Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዓረብ አገር ባንኮች ድጋፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እየተከናወኑ አለመሆናቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ውስጥ በዓረብ አገር ባንኮች ቃል ተገብቶላቸው የሚጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አለመቻሉን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የመጀመርያ አሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን፣ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያርብ ነው፡፡

በሪፖርቱ የበርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየት እንዳሳሰባቸው የምክር ቤት አባላቱ ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሰጡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ በዓረብ አገር ባንኮች በተለይም በዓረብ ሊግ አገሮች በሚተዳደረው የዓረብ ባንክ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት ቃል የተገባላቸው ፕሮጀክቶች፣ ‹‹እየዘገዩ ነው፣ ጉዳዩ ቢታወቅ ጥሩ ነው›› ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ መዘግየት አሳሳቢ በመሆኑ ጉዳዩ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ እየታየ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በግንባታ ሒደታቸው ላይ የመዘግየት ጥያቄ የቀረበባቸው ፕሮጀክቶች በመጪው ዓመት ፋይናንስ ተገኝቶላቸው ይጀመራሉ የሚል ተስፋ አለ ብለዋል፡፡

የዓረብ ሊግ አገሮች የጋራ ባንክ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ቃል ገብቶ የዘገየበት ምክንያት፣ ምናልባት ከአገሮቹ ጋር የተለወጠ ግንኙነት ይኖር ይሆን በማለት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ በአገሮች በመካከል ቋሚ የሚባል ግንኙነት ሊኖር እንደማይችልና ወዳጅነትም ሆነ አለመጣጣም ተቀያያሪ መሆኑን፣ እንዲሁም ግንኙነት ወጥ የሆነ ባህሪ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

‹‹የዛሬ ዓመት ከአንድ ዓረብ አገር ጋር የነበረን ግንኙነት ሊቀየር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በአንፃራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያና በዓረብ ሊግ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ተቀይሯል የሚያስብል ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡

እየተገባደደ ባለው የ2014 በጀት ዓመት በርካታ ቁጥር ያላቸው የፌዴራል መንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች በዋጋ ንረት፣ በፋይናንስ እጥረት፣ በፀጥታ ችግርና በአስተዳደራዊ ማነቆዎች መስተጓጎላቸውን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች ለፓርላማው አስታውቀዋል፡፡

ለአብነትም የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ፣ በ2014 ዓ.ም. በዋጋ ንረት ምክንያት 768 ፕሮጀክቶች ሥራቸውን ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ችግር ዕልባት ለመስጠት ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከማክሮ ኢኮኖሚክ አማካሪ ኮሚቴ፣ ከ38 ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከማዕከላዊ ስታትስቲክ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን አስተባባሪና ሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን በተደረገ ጥናትና የማስተካከያ ሥራ፣ ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ 99 ቢሊዮን ብር አንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በ2014 በጀት ዓመት በ20/80፣ በ10/90 እንዲሁም በ40/60  የመንግሥት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከ22ሺሕ በላይ ቤቶች ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ  የነበረ ቢሆንም፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ምንም ዓይነት ግንባታ አለመካሄዱን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች