Sunday, September 25, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የበጀቱ ነገር ገና ብዙ አለበት!

  የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሰባት በመቶ በታች መሆኑንና ይህም ከዕቅድ ከተያዘው በታች እንደሆነ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጪውን ዓመት በጀት ረቂቅ ሲያቀርቡ ተናግረው ነበር፡፡ በመንግሥት የተጠቀሰው የዕድገት አኃዝና በሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት የሚቀርበው ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ከባድ ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ ነው መባሉ ድንቅ ይላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኮቪድ-19፣ በተለያዩ ግጭቶችና በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚስተዋለው የነዳጅና የተለያዩ ሸቀጦች ዋጋ ንረት ኢኮኖሚው የደረሰበት ጫና ይታወቃል፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት በሚታይባት ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ በመንግሥት በአማካይ 40 በመቶ ገደማ መድረሱ ቢነገርም፣ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል የመስኩ ባለሙያዎች ይሞግታሉ፡፡ የአቅርቦት እጥረቱም ሆነ የየዕለቱ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪም ይናገራል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ለወደሙ መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ፣ ለዕዳ ክፍያ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታና የአገር ደኅንነትን ለማስከበር ይውላል በተባለለት በጀት፣ የደረሰውን ጉዳት እንዲያገግም በማድረግ የኢኮኖሚውን ዕድገት 9.2 በመቶ እንደሚሆን ትንበያ ተሰምቷል፡፡ የዓለም ባንክ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 3.3 በመቶ መሆኑን፣ የመጪው ዓመት ደግሞ ከ5.2 በላይ አያድግም ያለው ሰሞኑን ነው፡፡ ይህም ሌላ ግርታ ይፈጥራል፡፡

  የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት እንደተናገሩት በሚቀጥለው ዓመት በመላ አገሪቱ ጦርነት ቆሞ ምቹ ማክሮ ኢኮኖሚ እንደሚፈጠር ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ረቂቅ በጀቱም በፊስካል ፖሊሲው ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል የሚረዳ መንገድ እንደሚከተል፣ የዋጋ ግሽበቱን በአጭር ጊዜ ወደ ነጠላ አኃዝ ማውረድ አስቸጋሪ ቢሆንም በአዲሱ በጀት ዓመት ወደ 11.9 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታትና በተያዘው በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበት ባለሁለት አኃዝ ሆኖ መቀጠሉ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ፈተና እንደሆነ፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራውም አመርቂ ውጤት ያልታየበት ይኸው የዋጋ ግሽበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። በጀቱ ደግሞ በአብዛኛው ከጦርነቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳቶችና ለአገር ደኅንነት እንደሚውል ነው የተነገረው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት እንደሚቀጥል፣ ምክንያቱ ደግሞ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን ስለማይገኝ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡ ከመጪው ዓመት 781.6 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 234.4 ቢሊዮን ብር ጉደለት እንደሚያጋጥም ሲነገር፣ እንዲሁም ከውጭ ሊገኝ የሚችለው ብድርና ዕርዳታ አስተማማኝ አለመሆኑ ሲሰማ የዋጋ ግሽበቱ ይወርዳል ማለት ይከብዳል፡፡

  እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ካለው የሰላም ዕጦትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚስተዋለው ኢኮኖሚያዊ ጫና አኳያ፣ በጀትን በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም ይገባል መባሉ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በጀትና ሀብት ላይ የሚደርሰውን ዝርፊያና ብክነት ማቆም ካልተቻለ፣ በቀዳዳ ጄሪካን ውኃ ለመሙላት ከሚደረግ ከንቱ ልፋት አይተናነስም፡፡ በየቦታው የሚታየው የአስረሽ ምቺው ድግስና ከበርቻቻ መቆም አለበት፡፡ የእያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም ወጪ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉ በኦዲት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በሁሉም ባለበጀት መንግሥታዊ ተቋማትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በሚያቀርበው ሪፖርት መሠረት፣ በአጥፊዎች ላይ ምሕረት አልባ የሆነ ሕግ የማስከበር ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ሕዝብ ከገቢው በላይ ከሆነው የኑሮ ውድነት ጋር እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ውስጥ ሆኖ፣ በስሙ የሚያዘውን በጀት ሕገወጦች እንደፈለጉ ሲጫወቱበት ማየት ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካልን ፓርላማው ወጥሮ መያዝ አለበት፡፡

  ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ከፍተኛ የበጀት ጉድለት በሚኖርበት ጊዜ የመንግሥት ባህሪ ነው፡፡ መንግሥት ያለ ገደብ እየተበደረ ወይም ገንዘብ እያተመ ገበያው ውስጥ የሚረጭ ከሆነ ውጤቱ፣ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› ነው የሚሆነው፡፡ ገቢው ላይ አንዲት ሳንቲም ጭማሪ ሳያገኝ በምግብ፣ በቤት ኪራይ፣ በልጆች ትምህርት ቤትና በልዩ ልዩ ጉዳዮቹ በዋጋ ግሽበት የሚመታ ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ መንግሥት ከእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት መቆጠብ አለበት፡፡ ወጪዎቹን አብቃቅቶ ለታለመላቸው ዓላማዎች የማዋል ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ ማንም አያየኝም ወይም ሊቆጣጠረኝ አይችልም ብሎ ገንዘብ እያተመ ገበያውን ማተራመስ የለበትም፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጉዳይ፣ ባልተጠና መንገድ ገበያው ውስጥ እየገባ የሚወስደው አጉል ዕርምጃም ፈር መያዝ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት ቁጥጥር አደርጋለሁ ብሎ ገበያ ውስጥ ገብቶ ዳቦም ሆነ ቲማቲም፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮም ሆነ ሲሚንቶ ዋጋቸው የበለጠ ሲንር እንጂ ሲረጋጋ አልታየም፡፡ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች መመራት ያለበት የግብይት ሥርዓት የማንም መጫወቻ የሆነው፣ በመንግሥት አቅመ ቢስነት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡

  የመጪው ዓመት በጀት በከፍተኛ ጉድለት ታጅቦ ሲቀርብ ጉድለትን ለመሙላት ምን መደረግ አለበት የሚለውን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍተኛ ምርት ማግኘት አንደኛው ነው፡፡ በአገር ውስጥ ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይትና ሌሎች መሠረታዊ የምግብ ምርቶችን በከፍተኛ መጠን ማምረት ከተቻለ የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ ያግዛል፡፡ ገበያ ውስጥ የአገር ውስጥ የምግብ ምርቶች በብዛት ሲገኙ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለማቃለል ይረዳል፡፡ ከውጭ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ውስጥ በተቻለ መጠን በከፊል በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት ከተደረገ፣ ለውጭ ምንዛሪ የሚደረገው ሠልፍ ይቀንሳል፡፡ መንግሥትም የቅንጦት ተሽከርካሪዎችና የቤትና የቢሮ መገልገያ ዕቃዎች ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ምርቶች ከሸፈነ፣ ወጪ ለመቆጠብ የገባውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ብዙ ቀዳዳዎችን ይደፍናል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር የምርት ልውውጥ የማድረግ አዲስ እንቅስቃሴ ቢጀመር ደግሞ፣ ለምግብም ሆነ ለሌሎች ሸቀጦች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን በየተራ ለመቅረፍ ግን የባለሙያዎችን ዕገዛ ማግኘት የግድ ነው፡፡

  የመጪውን ዓመት በጀት ከሚፈትኑት በርካታ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ መንግሥት 40 በመቶ ገደማ የደረሰውን የዋጋ ግሽበት ወደ 11.9 በመቶ ለማውረድ ሲያቅድ፣ ትንበያው የተሠራባቸውን አመላካቾች አብሮ ቢያሳውቅ ጥሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከዘንድሮ የግብርና ምርቶች አምስት ሚሊዮን ኩንታል ያህል ቅናሽ እንደሚኖር የተነገረው ሰሞኑን ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያለው የምርት አቅርቦትና ከውጭ የሚገባው የምርት መጠን አስተማማኝ ባልሆነበት፣ በምን መመዘኛ ነው የዋጋ ግሽበት በዚህን ያህል መጠን ሊወርድ የሚችለው መባል ይኖርበታል፡፡ በሩሲያና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት እንደ ነዳጅ፣ ስንዴ፣ ዘይትና ሌሎች ምርቶችን እጥረትና የዋጋ ንረት ባባሰበት ወቅት፣ የዋጋ ግሽበቱ በዚህ መጠን ይቀንሳል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ እንደተባለው በኢትዮጵያ ጦርነት ቆሞ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ርብርብ ማድረግ ቢጀመር እንኳ፣ የዋጋ ግሽበቱ እንዲረጋጋ ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ባለበት እያረጋጉ ቀስ በቀስ ለማውረድ ደግሞ ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ድምፃዊው፣ ‹‹…የዓይኔ ነገርማ ገና ብዙ አለበት…›› እንዳለው፣ የበጀቱ ነገር ገና ብዙ እንዳለበት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  ብሔራዊ ባንክ ለፋይናንስ ተቋማት ለሚሰጠው ፈቃድና አገልግሎት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሊያስከፍል ነው

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ለሚሰጠው የፈቃድ፣ የብቃት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...