Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአክሬዲቴሽን ማረጋገጫ በአገር ውስጥ ለሚቀርቡ ሁሉም ምርቶችና አገልግሎቶች አስገዳጅ እንዲሆን ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአክሬዲቴሽን ማረጋገጫ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች በተጨማሪ በአገር ውስጥ ተመርተው ለሚቀርቡ ምርቶችም አስገዳጅ እንዲሆን ተጠየቀ።

ወደ ውጭ አገሮች የሚላኩ ምርቶች በተቀባዮች ጥያቄ የአክሬዲቴሽን ማረጋገጫ የሚያቀርቡ ቢሆንም፣ ለአገር ውስጥ ገበያ ከሚያቀርቡት ውስጥ በርካቶቹ ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ እንደማይገደዱ የሚገልጹት የብሌስ አግሪ ፉድ ላብራቶሪ የኢንስፔክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ አምቤ በቀለ፣ ይህም በምርቶቹ ጥራት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።

ለአገር ውስጥ ገበያ ምርቶችን የሚያቀርቡ አምራቾች ስለአክሬዲቴሽን ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ፣ በምርቶችም ሆነ በአገልግሎቶች ላይ በቂ ፍተሻ እንደማይደረግና ኅብረተሰቡም ማረጋገጫዎችን የመጠየቅ ልምዱ አነስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ላይ የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት ቢኖርም፣ እንደ ጥራጥሬና ቅባት እህል እንዲሁም ቅመማ ቅመም ያሉ ምርቶች ቁጥጥር ሳይደረግባቸው ለአገር ውስጥ ገበያ መቅረባቸው ጎጂ መሆኑን አክለዋል።

ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩትም በአስገዳጅነት ካልተጠየቁ በስተቀር የማቅረብ ልምዳቸው ዝቅተኛ መሆኑን፣ ይህም በዓለም ገበያ ላይ ያላቸው ተወዳዳሪነት እንዲቀንስና የምርቶቻቸውን ዋጋ ዝቅ አድርገው እንዲሸጡ ይገደዳሉ ብለዋል።

 የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ጽጌመላክ በበኩላቸው፣ ተቋማት አክሬዲቴሽን እያገኙ ያሉት በራሳቸው ፍላጎት በመሆኑ በርካታ ተቋማት የጥራት ማረጋገጫ እንዳያገኙ አስችሏል ብለዋል።

ለምርትና አገልግሎታቸው አክሬዲቴሽን ያገኙ ተቋማት ማረጋገጫውን ካገኙት የተሻለ ማበረታቻ ማግኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የአክሬዲቴሽን ሥርዓቱንም ከውጭ በሚመጡም ይሁን በአገር ውስጥ ምርቶች ላይ በሒደት አስገዳጅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ነገር ግን አስገዳጅ እስኪሆን ድረስ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ተጠቃሚዎች ምርትና አገልግሎቶችን ሲፈልጉ እንደ አንድ መሥፈርት ቢያስቀምጡት፣ ተቋማት ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚጠቅም ይገልጻሉ።

የምርትና አገልግሎቶችን ደረጃ የማውጣት ችግር የለም የሚሉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ እንዳለው መኰንን፣ ችግሩ የሚከሰተው አፈጻጸሙ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም የግሉ ዘርፍ በፍተሻ፣ ላቦራቶሪ፣ ማረጋገጫ መስጠትና መሰል የአክሬዲቴሽን ዘርፎች እንዲገቡ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ጥቂት ተቋማት የተስማሚነት ምዘናን በማሟላት ለኅብረተሰቡ ምርትና አገልግሎታቸውን እያቀረቡ ቢሆንም፣ በርካታ ተቋማት ማረጋገጫ ሳያገኙ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በመሆኑም አክሬዲቴሽን ማረጋገጫ ሳይኖራቸው የሚሠሩ ተቋማት ማረጋገጫውን በመያዝ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች