- ለ12ኛው የአየር ትራንስፖርት ኩባንያ ፈቃድ ተሰጠ
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ የመጪዎቹ 30 ዓመታት የአገሪቱን አቪዬሽን ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በዋናነት ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የት ላይ ትገኛለች? በቀጣዮቹ 30 ዓመታት በተለይም በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ የት ላይ ትደርሳለች የሚለውን የሚያመለክት ነው፡፡
የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የሚያቅፍ መሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ፣ የኤር ናቪጌሽን፣ የሴፍቲ፣ የሴክዩሪቲና ሌሎችም ይገኙበታል ብለዋል፡፡ በቀጣዮቹ 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ በየትኞቹ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል? ይህንንም በመሥራት ሒደት ውስጥ የተለያዩ ተቋማት ማን ምን ሚና ይኖራቸዋል? በምን አኳኋንስ ይፈጸማል? የሚለውን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ረዥም ዘመን ማስቆር ብቻ ሳይሆን እያደገ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ በቀጣይ ዕድገቱን ጠብቆ እንዲሄድና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው በቴክኖሎጂ በቅቶ መገኘት ሲቻል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ቴክኖሎጂን የመጠቀም፣ የማሻገርና በሒደትም የቴክኖሎጂ ባለቤት የሚኮንበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል የሚል እምነት መያዙን ተናግረዋል፡፡ ይህንን እምነት መፈጸም የሚቻለው በተደራጀና በታቀደ አኳኋን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዕድገቱን ቀጥሎ እንዲሄድ ካስፈለገ፣ ቴክኖሎጂ ላይ የሚኖረን ብቃት አስፈላጊ ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በተለይም ከቀጣዩ ዓመት አንስቶ በወጣቶች ላይ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው፣ ከአቪዬሽን ዘርፍ ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ፈጠራዎቻቸውን (ምርቶታቸውን) አስተዋውቀው፣ የቴክኒክና የግብዓት ድጋፍ እንዲገኙ ዕድሎች የሚመቻችላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ፍኖተ ካርታው ምን ይሁን የሚለው ከተወሰነ በኋላ በዝርዝር የዕቅድ ትግበራ (ኦፕሬሽናል ፕላን) የሚመራ ይሆናል ብለዋል፡፡
በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ማንነትና ብዛት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በጋራ የሚወሰን ቢሆንም፣ ለጊዜው ይህንን ሥራ የሚመራ የባለሙያዎች ኮሚቴ ከሁለቱም ተቋማት እንደሚዋቀር፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንንና ተመራማሪዎችን በማሳተፍ፣ እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ታክሎበት፣ የሌሎች አገሮች ልምድና ተሞክሮ እየተወሰደ የሚዘጋጅ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ መንግሥታዊ ተቋማት የፍኖታ ካርታ ዝግጅቱን ጨምሮ ሌሎች መሰል ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት በተጠናቀቀው ሳምንት አጋማሽ፣ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በተደረገው የስምምነት ሰነድ ላይ እንደተመላከተው፣ ተቋማቱ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) ከማዘጋጀት በተጨማሪ በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች የሚደገፉበት፣ የሚበረታቱበትና ዕውቅና የሚሰጥበትን የሕግ ማዕቀፍ በጋራ ያዘጋጃሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የብሔራዊ አቪዬሽን ፖሊሲ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይቶችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ረቂቅ ፖሊሲው የአቪዬሽን ትራንስፖርት ዘርፍ ፖሊሲን፣ የመንግሥት የልማት አቅጣጫን፣ አገሪቱ በዘርፉ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ፕሮቶኮሎችን፣ እንዲሁም የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን አኅጉራዊ ፖሊሲ (AFCAC) እንደ መነሻ በመውሰድና በተለያዩ ደረጃዎች የተሰጡ ግብዓቶችን አካቶ ለቀጣይ ዕርምጃ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር መላኩ ከዚህ በፊት መገለጹ ይታወሳል፡፡
በተያያዘም ኤር ኤክስፕረስ አፍሪካ የግል የአውሮፕላን አየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ ሆኖ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መመዝገቡን፣ የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንሙት ለማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁና በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የሚተገበሩ አምስት ደረጃዎችን በስኬት አጠናቆ በመገኘቱ ፈቃድ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
ግዙፉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጨምሮ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የአውሮፕላን አየር ትራንስፖርት ተቋማት 12 መድረሳቸውን አቶ አንሙት አስረድተዋል፡፡