Thursday, February 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ዋስትና አስይዞ ብድር የመውሰድ ፍላጎት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በማስያዝ ከባንክ ብድር ለመውሰድ የሚፈልጉ ደንበኞች ቁጥር እንደተጠበቀው አለመሆኑ ተገለጸ።

በአዋጅ ቁጥር 1147/2011 መሠረት ተንቀሳቃሽ ንብረትን ዋስትና በማስያዝ ዘመናዊ የብድር ሥርዓትን ለማስፋት ዓላማ አድርጎ፣ ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በማስያዝ ከባንኮች ብድር እንዲያገኙ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህም በተለይ አዲስ ካፒታል ለማግኘት፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል በሚል እንደ ተሽከርካሪ፣ እንስሳትና ሰብል የመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በማስያዝ ብድር የሚገኝበት አሠራር ነው።

ይህ ዓይነቱ አሠራር ብዙ ብድር የማያገኘውን የግብርናውን ዘርፍም የብድር መጠኑን ከፍ እንደሚያደርገው ታሳቢ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ባንኮች በተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚጠየቀው የብድር መጠን ከተጠበቀው በታች መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ብድር የመውሰድ አሠራር ግብርናውን ለመደገፍ የሚጠቅምና ሌሎች ከፍተኛ ማስያዣዎችን ማቅረብ የማይችሉ ደንበኞች በቀላሉ ብድር እንዲያገኙ ለማስቻል የታለመ ቢሆንም፣ ደንበኞች ግን በሚጠበቀው ልክ ወደ እዚህ ሥርዓት ገብተው ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም።

ተሽከርካሪዎችን በማስያዝ ብድር የሚወስዱ ደንበኞች ቁጥር የተሻለ መሆኑን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ነገር ግን እንደ ሰብልና እንስሳት ዓይነት ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው ብድር የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ይላሉ። ለዚህም የደንበኞቹ ፍላጎት አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ወደ ባንክ ሲመጡ የሚጠየቋቸውን የብድር ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት አለመፈለግ፣ አንዳንድ ጊዜም አለመቻል ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ከተሽከርካሪ ውጪ ያሉ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የባለቤነት ጥያቄ ሲነሳ በሕጋዊ መንገድ የተረጋገጠ የባለቤትነት ማስረጃ አለመኖሩ፣ ባንኮች በቀላሉ ንብረቱን ይዘው ማበደር እንዳይችሉና በርካታ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲጠይቁ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል። እንደ ሰብልና እንስሳት ዓይነት ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የኢንሹራንስ ሽፋን ስለሌላቸው፣ የብድር አሰጣጥ ሒደቱን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።

የንብ ባንክ የብድር ትንተና ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ሰማዬ በበኩላቸው፣ በተንቀሳቃሽ ንብረት ብድር እንዲሰጥ ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት በርካታ የብድር ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ተጠብቆ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ምክንያቱን ለማወቅ ባይቻልም እስካሁን ድረስ በተንቀሳቃሽ ንብረት ብድር ለማግኘት ለባንኮች እየቀረበ ያለው ጥያቄ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከግብርና ዘርፍ የሚቀርበው ጥያቄ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ  ከ144 ማኅበራት ጋር መሬታቸውን በመያዝ ብድር እንዲያገኙ ንግግር በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተሰብሳቢ ገንዘብን በመጠቀም ከተቋማት የብድር ጥያቄ ይቀርባል የሚል ግምት ቢኖርም፣ የለም በሚባል ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች