Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኩታ ገጠም እርሻ በተዛባ አረዳድና መንገድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

R2308 News Business S1

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰፊው በሥራ ላይ እየዋለ የሚገኘው የኩታ ገጠም የእርሻ ልማት በተዛባ አረዳድና አተገባበር እየሄደ መሆኑ ተነገረ፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሙያዎች ማኅበር ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የኩታ ገጠም እርሻ ልማት በሰፊው የሚገመግም ጥናት ቀርቧል፡፡ በዚህ ጥናት እንደተመለከተውም፣ የእርሻ ልማቱ የገበሬውን ፍላጎት በሚጋፋ መንገድ መተግበሩ ለዘርፉ አደጋ ነው ተብሏል፡፡

አርሶ አደሩ የራሴ የሚለው የግል መሬት ሳይኖረውና ማምረት የሚፈልገውን የምርት ዓይነትና መጠን በራሱ ሳይወስን ይዞታውን ለኩታ ገጠም እርሻ ካላዋለ መባሉ፣ የፖሊሲውን ዓላማ የሚያስት መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ኩታ ገጠም እርሻን አስገዳጅ አሠራር ማድረጉ፣ ከ1972 ዓ.ም. የኮሙኒስታዊው ደርግ አሠራር ጋር ሊያመሳስለው የሚችል ነው በሚልም ፖሊሲው ተተችቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ተካሂዶ በነበረው የግብርና ባለሙያዎች ማኅበር ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የአነስተኛ ባለይዞታ አርሶ አደሮች ለገበያ ተኮርና ዘመናዊ ግብርና ያላቸውን ሚና የተመለከተ ጥናት፣ የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) አቅርበው ነበር፡፡ በዚህ ጥናታቸው የችብቻቦ እርሻ ስለሚሉት ኩታ ገጠም (Cluster Farming) ምንነት በሰፊው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የመስኖ (በጋ) ስንዴ ስለሚባለው የእርሻ ልማትና በኩታ ገጠም እርሻ ይሳተፋሉ ስለሚባሉ የሙያ ማኅበራት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጥናታቸውም የኩታ ገጠም እርሻ (ክላስተር እርሻ) ምንነት የተዛባ አረዳድ እንዳለ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሥር ዓመቱ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ላይ ግብርና አንዱ ዋና ዘርፍ ተብሎ መቀመጡን ያመለከቱት ደምስ (ዶ/ር)፣ ግብርናን ለማዘመን የሚረዳ በማለትም የመስኖና ኩታ ገጠም እርሻ ሥራዎችን በዋናነት ማካተቱን ጠቅሰዋል፡፡

የተበጣጠሰ ይዞታ ይዘው የሚያርሱ አርሶ አደሮችን ይዞ ኢኮኖሚን ማሳደግም ሆነ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ስለማይቻል፣ በኩታ ገጠም እርሻ ያላቸውን አቀናጅተው እንዲያርሱ የሚያደርግ አሠራርን ዕቅዱ ማካተቱን ነው በጥናታቸው ያስቀመጡት፡፡ ይህ አሠራር ወደ መሬት ሲወርድ ግን የገበሬውን የማምረትና የምርት ዓይነት የመምረጥ ነፃነት እየተጋፋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አሠራሩ አሁን 200 እና 300 ገበሬዎችን በአንድ አሰባስቦ ይተግበር እየተባለ መሆኑ ደግሞ፣ እንደ 1972 ዓ.ም. የደርግ የግብርና ዕቅድ እያስመሰለው ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የእርሻ ልማት በዋናነነት አቅርቦትን (Supply) ሳይሆን የምርት ተፈላጊነትን (Demand) ባማከለ መንገድ መከወን ያለበት ነው ሲሉ ደምስ (ዶ/ር) በጥናታቸው ሞግተዋል፡፡ ገበሬው የራሱ ባልሆነችና በተበጣጠሰች ይዞታው የማምረት ነፃነቱ ሊረጋገጥለት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ይህን መሠረታዊ ጉዳይ ወደ ጎን በማለት የግብርና ቴክኖሎጂ እናቀርብልሃለንና በኩታ ገጠም ካለረስክ የሚል ጫና ማሳደሩ፣ ከዘርፉ አልፎ በአጠቃላይ የአገሪቱን ምርታማነት እንደሚጎዳ ነው ከ1972 ዓ.ም. ፖሊሲ ጋር በማነፃፀር ያስረዱት፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ገበሬዎች ነፃና የፈለጉትን ማምረት የሚችሉ አርሶ አደሮች ናቸው ብለን የምናምን ከሆነ፣ የፈለጉትን በፈለጉበት መንገድ እንዲያመርቱ መፍቀድ አለብን፤›› ሲሉ በጥናታቸው ሞግተዋል፡፡ በ1972 ዓ.ም. ዕቅድም ሆነ በአሁኑ የኩታ ገጠም እርሻ ዕቅድ ገበሬው የተሻሻለ ለእርሻ አሠራርና ቴክኖሎጂ ስለሚቀርብልህ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ራስህን አደራጅተህ ካላረስክ የሚል ግፊት እያሳደርንበት ነው በማለት፣ አሠራሩ የተሳሳተ ነው ያሉበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡

የመስኖ እርሻ ስለማቋቋምና ስለቴክኒክ ድጋፍም ቢሆን ሁለቱ ዕቅዶች በተመሳሳይ የተሳሰተ አቋም እንደያዙ ነው አጥኚው የጠቆሙት፡፡ ከዚህ ተነስተውም፣ ‹‹በኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ የእርሻ ስፋት ወሳኝነት የለውም፤›› የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን የሚናገሩት ደምስ (ዶ/ር)፣ ‹‹ወሳኙ ነገር እርሻን ገበያ ተኮርና ዘመናዊ ማድረግ ነው፤›› ሲሉ ለቴክኖሎጂ ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ዛሬ በቤት ውስጥ ሳይቀር በዘመናዊ መንገድ ገበያ ተኮር ግብርና ማካሄድ የሚቻልበትን ዕድል ቴክኖሎጂው መፍጠሩን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ‹‹በማይጨበጥ ዕቅድ አርሶ አደራችንን ግራ እያጋባን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመስኖ ስንዴ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል በሚል እንደ አፋር ባሉ አካባቢዎች በኋላቀር የጎርፍ መስኖ (የቦይ መስኖ) እርሻዎች መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አሠራር ሲገመገም መሬቱን ለጨዋማነት እያጋለጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ልክ እንደዚሁ ኩታ ገጠም እርሻ ተብሎ ዘመቻ በሚመስል ሁኔታ ገበሬው ላይ አዲስ አሠራር እየተጫነ ነው ይላሉ ደምስ (ዶ/ር) በጥናታቸው የደረሱበትን ሲናገሩ፡፡ ገበሬው ምን ዓይነት ምርት፣ መቼና እንዴት ማምረት እንዳለበት ያውቃል የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ዝም ብለን የፖለቲካ መጠቀሚያ ባናደርጋቸው፤›› ሲሉ ነው ምልከታቸውን ያጋሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች