Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በአሁኑ ወቅት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በእጅጉ ያሳስበናል›› አቶ ሔኖክ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በአንቀጽ 85 መሠረት መቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግበው ዕውቅና ያገኙትን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በሙሉ በመወከል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ በአዋጁ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ምክር ቤቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሠረት የእርስ በርስ አስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር በማስቻል፣ የሲቪል  ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመወከልም ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የሚሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሊከተሉት የሚገባውን የሥነ ምግባር ደንብና ማስፈጸሚያ ሥልት ማውጣትና አተገባበሩን በቅርበት የመከታተል፣ በድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር ላይ ለኤጀንሲውና ለቦርዱ ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ሥራ ያከናውናል፡፡ ሲሳይ ሳህሉ ከዚህ ቀደም በአገር በቀልና በውጭ ድርጅቶች በኃላፊነት፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት ትምህርት ዘርፍ በአማካሪነት ለአምስት ዓመት ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሔኖክ መለሰ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አመሠራረትና የሚያከናውናቸውን ተግባራት ቢነግሩን?

አቶ ሔኖክ፡- የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2020 ነው የተመሠረተው፡፡ ምክር ቤቱ በዋነኝነት ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንደኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፍን መወከልና ማስተባበር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የራስ በራስ አስተዳደር፣ ማለትም ተጠያቂነትና ግልጽነትን በዘርፉ ማስፈን ነው፡፡ ሁለተኛው ለዚህ የሚሆን የሥነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀትና ለተግባራዊነቱ ደግሞ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ባለሥልጣን በተለይ በምዝገባና በአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ማማከር ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሦስቱ ፕሬዚዳንቶችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ናቸው፡፡ እነሱም የተለያዩ የቦርድ ሥራ ያከናውናሉ፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ ምክር ቤቱ በምዝገባም ሆነ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ያማክራል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ ዕውቀቶችን ማደራጀትና ማሠራጨት፣ ይህንን ተከትሎ ደግሞ እነዚህ ዕውቀቶች ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ማስቻል፣ ከዚያም ባለፈ የፖሊሲ አድቮኬሲ ሥራ ማከናወንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ወይም ዘርፉን ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲያውቁት ማድረግ የሚሉትን ዓላማዎች መሠረት አድርጎ የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የሰቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ፡፡ ሁሉም  የምክር ቤት አባል ናቸው?

አቶ ሔኖክ፡- የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዘርፉን እንዲወክልና እንዲያስተባብር ሥልጣን ሲሰጠው፣ አባላቱ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ይህ ማለት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሆነው በባለሥልጣኑ የምዝገባ ሰርተፊኬት ሲያገኙ የዚህ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ የተለየ የሚጠየቁት አባልነት ወይም የሚመዘገቡበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተመዘገቡ ከ3,700 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ400 በላይ የሚሆኑት ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ280 በላይ የሙያ ማኅበራት፣ የሴቶችና የወጣቶች ፌዴሬሽኖች፣ የመምህራን ማኅበርና የኢኮኖሚክ አሶሼሽን፣ መሰል አገር በቀልና ሌሎች ድርጅቶች አሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ምዝገባ የማያደርጉ ከሆነ እንዴት አባል መሆናቸውን ሊያውቁ ይችላሉ?

አቶ ሔኖክ፡- እንግዲህ ይህ ምክር ቤት አዲስ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ ይፈልጋል፡፡ እስካሁን ለሁሉም ተደራሽ ነን ብለን አናስብም፡፡ ያው ሒደት ስለሆነ በተቻለ መጠን ምክር ቤቱም ያለውን ሁኔታ እያስተዋወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ስድስት ክልሎች የማስታወቂያ መድረክ አዘጋጅተን፣ በጥምረቶችና በድርጅቶች በኩል መረጃውን በተቻለ መጠን ለማድረስ ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ከ3,700 በላይ የሚሆን ቁጥር ላይ ለማድረስ ያስቸግራል፡፡ በዋነኝነት ግን በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው በተለይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ሆነው ሲመዘገቡ፣ ለሚወጡ ሕጎችና ለሚኖሩት እንቅስቃሴዎች እያንዳንዱ ማኅበር ንቁ ሆኖ ቢከታተል ምክር ቤቱ ምን እንደሚያደርግና እንደሚሠራ ማወቅ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ምክር ቤቱን ብቻ ሳይሆን የሚወጡ መመርያዎች ይዘት ምን ዓይነት እንደሆነና ሕጎች ማወቅ ድርጅቶችን የሚመለከታቸው ጉዳይ ስለሆነ፣ የራሳቸው ምክር ቤትና መመርያዎች ስለሆኑ ተከታትለው ቢያውቋቸው ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ስዚህ መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ በተለይ በእኛ ተቋም የአባላት ዳይሬክቶሬት የሚባል አለ፡፡ መረጃው በደንብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በተለያየ ሁኔታ መረጃውን ለማድረስ እኛም እየሠራን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ ሲሆኑ የሚያገኟቸው ጥቅሞች ምንድናቸው?

አቶ ሔኖክ– የሚወክልና የሚያስተባብር አካል መኖሩ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተለይ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ሲታይ ቀደም ብሎ በነበረው ክፍተት ምክንያት፣ ሁሉንም የሚወክልና የሚያስተባብር አካል ባለመኖሩ በርካታ ችግሮች ሲከሰቱ ነበር፡፡ ስለዚህ በጋራ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ መሥራት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም በዕውቀት ሐሳብን ወደፊት በማውረድ፣ ለምሳሌ ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ትልቁ ሥልጣን ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሥልጣን ቀደም ብሎ መንግሥት ያከናውነው የነበረ  ነው፡፡ ነገር ግን አሁን መንግሥት ፍላጎቱን በመግለጽ በሕግ አስቀምጦ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ራሳቸውን በራሳቸው ሊያስተዳድሩ ይችላሉ ብሎ ሲሰጥ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ባለቤትነቱ ከመንግሥት ወደ ራሳቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሲዞር የመሥራት ነፃነት ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የአገሪቱን ሕግ አክብረው እስከሠሩ ድረስ ነው፡፡ ሉዓላዊነትን ሳይጋፉ ሕግን ካከበሩ ሊደርሱባቸው የሚችሉ ተዕፅኖዎችን የመቋቋም አቅም ይሰጣቸዋል፡፡ በተሻሻለው ሕግ በርካታ ተገድበው የነበሩ ዘርፎች ላይ መሥራት ተችሏል፡፡ ስለዚህ ይህ ሲሆን ደግሞ ራስን በራስ ማስተዳደሩ ለሚያከናውኑት ሥራ ነፃና ገለልተኛ በመሆን ከተፅዕኖ ውጪ ሆነው እንዲሠሩ ትልቅ በር የከፈተ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ትልቁ ሥራ ዘርፉን መጠበቅና ድርጅቶቹ በነፃነት እንዲሠሩ ማስቻል፣ ሐሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ማድረግ፣ ዕውቀትን እያደረጁ እንዲያካፍሉ የሚያደርግ ጥቅሞችን ይሰጣል ማለት ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ምክር ቤቱ ለማኅበራቱ መብት ተቆርቋሪ ሆኖ ጥብቅና ይቆማል  ማለት ነው?

አቶ ሔኖክ፡- እንግዲህ አንዱ ትልቅ ነገር በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ የምፈልገው ይህ ምክር ቤት የተሰጡትን የውክልና፣ የማስተባበር፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የማማከር ዓይነት ወሳኝና ስትራቴጂካዊ የሆኑ ጉዳዮች ያከናውናል፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በየዕለት ተዕለት ሥራው የሚደርስበትን ወይም የሚገጥመውን ችግር እየተከታተለ መሥራትና ማገዝ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ምክር ቤት በመሆኑና ከምክር ቤቱ በታች ጥምረቶች አሉ፣ ፎረሞች አሉ፡፡ ይህ ማለት ተመሳሳይ ዓይነት ሥራ የሚሠሩ ድርጅቶች በጋራ መጥተው የሚወያዩባቸውና የሚሠሩባቸው መድረኮች በመኖራቸው፣ ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች አይሠራም፡፡ ነገር ግን በአገራዊና ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከቱ ሥራዎችን ነው የሚመራው፡፡ ይሁን እንጂ የምክር ቤቱን ጣልቃ ገብነት ወይም ተሳትፎ የሚፈልጉ ጉዳዮች ሆነው ሲገኙ፣ በተናጠልም ቢሆን ጉዳዮች እንዲታዩ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ድርጅቶችን እንጠብቃለን ስንል ይህንን ማለታችን በመሆኑ፣ በተለየ ሁኔታ የሚደርሱባቸው ችግሮች ካሉ ወደ ምክር ቤቱ መጥተው የመመካከርና ችግሮቻቸው ወደፊት መጥተው እንዲታዩ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ተግባራት አንዱ የመንግሥትን ፖሊሲ መገምገምና ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን የመንግሥት አካላትን ተጠያቂ እንዲሆኑ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አንዱ ትልቁ ሥራ አሁን የጠቀሰው ጉዳይ ነው፣ ማለትም ፖሊሲዎችን መከታተል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ፖሊሲዎች ተፈጻሚ ሲሆኑ በሕዝብ ላይ ቀጥታ የሆነ ጥቅም ወይም ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጀቶች እነዚህ ፖሊሲዎች የሕዝብን ተጠቃሚነት ያረጋግጣሉ ወይ? ሙሉ ናቸው ወይ? ክፍተት አለባቸው ወይ? ወይም አንዳንድ ጊዜ ፖሊሲም ላይኖር ይችላል፣ በዚህ ጊዜ ግብዓት በመስጠት ፖሊሲ እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ እንግዲህ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ሥራዎችን ሠርተዋል ቢባልም ነገር ግን አጥጋቢ አይደለም፡፡ አንደኛው ምንድነው? ለረዥም ጊዜ በመብት ወይም በአድቮኬሲ ሥራ እንዳይሠሩ ተገድበው ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን በእርግጥ ያ ነገር በሕግ ክልከላ የለበትም፡፡ ስለዚህ በስፋት እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን መሥራት አለብን ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሥራዎችንም እየሠራን፣ በዋነኝነት ግን በጥናት ላይ ተመሥርተን በመረጃና በማስረጃ ላይ የተደገፈ የፖሊሲ ግብዓት ማቅረብ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በእጅጉ ያሳስበናል›› አቶ ሔኖክ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት አገራዊ የፖለቲካ ቀውስ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- በዋነኝነት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ትኩረት ሰላም እንዲመጣና እንዲረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ፍላጎት መሳካትም በሚገባ መሥራት አለባቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በግጭትና በጦርነት ውስጥ ነው ያሳለፍነው፡፡ ይህ ጦርነት ደግሞ በጣም ብዙ ኪሳራ ከማድረሱ በላይ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ለደረሰው ጉዳትና መፈናቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የማይናቅ ሚና አላቸው፡፡ ያ ማለት ባላቸው ፋይናንስም ሆነ የተለያዩ ዕርዳታዎችን በማሰባሰብ የደረሰውን ኪሳራ በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ተችሏል፡፡ አሁንም ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው ያሉት፡፡ ሌላው በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በኩል ጥሪ ተደርጎላቸው በገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ምክር ቤቱም በመቀስቀስ ሀብት እንዲሰባሰብ የማድረግ ሥራ ሠርቷል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን በጉዳዩ ላይ የእኛን ምልከታና አቋም በመግለጫዎች ገልጸናል፡፡ ለሰላም ትልቁ አማራጭ ድርድር እንደሆነ፣ ያንንም እንደምንደግፍና የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን ለመንግሥትና ለተለያዩ አካላት ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ አሁንም ይህንን ችግር ሊፈታ ይችላል ብለን በምናስበው በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ሚና አለን ብለን እናስባለን፡፡ በዚህ ረገድ በተቋማችን ውይይት እያዘጋጀን እንገኛለ፡፡ አንዳንድ ውይይቶችንም ከኮሚሽኑ ጋርም ሆነ እርስ በርሳችን እያካሄድን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አገራዊ  የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ተሳትፏችሁ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ሥራ እያከናወናችሁ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከመጀመርያው ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ጀምሮ ስንሳተፍ ነበር፡፡ በየመድረኮቹና ፓርላማ ጭምር እየተገኘን ሐሳባችን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ እንግዲህ ኮሚሽኑ ከተቋቋመና ወደ ሥራ ከገባ በኋላ፣ ጉዳዩ ለአገራችንና ለሁላችንም አዲስ እንደመሆኑ መጠን በመረጃ ራሳችን ስናዘጋጅ ነበር፡፡ ምንድነው መደረግ ያለበት? በሚለው ላይ ራሳችንን ግልጽ የማድረግና የማብቃት ሥራ ሠርተናል፡፡ ሁለተኛ ለአገራችን አዲስ ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የሌሎች አገሮች ተሞክሮዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ምን ይመስላል? ተሳትፏቸው ምን ነበር? የሚለውን በጥልቀት ለመመርመር ሞክረናል፡፡ በዚህ ሒደት ያገኘነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ነው፡፡ እንዲያውም እንደ ቱኒዚያ ባሉ አገሮች ደግሞ የምክክር ኮሚሽን የተመራው ወደ አራት በሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ነበር፡፡ እኛም ከዚህ ለመማር ችለናል፡፡ ይህንን ዓይተን ደግሞ በአገራችን ደግሞ የእኛ ሚና የጎላ ነው ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ምን ዓይነት ሚና ይኖረናል? የሚለውን ጉዳይ በምክር ቤታችን ውስጥ መድረኮች በማዘጋጀት ውይይት አድርገናል፡፡ አንደኛው ጽንሰ ሐሳቡ ምንድነው የሚለውን ጉዳይና በኢትዮጵያ አገራዊ ኮሚሽኑ ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ላይ ተወያይተን፣ አንድ የምንሳተፍበትን አቅጣጫ የሚያሳይ ሰነድ አዘጋጅተናል፡፡ ከምክክር ኮሚሽነሮቹ ጋርም ተወያይተናል፡፡ ያን ያደረግንበት ዋናው ምክንያት የምክክር ኮሚሽኑ ምን ላይ ነው የሚያተረኩረው? ፍላጎቱ ምንድነው? የሚለውን ግልጽ የሆነ መረጃ ለማግኘት ስለነበር በሒደቱ በጣም የተሳካ ውይይት አካሂደናል፡፡ ከዚያ ባገኘነውና እኛም ባደረግነው ውይይት ራሳችንን ለማዘጋጀት ረድቶናል ብለን እናስባለን፡፡ አሁን የምናስበው ምንድነው? አንደኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ወጥ በሆነ መንገድ ሚናቸውን ቢወጡ ለአገር ጠቃሚ ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የእኛ ምክር ቤት ደግሞ ለማስተባበርና ለመወከል ሥልጣን እንደተሰጠው አካል ይህንን ሚና መጫወት እንፈልጋለን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የያዝነውን ጉዳይ ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች የማስተዋወቅ ሥራ ይጠብቀናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ መናበብ ያስፈልጋል፡፡ ከምክክር ኮሚሽነሮቹ ጋር በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለውን በተለይም እኛ ይኼ ምልከታ አለን፣ የቱ ጋ ብንተጋገዝ ይሻላል? የሚለውን እንናበባለን፡፡ በዚህ ሒደት እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች የምክክር ኮሚሽኑ ተፅዕኖ እንዳይደርስበት፣ በተለይ የሕዝብ ውስጣዊ ጉዳይ በመሆኑ ከየትኛውም አካል የሚመጣን ጫና ለመከላከል ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርባችሁ ትሠራላችሁ? ምን ዓይነት ባህል ነው ያላችሁ?

አቶ ሔኖክ፡- እዚህ ላይ እንግዲህ ወደኋላ መለስ ብዬ ብጀምር ደስ ይለኛል፡፡ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶች አሉ፡፡ ከመንግሥትና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከግል ድርጅቶችና ከሚዲያ ጋር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቀራርቦ መሥራታቸው እምብዛም የለም የሚል ድምዳሜ ከጥናቶቹ አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ይህ ምክር ቤት አዲስ እንደ መሆኑ መጠን አንዱ እያደረግነው ያለው ነገር ምንድነው? ከመንግሥትም ሆነ ከላይ ከተጠቀሱት አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል የሚል አቋም አለን፡፡ እንግዲህ ይህ አዲስ አካሄድ ነው፡፡ በዓለም ላይም የሚታወቀው በጣም ተቀራርቦ መሥራት ነው፡፡ ለአገር ልማትና ለዴሞክራሲ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለን እኛም እናምናለን፣ ዓለም እንዲህ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ስለዚህ ምን እያደረግን ነው? አንደኛ ብሔራዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶችና የመንግሥት የጋራ ፎረም አቋቁመናል፣  የምክክር መድረክ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከእኛ ሥራ ጋር ቅርብ ከሆኑ ተቋማት፣ በተለይ እንደ ሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎችም ጋር ተቀራርበን በጋራ ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ በሌላ በኩል ከፖለቲካ ፓርቲዎችና የጋራ ምክር ቤት ጋር በቅርብ ጊዜ ምክክር አድርገናል፡፡ አብረን መሥራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ተማምነን በጋራ ለመሥራት ወስነን ተማምነናል፡፡ ሦስተኛው የሚዲያና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች የጋራ ፎረም አቋቁመናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድም በጋራ የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ለመሥራት እየሄድን ነው፡፡ ይኼ ምክር ቤት በዋነኝነት እነዚህን ሥራዎችን ለመሥራት ነው ትልቁ ዓላማው፡፡ መንግሥት ያቀርበናል፣ አያቀርበንም የሚለውን ጉዳይ ተቀራርበን የምንሠራበት ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን በእውነት ለመነጋገር በጥርጣሬ የተሞላና አለመተማመን የሰፈነበት ነበር፡፡ ይኼ መለወጥ አለበት፡፡ የሁሉም አካል ዓላማው አንድ ነው፡፡ ሕዝብን ማገልገልና አገርን መጥቀም በመሆኑ ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ተባብረን ስንሠራ ደግሞ ሁሉም የሚኖረው ሚና አለ፡፡ መንግሥትም የመንግሥትነትን፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በተሰጣቸው ኃላፊነት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተሰጣቸው ልክ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በአገር ጉዳይ አንድ በሚያደርጉ ዕሳቤዎች ላይ አብረን መሥራት ይኖርብናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ አሁን ከሚስተዋለው ግጭት ወይም ጦርነት አኳያ በተለይ ከመንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ከገቡ ኃይሎች/አካላት መፍትሔ ለመሻት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ምክር ቤት ምን እያደረገ ነው?

አቶ ሔኖክ፡- ይህ እንግዲህ በቀጥታ ይመለከተናል፡፡ ምክንያቱም ይኼ አለመግባባት ሕዝባችን ላይ ችግር ያመጣል፡፡ በተለይ ሕዝብ ይሞታል፣ ይፈናቀላል፡፡ ስለዚህ እኛ በዋነኝነት የቆምነው ለሕዝብ በመሆኑ ጉዳዩ በጣም ያሳስበናል፡፡ በዚህ ረገድ የምናደርገው ምንድነው ሲባል እንመካከራለን፣ ሁኔታውን እንገመግማለን፣ ሐሳባችንን ደግሞ እናጋራለን፡፡ በተለይ ደግሞ ሁሉም አካል ችግሩን በውይይት እንዲፈታና ወደ  ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲመጣ ማስቻል ነው ሥራችን፣ የምንመክረውም ይህንኑ ነው፡፡ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ካለ በጣም ዝግጁ የሆነ ምክር ቤቱ ነው ያለን፣ ብዙ ጥረቶችንም እያደረግን ነው፡፡ እንግዲህ መሣሪያ ባይኖረንም ገለልተኛ ስለሆንን እንሰማለን ብለን እናስባለን፡፡ የምናደርገው እንግዲህ ድምፃችን ማሰማት፣ ምክረ ሐሳቦችን መሰንዘርና ያሉንን ምልከታዎች ቶሎ ቶሎ ማቅረብ ነው፡፡ እያደረግን ያለነውም ይኼንን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ  ከገባችበት ጦርነት ውስጥ በተወሰነ ደረጃ  ወጥታ ወደ ተሻለ ምክክር ለመሄድ ትሄዳለች ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት፣ እንደ አዲስ የጦርነት ነጋሪት  ጉሰማና ቅስቀሳ እየተሰማ ነው፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ ምክረ ሐሳባችሁ ምንድነው?

አቶ ሔኖክ– እዚህ ላይ እንግዲህ በጣም ግልጽ የሆነ መልዕክት ነው ያለን፡፡ እስካሁን የደረሰው ኪሳራ ከፍተኛ ነው፡፡ ያንን ኪሳራ መልሰን አልጠገነውም፣ ብዙ ጊዜ ይፈጅብናል፡፡ ነገር ግን ተመልሰን እንደዚህ ዓይነት የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ ስንሰማ በእጅጉ ነው የሚያስደነገጠንና የሚያሳስበን፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ችግር በዘለቄታዊነት ሊፈታ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ ሌሎች የሰላም አማራጮችን እስከ መጨረሻው ድረስ ሄዶ መጠቀም ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር እንግዲህ ያላገገመ ሕመም ውስጥ እያለን ሌላ ጥፋት ነው የሚሆነው፡፡ ስለሆነም ችግሩ እጅግ ያሳስበናል፣ እኛም እየገለጽን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በባለሥልጣኑ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትነት ተመዝግበው የት እንዳሉ የማይታወቁና ምን እየሠሩ እንደሆነ ለሕዝቡ ግልጽ ያልሆኑ፣ ለሀብት ምንጭነት እንጂ መሬት ላይ የሚሠሩት የማይታወቅ፣ የተወሰኑት ደግሞ በጥቂት ሰዎች ብቻ የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ቅሬታ ይሰማል፡፡ በዚህ ረገድ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምዝገባቸው መሠረት አለመሥራታቸውን እንዴት ታያላችሁ? ቅሬታውንስ እንዴት ትገመግሙታላችሁ?

አቶ ሔኖክ፡- ይህ እንግዲህ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዋናነት የያዘው ጉዳይ ነው፡፡ ተመዝግበው ምን እየሠሩ እንዳሉ የማናውቃቸው ድርጀቶች ይኖራሉ፡፡ ምክር ቤቱ አዲስ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ቅሬታ ስማቸው የሚነሳ እነ ማን ናቸው የሚለውን ነገር፣ በቅርበት ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር ተመካከርን የምንሠራበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ምክር ቤት ግን አንዱ የያዝነው የሥነ ምግባር ደንብ ተዘጋጀቷል፡፡ በቁጥራቸው ልክ ታትሞ ለሁሉም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዲስም ለሆኑት ጭምር እንሰጣለን፡፡ ስለዚህ ያሉበትን ሁኔታ ከባለሥልጣኑ ጋር ሆነን እናያለን፣ እንገመግማለን፡፡ ተመዝግበው ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ በዋነኝነት የእኛ አንዱ ሥራ ነው፡፡ ማለትም ራስን በራስ ማስተዳደር ሲባል እነማን ናቸው? ምንድነው የሚሠሩት? ከሕግ ውጪ የሚሠሩት ሥራ ምንድነው? ብለን በመለየት ዕርምጃ እስከ ማስወሰድ ደረጃ እንደርሳለን፡፡ ምክር ቤቱ በጣም አዲስ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ብልሹ አሠራርን እናጠፋለን ብለን እናስባለን፡፡ በጣም በትልቁ የምናየው ግን እንዲህ ዓይነት ድርጊ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች በቁጥር ብዙ ናቸው ብለን አናምንም፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹን ድርጅቶች እናውቃቸዋለን፡፡ በጣም መልካም ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥቂት የሚባሉ ድርጅቶች ትልቁን ሥዕል እንዲያበላሹ አንፈልግም፡፡ ተከታትለን የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው እናደርጋለን፡፡ ሥራው ቀጣይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፋይናንስ ምንጭ የተገደበ ነበር፡፡ አሁን ችግሩ ተስተካክሎ ነፃነት ተሰጥቷችኋል፡፡ ይህ አዲስ ነፃነት ምን ፈጠረላችሁ? ምንስ የተሻለ ተሳትፎ ልታደርጉ ትችላላችሁ? ከበፊቱ የተለየ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ ሔኖክ– አሁን ትልቁ ጉዳይ አንደኛው ሕጎች ሲወጡ ታሳቢ የሚያደርጉት ነገር ከኋላ ያለው ነገር ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ይህ ማለት በፊት የወጣው አዋጅ የፋይናንስ ሥርዓቱን ብቻ ሳይሆን፣ ከፋይናንስ ሥርዓቱ ጋር አብሮት የያዛቸው በርካታ ሥራዎች እንዳይሠሩ የገደበ ነበር፡፡ ዛሬ የምናወራውን የሰላም፣ የመብትና የዴሞክራሲ ጉዳይ በዚያ ጊዜ አይሠራም ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ የፋይናንስ አቅም እንዳያገኝና ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ የገደበ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህኛው አዲስ አዋጅ አንዱ የተሻሻለውና የወጣው ትልቁ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ የፋይናንስ ገደብ የለም፡፡ እንደገና ልንሠራባቸው የምንፈልጋቸው ሥራዎች ሁሉ ተፈቅደውልናል፡፡ ይህ በቀድሞው ሕግ ያልነበረ አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሕጉን ተከትሎ ደግሞ በርካታ ድርጅቶች በእዚህ ላይ ለመሥራት ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ነባር ድርጅቶች ደግሞ አንዳንድ ጉዳዮቻቸውን በአዲሱ አዋጅ አስተካክለውና አጣጥመው ለመሥራት እየሞከሩ ነው፡፡ አዳዲሶቹም እንዲሁ እየሠሩ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ምንድነው? ምን አመጣ? የሚባለው ነገር በሒደት ነው የሚታየው፡፡ ማለትም መጀመርያ ድርጅቶች ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ አንዳንዱ ሐሳብም የፋይናንስ አቅምም ጠፍቶበት የነበረውን በቀላሉ በሕግ በማሻሻል ብቻ የሚመለስ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ሀብት ማፈላለግና ማንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ ዕውቀቱንም ተገድቦ ከነበረበት እንደገና መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ ነገር ምንድነው? እነዚህ ጉዳዮች ላይ መሠራት ስለተቻለ ድርጅቶቹ በጋራም ይሁን በተናጠል አሁን መሥራት ጀምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወደፊት በተግባር በጊዜ ሒደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ራሳቸውን አጠናክረውና ሠርተው ውጤት ማሳየት አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ወር መጨረሻ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሳምንት ታከብራላችሁ፡፡ ይህ የምታከብሩት ሳምንት ዓላማው ምንድነው?

አቶ ሔኖክ– ይህ ብሔራዊ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች ባለሥልጣን ጋር በጋራ በሒልተን ሆቴል ‹‹ንቁ የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶች ለሰላምና ለዴሞክራሲ ልማት›› በሚል መሪ ቃል የሚከበር ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰላምም በልማትም የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ስለዚህ ዘርፉን ማነቃቃት እንፈልጋለን፡፡ የተነቃቁ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሲኖሩ ጥሩ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለን እናምናለን፡፡ ዋና ዓላማው ግን እነዚህን ድርጅቶች በማነቃቃት ለአገር ልማት ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ ነው በትልቁ ይዘነው የተነሳነው፡፡ ሌሎች ዝርዝር ዓላማዎችም አሉት፡፡ እነዚህን ዓላማዎች ለሕዝብና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ ምን እየሠሩ ነው? የሚለው መታወቅ አለበትና በዚህ መድረክ ሥራዎቻቸውን ወደፊት አምጥተው ማስተዋወቅ ይኖርብናል፡፡ ሌላው ጉዳይ የሲቪል ድርጀቶች ገጽታ የተበላሸ በመሆኑ ዕይታውንና ገጽታው መቀየር እንፈልጋለን፡፡ ይህ ሊቀየር የሚችለው ደግሞ ድርጅቶች ወደፊት መጥተው ሥራዎቻቸውን ለሕዝብም ሆነ ለባለድርሻ አካላት ይፋ ሲያደርጉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከባለድርሻ አካላት በተለይም ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ፣ እርስ በርስና ከሚዲያ ጋር ትስስሩን አጠናክረን በጋራ በአገራችን ጉዳይ ላይ ለመሥራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለን እናስባለን፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ዘርፎች የሚሠሯቸው በጎ ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህን ሥራዎች ደግሞ ለሕዝብ አቅርቦ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ልምዶቻቸውን ማከፋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሄዱበትን መንገድ ለሌላው ማሳየት አለባቸው፡፡ ከዚያ ባለፈ የተለያዩ መረጃዎችና ዕውቀቶች ይንሸራሸሩበታል፡፡ በዚህ በሚከበረው ሳምንት ሚዲያዎች ይመጣሉ፣ ድርጅቶች ይገኛሉ፣ በዕለቱ የሚቀርቡ ጉዳዮች ለሕዝብ ይቀርባሉ፡፡   

ሪፖርተር፡- በዓሉ በአዲስ አበባ ብቻ ነው? ወይስ በክልሎችም ይካሄዳል?

አቶ ሔኖክ፡- የሚከበረው የሲቪል ድርጅቶች ሳምንት ብሔራዊ በዓል በመሆኑ፣ አንድ ቦታ በአዲስ አበባ ብቻ ነው የሚከበረው፡፡ በዚህ ዝግጅት ውስጥ ከክልል የሚመጡ ጥምረቶች ተገኝተው ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ ሁኔታዎችንም እያመቻቸን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በዓል የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ይገኛሉ፣ ለሕዝብም ክፍት ይደረጋል፡፡ ሕዝቡ እንዲሰማ ቅስቀሳ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ ሕዝቡ ስለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማወቅ ያለበት ጉዳዮች እንዲደርሱ ይደረጋል፡፡ ቅስቀሳውን በማኅበራዊ ሚዲያም በመደበኛ መገናኛ ብዙኃንም እያስተዋወቅን ነው፡፡ ብሔራዊ የሲቪል ማኅብረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከሰኔ 25 እስከ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ በሒልተን ይከበራል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...