በትግርኛ ሙዚቃ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየገነነ በመምጣት ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ድምፃዊ ዳዊት ነጋ፣ ‹‹ወዛመይ፣ ዘዊደሮ፣ ቸኮላታ፣ ኣክሱማዊ፣ ብነፀላይ፣ ባባ ኢለይ›› በተሰኙት ሥራዎቹ የበርካቶችን ቀልብ መግዛቱ ይነገርለታል፡፡
ከአገር አልፎ በዓለም የሙዚቃ መድረክ የትግርኛ ሙዚቃን በሥራው ያስተዋወቀው ዳዊት፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከለቀቃቸው ዘፈኖቹ ውስጥ ‹‹ይኾኖ፣ ኣጆኺ ትግራይ›› ተጠቃሽ መሆናቸው በገጸ ታሪኩ ተመልክቷል፡፡
በመቐለ ከተማ በ1980 ዓ.ም. ተወልዶ ያደገው ዳዊት፣ በመጀመርያ በሰርከስ ትግራይ ቆይቶም በፖሊስ ኦርኬስትራ ማርሽ ባንድ በመግባት የሙዚቃ ሕይወቱን ጀምሮበታል፡፡ ከትግራይ ባህል የሚቀዱ ትውፊትን ከሚያንፀባርቁ ሥራዎቹ መካከል ‹‹ገለገለ መስቀል›› ተጠቃሽ ነው ይሉለታል፡፡
መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ የነበረው ድምፃዊ ዳዊት፣ ባደረበት ድንገተኛ ሕመም ሕክምና ሲከታተል ከቆየ በኋላ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በ34 ዓመቱ ማረፉ ተሰምቷል፡፡
ሥርዓተ ቀብሩ ትናንት ሰኔ 7 ቀን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመድ፣ አድናቂዎቹና የሥራ ጓደኞቹ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
ዜና ዕረፍቱን ተከትሎ ዳኒ ገብረ መድኅን የተባሉ ገጣሚ፣ በማኅበራዊ ገጻቸው ‹‹ሰላም ዕረፍ›› በሚል ርዕስ ስንኝ አሥረውለታል፡፡
‹‹ብዙም አልታመመ
ብዙ አልተንገላታ
በቀናት ሕመም ውስጥ
ከሥጋው ተፋታ፤
ማን ይህን አሰበ
ማንስ ምንስ ብሎ
ይጠብቀው እንጂ
ከዜማው ኮብልሎ፤
ይቀራል አላለም
ሊኖር ተነጥሎ
ግን የሆነው ሆነ
ሄደ እሱ ቸኩሎ፤
ምንስ አለው እና
መቅረትን ወደደ
ከዚህ ከዚያም እሳት
ነፍስ እየማገደ
አድክሞት ይሆናል
መሄድ የፈቀደ፡፡