Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአዳዲስ አትሌቶችን ያስመለከተው የሞሪሸሱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

አዳዲስ አትሌቶችን ያስመለከተው የሞሪሸሱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሲካፈል ቆይቷል፡፡ በተለያዩ ርቀቶች ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች በሻምፒዮናው ሲካፈሉ የቆዩ ሲሆን፣ አዳዲስ አትሌቶችም ብቅ ብቅ ያሉበት መድረክ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. 2020 በአልጄሪያ ሊከናወን የነበረው ሻምፒዮናው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መሰረዙን ተከትሎ ሞሪሸስ ሊከናወን ችሏል፡፡ ከሰኔ 1 እስከ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሜዳ ተግባር ጨምሮ በአጭር ርቀት፣ በመካከለኛና በረዥም ርቀት ተካፋይ ነበር፡፡

ሁለት ዓመት እየጠበቀ በሚሰናዳው በዚህም ሻምፒዮና የአዳዲስ አትሌቶችን ፊት ከመመልከት ባሻገር በቀጣይ በዓለም አትሌቲክስ መድረክ ላይ ደምቀው የሚታዩ አትሌቶች የሚገኙበት ውድድር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሞሪሼሱ ሻምፒዮና ላይ አራት ወርቅ፣ ስድስት የብር ሜዳልያና አራት የነሐስ ሜዳልያ በድምሩ 14 ሜዳልያዎችን በማምጣት አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በወንዶች 5,000፣ 10,000፣ 3,000 ሜትር መሰናክል እንዲሁም በሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል አራት የወርቅ ሜዳልያዎችን ማግኘት ችሏል፡፡

በወንዶች 5,000 ሜትር ኃይለ ማርያም አማር 13፡36.79 በማጠናቀቅ፣ 10,000 ሜትር ሞገስ ጥዑማይ 29፡19.01 በመጨረስ፣ በወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል ኃይለ ማርያም ተገኝ 8፡27.38 በማጠናቀቅ፣ በሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል ወርቅ ውኃ ጌታቸው ርቀቱን 9፡36.81 በመግባት የወርቅ ሜዳልያን ማግኘት የቻሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በ10,000 ሜትር ወንዶች ጭምዴሳ ደበሌ የብር ሜዳልያ በ3,000 መሰናክል ታደሰ ታከለ የብር ሜዳልያን ያገኙ አትሌቶች ሲሆኑ፣  በሴቶች 800 ሜትር ነፃነት ደስታ፣ በ5,000 ሜትር ፋንታዬ በላይነህ እንዲሁም በ3,000 ዘርፌ ወንድምአገኝ፣ በ20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ የኋላዬ በለጠ የብር ሜዳልያዎችን ማሳካት ችለዋል፡፡ በወንዶች 1,500 ሜትር እምባይ አደነ፣ በ20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ዮሐንስ አልጋው፣ በሴቶች 1,500 ሜትር አያል ዳኛቸው እንዲሁም  በ10,000 ሜትር መሠረት ገብሬ አማካይነት አራት የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝቷል፡፡

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በርካታ ተተኪ አትሌቶችን ከማግኘቷ ባሻገር፣ በኬንያ የበላይነት ሲወሰድባት የነበረውን የመካክለኛ ርቀት ወደ እጇ እየመለሰች መሆኗን ፍንጭ የታየበት ሻምፒዮና ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በ3,000 ሜትር መሰናክል ውድድርን በበላይነት የሚያጠናቅቁ አትሌቶችን እያፈራች ትገኛለች፡፡

በሻምፒዮና በወንዶችና በሴቶች 3,000 መሰናክል ወርቅ ማሳካት መቻሏ በርቀቱ ላለችው የበላይነት ማሳያ ነው፡፡ ከዚህም በሻገር በቀጣይ በአኅጉር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ አገራቸውን ወክለው መወዳደር የሚችሉ አዳዲስ ፊቶችን መመልከት የተቻለበት አጋጣሚን መፍጠር የቻለ ሻምፒዮና ነበር፡፡

በተለይ በ3,000 መሰናክል፣ 5,000 እንዲሁም በ10,000 ሜትር ርቀቶች ላይ የታዩት አትሌቶች በቀጣይ ተስፋ የተሰነቀባቸው አትሌቶች መሆን ችለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በጥቂት የዕርምጃ አትሌቶች ብቻ ተወክላ የሰነበተች ሲሆን፣ በዚህ ሻምፒዮና በወንድ ተወክላ የነሐስ ሜዳልያን ማግኘት መቻሏ በበርካቶች ዘንድ እንደ መልካም ጎን የተወሰደ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. 1979 መከናወን የጀመረው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ ተሰናድቷል፡፡ በተወሰኑ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ብቻ ተወስኖ ሲከናወን የሰነበተው ሻምፒዮናው ከዓመት ዓመት በርካታ ርቀቶችን በውስጡ እያካተተ መምጣት ችሏል፡፡

ኬንያ በአሥር ወርቅ፣ በአምስት ብር እና በስምንት የነሐስ በድምሩ 23 ሜዳልያዎች በአንደኝነት ስታጠናቀቅ፣ ደቡብ አፍሪካ በዘጠኝ ወርቅ፣ 13 ብር እና 14 የነሐስ ሜዳልይ በድምሩ 36 ሜዳልያዎች ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ ናይጄሪያ በአምስት ወርቅ፣ ሦስት የብር ሜዳልያና ሦስት የነሐስ ሜዳልያ በድምሩ 11 ሜዳልያዎች ሦስተኛነትን በመያዝ ሻምፒዮናውን ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በሻምፒዮናው በበላይነት ያጠናቀቁት አገሮች በሜዳ ተግባር እንዲሁም በበርካታ የመም ውድድሮች ላይ ተሳታፊ መሆን መቻላቸው በበላይነት እንዲያጠናቅቁ አስችሏችዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከመጀመርያው ጀምሮ እስከ 2018 ባሉት ሻምፒዮናዎች 41 ወርቅ፣ 57 ብር ሜዳልያ እንዲሁም 58 የነሐስ ሜዳልያ በድምሩ 156 በመሰብሰብ ከአፍሪካ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...