Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሥጋት የሆነው የጎርፍ አደጋ

ሥጋት የሆነው የጎርፍ አደጋ

ቀን:

R2308 Social 1

በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች የጎርፍ አደጋ ሲከሰት ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለዚህ የአየር ንብረት ለውጡ የራሱ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በመንግሥትና በማኅበረሰቡ በኩል መሠራት ሲገባቸው ያልተሠሩ የመከላከል ሥራዎች ለችግሩ እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡

ይህም ለሰውና እንስሳት ሕይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደምና ለነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ የዝናብ ወቅት በመጣ ቁጥር በውኃ ገብ አካባቢዎችና በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ሕዝቦች ደግሞ ይበልጥ የችግሩ ተጋላጭ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባም ስለጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት እንዲሁም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎችና መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች ለዓመታት ሲነገርና ምክረ ሐሳብ ሲቀርብ ቢቆይም፣ ችግሩ ዛሬም አልተፈታም፡፡

ዓምና በአዲስ አበባ በመካነ እየሱስ ሴሚናሬ ግቢ ውስጥ የተከሰተውና የስምንት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የጎርፍ አደጋ የቅርብ ትዝታ ነው፡፡

ዘንድሮ ደግሞ ሰሞኑን በጀመረው ዝናብ የጎርፍ አደጋዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥም አንድ ተማሪ በጎርፍ መወሰዱን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ተጀምረው የሚቆሙ ፕሮጀክቶች በመብዛታቸው፣ ለግንባታ የሚውሉ ቁሳቁሶች ቱቦዎችን መዝጋታቸው፣ ለፍሳሽ ተብለው የሚቆፈሩ ቱቦዎች በአግባቡ ባለማለቃቸውና በቁፋሮው ምክንያት የተበላሹ መንገዶች በአግባቡ  ባለመስተካከላቸው፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዬች በቆሻሻ የሚደፈኑበት ሁኔታ መኖሩና የሚመለከተው አካል ሁሉ ኃላፊነቱን በተጠያቂነት የሚወጣበት አሠራር ባለመዘርጋቱ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባሱ መንግሥት የተለያዩ ግብረ ኃይሎችን በማዋቀር አደጋውን ለመከላከል እየሠራ ቢሆንም፣ አሁንም ክፍተቱ እንዳለ ሰሞኑን የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ምስክር ናቸው፡፡

የእሳት አደጋ ሥጋትና አመራር ኮሚሽን፣ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ሥጋትና አመራር ኮሚሽን ቅድመ መከላከል ሥራ እየሠሩ እንደሆነ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች ቢያሳዩም፣ የጎርፍ አደጋው ዘንድሮም ቀድሟቸዋል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ በተከሰተው የዝናብ ዕጦት ምክንያት ድርቅ ሊታይ ችሏል፡፡

በዚህም የተነሳ ከፍተኛ የውኃና የግጦሽ እጥረት ሊከሰት እንደቻለ የገለጹት አቶ ደበበ፣ በተለይም በበልግ ወቅት የሚያበቅሉ ሥፍራዎች ላይ በቂ ዝናብ ባለመገኘቱ፣ የግጦሽ እጥረት ሊፈጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከሰኔ 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መተንበዩን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ የሚፈጠረው የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

የጎርፍ አደጋን በተመለከተ የውኃና ፍሳሽ፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣንና ሌሎች ተቋሞችን መጠየቅ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከክልሎች ጋር ፈጣን የተቀናጀ አሠራር መዘርጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ ሴክተር ተቀናጅቶ ቢሠራ የጎርፍ አደጋ እንደማይከሰትና አብዛኛው ችግር የሚከሰተውም ቅድመ መከላከል ላይ ባለመሠራቱ እንደሆነ አቶ ደበበ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅ፣ ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ፡፡ መካከለኛው ምዕራብና ምሥራቅ ደግሞ ተቀራራቢ የሆነ ዝናብ የሚያገኙ የአገሪቱ ክፍሎች ናቸው፡፡

ወደ አደስ አበባ ሲመጣ በተለይ ዓምና ያጋጠመው ከባድ ጎርፍ፣ የተመዘገበው ውድመትና ሞት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ ችግሩን ለመፍታት እንዲሠራ መሠረት የጣለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም በወቅቱ በተነገረው ልክ የመከላከል ሥራዎች ሳይጠናቀቁ፣ ጎርፍ አደጋ ማስከተል ጀምሯል፡፡

አምና በጀርመን አካባቢ በሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ስምንት ሰዎች መሞታቸውንና 500 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት መውደሙን የመካነ ኢየሱስ ሴሚነሪ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምሕረት ዓለም ለሪፖርተር ያስታወሱ ሲሆን፣ በወቅቱ ለተከሰተው ጎርፍ ዋነኛ መነሻው የጀርመንና ጎፋን የሚያሻግረው ድልድይና ቱቦዎቹ በደለል በመዘጋታቸው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ ክረምት የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ የቅድመ መከላከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጥናት አድርጎ ወንዙን በዘላቂነት ለመገንባት ስምምነት ላይ መድረሱን፣ ለግንባታውም 350 ሚሊዮን ብር ሊፈጅ እንደሚችል አክለዋል፡፡

ግንባታውንም ለመፈጸም ረዥም ጊዜ እንደሚጠይቅ ነገር ግን የአደጋው ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ በ500 ሺሕ ብር ወጪ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር ስምምነት በማድረግ ወንዙን የመጥረግ ሥራ እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ከትቦ ገንፍሎ የሚወጣን ፍሳሽ ለመቆጣጠር ተቋሙ በራሱ ወጪ በአንድ በኩል ፍሳሹ እንዲያልፍ ግንባታ መፈጸሙን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ ሥራዎች ከተጠናቀቁ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ሥጋት አይኖርም ያሉት አቶ ምሕረት፣ ይኼንንም ታሳቢ በማድረግ መንግሥት በሌሎች ቦታዎች ላይ የቅድመ መከላከል ሥራ ማከናወን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በከተማዋ 161 ቦታዎች ተለይተው የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ተጀምሯል፡፡

በዚህም መሠረት በተለያዩ ቦታዎች ለጎርፍ አደጋ የሚያጋልጡ ቦታዎች ቢለያዩም በዋናነት ፒያሳ፣ አምባሳደር፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወንዝ ዳርቻ አካባቢዎችና በሁሉም ክፍለ ከተማ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ተለይተዋል፡፡

በእነዚህም አካባቢዎች ወንዞች አቅጣጫ ጥሰው እንዳይሄዱ የድጋፍና የግንባታ ሥራ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች በአዲስ መልክ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ከመሥራት ባለፈ በቆሻሻ የተደፈኑ መስመሮችን የማፅዳት እንዲሁም የማደስ ሥራ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የቅድመ ዝግጅቱንም ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንና ከወንዞች ዳርቻና የአረንጓዴ ልማት ማስፋፊያ ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሠራ ይሆናል፡፡

በዘንድሮ የክረምት ወቅት ጎርፍና መሰል አደጋዎች ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ማስታወቁ የሚታወስ ቢሆንም፣ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ገና አላለቁም፡፡

ይህም አዲስ አበባን ለዳግም የጎርፍ አደጋ ሊያጋልጣት ይችላል፡፡ አምና ከባድ ጎርፍ በተከሰተበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ ችግሩ እንዳይከሰት የሚሠራ መሆኑን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ ሥራዎቹ ገና አልተጠናቀቁም፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ ገና የግንቦት ዝናብ ሳምንት እንኳን ሳያስቆጥር የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡

ባለፉት ዓመታትም በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ እንደነበር፣ 1,095,350 ዜጎች ላይ የጎርፍ አደጋ እንደደረሰና ከእነዚህም ውስጥ 313,179 ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም.   በአዲስ አበባ  የጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ አስከትሎ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ በአስኮ፣  በአደይ አበባ፣  በጀርመን  አደባባይና  በጎልፍ  ክለብ  አካባቢ  በደረሰው  ከፍተኛ  የጎርፍ  አደጋ  መንገዶች  ጭምር እንዲዘጉ ያደረገ ነበር፡፡ ዘንድሮስ የመከላከል ሥራው ተጠናቆ የከተማዋ የጎርፍ ተጋላጭነት ይቀንስ ይሆን?  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...