በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ይታመናል፡፡ እነዚህም አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ክህሎት አውጥተው እንዲሠሩ እንዲሁም ደግሞ ምቹ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው መንግሥት ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሠራ ቢሆንም ዘርፉ ላይ ግን አሁንም ቢሆን ክፍተት እንዳለ ይነገራል፡፡ ይኼም ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዳይሠሩ ማነቆ የሆነባቸው ሲሆን፣ ይህንን ክፍተት ለመታደግ የኢትዮጵያ ተኪ የወረቀት ቦርሳዎች አምራች ድርጅት እየሠራ ይገኛል፡፡ ተኪ የወረቀት ቦርሳዎች አምራች ድርጅት በአሁኑ ወቅት መስማት የተሳናቸው 27 ሴቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ስለሚሠራው ሥራ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅዋን ወ/ሮ ሚሚ ለገሰን ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ተኪ የወረቀት ቦርሳዎች አምራች ድርጅት እንዴት ተመሠረተ?
ወ/ሮ ሚሚ፡- በመጀመርያ ተኪ የወረቀት ቦርሳዎች አምራች ድርጅት ከመጠንሰሱ በፊት ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ አንዳንድ የእጅ ሥራዎች እሞክር ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በራሴ ሐሳብ አድርጌ እሠራቸው የነበሩ የእጅ ሥራዎች በብዛት ለማምረትና ወደ ገበያ ለማውጣት አቅም አልነበረኝም፡፡ ይኼም ለምን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ በውስጤ ይመላለስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በአንድ አጋጣሚ ክሌኔት የሚባል አንድ ስዊዘርላንዳዊ ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተን ሐሳቦችን በምንለዋወጥበት ወቅት ይኼን ድርጅት ሊጠነሰስ ችሏል፡፡ ድርጅቱንም ካቋቋምን በኋላ መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር ለመሥራት ፍላጎቱ ስላደረብን በጥቂት መስማት የተሳናቸው ሴት ልጆች ሥራችንን ልንጀምር ችለናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መስማት የተሳናቸው ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሥራ ስለማያገኙ እነሱ ላይ ብንሠራ የተሻለ ለውጥ ልናመጣ እንደምንችል በማመን ወደዚህ ሥራ ገብተናል፡፡ በዚህም የተነሳ ለብዙ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ መንገድ ከፍተናል፡፡ አብዛኛውን መስማት የተሳናቸው ሰዎች የእጅ ሙያ ኖሯቸው ዕድሉን ባለማግኘታቸው ብቻ ጎዳና ላይ ወጥተው ሲለምኑ ይታያል፡፡ ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ተቋማችን አሁንም ወደፊት ሆነ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው?
ወ/ሮ ሚሚ፡- በአሁኑ ወቅት የወረቀት ቦርሳዎችን በብዛት በማምረት ለሆቴሎችና ለተለያዩ ተቋሞች እያቀረብን ይገኛል፡፡ ያመረትናቸው ቦርሳዎች ለገበያ በምናቀርብበት ወቅት የምልክት ቋንቋ ተጠቅመን ነው፡፡ በዚህም ጊዜ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል በማሳመን ለገበያ እያቀረብን ይገኛል፡፡ በተለይም ሆቴሎች የምናመርትበት ቦታ ድረስ መጥተው ምርቱን ስለሚያዩ በብዛት እየገዙን ይገኛል፡፡ ተኪ የወረቀት ቦርሳዎች አምራች ድርጅት በአሁኑ ወቅት 27 መስማት የተሳናቸውን ሴት ልጆች ተጠቃሚ አድርገናል፡፡ ድርጅታችን አሁን ላይ ስድስት ዓይነት ቦርሳዎችን እያመረተ ሲሆን እንደየቦርሳው ዓይነቶች በቀን ከ1,000 እስከ 1,500 ቦርሳዎችን እያመረትን ለደንበኞቻችን እናቀርባለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአሜሪካ ኤምባሲ ባገኘነው 550 ሺሕ ዶላር 200 መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ በዚህም መሠረት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ሥልጠና በመስጠት ስለ ሥራው በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የምናደርግ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?
ወ/ሮ ሚሚ፡- በሥራችን ብዙ እንቅፋቶች ገጥመውናል፡፡ በተለይም ደግሞ ቦርሳዎችን ለማምረት የምንጠቀመውን ጥሬ ዕቃ ማግኘት ከባድ ችግር ሆኖብናል፡፡ በአገሪቱም አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት እንዲሁም ደግሞ የዶላር ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ለምርቶቻችን የሚሆኑ ግብዓቶች በየዕለት ዋጋ እየጨመሩ ይገኛል፡፡ ይኼም ሥራችን ላይ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ጥራታቸውንና ደረጃቸውን የጠበቁ ቦርሳዎች ለማምረት ደረጃውን የጠበቀ ወረቀት ያስፈልገናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የምንሠራቸውን ቦርሳዎች ለመሸጥም ሆነ ለማምረት የምንጠቀምበትን ቦታ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ዓይተናል፡፡ ይሁን እንጂ ከብዙ ትግል በኋላ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው ኮንዶሚኒየም ለጥቃቅንና አነስተኞች የታሰበላቸውን ቦታ መንግሥት ሊሰጠን ችሏል፡፡ የተሰጠን ቦታ መሀል ከተማ በመሆኑ የሠራናቸውን ቦርሳዎች እንደፈለግን ለመሸጥ ረድቶናል፡፡ ከዚህ በፊት ቦርሳዎችን በምንሸጥበት ወቅት በር ለበር እየሄድን ስለነበር ይህንን ችግር ሊቀርፍልን ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን በዘርፉ ላይ የተሰማሩት ሰዎች መስማት የተሳናቸው በመሆናቸው መንግሥት ከታክስ ነፃ አድርገን እንድንሸጥ ፈቅዶልናል፡፡ ይኼም የአብዛኛውን መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ችግር ከመቅረፍም አልፎ ለተለያዩ ቁምነገሮች እንዲበቁና በኑሮዋቸው መሻሻል እንዲያሳዩ አቅጣጫ ሰጥቶናል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ዓይነት ድጋፍ አድርጎላችኋል?
ወ/ሮ ሚሚ፡- ድርጅታችን በተደጋጋሚ ይጠይቅ የነበረውን የመሥሪያ ቦታ ስለነበር ይኼንንም መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግልን ችሏል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከታክስ ነፃ አድርጎን እንድንሸጥ ስለተፈቀደልን ለሥራችን ጉልበት እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ በቅርቡም አማራጭ ቦታዎችን አግኝተን ለመሥራትና አቅማችንን ከፍ እንድናደርግ መንግሥት የምንጠይቅ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የተለያዩ ቦርሳዎችን በብዛት ለማምረት አሁንም ያገኘነው የቦታ ይዞታ በቂ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይም ምርቶቻችንን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ደግሞ ያለንን አቅም ለማሳደግ በቀጣይ የምንጠይቅ ይሆናል፡፡ በቀጣይም መንግሥት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ አሠራር እንዲዘረጋ ጉትጎታ የምናደርግ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ምን ያህል ሠራተኞችን ይዟል?
ወ/ሮ ሚሚ፡- በአጠቃላይ 37 ሠራተኞች አሉን፡፡ ከእነዚህ 27ቱ መስማት የተሳናቸው ሲሆኑ አሥሩ ደግሞ ምንም ዓይነት የአካል ጉዳተኛ ያልሆኑ የአስተዳደር ሥራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በድርጅቱ ሥር ያሉ ሁሉም ሠራተኞች የምልክት ቋንቋ የሚችሉ ናቸው፡፡ በቀጣይ ድርጅታችን ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ በመያዙ በርካታ አካል ጉዳተኞች አካተን እንሠራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼን ማድረግ ከቻልን ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ መስማት የተሳናቸው ወገኖችን ከሥራ አጥነት መታደግ እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
ወ/ሮ ሚሚ፡- በቀጣይ ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ የአካል ጉዳተኞችን ሥራ ለመፍጠር ዕቅድ ይዘናል፡፡ የዘርፉ ተዋናይ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን ለማብቃትና ሴክተሩም ትኩረት እንዲያገኝ መንግሥትን በተደጋጋሚ የምንጠይቅ ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ከግብዓት አኳያ የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዲቀርፍልንና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥርልን ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡ በተለይም ደግሞ ለሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን ትኩረት ለአካል ጉዳተኞችም እንዲሰጥ ውትወታ የምናደርግ ይሆናል፡፡ ከተለያዩ አገሮች ከሚመጡ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ሠራተኞቻችን የልምድ ልውውጥ እንዲፈጥሩና በሥራቸው ዕውቀት እንዲቀስሙ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይኼ ከሆነ በርካታ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የተሻለ ቦታ እንዲደርሱ በር የምንከፍት ይሆናል፡፡