Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቴሌ ብር ከሃያ ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቴሌ ብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ከተደረገበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ፣ የ20.63 ቢሊዮን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር መደረጉን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በወዳጅነት አደባባይ ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ ኩባንያው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 12.7 ሚሊዮን ደንበኞችን ለማፍራት አቅዶ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት በቴሌ ብር የተመዘገቡ ደንበኞች ቁጥር 20 ሚሊዮን መድረሱ ተገልጾ፣ በእነዚህ ደንበኞች በዓመት ውስጥ የተደረገው ሞባይል ገንዘብ ዝውውር ከ20.6 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል ተብሏል፡፡

በኅዳር ወር ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ተሰጥቶት ይፋ በተደረገው የዓለም አቀፍ የሞባይል ገንዘብ ሐዋላ ዝውውር ከ36 የተለያዩ አገሮች ከ794 ሺሕ ዶላር በላይ መንቀሳቀሱን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኩባንያው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ከአገር ውጭ ባሉት ከፍተኛ ባንድዊድዝ ተሸካሚ የኢንተርኔት መገናኛ መስመሮች ላይ በገጠመው ችግር ምክንያት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት በመጠባበቂያ መስመሮች ብቻ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ወይም የፍጥነት መቀነስ ሊያጋጥም እንደሚቸል አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሴልስ አፊሰር አቶ መሐመድ ሐጂ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በምድርና ከባህር በታች በሚዘረጉ የኔትወርክ ኬብሎች (የሰብማሪን ኬብሎች) ላይ በደረሰ ጉዳት ወይም የመቆረጥ ችግር ለጥቂት ሰዓታት የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ተከስቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በትክክል ጉዳቱን ያደረሰው ክስተት ምንነት እንደማይታወቅ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎት መስተጓጎሉ በኢትዮጵያ ብቻ ያጋጠመ እንዳልሆነና ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ታንዛኒያ፣ ማዳጋስካርን ጨምሮ ፓኪስታን፣ ኢንዶኔዢያና ሌሎች የአፍሪካ፣ የእስያና የኦሺኒያ አገሮችን አጋጥሟል ተብሏል፡፡

አቶ መሐመድ እንደተናገሩት ጉዳት የደረሰባቸው የሰብማሪን ኬብሎች ኤኤኢ1 (AAE1) እና ኤስኤምደብሊው5 (SMW5) የሚባሉት ናቸው፡፡ በተለይም ጉዳቱ በአንዳንድ አገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ምክንያት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከተለያዩ አምስት አገሮች አቅጣጫ በሚመጣ የኔትወርክ ኬብል አገልግሎት በመስጠቷ ምክንያት ያጋጠመውን መስተጓጎል መቋቋም መቻሉን ተመላክቷል፡፡

በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም ከኢሚግሬሽንና ከዜግነት አገልግሎት ጋር በመተባበር የፓስፖርት አገልግሎትን በቴሌብር ለማከናወን፣ ሐሙስ ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ስምምነት ፈጽሟል፡፡

በቴሌ ብር መቅረብ የጀመረው አዲሱ አገልግሎት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት፣ ለማሳደስ፣ የጠፋ ፓስፖርትን ለመተካትና የተጎዳ ፓስፖርትን ለመጠገን ወይም ለማደስ የሚደረገውን ክፍያ ለማከናወን ይረዳል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት እንደተናገሩት፣ የክፍያ ሥርዓቱን ማዘመንና ማቅለል ብቻ ሳይሆን የኩባንያው ዕሳቤና ፍላጎት ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትና ከሚመለከታቸው ሌሎች የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በመነጋገር፣ የሚታደሰውን ፓስፖርት ደኅንነቱ ተጠብቆ ደንበኞች ደጅ ድረስ ለማምጣት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር ስምምነት መፈጸሙን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይህንን መሠረት በማድረግ በቀጣይ ቋሚ አድራሻ ላላቸው ዜጎች ደጃፋቸው ላይ እንዲዳረስ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ኢትዮ ቴሌኮም በሒደት ላይ የሚገኘውን የታለመለት የነዳጅ ድጎማ በቴክኖሎጂ በማገዝ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የነዳጅ ድጎማው የሚፈቀድላቸው አካላት ወይም መመርያው ወደ መሬት ሲወርድ የሚደጎሙት መኪኖች መመዝገብ ስለሚገባቸው፣ ይህንን ሥራ ከሚያከናውኑ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ኢትዮ ቴሌኮም እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢትዩ ቴሌኮም ድርሻ ሲስተሙን ማልማትና ማደያዎች በቴሌ ብር አማካይነት እንዴት አድርገው አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሆነ የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ በዚህ ወቅት ተገቢውን መሥፈርት ያሟሉ ተሽከርካሪዎች እየተመዘገቡ ናቸው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች