Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በምግብ ሸቀጦች ላይ የተደረገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ነዋሪውን አማሯል

ተዛማጅ ፅሁፎች

R 2308 News/Business B5

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት ውስጥ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ነዋሪውን አማሯል፡፡

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የግንቦት ወር አጠቃላይ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርትን ይፋ ባያደርግም፣ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ለሸመታ የወጡ ነዋሪዎች እንዳስታወቁት ባለፉት ሳምንታት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ቀደም ሲል ከነበሩት ወራት የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል፡፡

ሪፖርተር በአዲስ አበባ በተለያየ አካባቢ ከሰሞኑ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት አሳይተዋል በተባሉ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ ምልከታዎቸን አድርጓል፡፡

በግል ድርጅት ተቀጥራ እንደምትሠራ ያስረዳቸው ወ/ሮ ሠናይት መንገሻ እንዳስታወቀችው፣ በምትኖርበት ሾላ አካባቢ ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በተለይም በምግብ እህሎችና ሸቀጦች ከዚህ ቀደም ከነበረው የበለጠና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል፡፡

ለአብነትም የፉርኖ ዱቄት፣ ዘይት፣ እንቁላል፣ ምስር፣ ወተት፣ መኮረኒና ፓስታ እንዲሁም በደረቅ ሳሙና ላይ በሳምንትና ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ የታየው የዋጋ ማሻቀብ አስደንጋጭ መሆኑን አስረድታለች፡፡

ሾላ አካባቢ አንድ ኪሎ የፉርኖ ዱቄት ከዚህ ቀደም ይሸጥበት ከነበረው የ45 ብር ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት 60 ብር መግባቱን፣ በትንሳዔ በዓል ሰሞን አንድ ሺሕ ብር የነበረው አምስት ሊትር ዘይት በዚህ ወቅት እስከ 1,200 ብር እንደሚጠራ ታውቋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜያት የሳንቲሞችና የአንድ ብር ጭማሪ ይስተዋልበት የነበረው እንቁላል፣ በአጭር ቀናት ውስጥ የሦስት ብርና ከዚያ በላይ ጭማሪ አሳይቶ 12 ብር እየተሸጠ ይገኛል በማለት ሸማቾች ተናግረዋል፡፡

ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኙ የችርቻሮ መደብሮች የፉርኖ ዱቄት ከሁለት ሳምንት በፊት ይሸጥበት ከነበረው የ48 ብር የኪሎ ዋጋ በተጠናቀቀው ሳምንት 63 መድረሱን ለሪፖርተር ያስረዱት ሌላ ሸማች፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 950 ብር የነበረውን አምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይት በ1,100 ብር መግዛታቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

የአገር ውስጥ ምስር በኪሎ 140 የገባ ሲሆን፣ የውጭ የሚባለው 130 ብር እንደሚሸጥ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ሸማች ገልጸው፣ ይህም እስከ 20 ብር ጭማሪ የተስተዋለበት ነው፡፡

በጎፋ አካባቢ በተመሳሳይ የፉርኖ ዱቄት በ60 ብር፣ አምስት ሊትር ዘይት 1,100 ብር መኮረኒ በኪሎ ከ60 እስከ 65 ብር፣ ምስር በኪሎ 130 ብር፣ እንቁላል በ12 ብር መሸጡን ሪፖርተር ከሸማቾች ያረጋገጠ ሲሆን፣ ይህም ከሦስት ብር እስከ 150 ብር የደረሰ የዋጋ ጭማሪ በጥቂት ቀናት ውስጥ የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየዕለቱ እያሻቀበ የሚሄደው የኑሮ ውድነት የኅብረተሰቡ ፈተና ከሆነ ቢሰነብትም፣ የኑሮ ውድነቱን ለመግታት በመንግሥት በኩል የተወሰዱ ዕርምጃዎች የዋጋ ውድነቱን ሊቀንሱት አሊያም ባለበት ሊያረጋጉት አለመቻሉን ሸማቾችና ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑት ወተት፣ ቅቤ፣  ዓይብና ሌሎች ምርቶች እንዲሁም የእንቁላል ዋጋ ጣሪያ እየነካ ይገኛል፡፡ በተለይም ከሰሞኑ የወተት ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱ ሸማቾችን በምሬት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት በመጋቢት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 34.7 በመቶ፣ የምግብ ዋጋ ግሽበት 43.4 በመቶ መድረሱን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን፣ የሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጋር ሲነፃፀር በ42.9 ከመቶ የበለጠ አኃዝ አሳይቷል፡፡ የግንቦት ወር የዋጋ ግሽበት በአንፃሩ እስካሁን በአገልግሎቱ ይፋ አልተደረገም፡፡

በገበያው አለመረጋጋት ሰበብ እየተንሰራፋ ያለው የኑሮ ውድነት በዝቅተኛ ደመወዝ ኑሮውን ከእጅ ወደ አፍ እየመራ ባለው ሠራተኛ ላይ የፈጠረው ጫና ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ መንግሥት ለችግሩ ልዩ ትኩረትና አስቸኳይ መፍትሔ በመስጠት፣ የሠራተኛው ኑሮ እንዲስተካከል የሚያግዙ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በቅርቡ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

መንግሥት በ2015 ዓ.ም የዋጋ ንረቱ ወደ 11 በመቶ ዝቅ ይደረጋል በማለት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የመንግሥት ዕቅድ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ 36 በመቶ የደረሰውን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በአንድ ጊዜ በ25 በመቶ ቀንሶ 11 በመቶ ማድረስ ከባድ ብቻም ሳይሆን የማይታሰብ መሆኑን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት የ2015 ዓ.ም. የረቂቅ በጀት ገለጻ በቀረበበት ወቅት እንዳስታወቁት፣ የዋጋ ንረትን በተመለከተ ባለፉት ዓመታና በተያዘው የበጀት ዓመት ሁለት አኃዝ ዕድገት በማሳየጡ የኢኮኖሚው ከፍተኛ ፈታኝ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡

በኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ አመርቂ ውጤት ያልታየበት የዋጋ ንረት ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አህመድ፣ ከታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ከተመዘገበው 10.4 በመቶ ጭማሪ ጀምሮ በተከታታይ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት በሚያዚያ 2014 ዓ.ም. የ36.6 በመቶ ዕድገት መታየቱን አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች