራክ’ መፍትሔ ሆኖ መገኘቱ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፤›› አለኝ። ‘እኛማ ተናንቀን ምድር ጠቦናል’ ነው እኮ ነገሩ። እኔነት አልገራ ሲል ታዲያ ምን ይሁን? እስኪ ቆይ! ለመሆኑ ይኼ ሲኖትራክ የሚሉት ነገር ለከተማ የተሠራ ጥሩንባ የለውም እንዴ? በከተማ መሀል አስደንጋጭ ጥሩንባውን ሲለቀው እኮ አንዱን ከሌላው እያላተመ ፈጀን፡፡ ትራፊክ ፖሊስ ይሰማል!

አዛውንቱ ባሻዬ መቼ ዕለት ነው አንድ ምሳሌ አጫወቱኝ። ሰውዬው ኑሮ አሰልቺና ድግግሞሽ ሆነበት። የዕለት ተዕለት ውጣ ውረዱን ለመርሳት አውጠነጠነ። ወደ አንድ መምህር ሄዶ፣ ‹‹በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም። የዓለም ነገር ሞላ ሲሉት ይጎድላል፣ ጎደለ ሲሉት ይሞላል። ከዚህ ወዲያ ከሚታየው ነገር ባሻገር ወደ የማይታየው ዓለም ገብቼ በአዕምሮ ነቅቼ ለመኖር ቆርጫለሁና ይምሩኝ…›› ይላቸዋል። ‹‹መልካም! አሁን በመንገድ ስትመጣ ምን አይተሃል? አዕምሮህ ውስጥ የሚመላለሰው ምንድነው?›› አሉት። ‹‹በመንገድ አንድ አህያ አይቻለሁ። በአዕምሮዬም ያለው እሱ ነው..›› አላቸው። ‹‹በል ተቀመጥና መጀመርያ አህያውን ከሐሳብህ አውጥተህ ጣል…›› ይሉታል። ቢለው ቢለው አልቻለም። ኋላም ወደ መምህሩ ቀርቦ፣ ‹‹መምህር ሆይ አቃተኝ…›› ቢላቸው፣ ‹‹በመንገድ ላይ ያየኸውን የትም የማታውቀውን ያንተ ያልሆነውን አህያ ከሐሳብህ ማውጣት ካቃተህ፣ ታዲያ አንተ እንዴት ነው እኔነትህን አውጥተህ መጣል የምትችለው?›› አሉት ይባላል። አደራ ደግሞ ደላላው አንበርብር ነግሮን ነው ብላችሁ ነገር ዓለሙን ረስታችሁ ከራሳችሁ ጋር እየተወዛገባችሁ እንዳታሳሙኝ! በሉ እንሰነባበት። እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ተያይዘን ወሬ የምንሰልቅባት ግሮሰሪያችን በረንዳ ላይ ተሰይመናል። አጠገባችን ያለ ዕውቀት በድፍረት ስለዓለም የፖለቲካ አካሄድ አንዱ ይቦተረፋል። ሰምተን እንዳልሰማን ብናልፈው ደግሞ አንዱ በጎን አንብቦ ስለማያውቀው ‹‹ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም›› ይቀደዳል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እንዲያው እንዲህ ኃፍረት ሙልጭ ብሎ ይጥፋ? ሰው ቢሰማኝ ምን ይለኛል የሚል ይጥፋ?›› ይለኛል። ‹‹ሁሉም ተንታኝ፣ ሁሉም አዋቂ። ሁሉም የፊቱና የኋላውን እኩል የማወቅ አቅም ያለው ሆኖ የተፈጠረበት እንደዚህ ያለ ዘመን ያለ አይመስለኝም…›› እያለ የባሻዬ ልጅ ሲናገር አንዱ ብድግ ብሎ፣ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ…›› አለ። እሺ ቀጥል አልነው። እሱም የእኛን ትዝብት ተጋሪ ሆኖ ኖሮ፣ ‹‹እኔ ምንም ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ አለ። እሱም ምንድነው? ይኼ ሁሉ ተንታኝ፣ ይኼ ሁሉ ምሁር፣ ይኼ ሁሉ ተዋናይ፣ ይኼ ሁሉ መካሪ፣ ይኼ ሁሉ ተሟጋች ባለባት አገር እንዴት ሦስት ሺሕ ዘመን በጦርነት ብቻ አለፈ? ይህችን ብቻ መልሱልኝ…›› ብሎ ተቀመጠ። ‹ደህና ነገር የሚያወራ መስሎኝ› እየተባባለ ሁሉም ፊቱን ከእርሱ አዞረ። ችግር የማይፈታ ዕውቀት፣ አቅጣጫ የማይወስን ትንታኔ፣ ዘዴና ብልኃት የማያፈልቅ ኢንፎርሜሽን፣ እንዲያው ብቻ በየሄድንበት ለወንበር ማሞቂያ አልኩ ለማለት ተብሎ ሲቀደዱ ውሎ ሲቀደዱ ማምሸት፣ ደግሞ ከእሱም ብሶ አለመደማመጥ፣ መናናቅ፣ መገለማመጥ፣ ማን ስለሆንክ? ማን ስለሆንሽ? ስንባባል ስንኖርን አያሳዝንም? አሁንስ በዛ! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት