ቋራ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለውንና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ባለ 48 እና 30ፎቆች ያሉት መንታ ሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ከቻይናው ሲሲኢሲሲ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡
ለመኖሪያና ለተለያዩ የቢዝነስ አገልግሎቶች ይውላል የተባለው ይህ መንታ ሕንፃ የሚገነባው አዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ እንደሆነ ስምምነቱ በተጠናቀቀው ሳምንት በተፈጸመበት ወቅት ተገልጿል፡፡
ከዚህ ሕንፃ ሌላ በሁለተኛ ምዕራፍ የሚሠራ ለፓርኪንግና ለሆቴል አገልግሎት የሚውል ሕንፃ እንደሚገነባም ታውቋል፡፡ በመጀመርያው ምዕራፍ የሚገነባው ባለ 48 እና ባለ 30 ፎቅ መንታ ሕንፃ መካከል አንደኛው የሕንፃው ክፍል ሙሉ ለሙሉ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውል ሲሆን ባለሁለት፣ ባለሦስትና አራት መኝታ ክፍሎችን የሚይዝ ነው፡፡ ይህ የሕንፃ ክፍል 30 ፎቆች ይኖሩታል፡፡
ሌላው የሕንፃ ክፍል ደግሞ ለተለያዩ ቢዝነሶች የሚውል ሲሆን 44 ፎቆችና 219 ሜትር ርዝማኔ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ የዚህ ሕንፃ ርዝማኔ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ረዥሙ ሕንፃ በመባል ከሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ የሚበልጥ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ መሃንዲስ የዥቅአ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አማካሪ ሥራ አስኪያጅ ውብሸት ዥቅአለ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ ርዝማኔ 209 ሜትር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ውብሸት (ዶ/ር) ገለጻ ይህ ፕሮጀክት ከባንክ ውጪ በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ የሚገነባ ትልቁ ፕሮጀክት ነው፡፡ የሕንፃው ከምድር በታች አራት ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን የዲዛይን ሥራውም በተለየ መልኩ እንዲከናወን መደረጉ ተግልጿል። በፎቆች መካከል የአረንጓዴ መናፈሻ ስፍራን (ግሪን ኤርያ) ያካተተ ሲሆን አዲስ አበባን ከአራቱም አቅጣጫ ለመመልከት የሚያስችል እንዲሁም በአራት መንገዶች መካከል የሚገነባ ነው፡፡
የሕንፃውን ግንባታ በስድስት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን ፣ በቅድሚያ ግን የመኖሪያ ቤቶቹን ክፍል የያዘው ሕንፃ ይገነባል፡፡ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ የመኖሪያ ቤቶቹን በኪራይና በሽያጭ የማስተላለፍ ዕቅድ ተይዟል፡፡
የመጀመርያው ምዕራፍ መንታ ሕንፃ በ5,743 ሜትር ስኩዌር ቦታ ላይ የሚሠራ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍና ዲዛይን መረጣ ላይ የሚገኘው ሌላ ሕንፃ ደግሞ ከዚሁ ሕንፃ ትይዩ ባለ አራት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ይሆናል፡፡
ካሳንቺስ አካባቢ በሊዝ በተረከበው በተለይ የሚገነባው ይህ ዘመናዊ ሕንፃ በምዕራፍ ሁለት ከሚገነባው ሕንፃ ጋር በመንገድ የሚገናኝ ይሆናል ተብሏል፡፡
የዚህን ግዙፍ ሕንፃ ዲዛይኑና የኮንስትራክሽን ግንባታውን በማጣመር ለመሥራት ውለታ የፈጸመው የቻይናው ተቋራጭ ሲሲኢሲሲ ሲሆን ፤ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከገነባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ አብዛኛዎቹን የኢንዱስትሪ ፓርኮችም የገነባውም ይኸው ሲሲኢሲሲ ኩባንያ፣ ከዚህ በተጨማሪም በትላልቅ የመንገድ ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ የሕንፃው ባለቤት የሆነው ቋራ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወነ የግል ማኅበር በነዳጅ ማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማራው የጉምጁ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እህት ኩባንያ ሲሆን፣ በተለያዩ የቢዝነስ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችም አሉት፡፡
ከትናንት በስቲያ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት ቋራን በመወከል የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ የሽዋስ ሲሆኑ ሲሲኢሲሲን በመወከል ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሊዩ ዶንግ ናቸው፡፡
ዥቅአለ ኮንስትራክሽንና ማኔጅመንት ኮንሰልታንት ከእነዚህ ሕንፃዎች ሌላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ ግንባታ ከፕሮጀክቱ ጥንስስ ጀምሮ በከፍተኛ አማካሪነት እንዲሁም አዲስ በሚገነቡት የአቢሲኒያና የአማራ ባንክ ሕንፃ ግንባታ ላይ በተመሳሳይ በማማከር ሥራ ላይ እየሠራ ነው፡፡